Monday, 8 July 2013

የብርሃን ልክፍትን በጨረፍታ(ደረጀ ሀብተወልድ)

July 8, 2013

የመጽሐፉ ርዕስ፦ የብርሃን ልክፍት(ስብስብ ግጥሞች)

ደራሲ፦ ዮሐንስ ሞላ
የሽፋን ምስል ዳዊት አናጋው
ገጽ፦108
የተካተቱት ግጥሞች፦72
ዋጋ፦ 28 ብር (18 ዶላር)
ብዙ ጸሀፍያን (ገጣምያን) የራሳቸው የአፃጻፍ ዘይቤ እንዳላቸው ሁሉ ፤ ዮሐንስ ሞላም የራሱን ዘይቤና ስልት ይዞ በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ መድረክ ብቅ ያለ ወጣት ገጣሚ ነው። ከሚያነሳቸው ጭብጦች፣ በአጭር ግጥሞች ጥልቅ መልዕክቶችን ከመግለጹ እና  ዘለግ ባሉ ስንኞች  ቃላትን እያነሳና እየጣለ ከማጫዎቱ አንፃር ከየትኞቹ የአገራችን  ገጣሚያን ጋር እንደማመሳስለው  አላውቅም። በስወድሽ ግጥሞቹ ገብረክርስቶስን የሚያስታውሰኝ ዮሐንስ ሌላ ቦታ ሌላ መሰሎ ይከሰትብኛል። ስለዚህ የማን ተጽዕኖ እንዳለበት   ወይም  የማንን ፈለግ እንደሚከተል ራሱ  ዮሐንስ ቢነግረን ይመረጣል።በኔ በኩል ግን ዮሐንስ እየገጠመ ያለው፤ እንደ ዮሐንስ ነው ብዬ ማለፉን እመ ጣለሁ-አንደ ዮሐንስ አድማሱ ሳይሆን እንደ ዮሐንስ ሞላ።

ብዙውን ጊዜ ሥነ- ግጥም  በአንባቢያን ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው በውስጡ የጠራ ሀሳብ ሲይዝ እና ያም ሀሳብ ስርዓቱንና  ምቱን(rhythm) ጠብቆ በተገቢው ቃላት ሲገለጽ ነው። ከዚህ አንፃር አንዳንዶች የጥሩ ሀሳብ ባለቤቶች ሆነው ያን ሃሳባቸውን የሚያዋቅሩበት ቃላት ሲቸገሩ፤ ሌሎች  ደግሞ የቃላት ሀብታሞች ሆነውና የስንኝ አጣጣሉን አግኝተውት ሳለ፤ በሀሳብ ድርቀት ይሰቃያሉ።በዚህም ምክንያት  ይመስላል  አልፎ አልፎ ሀሳብ የሌላቸው ወይም መልዕክታቸው ያልጠራ ግጥሞች – ቤት ስለደፉ ብቻ ግጥም እየተባሉ ወደ መድረክ ሲወጡ የምናየው።

የዮሐንስ ግጥሞች  በሀሳብም፣ በቃላትም፣በስንኝ አወቃቀርም  የተጠቀሰው ዓይነት ህጸጽ አይታይባቸውም።
የኳስ አፍቃሪዎች፦”ቀ ቁ ቂ ቃ
አንድ ጎል በደቂቃ “ እያሉ እንደሚጨፍሩት ፤ ዮሐንስ ትርጉም የለሽ  ቃላትን  ለቤት መምቻ ብቻ በዘፈቀደ አልተጠቀመባቸውም።ቃላትን በተገቢውና በትክክለኛው ቦታ እየሰካ ነው ያጫዎታቸው፦
ለምሳሌ” የእኔ ፍቅር ላንቺ “ በተሰኘው ግጥሙ ላይ፦
“…እንደ ሸማ ጥለት፣ ካሎስ-ሳባ ጥምረት፣
እንዳ’ደዋወሩ፣እንደ ድር ማግ ሥምረት፣
ሞያ እንደጎበኘው፣ እንደ ድርብ ኩታ፣
እንደ ቀጭን ፈትል፣እንደ ልስልስ በፍታ…
እንደ እስረኛ ባሪያ፣ እንደ ፍች ናፋቂ፣
ፍርድ እንደሚፈልግ ዝም ያልኩኝ ጠባቂ…..
እንደ እመጫት ድመት፣ ሙጭሊት እንደራባት፣
እንደ ክረምት ውሻ፣ ባሏ እንደናፈቃት…”

