Friday, 19 July 2013

አለን ብለን እንዳናወራ!


ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
“እናት ሀገሬ ኢትዮጵያ አንዲት ናት!” ብሎ ለአሃዳዊ ግዛቷ ዐፄ ቴዎድሮስ ቆላ ደጋ የተንከራተተላት ኢትዮጵያ፣ “ኢትዮጵያዬ…” እያለ ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በ‹ጃ ያስተሰርያል› አልበሙ የሚያለቅስላት ኢትዮጵያ፣ “እምዬ ኢትዮጵያ … ተራራሽ አየሩ…” እያለ ቴዎድሮስ ታደሰ ያቀነቀነላት ኢትዮጵያ፣ … አሁን የገባችበትን ማጥ ስናይ ናላችን የሚበጠበጥ የወዲያኛው ትውልድ አባላት ጥቂቶች አይደለንም፡፡ በሀገር ውስጥ የምኖረው እኔ ለጉድ የጎለተኝ ሰውዬ በዐይኔ በብረቱ የማየውን ሀገራዊ ስንክሣር xenedtlmdwe እንደተለመደው ጥቂት ላዋራችሁ ነውና ትንሽ ትቆዝሙ ዘንድ ፈቃዳችሁ ይሁንልኝ፡፡


በመጀመሪያ ‹ኢትዮጵያ ዐፄው ህመሟን አባባሱባት – ደርጉ ጣዕረ ሞቷን አጣደፈው – ወያኔው ገደላትና ቀበራት› በሚለው የብዙዎች እሳቤ የማምን መሆኔን መግለጽ እወዳለሁ – እየሞቱ ይሉኝታ የለም፡፡ ትንሣኤ ሙታን የመኖሩ ዕድል በታሳቢነት ተይዞልኝ የዘመኑ ግልጽ እውነት ታዲያን እንደዚያ ይመስለኛል፡፡ ይህችን ሀገር አንዳቸው ከአንዳቸው እየተቀባበሉ ወረደ መቃብሯን እንዳፋጠኑት ለማንም ግልጽ ነው፡፡ በአገዛዛቸው ወቅት የሚለብሱት ፖለቲካዊ ካባ ይለያይ እንጂ፣ በሀገርና በሕዝብ ያደረሱት ወይ የሚያደርሱት ጥፋትና በደል በደረጃ አይመሳሰል እንጂ፣ ለሕዝብና ለሀገር ያላቸው ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት የአንዳቸው ከአንዳቸው በተለይም የሁለቱ ከሦስተኛው የሚቀራረብ አይሁን እንጂ ለጥፋተኝነቱ ሁሉም በየደረጃው ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በቀ.ኃ. ሥላሤ ህመሟ እንደጸናባት፣ በደርግ ጣዕረ ሞት ውስጥ እንደገባችና በወያኔው የማፊያ ቡድን የከፋፍለህ አውድም ዘመነ ጽልመት ደግሞ ለይቶላት እንደሞተችና በምዕራባውያንና ምሥራቃውያን የፖለቲካ ሊቃነ ጳጳሣት ጉዞ ፍትሓት አማካይነት የቀብር ሥነ ሥርዓቷ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ መመሥከር ይቻላል፡፡ (ዐፄው በሥልት ያስወገዷቸውን አንጎሎች፣ ደርጉ በምሕረት የለሽ ጭካኔው የጨፈጨፋቸውን ሀገር ገምቢ ወጣቶችና የጦር አበጋዞች ስናስታውስ የመረገማችን ዕዳና ባሳለፍናቸው ጥቂት የማይባሉ አሠርት ዓመታት ውስጥ የዕዳችን ተከፍሎ አለማለቅ ክፉኛ ይሰማናል፤ አለመታደላችን በሚያስከትልብን ጸጸትም ለማንወጣው ውስጣዊ ቁጣ እንዳረጋለን – ጨጓራን ለመላጥ፡፡ የቀደሙት ሁለቱ አመቻችተውት በሄዱት ገላጣ ቦታ ላይ ወያኔ ያለ ተቀናቃኝ ጉብ አለበት፤ ይሄ የወያኔ ጥፋት አይደለም፡፡ ጥፋቱ መደላድሉን አበጅተው የጠፉት ወገኖች ነው፡፡ ሀገር በስንት ወጪ ያሰለጠነቻቸውን በተለያዬ የሙያ ዘርፍ የሰለጠኑ ምሁራንን በቀይ ሽብር መፍጀትና በርካታ የጦርና የፖሊስ ጄኔራሎችን በአንድ ቀን ጀምበር መረሸን ማለት የጠላትን የ500 ዓመት ጦርነት በ500 ዓመታት ማሳጠር ማለት መሆኑን ዛሬ ላይ ሆነን ሳይሆን ያኔውኑ ማሰብ ይገባ ነበር፡፡ ለአንድ ሰው የሥልጣን ጥም እርካታ ወይም ወንዝ ለማያሻግር ርዕዮተ ዓለማዊ ፍልስፍና ሲባል ሀገር ጠፋች፤ ወገን ተሰደደ፤ ርሀብና ድርቅ፣ ጦርነትና ግዞት ባል ሆኑ፤ በስተመጨረሻም ዘረኝነትና ጎጠኝነት አዲስ የፖለቲካ ዘይቤ ሆነው በመተከላቸው አካማሌ ሆነን ከሀገርም ከሰውም ተራ ወጥተን ቀረን፡፡)
ትናንትና ወደ አንድ ወንድሜ ቤት ሄድኩ፡፡ ወንድሜ የምለው ላለማራቅ እንጂ የብዙ ዘመን ጓደኛየ ነው፡፡ እቤቱ ስደርስ የአሥር ዓመት ዕድሜ ልጁን አጠገቡ አስቀምጦ ጋቢውን ለብሶ ልቅሶ የተቀመጠ መስሏል፡፡ የወረወርኩለትን የተለመደ ሰላምታም በቅጡ ሊቀበለኝ አልቻለም፡፡ ደነገጥኩ፡፡ “እንዲህ ሆነን ዐረፍነው!” ይለኛል – የሚለው ሳይሆን ያለበት ምክንያት ሳይገባኝ፡፡
“ይሄውልህ ዳግምዬ፡- ጉዴን ስማልኝ – አሁን እኔ ሰው ነኝ? ከአሁን በኋላስ በሕይወት መኖር አለብኝ? ሀገርስ አለኝ? መንግሥትስ አለኝ? ኧረ ምንድን ነኝ ለመሆኑ? ወዴት እየሄድን ነው? ከእንግዲህ ምን ይዋጠኝ? …”
መነሻው በማይታወቅ የብሶት እሩምታ ብዙ መቆየቱ አስጨነቀኝና አቋርጬው “እንዴ! ምን ሆነሃል? አለወትሮህ ዛሬ ምን ነክቶሃል?” ስል ጠየቅሁት፡፡ ሊያዳምጠኝ አልቻለም፡፡ ብሶቱን ማዥጎድጎዱን ቀጠለ፡፡ የአፍንጫና የጉንጭ አምላክ ባይታደጋቸው ኖሮ በሚያስፈራ አኳኋን ተጉረጥርጠው ከማኅደራቸውም ወጥተው የሚታዩት ዐይኖቹ ወደመሬት ወርደው ሊፈጠፈጡ ምንም አልቀራቸውም፡፡ እንዲሰክን ውትወታየን አላቋረጥኩም፤ ተሳካልኝ – ቀስ እያለ በረድ ማለት ጀመረ፡፡
“ይሄውልህ፡፡ እንደምታውቀው ይህ የመጨረሻው ልጄ ነው፡፡ ዕድሜው አሥራ አንድ ዓመት ነው፡፡ ገቢየ አነስተኛ በመሆኑ የማስተምረው በመንግሥት ትምህርት ቤት ነው፡፡ እንደ መጥፎ ልማድ ሆኖብኝ ልጆቼን የመከታተል ባህል ከዱሮውም  አላዳበርኩም፡፡ በዚህ አዝናለሁ፡፡ በስንትና ስንት ሀገራዊና የመሥሪያ ቤት ችግር ስለምወጣጠር እቤት ገብቼ እንደብዙ አባቶችና እናቶች ‹ዛሬ ምን ተማርክ? ሰሞኑን ምን ተማርሽ?› ማለቱን አላዘወተርኩም – እንዲያው በደፈናው እመክራለሁ ፣ እንዲተጉ አስጠነቅቃለሁ እንጂ ጠለቅ ብዬ የምከታተለው ነገር የለኝም፡፡ እናታቸውም ከኔ የበለጠች ሰነፍና ዝንጉ ናት፡፡ ዛሬ ታዲያ በጋው ከመድረሱ እስኪ አንዳንድ ነገር ላስጠናው ብዬልህ መጽሐፍ ገዝቼ ላስነብበው ስል በመጪው የ2006 መስከረም አምስተኛ ክፍል የሚገባ ልጅ ከነአካቴው ማንበብ አይችልም፡፡ እነ ‹ጀ፣ኀ፣ኸ፣ጨ፣ጰ›ን ይቅርና የ‹ሀ›ንና የ‹ለ›ን ዘሮች እንኳን አልለየም፡፡ እንግሊዝኛውንማ ተወው፡፡ ይገርምሃል – የመጀመሪያውን ሆሄ ስትጠራለት ብቻ በሽምደዳ የያዘውን እንደበቀቀን ያነበንባል እንጂ ፊደላቱን ለይቶ በዘር በዘራቸው አያውቃቸውም፤ በዚያም ምክንያት ማንበብ ፈጽሞ አይችልም፡፡ ይሄ ታዲያ አያሳንቅም ትላለህ? ሞት ሲያንሰኝ ነው!”
