July 24, 2015
ይገረም አለሙ
ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ ሰሞኑን የተናገሩትን ስሰማ አስር አመት ወደ ኋላ ተመልሼ አንዳስብ ግድ አለኝ፡፡ ፕ/ሩ ኢትዮጵያም ሆኑ አሜሪካ ወይንም አስመራ ሰላማዊ ተጋይም ሆኑ ሁሉን አቀፍ የትግል ስልት አራማጅ እምነት አስተሳሰባቸው የማይለዋወጥ መሆኑን ለመገንዘብ ቻልኩኝ፡፡
ጊዜው 1997 መጨረሻ ወቅቱ ሕዝብ ይመርጣል ጠመንጃ ያሸንፋል ሆኖ የፖለቲካው አየር የጋመበት ቅንጅትም ወያኔም በየራሳቸው በጭንቅ ውስጥ የነበሩበት ነው፡፡ የወያኔ ጭንቀት ሥልጣኑን ላለማጣት ሲሆን የቅንጅት ጭንቀት ደግሞ ሥልጣን ወይንም ሞት የሚለው ወያኔ ወንበሩን ከሚያጣ ሀገር ቢፈርስ ሕዝብ ቢጨራረስ ደንታ የሌለው በመሆኑ ነገሮች ወደዚህ አንዳያመሩ በማሰብ ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ ሆነው ቅንጅቶች ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር ለመወያየት አዲስ አበባ ላይ በየሳምንቱ ቅዳሜና ዕሁድ በየወረዳዎች ስብሰባዎችን ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል ለተወካዮች ምክር ቤት የያኔው ዶ/ር ብርሀኑ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ተወዳድረው በተመረጡበት ወረዳ 23 ብስራተ ገብርኤል አካባቢ በተጠራ ስብሰባ ላይ የወረዳው ነዋሪ ባልሆንም ተገኝቻለሁ፡፡ወደ አዳራሹ የመጣ ማንም ኢትዮጵያዊ የነዋሪነት፣ የአባልነት፣ የጎሳም ሆነ የኃይማት ልዩነት ገደብ ሳይደረግበት ስብሰባውን የመሳተፍ ሙሉ መብት ነበረው፡፡
መድረክ ላይ ያሉት ሰዎች ተራ በተራ ንግግር ሲያደርጉ የዶ/ር ብርሀኑ ተራ ደረሰ፡፡ (በወቅቱ በነበራቸው ማዕረግ ነው የምጠራቸው)የዶ/ሩ ንግግር የተሰብሳቢውን ስሜት በመቆጣጠሩ አዳራሹ በጭብጨባ ተናውጧል፡ “ወያኔዎች ያለ ጸብና ቅራኔ መኖር አይችሉም፣እኛ ደግሞ አንጣላቸውም፤የሚጣሉት ሲያጡ ርስ በርሳቸው ይጣላሉ፣… እኛ በምንም መልኩ አነርሱን አንሆንም ፣እነርሱን የሆን እለት ተሸንፈናል ማለት ነው፤” አዳራሹ በጭበጨባ ቀለጠ፡፡ ዶ/ር እየተናገሩ ነው “ ዛሬ እዚህ አዳራሽ የተገኛችሁ ሁሉ ወደየቤታችሁ እንደተመላሳችሁ የተጣላችሁት የኢህአዴግ አባለል ካለ የበደላችሁ እሱ እንኳን ቢሆን እናንተ ይቅርታ እየጠየቃችሁ ታረቁ” ተቃውሞ የለም ድጋፍ ጭብጨባ ብቻ እንደውም አንዳንድ ወጣቶች በድምጽም እሺ ሲሉ ይሰማ ነበር፡፡ እኔ ግን በተመስጦ እያዳመጥኩ በሀሳብ ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየነጎድኩ አእምሮየ እጆቼን ለጭብጨባ ማዘዝ አልተቻለውም፡፡ የዶ/ር ብርሀኑ ንግግር ቀጥሏል፡፡
በየመድረኩ ሆነ በመገናኛ ብዙኃን ከፖለቲከኞቻችን ( በሁሉም ጎራ ካሉት) በአብዛኛው ስንሰማ የኖርነው ልክ ልካቸውን መንገር በሚል አስተሳሰብ የተቃኘ፣ የጠላትነት ስሜት የሚንጸባረቅበት እናሸንፋችኋለን ልክ እናስገባችኋለን ወዘተ በሚል ፉከራ የታጀበ የበቀል ቃና ያለው ወዘተ ንግግር በመሆኑ ነበር የዶ/ር ብርሀኑ ንግግርና አነጋገር በተመስጦ ያነጎደኝ፡፡
የዶ/ር ብርሀኑ ንግግር የቅንጅት አመራር አባል ያውም በምርጫ አሸንፎ ተሸንፈሀል የተባለ ፖለቲከኛ ሳይሆን ከፈጣሪ የተላከ በአንድ እጁ እየሱስ ክርስቶሰ የተሰቀለበትን የፍቅርና የነጻነት መሰቀል በሌላ እጁ ቃሉ የተጻፈበትን ቅዱስ መጽኃፍ ይዞ በፈጣሪ ስም የሚያስተምር የኃይማኖት ሰባኪ ነበር የሚመስለው፡፡
ከሀይማኖት ሰባኪም ስለ ፍቅር ስለ አንድነት ስለ ይቅር ባይነት ለመስበክ ተዘጋጅቶ የመጣ የዚህችን አለም ህይወት አሸንፎ ራሱን የሰጠ መምህር ነበር የሚመስሉት፡፡