እያለ እንደ ጅረት ባፈሠሰው የግጥም ጎርፍ ላይ የተጠቀማቸውን ቃላትና የገቡበትን ስፍራ ስንመለከት  ፤ዮሐንስ የቃላት ሐብታም ብቻ ሳይሆን  የቃላት ሀብቱን በተገቢው ቦታ የሚጠቀም(የማያባክን) ገጣሚ መሆኑን እንረዳለን።
ገጣሚ መንፈሳዊና ደፋር  ነው።መንፈሳዊ ስል ከውስጡ  የሚያፈልቃቸው ሀሳቦች ከሰውኛውና ከሳይንሳዊው አስተሣሰብ ያፈነገጡ ናቸው ማለቴ ነው።በባህር ላይ መራመድ፣ተራራን በእምነትና በቃል ማፍለስ፣ በእሳት ላይ መሄድ…የመሣሰሉት በመንፈሳዊ መጽሕፍት የተጠቀሱት ተኣምራት፤ ለአንድ ዓለማዊ ወይም ሳይንሳዊ ሰው ቀልዶች ሊሆኑ ይችላሉ። ለገጣሚ ግን አይደሉም። ገጣሚው ራሱ እነዚህን ተዓምራት በየስንኞቹ  ሢያደርጋቸው ይስተዋላልና።   አንድ ገጣሚ  በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት የምትገኝ ፍቅረኛውን ሲናፍቅ  ስለ ቪዛ፣ስለትኬትና ስለትራንስፖርት ዋጋ ሲጨነቅና ሲያስብ አይታይም።

፦”ባሳብ ፈረስ ሆኜ-እየገሰገስኩኝ ፣
ጋራውን አልፌ- ወዳንቺ መጣሁኝ “  ሲል ነው የምንሰማው። በቃ  በተመስጦ  ወዳሰኘው ይከንፋል።የአገር መለያየት፣ የተራራ መግዘፍ፣ የአድማስ ርቀት…አያግደውም። እንደ በቅሎ እየሰገረ፣ እንደ ፈረስ እየጋለበ፣ እንደ አሞራ እየበረረና እየተሽከረከረ   ዱሩን፣ጢሻውንና ባህሩን..እየሰነጠቀ በሀሳብ ይነጉዳል።አንዳች የሚያስፈራው ቅጥር  ሳይኖር ውስጡ የተሰማውንና አምጦ የወለደውን  ይዘረግፈዋል።
ዮሐንስ፤”ጨዋታ ዝክረ-ዋልድባ ወዝቋላ”  በሚለው ግጥሙ ላይ፦
ከጠቆረው ሰማይ፣
አፍጥጬ ወደ ላይ፣
ተአምር ተማጽኜ፣ትልቅ ተስፋ አዝዬ፣
ዳገቱን ወጥቼ..ቁልቁለት ወርጄ፣
ከላይ ታች ታግዬ፣
ከእሳቱ ጋር ልፊያ፣
ከአየሩ ጋር ግፊያ፣
ከነፋስ ጋር ግጥሚያ….. “እያለ፤  ማንም ዓለማዊ ሰው ሊገዳደራቸው ከማይችል ተፈጥሮዎች ጋር ግብግብ  ገጥሞ እናየዋለን።
…ፍሙን ረግጬ፤እቶኑን ጨብጬ፣
ከእሳት ተሯሩጬ ከፍም ተፋጥጬ፣” እያለ የፍልሚያውን ከባድነት ከዘረዘረ በሁዋላም፦
……
እሪ በል ጠላቴ፣
እልል በል ወዳጄ፣
ገባሁ ረትቼ ፣ድል ቆመ ከደጄ” በማለት ከነፋስ ተጋፍቶ፣ ከእሳት ተላፍቶ፣  ፍም ጨብጦና እቶን ረግጦ  በስተመጨረሻ  ማሸነፉን ይነግረናል።ይህኔ የነ ሱዛን ኮሊን Catching Fire  ትዝ ሊልዎት ይችላል።
ከላይ እንዳልነው ገጣሚን  ጋራ አያግደውም፣ባህር አያሰጥመውም፣ እሳት አያቃጥለውም ።የሚረታው፣ የሚያቃጥለውና የሚያሰምጠው ፍቅር ብቻ ነው።እውነተኛ ገጣሚ መንፈሳዊና ደፋር ነው ስንል  ግን ይህን ብቻ ማለታችን አይደለም። ከውስጡ የተወለደውን እንዳለ ለመዘርገፍ የማያመቻምች፣ የህረተሰቡን የልብ ትርታና የያየውን እውነታ  ለማውጣት  የማያፈገፍግ፣”እነ እገሌ ይከፋሉ፤እነ እገሌ ይደሰታሉ”በሚል ስሌት  የወለደውን ልጁን(ግጥሙን)  በጥገና የማያንሻፍፍ እና  ብዕሩ  አድርባይ ያልሆነ  ማለታችን ጭምር ነው።