ችግሩ አሁን ገባኝ፡፡ ‹ያሳንቃል› ብዬ አስተያየቴን ለመስጠት ግን ከበደኝ – ሆድ ለባሰው ማጭድ አታወሰው ይባላል፡፡ ወዳጄ ዛሬ ገና አንድ ነገር የገባው ይመስላል፡፡ በየቤታችን ያለውን ጉድ ቢሰማ ምን ሊል ነው? በደመ ነፍስ የምትነዳ ሀገር ውስጥ መኖራችን ዛሬ ገና ነው የታየው መሰለኝ፡፡ አሁን ምን ማድረግ እንደሚችል አላውቅም፡፡ ምን ብዬ እንደምመክረውም ግራ ገባኝ፡፡ “የምትችለውን አድርግለት እንጂ ያን ያህል ዕብድ አትሁን፤ አንተ ብታብድ ልጆችህም አንተም ሁላችሁም ትጎዳላችሁ እንጂ የሚጠቀም የለም፤ አይዞህ – በሁላችንም ቤት ያለ ነው” እያልኩ አጽናናው ገባሁ፡፡ ብዙ አብነቶችንም እየጠቀስኩ ያለንበት አደገኛ ሁኔታ እገልጥለት ያዝኩ፡፡
ይሄውልህ – የአንድ ዘመዴ ሴት ልጅ ሰባተኛ ክፍል ደርሳለች፡፡ በዕውቀት ግን አዲስ ከተወለደ እንኳን ሕጻን አትሻልም፡፡ አታነብም፤ አትጽፍም፡፡ ግነት እንዳይመስልህ – አታነብም ፤ አትጽፍምም፡፡ እንዴት ሰባተኛ ክፍል ደረሰች ብሎ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ይህን ጥያቄ የሚመልስልን ግን ጊዜው ሲደርስ ራሱ ወያኔ ይሆናል – ለአሁኑ ግን “ ባልተማረ መምህር ስለሚማሩ፣ በአብዛኛው የሙያና የሀገር ፍቅር በሌለውና አነስተኛ ክፍያ በሚከፈለው  መምህር ስለሚማሩ…” ብለን እናልፋለን፡፡ በሠፈሩት ቁና መሠፈር አለና ያኔ እነማን ማይም ሆነው ቀርተው እነማን እንደተማሩ፣ እነማን መንገድ ጠራጊ ሆነው ቀርተው እነማን መሀንዲስና ዶክተሮች ሆነው ከፍተኛ ደረጃ እንደተቆጣጠሩ ሲጠየቁ ወያኔዎች ራሳቸው ሊመልሱት የሚገደዱበት ምድራዊና መለኮታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ሰው ለሆነ ፍጡር የኢትዮጵያ ሁኔታ እጅግ የሚዘገንን ነው፡፡ ጣሊያን እንኳን ይህን ያህል አልጨከነም፤ ይህን ያህል ሕዝብን አላደደበም፤ ይህን ያህል ሰውን ከእንስሳት በታች ቆጥሮ ወደ ድንጋይነት አልለወጠም፡፡ ይህን ያህል ዜጎችን ለይቶ አንዱን በሃሳብም በቋንቋም እንዲበለጽግ ሌላውን በሁሉም እንዲደኸይ አላደረገም፡፡ የወያኔን ይህን መሰል ኃጢኣትም እንበለው ወንጀል ሰይጣን ራሱም ቢሆን ከአሁን ቀደምም ሆነ ወደፊት ሊሠራው አንጀቱ የሚጨክንለት አይመስለኝም፡፡ የነዚህ ወያኔዎች አንጀት የተሠራው ግን አይገባኝም፤ ምናልባት ከጅብ ቆዳና ከባሌስትራ ሳይሆን አይቀርም፡፡
እኔ ያጽናናሁት እየመሰለኝ እንዲህና እንዲያ እያልኩ የማውቀውንም የሰማሁትንም ዘለባበድኩለት፡፡ በዲግሪ ከተመረቁ ወጣቶች ብዙዎቹ ስማቸውን በእንግሊዝኛ ይቅርና በሌላ በቅርብ በሚያውቁት ሀገርኛ ቋንቋ አስተካክለው እንደማይጽፉ አከልኩለት፡፡ ዛሬ ዛሬ ዕድሜ ለወያኔ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ይቅሩና የኮሌጅ ተማሪዎች ሳይቀሩ የለዬላቸው ማይማን ናቸው፡፡ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ የሚበረታቱት ጫት ቤት እንዲውሉ፣ ሺሻ እንዲምጉ፣ አረቂና ጠላ እየተጋቱ በመስከር ጭንቅላታቸውን እንዲያላሽቁ፣ ሀሽሽና ቁማር ቤት እንዲያዘወትሩ፣ ከሃይማኖትና ከሞራል እንዲያፈነግጡ፣ ወጥ ማንነት ኖሯቸው ለአብሮነት የጋራ ሕይወት እንዳይጥሩ ነው…፡፡ ወያኔ የውጪ ወራሪ ኃይል ይመስል ከውጪ ወራሪና ቅኚ ገዢም በከፋ ደረጃ የራሴ በሚላቸው “ሕዝቦቹ” ላይ እየፈጸመ የሚገኘው ግፍና በደል ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ ለዚህም ነው የሀገሩ ባንዲራ የተበጣጠቀችበት ወጣቱ ትውልድ በማንነት ኪሣራ እየዳከረ የራሱን ሰንደቅ ሳይሆን በህልም የሚቀላውጣቸውን የፈረንጆችን ዕራፊ ጨርቅ የሚመስል ባንዲራ ግንባሩ ላይ አሥሮ የሚታየው፤ ለዚህም ነው ወጣቱ የአነጋገር ሥልቱ፣ አካሄዱና አለባበሱ ሳይቀር በፊልም የሚያየውን እየኮረጀ ከነሱም ከራሱም ሳይሆን በመሀል ከራዳር እንደወጣ አውሮፕላንና ኮምፓስ እንደሌላት መርከብ የትሚናውን ጠፍቶ ራሱንም ለመፈለግ ፍላጎት አጥቶ በሁለት ዓለማት ስብዕና እየባዘነ የሚታየው፡፡ ምን አለ በለኝ – ወጣቱን ለዚህ ያበቁት ወያኔዎችና ለወያኔዎች ምቹ ሁኔታን የፈጠሩ እርጉማን ሁሉ ዋጋቸው ይሠፈራል፡፡
ወዳጄን ለማስተዛዘን በምሥጢር መያዝ የሚገባኝን ብዙ ዘግናኝ ሀገራዊ እውነቶችን ዘከዘክሁለት – ሴትዮዋ ‹መንግጌ አባስኳት› እንዳለችው ጓደኛየ ሶበረልኝ ብዬ ላጥናናው በምነግረው እውነተኛም የተጋነነም ታሪክ በቀላሉ ሊጽናናልኝ ግን አልቻለም፤ “ወደዚህ ቤት ያመጣኝን እግሬን በሰበረው” አልኩና ተማረርኩ – መማረር ችግርን የሚፈታ ይመስል፡፡
እኔ ግን ቀጠልኩ፤ አልኩም፡- ቢኤውን ከያዘ ገና አራት ዓመት በቅጡ ያልደፈነ የአንድ ጓደኛየ ልጅ ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በማስተርስ ዲግሪ ይመረቅና ማመልከቻ እንድጽፍለት ወደኔ ዘንድ ይመጣል፡፡ ይህን ምን ይሉታል?
ማመልከቻ ጻፍልኝ፤
የምን ማመልከቻ?
