Wednesday, 22 January 2014

በሰማያዊ ፓርቲ ስም አመሰግናለሁ! (ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም)

January 22, 2014
Semayawi party chairman Engineer Yilkal Getnet's Washington D.C. meeting.
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ


ባለፉት በርካታ ሳምንታት በተናጠል እና በቡድን እየሆናችሁ በአሜሪካ እና በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች የስብሰባ አዳራሾች በመገኘት ለሰማያዊ ፓርቲ ድጋፋችሁን ላደረጋችሁ ወገኖቼ ሁሉ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ!
ባለፈው ሳምንት ኢትዮሜዲያ/Ethiomedia.com የተባለው ድረገጽ ባወጣው ዘገባ መሰረት ሰማያዊ ፓርቲ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ ትግል ሂደት “አዲስ የተቃውሞ ኃይል” ሆኖ በመቅረብ ሰላማዊ የስርዓት ለውጥ ሽግግር ለማምጣት “አዲስ ተስፋን ፈንጣቂ” ሆኗል በማለት ገልጾታል፡፡ 

ወጣቱ እና መንፈሰ ጠንካራው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በተለያዩ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ከተሞች በመዘዋወር በተስፋ፣ በሰላም እና በአንድነት መሰረት ላይ ፍቅር የነገሰባት አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ሰማያዊ ፓርቲ ያለውን ራዕይ ለኢትዮጵያውያን/ት ግልጽ አድርጓል፡፡

እ.ኤ.አ ዴሴምበር 15/2013 በሰሜን አሜሪካ በአርሊንግተን ከተማ የመጀመሪያው ስብሰባ በተደረገበት ዕለት ይልቃል ለስብሰባው ታዳሚዎች ወደ አሜሪካ የመጣሁት ገንዘብ ለማሰባሰብ ወይም ገንዘብ ለመጠየቅ ሳይሆን ወደዚህ የመጣሁበት ዋናው ምክንያት የሰማያዊ ፓርቲን ራዕይ፣ አቋም እና ፕሮግራም፣ እንዲሁም ፓርቲው በተቋቋመ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን በርካታ ተግባራት እንዲሁም ፓርቲውን አስመልክቶ ለሚነሱ ጥያቄዎች እና ማብራሪያ ለሚጠይቁ ጉዳዮች እዚህ ለሚኖሩት ኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቼ ለማስተዋወቅ እና ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው ብሏል፡፡ የፓርቲው አፈቀላጤ በመሆን ፓርቲውን በማስተዋወቅ ረገድ እጅግ ስኬታማ ስራ አከናውኗል፡፡ የቀረቡለትን ሁሉንም ጥያቄዎች ምንም የሚያደናግር ነገር ሳይጨምር ወይም ግልጽ በሆነ መልክ ለታዳሚው አብራርቷል፡፡ የፖሊሲ ጉዳዮችን በጥንቃቄ እና አርቆ አስተዋይነትን ባካተተ መልኩ ምላሽ በመስጠት ለማስተናገድ ሞክሯል፡፡ ለታዳሚዎች ያቀረባቸው ገለጻዎች የተሟሉ እና  የሁለተኛ ደረጃ መረጃ ምንጮች ሆነው በሀአዝ የተደገፉ መረጃዎች ነበሩ፡፡ ልዩ በሆነ አመክንዮአዊ ገለጻ እና የተሳታፊውን ቀልብ በሚገዛ አንደበተ ርዕቱ የቋንቋ አቀራረብ የታዳሚውን አውድ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮት ነበር፡፡ በዚህ ፓርቲውን በማስተዋወቅ የጉዞ ሂደት ጊዜ ከሰማያዊ ፓርቲ እና ከይልቃል ጎን በመሰለፍ ቀጣይነት ያለውን የበኩሌን ድጋፍ በማድረጌ ታላቅ ኩራት ይሰማኛል፡፡