ለምሳሌ በብርሃን ልክፍት መድብል ውስጥ  “ምንዱባን” የተሰኘው ግጥም፤ ዮሐንስ የሚያየውን እውነታ አምጦና የህዝብን የልብ ትርታ አዳምጦ የወለደውን ግጥም   እንደወረደ  የሚያቀርብ ደፋር ገጣሚ መሆኑን ያመላክተናል፦
የሰጡትን ማብቀል እየቻለ አፈሩ፣
ዘር እየመረጡ፣ዘር እየቆጠሩ፣
ዘር እየለቀሙ፣ዘር እየሰፈሩ፣
ዘር እያቀለጡ፣ዘር እያነጠሩ፣
ዘር እያንጓለሉ፣ዘር እያበጠሩ……” እያለ ነው ዮሐንስ በምንዱባን ላይ የተቀኘው።ዮሀንስ በዚህ ቅኔያዊ ግጥሙ  ዘረኝነትን -በእህል ዘር አስመስሎ በመግለጽ፤ የዘሩ (የዘረኝነት)መጨረሻ ሊያምር እንዳልቻለ ይነግረናል።ገጣሚው  ከዚህም ባሻገር፦ዘር መምረጥ፣ዘር መቁጠር፣ዘር መልቀም፣ዘር መስፈር፣ዘር ማንጓለል ፣ዘር ማበጠር…እያለ አንድን ቃል አብረውት ከሚሄዱ ብዙ ቃላት ጋር እያሰናሰለና እያዋደደ በመግጠም ፤ልዩ ችሎታውንም ያሳየበት ግጥም ነው።
በ”ግርማ ሞገሳ’ሟ እቴ” ፣ በ “ሀ ሁ/አ ኡ፣ እና  በ “እንጉርጉሮዎቹ”ም ዮሐንስ   ደፋርና ቀጥተኛ ብዕር እንዳለው፣ በህብረተሰቡ ልብ ውስጥ ያለውን ነገር  ወደ አደባባይ ለማውጣት  የማያንገራግር  ገጣሚ መሆኑን ነው የምናየው።
ዮሐንስ፤ በብርሃን ልክፍት የዳሰሳቸው ቁም ነገሮችና ማህበራዊ ጉዳዮች በርካታ ናቸው። የቱን አንስቼ  የቱን እንደምተው  አስቸግሮኛል። ሁሉንም እንዳንዘረዝረውም የወረቀት ገጽና የአየር ሰዓት ይወስነናል። ስለዚህ እንደ አጀማመራችን  አልፎ አልፎ በጣም በጥቂቱ  መቃኘታችንን እንቀጥላለን፦