የሥራ ማመልከቻ፤
ለየትኛው መሥሪያ ቤት?
ለ … ት/ቤት ነው የምትጽፍልኝ፤ አንድ የእንግሊዝኛ መምህር ይፈልጋሉ አሉ፤ በራፖርተር ጋዜጣ ወጥቷል፡፡
በ‹ሪፖርተር› ማለትህ ነው? ታዲያ አንተው አትጽፍም እንዴ? በቋንቋ አይደል እንዴ የተመረቅኸው?
አይ፣ ግዴለህም አንተው ጻፈውና ባይሆን እኔ የምጨምረውን እጨምራለሁ ወይ እቀንሳለሁ፡፡
የለም፣ እንደሱማ አይሆንም፤ አንተው ጻፍና እኔ ኋላ ላይ ልይልህ፡፡
በዚህ ተስማማንና የሚከተለውን የማመልከቻ ደብዳቤ በእንግሊዝኛ ጽፎ አሳየኝ፡፡
Deer Sirs or deer madams:
I was written these letter for apply to the teacher post advertising on the reporters newspaper printed dated on julay 18, 2013(hamillie 11/2005). I am interesting to hire you in your school, if possible.
My name is Gudayehu Zendro and I am 27 old. I am graduation from Addis Ababa University in MA degree for about english. I can writting  and speeking English very good and I can teaches these languge on your school if you gives me the chances to accepted me their and allow me to work with no matter salary amount to paid me.
As high school english teacher, I worked in Zebider school for 2 yers. On top of that I have been written two modules and I have been served another school for six months. And I had made unit ledder their four a month.
If you chose or selects me to your butifull school, by the way I love it, I will is happy to becoming interviewed on your inconvenient time and don’t afraid me to contact me anytime you may dislikes.
Semisterly yours,
Tank you very match
ማሽላ እያረረ ይስቃል እንላለን – አበውም ይሉት ነበር፡፡ ይህ ማመልከቻ ቀልድ ቀመስ መሆኑን የሚያጣው ያለ አይመስለኝም – ግን ጠጣር እውነትን ያዘለ ነው፡፡ አንድ ሂስ እቀበላለሁ – ‹ትንሽ ጨከን ብለሃል› ለሚለኝ እውነት ነው እላለሁ፤ የጨከንኩ ይመስላል፡፡ ሆድ ቢብሰኝ ነውና አትታዘቡኝ፡፡ ነገር ግን መሬት ላይ ያለው እውነት ከዚህ ብዙም የሚለይ እንዳልሆነ ብዙ ተጨባጭ ማስረጃዎችን በማቅረብ ማስረዳት ይቻላል፡፡ ከበርካታ ‹ምሁራን› ይህን መሰል ወይም ወደዚህ የሚጠጋ አስደንጋጭ የማመልከቻ ወይም የሌላ ጉዳይ ጽሑፎችን ማየት ከጀመርን ውለን አድረናል፡፡ ዘመኑ የቴክሎጂ በመሆኑ ዕድሜ ለዚህ ለኮፒ/ፔስት አዳሜ ከየድረገ ገጹ እየኮረጀ ወይም በተቀጣሪ አሰለጦች እያሠራ በዲግሪ ይንበሸበሻል – ሥራው ዓለም ላይ ግን ከዜሮ በታች ነው – የዱሮ ስምንተኛ ክፍል የዛሬን የዲግሪ ምሩቅ ሰጥ ለጥ አድርጎ ያሰለጥነዋል ይባላል፡፡ በቴክኒክ ሥራዎች ከሆነ በተለይ ልዩነታቸው ሰማይና መሬት ነው – ደመወዙ ግን ግፍ የሚታይበት ነው – ዲግሪ የሌለው ነገር ግን ሥራውን በዘመኑ ቋንቋ አድምቶ የሚሠራው የሚከፈለው መሃያ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ እይዐርግ እይወርድ – ወጣም ወረደ – ይህ በወያኔ ሆን ተብሎ የታወጀ የትምህርት ጥራት ዝቅጠት – መቅሰፍትም ሊባል ይችላል – ሀገሪቱን ሰው አልባ የሚያደርግና የነገ ሀገር ተረካቢ የሚያሳጣ ከችግሮች ሁሉ የከፋው አደገኛ ችግር ነው – ርሀብና ጠኔ የሚገድለው አካልን ነው፤ ያልፍማል፡፡ የትምህርት ጉዳይ ግን ከሀገር ኅልውና መቀጠል አለመቀጠል ጋር በቀጥታ የተቆራኘና መንፈስን የሚገድል ነው፡፡ ብዙዎቻችን በዚህ ረገድ ጠፍተናል፡፡ያልጠፋን እንዳይመስለን፡፡
በዚህ ላይ አንድ አስገራሚ ነገር ለመጨመር ያህል – የዘመኑ ምሩቃን አለማወቃቸውን በጭራሽ አያውቁም፡፡ አለማወቅን አለማወቅ የመሰለ ጠንቀኛ ችግር ደግሞ የለም፤ አለማወቅን አለማወቅ አንድም ዕብሪታዊ ደደብነት ነው አንድም ትዕቢት ነው – ወይም የሁለቱ ቅልቅልም ሊሆን ይችላል፡፡ አለማወቅን አለማወቅ ያልታወቀ በሽታ እንደማለት ነው – መድሓኒት የማይገኝለት፡፡ በሁሉ ዘርፍ ሀገር እየጠፋች የምትገኘው አለማወቃቸውን ባለማወቅ እነሱ የሚያውቁት ሁሉ እንደትክክለኛ ዕውቀት እንዲወሰድ በሚፈልጉ ጭንቅላታቸው በትምክህት ሞራ ወይም በማይምነት ጥቁር ሱቲ በተሸፈነ ሰዎች ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ማስታወቂያ የሚጽፍ ድርጅት ከደንበኛ የተሰጠውም እንኳን ቢሆን ተማክሮ ይለውጣል እንጂ ”enklish gramer school”  የሚል ማስታወቂያ ትልቅ ቢልቦርድ ላይ ጽፎ ሊሰጥና በዕውቀትና ጥበብ አምባ ላይ ልግጫና ፌዝ እንዲበረታ ሊያደርግ አይገባም፡፡ በዚህ ረገድ የምናያቸው ብዙ ጥፋቶች እንግዲህ ‹ዕውቀት ከኔ በላይ ላሣር!› ባሉ የወቅቱ ምሁራን ወይም ‹ኮሌጅ የበጠስን ነን› በሚሉ ሰዎች የተሠሩ ናቸው ማለት ነው – መዝገበ ቃላትን እንኳን ማገላበጥ ማንን ገደለ? ኧረ ወዴት እየሄድን ነው ጎበዝ! ለማለት የፈለግሁት ይበልጥ ግልጽ እንዲሆን እፈልጋለሁ – አንሳሳት ወይም ሰው አይሳሳት እያልኩ አይደለም፡፡ ስንሳሳት ግን ስህተትን ባህላችን ለማድረግ ቆርጠን የተነሣን መሆናችንን በሚያሳብቅ ሁኔታ መሆን የለበትም ነው እያልኩ ያለሁኝ፡፡ እንጂ ያልሞተ ይሳሳታል -  ቆም ብሎና በምክክር ግን ይታረማል፡፡ የአሁኑ ዘመን ግን በሁሉም አቅጣጫ ሲመዘን ስህተት እንደቅቡል ይትበሃል በመንሠራፋት ላይ የሚገኝ ይመስላል፡፡ መሳሳት እንደጀብድ የሚቆጠርበት ዘመን ላይ ሳንገኝ አልቀረንም፡፡ ሰውን ስህተቱን ስትነግረው ‹ምን ይጠበስልህ!› ለማለት “So what?” ይልሃል፤ ታፍራለህ – ትደነግጥማለህ፤ ለሌላ ጊዜ አፍህን በዳቦ ወይም ዳቦም ባቅሙ ካረረብህ በመዳፍህ ትይዛለህ፡፡ አቤት! አቤት! አቤት! ያለንበት ዘመን!!