ለሰማያዊ ፓርቲ የሞራል ድጋፍ እና የገንዘብ እርዳታ ላደረጋችሁ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ፣ በአትላንታ፣ በሀውስተን፣ በዳላስ፣ በሳንጆሴ፣ በሎስአንጀለስ፣ በላስቬጋስ እና በሲያትል ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቼ በሙሉ ከልብ የመነጨ ምስጋናየን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ፡፡ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ፣ በእናንተ ኮርቻለሁ!
በሰሜን አሜሪካ ከተሞች ለሰማያዊ ፓርቲ በተዘጋጁት የስብሰባ መድረኮች ላይ ለተገኛችሁ፣ ስብሰባውን በአንክሮ በመከታተል ለተሳተፋችሁ፣ ጠንካራ ጥያቄዎችን በማቅረብ ተሳትፏችሁን ላደረጋችሁ እና ለፓርቲው ህልውና ማጠናከሪያ የገንዘብ ድጋፍ ላደረጋችሁ ኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቼ ሁሉ በሰሜን አሜሪካ የሰማያዊ ፓርቲ ድጋፍ ሰጭ ቡድን ስም ታላቅ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዝናቡን፣ ደመናውን፣ በረዶውን እና ጨለማውን በጽናት በመቋቋም ስብሰባዎችን ለተሳተፋችሁ እና የማይታጠፈውን ድጋፋችሁን ላደረጋችሁ የፓርቲው አባላት እና ንቁ ደጋፊዎች በሙሉ በሰማያዊ ፓርቲ ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ፡፡ የእናንተ ድጋፍ ታላቅ ለውጥ አስገኝቷል፣ ወደፊትም ያስገኛል፡፡

የሰማዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ይልቃልን ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካን ጉብኝቱን በማስመልከት አጠቃላይ የተሰማውን ስሜት እንዲገልጽልኝ ላቀረብኩለት ጥያቄ ሊገልጸው ከሚችለው በላይ እንደተደሰተ እንዲሁም ለወገኖቹ ከፍተኛ ምስጋና እና አድናቆት ያለው መሆኑን ገልጿል፡፡ በየቦታው ባገኛቸው ስለሀገራቸው ፍቅር እና ጅግንነት የተሞላበት ስሜት በሚያንጸባርቁ ኢትዮጵያውያን/ት ስሜት እጅግ ተደምሟል፡፡ በእነርሱ ከልብ የመነጨ የአገር ወዳድነት ስሜት በመመሰጥ ለወደፊቷ አዲሲቷ ኢትዮጵያ መመስረት የበለጠ ጥልቅ ስሜት እንዲኖረው አድርጎታል፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ ወጣቶችን ለመርዳት የሰጧቸውን ምክሮች እና ያደረጓቸውን ውይይቶች በተመስጦ አዳምጧል፡፡ ይልቃል በዚህች አጭር ጊዜ ውስጥ በአሜሪካ ለሰማያዊ ፓርቲ ለተደረገው ከፍተኛ እርዳታ እና እገዛ ብቻ አይደለም ከፍተኛ ምስጋናውን ያቀረበው እና የተደነቀው፣ ሆኖም ግን በኢትዮጵያውያኑ/ቱ መከባበር፣ ፍቅር እና በሁሉም ዘንድ ስላስተዋለው መናበብ ጭምር እንጂ፡፡

ጉብኝቱ የሚፈጥራቸው ስዕሎች፣
የሰማያዊ ፓርቲ የአንድ ጊዜ ጉብኝት ትምህርታዊ፣ ቀስቃሽነት፣አረጋጋጭነት፣ እና ስሜታዊነት የተንጸባረቀበት ልምድ መስሎ ሊታየን ይችላል፡፡ ለእኔ የጉዞው ጉብኝት “የእውነት ድርጊቶች“ ማቀነባበሪያ ትውስታ ሆኖ ይታየኛል፡፡ እኔ ስለኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስለታሪካዊ ዕጣፈንታቸው ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እናገር እና እጽፍ ነበር፡፡ ያ ህልም አሁን እውን ሆኖ በፖለቲካ ድርጅት ማቋቋም (በእኔ እምነት የወጣቶች ንቅናቄ) የተከሰተ ሲሆን ይህም የወጣቶች፣ ለወጣቶች፣ በወጣቶች የተመሰረተ ፓርቲ ነው፡፡ ከዚህም በላይ በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ ህዝብ እድሜው ከ35 ዓመት በታች የሚሆነውን 70 በመቶ የያዘው የወጣቱ ህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡
የኢትዮጵያ አቦ-ጉማሬው ትውልድ (የቀድሞው ትውልድ) አባል ሆኘ ከኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ (ወጣቱ ትውልድ) ጋር ተቀራርቦ የመስራት ዕድሉን በማግኘቴ ታላቅ ክብር እና ሞገስ ይሰማኛል፡፡ እነዚህ የወጣቱ ትውልድ አባላት አስደናቂዎች ናቸው፡፡ በአእምሯቸው ፈጣንነት፣ በአስደናቂ እይታቸው እና አመለካከታቸው፣ እርምጃ ለመውሰድ ባላቸው መንፈሰ ጠንካራነት፣ የቴክኖሎጅ እድገትን ለማምጣት ባላቸው በጎ አመለካከት እና ብቃት፣ በቴክኒክ እና በድርጅታዊ ክህሎት ፈጣን ችሎታቸው እና መግባባትን በተላበሰ መልክ በሚያደርጓቸው የስራ ግንኙነቶች በጣም እደነቃለሁ፡፡ አቦሸማኔውን (እራሴን “የአቦ-ጉማሬው ትውልድ” አባል አድርጌ ብቆጥረውም ቅሉ የመካከለኛው ትውልድ አባል ዋና ተግባሩ የአቦሸማኔውን እና የጉማሬውን ትውልዶች የሚያገናኙ ድልድዮችን መገንባት) በምክር እና በሀሳብ ማገዝ፣ የምክር አገልግሎት መስጠት፣ ጥያቄዎችን መመለስ እና በተፈለግሁበት ጊዜ ሁሉ እየተገኘሁ ስለሰማያዊ ፓርቲ አስረጅነት ምስክርነቴን የመስጠት ሚና ከልብ የምደሰትበት ተግባር መሆኑ ላይ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡

በሰማያዊ ፓርቲ የጉብኝት ጉዞ ጊዜ ያለንን የጋራ ስብስብ ልምዶች በተሻለ መልክ የሚገልጸው አንድ ቃል “መከባበር” የሚለው ነው፡፡ ፍቅር እና መተባበርን በተላበሰ መልኩ ሁሉንም ዜጎቿን በእኩልነት እና የእያንዳንዱን ዜጋ መብት እና ክብር በሚጠብቅ ግንኙነት ላይ ተመስርቶ ፍቅር የነገሰባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ኢትዮጵያውያን/ት በየሄድንበት ሁሉ ከልብ በመነጨ መልክ ሲያደርጉት የነበረው ተሳትፎ እና አቀባበል ስሜታችንን ገዝቶ ከልብ እንድንመሰጥ አድርጎናል፡፡ ኢትዮጵያውያንን/ትን በመከፋፈል እና ከሰብአዊነት በማውረድ በጎሳ፣ በኃይማኖት፣ በክልል እና በቋንቋ በመለያየት የሚያራምደውን ስርዓት በመቃወም ሀሳባቸውን በግልጽ ሲያራምዱ በነበሩት ኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቻችን ከልብ ተመስጠናል፡፡ ካለፉት ስህተቶች እንድንማር እና በትግል ሂደቱ ወቅት በውል ተለይተው የሚታወቁ ስህተቶችን ልናስወግድ የምንችልባቸውን መንገዶች እንድንገነዘብ ገንቢ የሆነ ምክራቸውን ሲሰጡን ለነበሩት ወገኖቻችን ሁሉ ከልብ የመነጨ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ ውድቀትን እራሱን በምንም ዓይነት መንገድ እንዳንፈራ፣ ሆኖም ግን ውድቀትን መፍራት ሽባ እና አቅመቢስ እንደሚያደርገን ፍቅር የተላበሱት ወገኖቻችን አጽንኦ በመስጠት የመከሩን ምክር በልባችን ሰርጾ በደምስራችን ሁሉ ተዋህዶ እንድንደፋፈር እና በሞራል እንድንሞላ ስንቅ ሆኖናል፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ለማምጣት ለምናደርገው ትግል የቱንም ያህል ጊዜ ቢወስድም ከጎናችን በመቆም ትግሉን በሞራል፣ በገንዘብ እና በማቴሪያል ለማገዝ ቃል በገቡልን ወገኖቻችን እጅግ ተደስተናል፡፡ ቅንነት በተሞላበት መንፈስ ስለሰማያዊ ፓርቲ ምንነት ከአንዳንድ ወገኖቻችን የበለጠ ለማወቅ እና ከጎኑ ለመሰለፍ እንዲችሉ ለማድረግ የነበረው ጉጉት እና ሲንጸባረቅ የነበረው የተነሳሽነት ስሜት በደስታ እንድንሞላ አድርጎናል፡፡