የሰው ልጅ ብዙ ጊዜ የሚፈልገው የሌለውን፣ የሚያሳድደውም የሚሸሸውን ለመሆኑ ብዙዎቻችን የማናስተውለው እውነታ ነው። ዮሐንስ ይህን እውነታ “ምናልባት ከቀረሽ”በሚለው ግጥሙ ላይ በሚገባ ገልጾታል። ዮሐንስ በዚህ ግጥሙ  ያፈቀራትንና ቃል የገባችለትን ፤ሆኖም  የእሱ ለመሆኗ ገና እርግጠኛ ያልሆነባትን ልጅ በናፍቆት ተውጦ በጉጉት ሲጠብቃት እናያለን።እሱ ወደሷ አንጋጦ በተስፋ ሲጠብቅ-በአንፃሩ ከሁዋላው  እሱን ያፈቀረች ሌላ  ሴት ልትኖርና ልትጠብቀው እንደምትችልም ጠርጥሯል።እሱ አንዿን  ሲያሣድድ፣ ሌላዋ እሱን እያሳደደችው እንዳይሆን ሰግቷል፤ሸክኳል።
እናም፦
የፈጀውን ፀሐይ፣ ያሻውን ጨረቃ፣…ይፍጅና መምጣትሽ፣
ምጭልኝ ዓለሜ፣ በዕድሜዬ ድረሽ፣ መሞቴ ሳይቀድምሽ፣
የኔ ቃል አንቺ ነሽ! ሌላ የታ’ውቃለሁ?
ቃልሽኝ ከጠበቅሽ…እጠብቅሻለሁ!
ሆኖም በምናልባት…
ድንገት ‘ማትመጪ እንደሁ፣ ሀሳብሽን ቀይረሽ፣ጉዞሽ ከታጎለ፣
አደራ ላኪብኝ!..ማስጠበቅ ጡር አለው፣ ‘ሚጠብቀኝ ካለ። “ሲል እንሰማዋለን።