የአዲስ አበባን የመንገድ ላይ ማስታወቂያዎችን፣ የንግድና የአግልግሎት ማግባቢያና ማሻሻጫ በራሪ ወረቀቶችን … ብንመለከት ብዙዎቹ የሚታዩባቸው የፊደላት ስህተትና የሃሳብ ፍሰት አለመጣጣም የወያኔው የማፊያ ቡድን ትምህርትን በማውደም ሀገርን ተረካቢ አልባ አድርጎ ለማስቀረት የነደፈው ዕቅድ ምን ያህል እንደተሳካለት ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም ለንግድ ቤቶችና ለትምህርት ቤቶች የሚሰጡ ስያሜዎችን ስንመለከት ሀገራችን ምን ያህል በማንነት ኪሣራ ውስጥ እንደተዘፈቀች እንረዳለን፡፡ በሀገር ውስጥ እያሉ በሀገር ውስጥ መኖራቸውን ማመን በማይፈልጉ ኢትዮጵያውያን ለልጆች የሚወጡ ስሞችና ለተቋማት የሚሰጡ መጠሪያዎች በግልጽ የሚያሳዩን ነገር ቢኖር ከሞላ ጎደል ሁሉም ሰው በገዛ ሀገሩና በገዛ ቋንቋና ባህሉ ላይ ማመጹን ወይም መሸፈቱን ነው፡፡ አለበለዚያ እነታንጉትና አንጓች እነጫልቱና ዘርመጪት ተዘንግተው ባልጠፋ የሰው ስም ‹ሊሊ፣ ቲቲ፣ሊዱ› ባልተባለ፤ ባልጠፋ የትምህርት ቤት ስም ‘School of Americana’ ፣ እነመቻልና ቡቺ ተረስተው ባልጠፋ የውሻ ስም ‹ጃኪ. ሮኪ› ባልተባለ፣ ባልጠፋ ሀገርኛ የንግድ ቤት ስም ‘ቴክሳስ ጫማ ቤት›ና ‹አልባንያ ቁርስ ቤት’ ማለቱም ለትዝብት ከመዳረግ ውጪ የሚፈይደው አንዳች ነገር እንደሌለ በታወቀ፡፡ ቦሌ መንገድ ብትሄድ ከቋንቋው ጀምሮ አለባበሱና የሰውነት መለወጫ ኮስሞቲክሱ ድረስ ሲታይ “ኢትዮጵያ ውስጥ ነው እንዴ ያለሁት? ለመሆኑ ይህች ሀገር የማን ናት?› ማለትህ አይቀርም – እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ፤ የውጪውማ ቢያንስ ርቀዋልና ግዴለም ሊባል ይችላል፡፡ የትናንት አበቅየለሽ ወይ አምለሰት ዛሬ ቦሌ ገብታ በሞተ ከዳ የነጭ ጋለሞታዎች ፀጉርና ሰይጣናዊ ቅብዓ-ርኩስ ፈረንጅ መስላና ስሟን ወደ ቲና ለውጣ መቀመጫዎቿን ቆላ ደጋ ደንገላሣ እያዝበጠበጠች ስታዩ በትውልዱ የቁም ሞት ታለቅሳላችሁ – ወይኔ ምነው ይህን ሳላይ እንዳያት ቅድማያቶቼ አፈር ውስጥ ገብቼ በመሸግሁ – እያላችሁ፤ ‹ይህችን ሀገር ማን ነው የሚረከብ?› ብላችሁም የሚረከባት የሚጠፋ ይመስል በ‹ከንቱ› ልትጨነቁ ትችላላችሁ – ‹ይብላኝ ለእኛ እንጂ ተረክቦ የሚግጥ ውሻና ግሪሣማ መች ጠፍቶ ያውቅና!› ለማለት ፈልጌ ነበር ግን ቀና ሀገራዊና ሕዝባዊ ዓላማቸውን ያልተረዳሁላቸው መስያቸው ከወደፊት መሪዎቼ ጋር ያቃርነኛልና ይሄኛውስ ይቅርብኝ – ግን ግን ሳስበው ‹ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከምቢያው ቂጢጥ› እያለ ተቸገርን እኮ ምዕመናን፡፡ መጥኔ ለሚቆዩ! መጥኔ ለወጣቶች፡፡
ጎበዝ – ተወርረናል! እነዚህ ወያላ ወያኔዎች ሀገራችንን ሙሉ በሙሉ አዋርደዋታል፡፡ ሰው ራሱንና ሀገሩን እስኪጸየፍና አምርሮ እስኪጠላ በሀገሩ ላይ አመጽ እንዲያስነሳ አስገድደውታል፡፡ ከቦሌ እስከ ጉለሌ፣ ከኮተቤ እስከ ካራቆሬ፣ ከሳሪስ እስከ እንጦጦ መላዋን አዲስ አበባ ብትጎበኙ ብዙ ጉድ ታያላችሁ፡፡ ቋንቋችንን መጠየፍ፣ ባህላችንን መጠየፍ፣ ራሳችንን መጠየፍ፣ አብሮነታችንን መጠየፍ፣ መተሳሰብንና መተዛዘንን መጠየፍ፣ ሰብኣዊነትን መጠየፍ፣ ወገናዊ ፍቅርን መጠየፍ፣ ዕውቀትን መጠየፍ፣ ጥበብን መጠየፍ፣ ዕርቅን መጠየፍ፣ ተቻችሎ መኖርን መጠየፍ፣ አማራ ትግሬን መጠየፍ፣ ትግሬ አማራን መጠየፍ፣ ኦሮሞ – አማራ – ትግሬ – እርስ በርስ መጠያየፍ… ሁሉን መልካም ነገሮች መጠየፍ አብዝተናል፡፡ የእርግማኑ ዑደታዊ ጡዘት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከርሯል – ለጤናም አይመስልም ፡፡ በምትኩ በራስ ወዳድነትና በግለኝነት ሱስ መለከፍ፣ በሴሰኝነት ዳንኪራ መጠመድ፣ በሥልጣን አራራ መቃተት፣ በዘረኝነት የደዌ  ልክፍት መንጠራወዝ የዘመኑ ፋሽናችን የሆኑ ይመስላል፡፡ (በነገራችን ላይ በአዲሱ የወያኔ ቤተ ሙከራዊ የሕዝብ ቆጠራ ትግራይ ክልል የመሪነቱን ሥርፋ – ማለትም ሥፍራ – ስትይዝ ሶማሌ ሁለተኛ – ኦሮሞ ሦስተኛ – አማራ አራተኛ እንደሆኑ ሰማሁ፡፡ የዕብድ ቀን አይመሽም፡፡ የወያኔ ቀንም አልመሽ ብሎ በቴዲ አፍሮ ምናባዊ ግሩም አገላለጽ – በእያነቡ እስክስታ ውስጣችን እያረረና በሀዘን እየተኮማተረ በዕድለቢሶቹ የወያኔ ተውኔቶች ግን መገልፈጣችንን ቀጥለናል – አንድ ቀን እንኳን ተኣማኒ ትያትር መድረስ እንዴት ያቅታቸዋል? ለምን ሰው አይቀጥሩም፡፡ ይህን የ‹ቁጥር መበላለጥ› አሁን ቢያስጠጉት፣ ትንሽ ቆይተው ቢያቀርቡት፣ ከዛም ቢደርቡት… አሁን ምን አጣደፋቸው? ለነገሩ ማን ነው ወንዱ “ የጅብ ችኩል …” ብሎ ስማቸውን በከንቱ የሚያነሳ ? ከፉኛ ንቀውናል እኮ!