ፖለቲካ መጠላላት በሆነበት ሀገር፤ አይደለም በአላማ ተለይቶ የሚታገልን በአመለካከት የተለየን ካላጠፉ አንቅልፍ የማይወስዳቸው በበዙበት ዘመን፤ የፖለቲካው ጨዋታ ጥሎ ማለፍ የሰዎቹ ባህርይ ጥላቻና በቀል የሚንጸባርቅበት በሆነበት ከዚህም በላይ ስሜት ፖለቲካውን በተቆጣጠረበት በዛ ወቅት ከዶ/ር ብርሀኑ አንደበት የተደመጠው ንግግር ቀልብ የሚስብ ብቻ ሳይሆን ሁለንተናን የሚገዛ ነበር፡፡ እናም ፈጣሪ ይህችን ሀገር ሊታረቃት ይሆን! ከመገዳደል አዙሪት ልንወጣና የዴሞክራሲ ቀንዲል ልናይ ይሆን!ወዘተ እያልኩ ራሴን እየጠየኩ ተስፋና ጨለማ በአንድ ላይ እየታዩኘ ነበር በሀሳብ የነጎድኩት፡፡
ግና ተስፋዬ እንደ ጉም ሲበን ወራት አልተቆጠሩም፡ እኚህ ፍቅርን የሰበኩ ይቅር ባይነትን ያስተማሩ የአንድ ሀገር ልጅነት ከፖለቲካ አመለካከት ልዩነት በላይ መሆኑን በተግባር ለማሳየት የጣሩ ሰው ወንጀለኛ ተብለው ከትግል ጓዶቻቸው ጋር ታሰሩ፡፡ ከመታሰራቸው በላይ ዘር ማጥፋት ሀገር ክህደት ህገ መንግሥታዊውን ሥርዓት በኃይል ለመጣል መሞከር ወዘተ በሚል መከሰሳቸው የሀገራችንን መጻኢ እድል ጨለማነት በበግልጽ ያሳየ ነበር፡፡
ዶ/ር ብርሀኑ በቃሊቲ ወህኒ ቤት ሆነው በጻፉት የነጻነት ጎህ ሲቀድ በተሰኘው መጽኃፋቸው የገለጹት ከላይ የገለጽኩትን እምነት አመለካከታቸውን የሚያንጸባርቅ የሰላም ደቀ መዝሙርነታቸውን የሚያሳይ ለመሆኑ ያነበበ ሁሉ የሚያረጋግጠው ይመስለኛል፡፡ ከሁለት አመት የእስር ቆይታ በኋላ አሜሪካ ሄደው ወያኔ በሰላማዊ ትግል ብቻ ስልጣን አንደማይለቅ በተግባር አረጋግጠናል፤ነጻነት ከተመኘን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ አንባገነን አገዛዝ አንዲላቀቅ የምንፈልግ ከሆነ ትግሉ ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት ብለው ግንቦት 7ን ሲመሰርቱም ጡንቻ ወለድ የሆኑ ቃላት አልተሰሙባቸውም፡፡ አሸባሪ ተብለው በሌሉበት ተከሰው ሞት ቢፈርድባቸውም የጥላቻና የበቀል ስሜት አልተንጸባረቀባቸውም፡፡
እነሆ ልክ ከላይ የገለጽኩትን ቃል በተናገሩ አስር አመት (በምርጫ ማግስት መሆኑም ያመሳስለዋል) የጠመንጃውን ትግል ለመምራት ወደ አስመራ ሲያመሩ፤ ..ደም መፋሰስ ውስጥ ሳንገባ የሀገራችንን ችግር ቁጭ ብለን በመነጋገር ብንፈታ እንወድ ነበር.ይህ ጦርነት ወደንና ፈቅደን ሳይሆን በወያኔ እብሪት ተገደን የገባንበት በመሆኑ ገደልን እያልን የምንፎክርበት አይደለም፡፡ ከሁለታችንም የሚሞተው ወገን በመሆኑ እናዝናለን፤ አሁን ቢሆን ወያኔዎች ለድርደር ፈቃደኛ ከሆኑ እኛ ጦርነት ምርጫችን አይደለም፤ወዘተ ማለታቸውን ሰማን፡፡ (ቃል በቃል አልጠቀስኩ ይሆናል) ይህም ዶ/ር ብርሀኑ የሚናገሩት በወቅታዊ ትኩሳት እየተገፉ፣ምን ብናገር አድማጭ ጆሮ አገኛለሁ በሚል ስልት ሳይሆን የሚያምኑበትን ለመሆኑ ይህ በትንሹ በአስር ዓመታ ውስጥ ከነገሮች መለዋወጥ ጋር ያልተለወጠው ንግግራቸው በቂ ማረጋገጫ ይመስለኛል፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደትና አመታት ያልተለወጠ አላማና እምነት ከዚህ በኋላ ይለወጣል ተብሎ ባይሰጋም በእምነት ዓላማቸው እንደጸኑ ለድል እንዲበቁና በኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፋች እንዲሆኑ ፈጣሪ ይርዳቸው፡፡
ነጻነቴን የምንል፤ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊት ሀገር ሆና ለማየት፣ (ለእኛ ባትደርስ ለልጆቻችን) የምንመኝ ዜጎችም በምኞትና በፍላጎት ብቻ የሚገኝ አይደለምና የዶ/ር ብርሀኑን ባታደልም በያለንበት በምንችለው ድጋፍ መስጠት ይገባናል፡፡ካልሆነም አደናቃፊ ከመሆን መቆጠብ፡፡
No comments:
Post a Comment