ዮሐንስ በግጥሙ ያነሳው ሌላ ነጥብ ጊዜን  ይመለከታል።አብዛኞቻችን  ኢትዮጵያውያን  7 ሰ ኣት ተቀጣጥረን 10 ሰ ዓት የምንገናኝ ዜጎች ብንሆንም ወጉ አይቀርምና በየጓዳችንና በየታክሲዎች ሳይቀር የሚለጠፍ፦
”ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ፣
ጊዜ ታክሲ አይደለም፣አይጠብቅም ቆሞ”የሚል የቆየ ስንኝ አለን። የዚያኑ ያህልም የአገራችን ጸሀፊዎችም ስለ አላፊው ጊዜ፣ስለ አላፊው  ዘመን በየራሳቸው አተያይና አገላለጽ  ብዙ ነገር ብለዋል።ለምሳሌ ጋዜጠኛና ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም  “ኗሪ አልባ ጎጆዎች” በተሰኘው ተወዳጅ የግጥም መድበሉ ይህን  ነገር የገለጸው፦
“እኛ’ኮ ለዘመን፣
ክንፎቹ አይደለንም፣
ሰንኮፍ ነን ለገላው፣
በታደሰ ቁጥር፣ የምንቀር ከሁዋላው።” በማለት ነው። ዮሐንስ  ደግሞ  በራሱ አተያይ  “ምኞት” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ግጥም ፦
የሰዓት ቆጣሪው፣
የጊዜ ቀማሪው፣
ያ ቀጭኑ ሽቦ፣
ስንዞር አብሮን ዞሮ፣
ስንበርም በ’ሮ፣
አብሮን እንደዋለ…
ስንተኛም እንደኛ፣
ምናለ ቢተኛ “ እያለ ስለጊዜ የቁጭት ምኞቱን ሲገልጽ ይታያል።የዮሐንስ የጊዜ ቁጭት ግን በዚህ አይበቃም። በህብረተሰባችን ዘንድ የሚታየው፦ ጊዜን በአግባቡ ያለመጠቀም ነገርም  ገጣሚውን አሣስቦታል።ዮሐንስ በብዙዎች ዘንድ ፦ “ጊዜውን እንግፋው፣ ጊዜውን እንግደለው…”የሚለውን አባባል በገጣሚ ዓይኑ አይቶ በዝምታ ሊያልፈው አልፈለገም፦
እናም፦”ሆድ ሲያውቅ “ በሚለው ግጥሙ፦
በቧልት ላላገጠ፣በፌዝ ለዘለለ፣
ብሩህ ተስፋን ነፍጎ፣ጸጸትን ካደለ፣
የሰው ፊት ካሳዬ፣ዝቅ አ’ርጎ ካዋለ፣
ጊዜ ገደለ እንጂ፤መቼ ተገደለ?!”ይለናል።
ሌላው በዮሐንስ መድበል የተዳሠሰው ቁም ነገር  እንባን ወይም ለቅሶን የሚመለከት  ነው።
ዮሐንስ፦ “አታልቅሽ” በሚለው  ግጥሙ በታሪክ ስህተት ሳቢያ የሚወለድ  ፀፀትና ቁጭት፤ ስህተትን ለማረምና ለማስተካከል  እስካልጠቀመ ድረስ ከተራ የለበጣ ለቅሶነት የዘለለ እንዳሆነ  ይነግረናል። የዚህ ዓይነቱ፦ ልባቸውን ሳይሆን ልብሳቸውን ከቀደዱ ሰዎች የሚወጣ እምባ ደግሞ መጣ ቀረ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ  ይነግረናል። ሎሬት ጸጋዬ የቴዎድሮስ ስንብት በመቅደላ በተሰኘውና ዓፄ  ቴዎድሮስን ባናገሩበት ግጥማቸው፦
“…ሰለዚህ ለራስሽ እንጂ፥ ልቅሶሽ ለኔ ምን ሊረባ?
ብቸኛ ምሬት ነው ኃይሉ፥ ወኔ መሰለቢያው ነው እንባ፡፡” እንዳሉት ሁሉ፤ዮሐንስም አታልቅሽ በተሰኘው ግጥሙ፦
የዐይን ኳስ ተጨምቆ፣
ሽፋሽፍት ተላቆ፣
ቁልቁል ተሸምድዶ፣
ከጉንጪ ላይ ወርዶ…
የታሪክ  ቋጠሮ ለይቶ ካልፈታ፣
ተስፋን አቀራርቦ፣ካልቸረ እፎይታ፣
ፈሰሰ፣ደረቀ…እንባ ቀረ መጣ፣
ከቶ ምን ሊረባ? “ ይለናል።
በብርሀን ልክፍት ከተሰባሰቡት 72 ግጥሞች አንዷ “ረቡኒ”ነች። ረቡኒ ቃሉ ዕብራይስጥ ሲሆን ትርጓሜው፦”መምህር ሆይ!” ማለት ነው።ታላቁ መጽሀፍ፤ ማርያም መግደላዊት  በትንሳኤ ማግስት ኢየሱስን  በዚህ ቃል እንደጠራችው ይነግረናል።
ዮሐንስ “ረቡኒ”በተሰኘችው ውብና አጭር ግጥሙ ፦
ቤትህ የማር ሀገር፤ልብህ የማር ቀፎ፣
ጣ’ም የሚበስልበት፣ ቀለም ተንጠፍጥፎ፣
ፍቀድልኝና ልዋል ከእግሮችህ ስር፣ ላንጋጥ አሰፍስፌ፣
ካ’ፍህ ማር ጠብ ሲል፣እንዳይወድቅ ካፈር፣
እንዲገባ ካ’ፌ”       በማለት  ለዕውቀት ወይም ለአዋቂዎች ያለውን አክብሮት እንዲሁም ፤ እሱም  ከአዋቂዎች እግር  ስር ሆኖ  አብዝቶ የመማርና የማወቅ ጉጉቱን ቅኔ ባዘሉ ስንኞቹ ሲገልጽ እናየዋለን።

“የትውልድ ጠባሳ፣ሥጋ ደካማ፣አተርፍ ባይ አጉዳይ…ወዘተ” በአጭር ስንኞች ታላላቅ ቁም ነገሮች የታጀሉባቸው የዮሐንስ ውብ ግጥሞች ናቸው።ወጣቱ ገጣሚ የመጀመሪያ በሆነው የብርሃን ልክፍት  የግጥም ስብስብ  በተለያዩ የስንኝ አጣጣሎችና ምቶች አያሌ ጭብጦችን ለመዳሰስ ሞክሯል።አጠቃላይ መጽሐፉን አገላብጠን ስናነበው ዮሐንስ የበሰለ እንጂ ጀማሪ ደራሲ አይመስለንም።በመጀመሪያ ሥራው ይህን ያህል ከሰጠን ለወደፊቱ ምን ያህል ሊያበረክትልን እንደሚችል መገመት አይከብድም። እናም እንትፍ፣እንትፍ፣ እደግ ተመንደግ ብለን ልንመርቀው ይገባል።
በመጨረሻ የማነሳቸው ነጥቦች
-የመጽሐፉ ርዕስ የብርሃን ልክፍት  ቢሆንም፤ ይህ ግጥም በመጽሐፉ ውስጥ አልተካተተም። ይህ ነገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ መምጣቱ ቢገባኝም፤ በኔ በኩል ግን  የብርሃን ልክፍት የተሰኘችውና በፌስ ቡክ አስፍሯት ያየሁዋት ግጥም  በስብስቡ ብትካተት፣አለያም በስብስቡ ከተካተቱት ግጥሞቸ አንድኛቸው የመጽሐፉርዕሶች ቢሆኑ እመርጣለሁ።ሆኖም ከመጽሐፉን ርዕስ ማራኪና ሳቢነት አንፃር ከነዚህ ሁለት አማራጮች የኔ የመጀመሪያው ምርጫ የብርሃን ልክፍት ግጥም ብትካተት የሚል እንደሆነ መጠቆም እፈልጋለሁ።

-ዮሐንስ በግጥሞቹ አዲስ የቃላት አጠቃቀምን ይዞ መጥቷል። ለምሳሌ “ፍቅሬ ሙዚቃዬ” በተሰኘው ግጥሙ  “ወርቅ ቢሆን” ለማለት ፦ቢወረቅ፣ ጨርቅ ቢሆን ለማለት፦ “ቢጨረቅ” ሲል እናየዋለን። ከዓመታት በፊት  እነ ዶክተር (ተባባሪ ነፕሮፌሰር) ፈቃደ አዘዘ አንዳንድ የእንግሊዝኛ ቃላትን በዚህ መልክ እያመጣን በአማርኛ ብንጠቀምባቸውስ? የሚል ሃሳብ ሲያነሱ ሰምቻለሁ። ለምሳሌ “ክላሲፊኬሽን” የሚለውን ቃል “ክልሰፋው እያልን እንጠቀም የሚል ነበር የነ ዶክተር ፈቃደ ሃሳብ። ይህ ሃሳብ በህብረተሰቡ ወይም በጸሀፍያን ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ ምን ያህል ርቀት እንደሄደ አላውቅም። አንድ የማውቀው ሀቅ ቢኖር፤  በአገራችን እንደዚህ ዓይነት አዳዲስ ሃሳቦችን ለመቀበል የሚፈቅዱ እንዳሉ ሁሉ፤ በአንፃሩ “ሀ”ይሌ   ገብረሥላሴን ወይም ኢንጂነር “ሀ”ይሉ ሻውልን እንዴት በፎሌው “ሀ” ትጽፋቸዋለህ? ብለው የሚቀየሙ  ሰዎችም ጭምር መኖራቸውን ነው። ስለዚህ ዮሐንስ ይዟቸው የመጣቸው እነዚህ የቃላት አጠቃቀም ተቀባይነት ማግኘታቸውን ወይም አለማግኘታቸውን ወደፊት የምናያቸው ይሆናል። አለያም በጉዳዩ ዙሪያ የሥነ-ጽህፍ ሰዎች ሊነጋገሩበት ይችላሉ።