አነሳሴ ትምህርት ሞታለች ነው፡፡ በአዲስ አበባ ሁለት ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ልጠቁም፡፡ እጅግ ውድ የሆኑ የግል ት/ቤቶችና የመንግሥት የሚባሉ የተዋጣላቸው ትውልድ ገዳይ ት/ቤቶች፡፡ የግሎቹ ዋጋቸው ለድሃው ቀርቶ ለንዑስ ከበርቴ ተብዬውም አይቀመሱም፡፡ የማኅበረሰብ ክፍፍሉ ሁለት መደብ ሆኗል – አንድም ያለው አንድም የሌለው፡፡ በያለውና በየሌለው መካከል ያለው ክፍተት የሰማይና ምድርን ርቀት ያስከነዳል፡፡ በድሆች ትምህርት ቤት ከነአካቴው ትምህርት የለም ማለት እንችላለን – ያለው ኮታና ቀልድ ነው፡፡ ወያኔ ለወሽካታው የእስታትስቲክስ መዝገቡ ሲል ይህን ያህል ት/ቤት ተከፈተ፤ ይህን ያህል ልጅ ተመዘገበ … ለሚለው የማስመሰያና ፈንድ ማወራረጃ ድራማው እንጂ ከአንጀት አዝኖ ትውልድን በተገቢው ዕውቀት ለመቅረጽ የሚፈልግ መንግሥት አይደለም፡፡ የትምህርት አመራሩ በጠቅላላውና በየትኛውም እርከን በወያኔዎች መያዙ ችግር እንደሌለው ቆጥረን ሥራው ሲታይ ግን የግብር ይውጣና እውነትም የጠላት ሤራ ትግበራ ይመስላል፡፡ የትምህርት ባለሞያ ይባልና ሰውዬው የሰለጠነው ግን ውትድርና ወይም ቆዳ አፋፋቅና ዓሣ ማስገር ሊሆን ይችላል፡፡ ለነገሩ የፖሊስ አዛዥን የትራንስፖርት ሚኒስትር ከማድረግ የማይመለስ የጉዶች መንግሥት እንጨት ጠራቢን አልጋ አንጣፊ፣ የቢሮ ጸሐፊን ገንዳ ጠባቂ አድርጎ ቢመድብ አይገደውም – አድርገውታልም፡፡ ዋና ዓላማው ሀገርን ማውደምና ትውልድን በቀቢጸ ተስፋ ሀሽሽ ማደንዘዝ፣ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተብዬውንም በሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ማታለል ነው፡፡ ይህ ሀገራዊ አሳዛኝ ቲያትር እስከመቼ ይዘልቃል? ጊዜና እግዚአብሔር የሚፈቱት ነው፡፡ እኛ ግን ግዴለም ዝም ብለን በባዶ ቦታ እንፋጅ፤ ባገኘነውም መድረክ ሁሉ እናምቧትር – ሕዝቡንም ከምጣድ በማይወጣ የተስፋ ዳቦ እንቀብትት፡፡ አየ እኛ!! መጨረሻችንን ያዬ፡፡
በግሉ ዘርፍ ብዙ ት/ቤቶች አሉ – ጥሩዎችም አስመሳዮችም፤ በጣም ውዶችም መለስተኛ ውዶችም (ወላጅን ለማታለል በተማሪ መግቢያና መውጫ ሰዓት ያልተማረ ደንቆሮ ፈረንጅ ቀጥረው በር አካባቢ የሚያቆሙ ት/ቤቶች እንዳሉ ሰምታችኋል? ለማስታወቂያ፡፡ የገዛውን ትልቅ አሮጌ አውቶቡስ ያላንዳች ሥራ ባዶውን ከተማዋን የሚያዞር የኮሌጅ ባለቤት እንዳለስ ታውቁ ነበር? ከመሪ እስከ ነጋዴ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ፣ ከነጭ እስከ ቢጫ – ደካማ ሥነ ልቦናችንን የማይጠቀም የለም፡፡) በነዚህ የግል ትምህርት ቤቶች ከሚማሩት ተማሪዎች ውስጥ በጨዋ ግምት ከ90 በመቶ የማያንሱት የወያኔ ልጆች መሆናቸው በስፋት ይወራል፡፡ ሌላው አቅም ስለሌለው ልጆቹን የሚልከው አንድም ወደ መንግሥት ት/ቤቶች አለዚያም ወደሸቅልና ወደ ጎዳና ተዳዳሪነት – ወደሽርሙጥና – እልፍ ሲልም ወዳረብ አገር ግርድና … ነው፤ በወያኔ አልፎልናል(ሴቷ ልጄ ለአቅመ -ዐረብ ግርድና አልደርስ ብላኝ ተቸግሬያለሁ – ወያኔ ሌላ ምን አመጣልኝ?)
[ኅያው አባት ቅዱስ እግዚአብሔር ሆይ! የኔን የባርያህንና የመሰል ወንድምና እህት ኢትዮጵያውያን ወገኖቼን ዕንባ አብስ! በቃችሁ በለንና ከነዚህ የሲዖል ትሎች ነጻ የወጣን እንድንሆን አድርገን፤ ከዚህ ውጥንቅጥና የተደራረበ ችግር የሚያወጣን በቅዱስ መንፈስህ የሚመራ አንድ ሙሤያዊ ኃይል በአፋጣኝ ላክልን፤ እንደኛ የኃጢኣት ቁልል ሣይሆን እንደምሕረትህ ብዛት ይሁንልን፤ አሜን፡፡]
ኢትዮጵያ ሳያናግሯት ብዙ እየተናገረች ናት፡፡ ወደ በረንዳዎች ሂዱ፤ ወደ ት/ቤቶችም ሂዱ፤ ወደ ንግድ ቤቶች ሂዱ፤ ወደ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሂዱ… ብቻ እናንተ ለመሄድ አትሰልቹ እንጂ ወደ የትም ሂዱ፡፡ ወደ ገጠርም ውጡ፤ ወደከተሞችም ግቡ፡፡ በምትሄዱባቸው ጥቅም የሚያስገኙ ቦታዎች ሁሉ ቀድመው የሚጠብቋችሁ ወያኔዎች ናቸው – ‹የታገልንበት የደም ዋጋችን ነው› እያሉ በግልጽ ሲቦጠቡጡ ታያላችሁ፡፡ በዚህ ታሪካዊ ስብራታችን ልባችሁ ይነካል፡፡ ‹ሰው እንዴቱን ያህል ክፉ ቢሆን ነው መሰል ወንድሞቹንና እህቶቹን ከሁሉም ማዕዶች አውጥቶ በኅሊናዊና እውናዊ ርሀብ እየገረፈ የራሱን ኑሮ ብቻ የሚያመቻቸው?› ብላችሁ ለሰው ልጅ አጠቃላይ ተፈጥሮ ትጨነቃላችሁ፡፡ ይህን ግላዊ ምቾቱን ለማረጋገጥ ሲልም የሚሠራውን የመቶና የሁለት መቶ ዓመታት ሲአይኤያዊና ሞሳዳዊ ሸርና ተንኮል ስታስቡ ደግነቱ እግዚአብሔር በመሃል በመኖሩ እንጂ ተስፋ ቆርጣችሁ እናንተም የክፋትን መንገድ ልትከተሉ ትከጅላላችሁ፡፡ ግን እንተማመን – እንደጠቢቡ አባባል ሁሉም ነገር ከንቱና የከንቱ ከንቱ ነው፡፡
እዩልኝ እንግዲህ – በግል ት/ቤቶች የሚማሩ የወያኔ ልጆችን የማውቅበት መንገድ አለኝ፡፡ እውነት እላችኋለሁ – ቁም ነገረኛ ልጅ የወጣላቸውን ቱባ ወያኔዎች ማስታወስ አልችልም፤ ስም እያነሳሁ ማፍረጥረጥ ባላቃተኝ – ነውር ባይሆንብኝ፡፡ ገንዘብና ሥልጣን አላግባብ ከተያዘ እንደማባለጉ የነዚህ ወያኔዎች አብዛኞቹ ልጆች ገና ከአሁኑ ጠፍተዋል፡፡ ለመጥፋት የወላጆቻቸውን ዕድሜ ያህል መጠበቅ አላስፈለጋቸውም – አሸዋና ድንጋይ ላይ በዕለተ ሰንበት የተዘሩ የእርኩሳን ዝሪቶች ናቸውና፡፡ ሕዝብ የረገመው፣ ሀገር ያሳቀለው ዜጋ መቅኖ የለውምና እነዚህ ልጆች ምንም እንኳን በልዩ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ ቢመዘገቡም ገንዘቡ አናታቸው ላይ ወጥቶ ስላሰከራቸው አይማሩም፤ ትምህርት ቤት አይገቡም፤ ቢገቡም በዲሲፕሊን ችግር ት/ቤቱን ያውካሉ፡፡ ሊባረሩ ሲወሰን የትምህርት ቢሮ ባለሥልጣናት ከሚኒስትር ጀምሮ ተረባርበውና የት/ቤቶችን ባለቤቶች በ‹ት/ቤታችሁን እንዘጋባችኋለን› አስፈራርተው ራሳቸው ያወጡትንና ያሰራጩትን ሕግ በመጣስ ያስመልሷቸዋል፡፡ ሕግ በየትም አይሠራም፡፡ በትምህርትም ሆነ በሌላው ዘርፍ ወያኔን በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ የሚነካ ሕግ ሥራ ላይ አይውልም፡፡ ሀገሪቱ በወለድ አግድ በነሱው ሥር ስለዋለች ሕግ የሚሠራው ለሌሎች ምሥኪኖች እንጂ ለወያኔዎች አይደለም፡፡ የምለው የምታውቁትን እንደሆነ ባውቅም እንደመምሬ አውግቼው እየደጋገምኩ ላውጋችሁ ብዬ ነው፡፡ በዚህ እንኳን ቢወጣልኝ፡፡ ጨስን እኮ ምዕመናን!!
በአንድ ‹ምሁር› አነጋገር ፈገግ ላሰኛችሁ ልሞክርና አንዳንድ ነገሮችን ጣል ጣል አድርጌ ልሰናበታችሁ፡፡ ሰዎች አንዱን ጓደኛቸውን ሲተርቡት የሰማሁት እውነተኛ ታሪክ ማለትም ገጠመኝ  ነው፡፡ የዩኒቨርስቲ ጓደኛውን ለበርካታ ዓመታት ሳያየው የኖረ አንድ ሰው ያን ድራሹ የጠፋበትን ጓደኛውን መንገድ ላይ አገኘው አሉ፡፡ ያኔ እንደምንም ለየው(ዐወቀው)ና “እንዴ! አንተ እንትና የምትባለው የዩኒቨርስቲ ጓደኛየ አይደለህም እንዴ? በስማም! በጣም develop አድርገሃል፤ በድምጽህ እኮ ነው ያወቅሁህ!” ብሎት ዕርፍ፡፡ ምን ማለቱ መሰላችሁ ‹ ወፍረሃል፤ ተለውጠሃል፤ ተስማምቶሃል…› ማለቱ ነው፡፡ አንዱ ምሩቅ ደግሞ እንዲህ ብሏል አሉ፡- ‹ፐ ፐ ፐ ያ ልጅ እንዴት ያለው cooked የሆነ ልጅ መሰለህ!› – የዚህኛውስ ገባችሁ? የአማርኛውን በቀጥታ ተርጉሞ ‹በሳል ልጅ› ለማለት ነው፡፡ የወያኔን ጊዜ ምሁራን – ሁሉም አይደሉም በነገራችን ላይ – ገድል እንጻፈው ብንል አውሎ ያሳድረናል፡፡ እዚህ ላይ በራሳቸው ጥረት በግል በሚያደርጉት ጥናትና ምርምር ምክንያት ራሳቸውን በዕውቀት ያደረጁ፣ በየትኛውም የተሰማሩበት መስክ የማያሳፍሩ ወጣትና ጎልማሣ ምሁራን መኖራቸውን መጠቆም እፈልጋለሁ – በደረቅ አበሳ እርጥብ መቃጠል የለበትም፡፡ እነዚህኞቹ ወገኖች በልዩ ድካማቸውና ያልተቆጠበ ጥረታቸው ከወያኔ ሀገርንና ትውልድን የማምከን ሤራ ያመለጡ ናቸውና የምሥጋና ብፅዓት ይገባቸዋል፡፡
በሌላ አቅጣጫ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው እንዳይኖሩ ሲገደዱ ወደ ውጪ በመፍለስና በመሰደድ በነዚያ ሀገሮች በሚገበዩት ዕውቀትና ጥበብ ለወደፊቱ ሀገራቸውን የሚጠቅሙና በእንደገና ግንባታው በከፍተኛ ደረጃ የሚሣተፉ እንደሚሆኑ ከፍተኛ ግምት አለኝ – በበኩሌ፡፡ እናም ተስፋዎቻችን ናችሁና በርቱልን እላለሁ – ፍሉሳንን፤ ደግሞም ከብት እንጂ በየሄደበት እሚለምድ እናንተ ሰዎች በመሆናችሁ ቆንጆና ገና ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር ባለቤትም ስለሆናችሁ ልቦናችሁን ወዳገራችሁ ማቅናት ይኖርባችኋል፤ ጠፍታችሁ እንደምትቀሩ ሳይሆን አንድ ቀን የራሳችሁ ሀገር ባለቤት እንደምትሆኑ አስቡና ዓላማችሁን ከዚህ ቅዱስ ሃሳብ ጋር ቃኙ፡፡ በሀገር ቤቱ ግን ብዙም ተስፋ አናድርግ፡፡ በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂቶች በስተቀር ብዙዎቻችን ራስ ወዳዶችና ለወያኔው ሥርዓት አጎብዳጆች ነነ፡፡ ቄስ የለ፣ ገበዝ የለ፣ ጳጳስ የለ፣ ኤጲስ ቆጶስ የለ፣ ምሁር የለ፣ ጨዋ የለ፣  ከሞላ ጎደል ሁላችንም ተንበርካኪዎች ሆነናል፡፡ ‹ጊዜው ነው› ልበልና በጊዜ ላላግጥ ይሆን? እኛው ነን! ጥፋተኞች እኛው ነን፡፡ ቆይ ልኮርጅ፡- የውድመታችን መሃንዲሶች እኛው፤ የመጥፋታችን የገንዘብ ምንጮች እኛው፤ የችግሮቻችን መፍትሔዎች እኛው … ታላቁን ግድብ በሚመለከት ‹ታላቁ› መሪያችን እንዲህ የመሰለ ቀልድ ሲናገር ሰምቻለሁ፡፡
ሀገር ስትጠፋ ሃይ የማይል የሃይማኖት አባት የጥፋት ተባባሪ ከመሆን አይዘልም፡፡ ሀገር ስትጠፋ ሃይ የማይል በሀገር ሀብት የተማረ ምሁር የጥፋት ተባባሪ ከመሆን አይድንም፡፡ ግፍና በደል ሲፈጸም ዝም ብለን ያየን ሁሉ – በቻልነው ያልተቃወምን ሁሉ – ኋላ ላይ የየድርሻችን ወዮታ አለብን፡፡ ስለዚህም ነው በኢትዮጵያ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ የዘመናዊ ትምህርት ምሁርና የሃይማኖት አባትም ሆነ ተራ አገልጋይ የለም በሚለው የማምነው፡፡ ውሸት ነው፤ ሁላችንም ማለት በሚቻል መልክ ለሩህያችን እንሳሳለን – ሥጋችንንም ከሁሉም አስበልጠን እንወዳለን፡፡ ለኅሊናውና ለነፍሱ ያደረ ሰው ሥጋውን ይጠየፋል፤ ለኅሊናውና ለነፍሱም አድሮ ግፍን ይቃወማል – በዚያም የጽድቅ ሥራው የሞት ጽዋንና የእሥራት መቁነን ሳይቀር ይጋፈጣል፡፡ እነ አንዷለም አራጌና እስክንድር ነጋ የነፍሳቸውን መክሊት ተረድተው የኢትዮጵያዊነታቸውን አሥራት ብኩራት እየከፈሉ በመገኘታቸው እቀናባቸዋለሁ፡፡ የነሱን ያህል በማይሆን አነስተኛ ወጪ ሀገራችንን ከክፋት መታደግ የምንችል ሚሊዮኖች ዝም ብለን ተቀምጠን ስመለከት ደግሞ በራሴ አፍራለሁ፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር መባሉም ለዚህ ነው፡፡ በሀገር ደረጃ ግፍና በደል ናኝቶ ሕዝብ ሲረገጥና ሲጨቆን ዝም የሚል የሃይማኖት አባት ካለ ያ ሰው የሰይጣን ተባባሪ መሆኑን ለመገንዘብ መጽሐፍ መግለጥ ወይ ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልግም፡፡ ለሥጋው ያደረ ነፍሱን እንደሚያጣ ከኔ የበለጠ ቀሲስ አስመሮምና ደብተራ ጓንጉል ያውቃሉ፤ ግፍ ሲፈጸም ‹ተው! በሠይፍ የሚገድሉ በሠይፍ ይገደላሉ› ብሎ የማይገስጽ የሃይማኖት አባት ለዓለማዊ ኑሮው የተሸነፈና ለመብል መጠጥ እንዲሁም ለርክብክብ ሥጋ የተንበረከከ መሆኑ ግልጽ ነው – ቃሉም ጠፋኝ፡፡ ሰውንና ሥልጣኑን በመፍራት የእግዚአብሔርን ቃል የሚሽሩ ካህናትና ጳጳሳት በእግዚአብሔር ኅልውና ስለማመናቸው ማወቅ ይከብዳል፡፡ እውነትን የሚቀብሩ ሀሰትን ግን የሚያነግሡ ካህናትና ሊቃነ ጳጳሣት በእግዚአብሔር የማያምኑ ለጨለማው ንጉሥ ግን ቅን ታዛዥ የሆኑ የሥጋዊው ዓለም ሰዎች ናቸው – በዚያ ላይ ‹ለሁለት ጌቶች አትገዙ› የሚለውን ቅዱስ ቃል ለሥጋቸው ሲሉ ሽረውታልና ጽድቅ ከነሱ ጋር አትገኝም፡፡ እንቅልፍ የሞት ታናሽ ወንድም እንደሆነ ሁሉ ኃጢኣተኝነትም የሰይጣናዊነት መገለጫ ነውና ከሚባርኩን ውስጥ የትኞቹ በወዲያኛው ሊባረኩ እንደሚችሉ ለማወቅ ጥልቅ መንፈሳዊነትንና ልባዊ ጸሎትን ይጠይቃል፡፡ ይህን በማይም ቃሌ የምናገረውን ማስተባበል የሚቻለው አንድም ካህን ሊኖር አይችልም፤ ቢኖር እርሱ አንድም ገነት ውስጥ ነው አንድም እኔ አላውቅም፡፡ መሀል ቤት እንደሌለ ግን ይገባኛል፡፡ በተጠየቁ መሠረት ጽድቅና ኩነኔ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሊሆኑ አይችሉም፤ ጧት ማጉራትና ማታ ዳዊት መድገም እንደማይቻል ሁሉ በእግዚአብሔር ስም እየነገዱ ፍጡራኑን ለአረመኔዎች ጅራፍ አጋልጦ ከአረመኔዎች ጋር መሞዳሞድና ዲያብሎሳዊ ቅኔ ማኅሌት መቆም አይቻልም፡፡ ይህን እውነት ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖረ ነግር ግን ለሥጋው ተሸንፎ መስቀሉን ለኃጥኣን ግሣጼ ያላዋለ የሃይማኖት አባት ነኝ የሚል ሐሳዊ መሢሕ ሁሉ ይገንዘብ፡፡ ደረታቸውን ለጦር አንገታቸውን ለሠይፍ የሰጡ እነቅዱስ ጳውሎስንና መጥምቁ ዮሐንስን ያስቧል፡፡ ባማረ ፎቅ እየኖሩ፣ ያማረን እየለበሱ፣ በዲኤክስና በቪታራ እየተንፈላሰሱ የክብር አክሊል ይገኛል ማለት ዘበት ነው – እንደዚህስ የዚያኛው ጎራ አባላትም አያቅታቸውም፡፡ ቀደምት ጻድቃንና ሰማዕታት ያን ሁሉ መለኮታዊ ክብር የተጎናጸፉት የተላጠ ሙዝ እንደሚመስሉት እንደኋለኞቹ ዘበናይ አባቶች በወርቅና በነሐስ መስቀል እየተሸሞነሞኑ፣ ከእግዚአብሔር ይበልጥ በምዕመናን ዘንድ እንደጣዖት ሊከበሩ እየቃጡ፣ መንፈሣዊ ተልእኳቸውን ንቀው (ፈጣሪን ንቀው) ከዓለማዊ መንግሥታት ጋር በመሻረክ ለዓለማዊ ድሎታቸው እያደሉ፣ ከቃለ ዐዋዲው ውጪ አሥሩ ቦታ እየደቀሉና በድብቅ ልጅ እያሳደጉ የሁለት ዓለም ሰዎች ሆነው  ሳይሆን የተቆጠረች ውሱን ሽምብራ እያንቀራጩና ዐይን ያላያት ሥጋ ያልሳሳባት የበረሃ ቅጠል ተሲያት ላይ ቀንጥሰው እየቀመሱ፣ ከእባብና ዘንዶ እንዲሁም ከአንበሣና ከነብር ጋር በዱር በገደል እየታገሉ፣ ከከሃዲያንና ከአረመኔ መንግሥታት ጋር እየተፋለሙ ነው፡፡ መንፈሣዊ ተጋድሎ ቀላል አይደለም፤ በዘረጥ እምቦጥም የሰማያዊ መንግሥት ወራሽ አይኮንም፤ ልብ እንበል – ከዚህ አኳያ ቤተ ክርስቲያናችን ብዙ የምታወራርደው ዕዳ ከፊት ለፊቷ ተደቅኗል፡፡ በግልቡ ለየዋሃን እንደሚታየው ነገሩ ጥምጥም የማሳመርና ቃለ እግዚአብሔርን የማነብነብ ወይም በያሬዳዊ ዜማ ምእመናንን የመመሰጥ ጉዳይ አይደለም … ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድስ ጊዜው ሲደርስ በግልጽ ለመነጋገር ያብቃን፡፡
ልጨረስ ነው አይዞህ፡፡ የኑሮ ውድነቱ እንደወትሮው ሁሉ ህዝብን ባልተወለደ አንጀቱ እየሸነቆጠ ነው፡፡ ቲማቲምም ባቅሙ 25 ብርን ከዘለለ ሰነበተ፡፡ ዱሮ የሥጋ ቁርጥ ነበር የሚያምረን፡፡ አሁን ደግሞ የቲማቲም ቁርጥ – ሰላጣ ከሥጋ ቁርጥ ሊስተካከል ተቃርቧል፡፡ ሥጋ ለብዙዎቻችን የመዝገበ ቃላት ቃል ከሆነ ከረመ፡፡ የ300 ብር ደሞዝተኛ በአማካይ የ150 ብር ቁርጥ ሲበላ ይታይህ፡፡ የ600 ብር ደሞዝተኛ የ180 ብር ኪሎ ቅቤ ሲገዛ ይታይህ፡፡ የ1000 ብር ደሞዝተኛ የ40ና 50 ብር እዚህ ግባ የማይሉት አንድን ሕጻን እንኳን የማያጠግብ የበሬ ይሁን የበግና የፍየል ወይም ለባህላዊና ሃይማኖታዊ የአመጋገብ ሥርዓታችን እንግዳ የሆነ የሌላ ፍጡር ሥጋ ጥብስ እቡና ቤት ገዝቶ ሲመገብ ይታይህ፡፡ የ1500 ብር ደሞዝተኛ በደህናው ቀን ለገዛው አልጋው የ700 እና የ800 ብር ብርድ ልብስ ወይም የ450 እና የ600 ብር አንሶላ ሲገዛ ይታይህ፡፡ የ400 ብር የጽዳት ሠራተኛ በታክሲና በከተማ አውቶቡስ ስትጓዝና የ15 ብር የፍራፍሬ ጭማቂ ስትጠጣ ትታይህ፡፡ እኔ ዳግማዊ መጠኑን በጭራሽ በማልነግርህ የሦስት ሺህ ብር ወርሃዊ የተጣራ ደመወዜ ለአሥር ቤተሰቤ የሚበቃ (ለሥጋና ወተቱ ዐርብና ረቡዕን ሳይጨምር) በየቀኑ 3 ኪሎ ሥጋ፣ 3 ኪሎ ጤፍ፣ ግማሽ ሊትር የምግብ ዘይት፣ ለአንድ የወንድና ለአንድ የሴት በድምሩ ለሁለት ዕድሮች የሚከፈል፣ አንድ ሊትር ላምባ፣ 3 ነጠላ ሻማዎች፣ 3 ሊትር ወተት፣ 3 ኪሎ አትክልትና ፍራፍሬ፣ 3 ጃምቦ ድራፍት፣ 3 ለስላሳ (ከውኃ ጋር አብቃቅቶ ለመጠጣት)፣ 3 ቡና፣ 6 ኪሎዋት ኮረንቲ፣ ሩብ ኪዩቢክ ሊትር ውኃ፣ በአማካይ አሥር የቤት ሥልክ ጥሪ፣ በቤተሰብ የሚከፋፈል የ100 ብር ሞባይል ካርድ፣  አንድ ኪሎ ከሰል፣ ግማሽ ኪሎ ስኳር ከነቀጠፉ፣ የ30 ኪሎ ሜትር ቤት/መሥሪያ ቤት ደርሶ መልስ ጉዞ፣ ኦ! ደከመኝ … ይህን ሁሉ ስገበይ ይታይህ፡፡ ባይገርምህ ከ40 ዓመታት በፊት በነበረ ገበያ እነዚህንና ሌሎችንም ጨምሮ ቤትን ለማሟላት በከፍተኛ ግምት የ200 ብር ደሞዝተኛ ብቻ መሆን ነበር የሚያስፈልግ፡፡ ዛሬ ወያኔ መጣና ሁሉን ነገር እንዳይሆን እንዳይሆን አደረገና የአሥር ሺህ ብር ደሞዝተኛ ሳይቀር በኑሮው ብዙ እየጎደለበት ከድሃው ጋር የሚያላዝን ሆኗል፡፡ አልፎለት የምታየው ኅሊናውን በየቤቱ ታዛ ሸጉቦ አቅሉን ለገንዘብ ሸጦ በመጣው ይምጣ ከወያኔ ጋር የወየነ ብቻ ነው – ወቅቱ ራስን የማዳን ነው፡፡ ተንደላቅቀህ ለመኖር ኅሊና፣ አእምሮ፣ አስተሳሰብ፣ አመለካከት፣ ምናምን እንዲኖርህ አያስፈልግም፡፡ ሌላውና ብዙኃኑ ይልሰውንና ይቀምሰውን አጥቶ በሞትና በሕይወት መካከል እየተንጠራወዘ በሆዳቸው የሚያስቡና ነገን የማያውቁ ብቻ በቆንጆ ሁኔታ እየኖሩ ናቸው፡፡