-በብርሃን ልክፍት ያስተዋልኩት ሌላው ነገር  ገጣሚው “ይጠጥራሉ”ብሎ ላሰባቸው ቃላት-የቃላት መፍቻ ማዘጋጀቱን ነው። በኔ በኩል ለግጥም መጽሐፍ የቃላት መፍቻ ማዘጋጀቱ አስፈላጊ ሆኖ አልታየኝም።ግጥም-ግጥም ነው።  አንባቢ ደጋግሞ በማንበብ እንዲመራመርበት ዕድል ሊሰጠው ይገባል።አንዳንድ ግጥም ተደጋግሞ እየተነበበም   ሊጠጥር ይችላል። ይህ የግጥም አንዱ ባህርይ ስለሆነ ደራሲውን ሊያስጨንቀው አይገባም።ዮሐንስ የቃላት መፍቻ ያዘጋጀው  ለአንባቢ ከመጨነቅ እንደሆነ ግልጽ ነው። “አይገባቸው ይሆን?” የሚለው ይህ ጭንቀቱ፤ በ አንዳንድ ግጥሞቹ  ሳይቀር አልፎ አልፎ ሲከሰት ይታያል።ለምሳሌ “አደራ” የተሰነችውን የዮሐንስን ውብ ግጥም እንቃኛት፦
ሥጋዬ ሲበላ…ፈቀድኩ አባያቸው፣
ደሜንም ሲጠጡት፣ይሁን አጣጪያቸው፣
አጥንቴም ሢሰበር፣ ከቻልሽ አሳብሪያቸው፣
ልቤን ሲጠጉ ግን፣
ውስጥ አንቺ አለሽና፣ ሰው አለ በያቸው።”  ይላል።  እንደ እኔ በመጨረሻው ስንኝ ላይ፦ “ውስጥ አንቺ አለሽና” የሚለው ሀረግ አስፈላጊ አልነበረም ባይ ነኝ። “ውስጤ ሲጠጉ ግን፣ሰው አለ በያቸው” በቂ ነበር። “ሰው አለ” የሚለው፤ ከውስጥ ያለ ሰው መሆኑ ግልጽ ነው።ማለትም  ወደ ልቡ ሲጠጉ ‘ሰው አለ!’  ካለች-እሷ በልቡ ውስጥ ለመኖሯ በቂ ማረጋገጫ ነው። ከዚህ በላይ ሄዶ  ለማረጋገጥ መሞከር አይጠበቅበትም። “ውስጥ አንቺ አለሽና” የምትለው ሀረግ ዮሐንስ ነገሩን  ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ መጨነቁን ነው የምታሳየው።የዚህን ያህል ርቀት ሄዶ ለ አንባቢ መጨነቅ፤ በግጥሙ ላይ አላስፈላጊ ልባሰን መደረብ ስለሚያስከትል ለወደፊቱ በጥንቃቄ ማየት የስፈልጋል። ይህም ሆኖ ፤በልቤ ከቀሩት የዮሐንስ ግጥሞች   አንዷ ይህችው  ፦ “አደራ” የተሰኘችው ናት።
ዮሐንስ ከፈቀደልን፦”ውስጥ አንች አለሽና” የምትለውን ሀረግ  አውጥተን እስኪ እንድንደግማት ፦
“ሥጋዬ ሲበላ…ፈቀድኩ አባያቸው፣
ደሜንም ሲጠጡት፣ይሁን አጣጪያቸው፣
አጥንቴም ሢሰበር፣ ከቻልሽ አሳብሪያቸው፣
ልቤን ሲጠጉ ግን፣ ሰው አለ በያቸው። “   ይበል ብለናል ጆ!!!
ቅኝቴን በየትኛው ግጥም ልቋጨው? በአሻም እቴ? በጸጸት? ወይስ በእውነት እናውራ ካልሽ?…ምርጫው ከባድ ነው። ግዴለም በ”የቸገረ ነገር”ልሰናበታችሁ መሰል፦
የቸገረ ነገር
በአፈርማ ምድር፣
ባቄመ ሰማይ፣
እውር እየመራ፣
ይዘለቃል ወይ?!
ዮሐንስ ሞላ፤ እደግ ተመንደግ! ኑርልን!ፃፍልን!

No comments:

Post a Comment