ባክህን ትንሽ ላክል – መለየቱ አሳሳኝ፡፡ የ700 ብር ደሞዝተኛ ፖሊስ የ800 ብር ቤት ተከራይቶ ከነቤተሰቡ ሲኖር ይታያችሁ፡፡ የ500 ብር ደሞዝተኛ ርካሹን የ300 ብር ጫማና የ16 ብር ካልሲ ሲገዛ ይታያችሁ፡፡ ዛሬ ሸሚዝ ለመግዛት ቁብ መግባት አለብህ – ጥሩ ሸሚዝ ከብር 400 ይጀምራል፡፡ የጥንቱ የ120 ብር የሎንዶን ሱፍ ዛሬ ከ12000 ብር በላይ ነው፤ የቻይና ፍርጅድ ሱፍ ራሱ ከ2000 ብር በላይ ይሸጣል – እንደዝምብ አማካይ ዕድሜ አገልግሎታቸው በ15 ቀናት ውስጥ በሚጠናቀቅ የፎርጅድ ዕቃዎች ተጥለቅልቀናል – ለነገሩ ሁሉም ነገራችን ፎርጅድ ሆኗል፤ ትምህርቱ፣ ሰው ሁሉ ፎርጅድ፣ መስተንግዶው ፎርጅድ፣ ፈገግታው ፎርጅድ፣ አገልግሎቱ ፎርጅድ፣ ቅዳሤውና ማኅሌቱ ፎርጅድ፣ ንስሃ አባቱ ፎርጅድ፣ ስብከቱ ፎርጅድ፣ … ፎርጅድ ያልሆነውና ጄኒውን የምንለው እንደእንስሳት ኖረን እንደሰው መሞታችን ብቻ ነው፡፡ ምን አለፋህ ወንድሜ – የምንኖረው በተዓምር ነው፡፡ የሰዎችን ገቢ ስትሰሙና ቀኑ እንዴት ነግቶላቸው እንደሚመሽ ስትታዘቡ ከአእምሮ በላይ በሆነ አንዳች ስሜት ትወጠራላችሁ፡፡ የመንግሥትን ጭካኔ አይታችሁ፣ የግል ኢንቬስተሮችንና ሀብታሞችን አረመኔነት ተመልክታችሁ በሥራቸው የሚገኙ ምዝብር ድሆች እንዴት እንደሚኖሩ ስታጤኑ መፈጠራችሁን ትጠላላችሁ፤ የዓለምን  ፍጻሜም ትመኛላችሁ – ልክ እንደኔ፡፡ ‹ሰውን መግዛት እያስራቡና እያሰቃዩ ነው› የሚለው ነባር የኢትዮጵያው ብሂል ይከሰትላችኋል፡፡ መንግሥትና አብዛኛው ኢንቬስተር sadist ናቸው ተብሎ ቢታመን ድርብርብ እውነት ነው፡፡
ሰሞኑን ደግሞ ይሄ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚባል የቅዱሱን ስም አላግባብ አስካሪ መጠጡ ላይ የለጠፈ ቢራ ኮማሪ ድርጅት አብዝቶታል፡፡ ከወያኔ ጋር እየተባበረ በብሻን ጮረሬ የፋብሪካ ጠላው ሕዝብን መግፈፉ አነሰውና በየስድስት ወሩ በሚጨምረው ዋጋው ምድረ መኢጠማን (መላው የኢትዮጵያ ጠጪዎች ማኅበር) እያማረረው(ን) ይገኛል፡፡ ነሸጥ ባረገው ጊዜ ሁሉ እየባነነ በሚጨምረው ዋጋ የአንድ ነጠላ ድራፍት ዋጋ ከ85 ሣንቲም እኔ የማውቅለት ዋጋ ተነስቶ ዛሬ 6 ብር እንዲደርስ አድርጎታል፡፡ ከግንቦት 97 በፊት ባማካይ 2.70 የነበረው ጃምቦ ዛሬ በብዙ ቦታዎች 12 ብርን አሻቅቧል፡፡ የሚገርመው ጊዮርጊሶች ከጨመሩ ሌሎቹም እንዲጨምሩ መገደዳቸው ነው፡፡ የሕዝቡን – ማለትም የጠጪውን ማኅበረሰብ የልብ ትርታና የሥነ ልቦና ቀመር ሳይረዱት አልቀሩም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዋጋ ሲጨምር ገበያ ይደራል፡፡ በውሰት አገላለጽ ባሕርያችንን ለመጠቆም ያህል – እኛ ኢትዮጵያውያን ወደ አውሮፓውያን የገበያ ሥሪት ከምንገባና መብታችንን በጋርዮሻዊ አድማ ከምናስከብር ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ሳይቀላት አይቀርም፡፡ የምንገርም ሕዝብ ነን፡፡ ድራፍትና ቢራ የዕድሜ ማራዘሚያ ኤ.አር.ቪ የሆነ ያህል፣ ድራፍት ለአንድ ሣምንት ባንጠጣ የምንሞት ይመስል፣ አልኮል መጠጣትን ለአንድ ቀን ብንተው የምንዋረድና ድህነታችንን ለ‹ጠላት ለወዳጅ› የገለጥን ይመስል … በራሳችን ገንዘብና በድንቁርናችን ምክንያት ሻጮችና ኮማሪዎች በላያችን ላይ ለዘላለሙ እንዲነግሡብን ተመቻቸንላቸው፡፡ አህያና አጋሰስ መጋጃ ሆንልናቸውና አምቡላቸውንና አተላቸውን በፈለጉት ዋጋ ይቸረችሩልን ያዙ፡፡ በመሠረቱ ይሄ የኛ እንጂ የነሱ ጉዳይ አይደለም፡፡
እነሱማ ከመንግሥት ጋር እየተመሳጠሩ ገቢያቸውንም በስንጥቅ ትርፍ እያሳደጉ በሚከፍሉት ከኛው አላግባብ የሚዘረፍ የመንግሥት ግብርም መትረየስ ከነአረሩ እየተገዛ በኛው በድሆቹ ልጆች አናት ላይ ይርከፈከፋል – መብታችንን በጠየቅን ቁጥር፡፡ በእግረ መንገድም በቡና ቤት ለመዝናናት አቅም ያጣን ዜጎች እንደዶሮ በጊዜ ወደየቤታችን ስንሰተር መንግሥትን አናማም፤ አንቦጭቅም፡፡ ያኔ ወያኔው አንጻራዊ ዕረፍት ያገኛል፡፡ ለአንድ ቡና ወይ ማኪያቶ  8 እና 10 ብር ካልከፈልክ፣ በተለይ በቦሌ መስመር ለአንድ ኬክ ሃያና ሠላሣ ምናምን ብር ካልተዘረፍክ፣ ከጉሮሮ ለማያልፍ በአረፋ የተሞላ አንድ ድራፍት አሥራ ምናምን ብር ቁጭ ካላደረግህ፣ … እንዲያው ተጎልተህ የማንን ወንበር ታሞቃለህ? ማንስ ያስቀምጥሃል? ኤዲያ! የኢትዮጵያ ነገርስ … ምነው እግዜሩም እንደሰው ጨከነ ግን? እነዚህ ወያኔዎች እኮ የማይገቡበት የለም፤ እሱንም ‹ሆስቴጅ› አድርገውት ይሆን እንዴ? መጠርጠር ነው! ለማንኛውም እንዲህ ማለቴን አትፍረዱብኝ – ቢጨንቀኝ ነው – “እስከማዕዜኑ ትረስዓኒ ሊተ” ብሏል አሉ  ዳዊት እንደኛው ቢጨነቅ፡፡ ኢዮብም ክፉኛ ይወቅስ ነበር፡፡
ያገሬ ባላገርስ እንዲህ ያለው ወዶ ነው?
ቀና ብዬ ባየው ሰማዩ ቀለለኝ፤
አንተንም ሠፈራ ወሰዱህ መሰለኝ፡፡
እርግጥ ነው – የእግዚአብሔርን ሥልጣንና ኃይል አይዘባበቱበትም፤ ሰው ሲጨነቅ ብዙ ይላል እንጂ የፍርዱ ቀን መምጣቱ በጭራሽ አይቀርም፡፡ እንዲያውም ወንጀልና የክፋት ሥራ ሲበዛ ቀኑ እንደቀረበ ምልክት ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ እንደኔ ዓይነቱ ሆደ ባሻ ሰው ብዙ ያስቀይማልና በድምብርብር አነጋገሬ የተከፋችሁ ይቅርታ ታደርጉልኝ ዘንድ ከልብ እለምናለሁ፡፡ ቻው፡፡

No comments:

Post a Comment