በጉብኝት ጉዞው ጊዜ ባካሄድናቸው በአንዳንድ የስብሰባ ቦታዎች በወገኖቻችን የተነሱ ጥቂት ጨለምተኝነት የተንጸባረቀባቸው ስሜቶችንም በማስታወሻችን ከትበን ይዘናል፡፡ አንዳንዶቹ ተስፋ በቆረጠ መልኩ ብሩህ ነገር እንደማይታያቸው የሰጡት አስተያየት ከእውነታው ውጭ እንደሆነ ስለምናምን እንድናዝን አድርጎናል፡፡ ምክንያቱም አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ካልተሳካ በሌላ ጊዜም አይሳካም የሚል ሃይማኖታዊም ሆነ ሳይንሳዊ አመክንዮ የለም፡፡ ጨለምተኝነታቸውን የበለጠ ለማስረገጥም እንዲህ ብለዋል፣ “ከእናንተ በፊት ሁሉም ወደ እኛ የመጡት ሁሉ ስኬታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል፣ የእናንተስ እጣፈንታ ከዚያ የማይለይ ላለመሆኑ ምን ማረጋገጫ አለን? እናንተም ስኬታማ ላለመሆን ትችላላችሁ“ በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህን በማለት ያቀረቧቸውን ቅሬታቸው በሚገባ እንረዳለን፡፡ ሌሎቹ እብሪት አዘል አስተሳሰብ የያዙ ወገኖቻችን ደግሞ የወጣቶችን የብሩህ አእምሮ ባለቤትነት እና የአዳዳስ ሀሳቦች አፍላቂ እና ፈጣሪዎች ስብዕናን አሳንሶ በማየት  ወጣቶቹ ምን እንደሚሰሩ አያውቁም በማለት እንደሚያስቡ እና ወጣቶቹ ምን መስራት እንዳለባቸው እና መስራት እንደሌለባቸው ለመስበክ ሲሞክሩ ስንሰማ በጣም አስገርሞናል፡፡ እኛ ለዚህ ግድ የለንም፡፡ 

ምንጊዜም ለመማር ዝግጁ ነን፡፡ እንዲህ በሚሉት የቶማስ ጥርጣሬዎች ተይዘን ነበር፣ “ሲመጡ እና ሲሄዱ አይተናል፣ ከሌሎች የተለዬ ሆናችሁ የምትታዩበት ነገር የለም፣ እናንተን ልዩ የሚያደርጋችሁ የሚለያችሁ ነገር ምንድን ነው?“ ለጉዳዩ ትኩረት ባለመስጠት ትንሽ የንቀት ስሜት በተቀላቀለበት አኳኋን ሲጠይቁ ነበር፡፡ ጥርጣሬ የእምነት መሰረት ነው፡፡ ፍቅር የነገሰባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ወጣት የህብረተሰብ ክፍል ተዋናይነት በእርግጥም በቀድሞው ትውልድ ድጋፍ ትገነባለች በማለት እነርሱን ለማሳመን ማድረግ ያለብንን ሁሉ አድርገናል፡፡ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የሆድ ቁርጠት የሆነባቸውን፣ የደስታ ስሜት የራቃቸውን፣ የሚያጉረመርሙትን እና የሚያማርሩትን ወገኖቻችን ትዕግስት በተሞላበት ሁኔታ እና በከበሬታ አዳምጠናቸዋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ በቂ ምክንያቶች ነበሯቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪም ስለእራሳችን እና ምን ማድረግ እንዳለብንም ተምረናል፡፡ የትግል ስልታችንን ማስረዳት እና መግለጽ ነበረብን፡፡ እንዲህ የሚል ጥያቄም ቀርቦልን ነበር፣ “እስከ አፍንጫው ድረስ የጦር መሳሪያ የታጠቀ እና በፖሊስ እና በደህንነት ኃይል የተደራጀ ጨካኝነት የተሞላበት ታሪክ ያለው አምባገነን ገዥ አካል ድል ለማድረግ እንዴት ይቻላል ብላችሁ ታስባላችሁ?“ የእኛ መልስ ጋንዲ ከሰጡት መልስ ጋር ተመሳሳይ ነበር፣ እንዲህ የሚል፣ “ጥንካሬ ከአካላዊ ብቃት የሚመጣ አይደለም፣ ወይም ደግሞ ከጠብ መንጃ፣ ከታንክ እና ከጦር አውሮፕላን የሚመጣ አይደለም፣ ጥንካሬ ወዲያውኑም ድል የሚመጣው ከማይበገረው ጽኑ  እምነታችን ነው፡፡“ በሰላማዊ ትግላችን ላይ ማህለቁን የጣለ የማይበገር ጽኑ እምነት አለን፡፡ በፍቅር የተሞላ የማይበገር ጽኑ እምነት ምንጊዜም ሊሸነፍ አይችልም፡፡

ምንጊዜም ቢሆን ለውጥ በአጠቃላይ በህብረተሰቡ ውስጥ ከመምጣቱ በፊት በእያንዳንዱ ወንድ እና ሴት ልብ እና አእምሮ ውስጥ መስረጽ እንዳለበት አስተምረናል፡፡  ስለዚህም እኛን ጥላሸት ለመቀባት ከሚፈልጉት ወገኖቻችን ጋር ትግል ከመጀመራችን በፊት በልቦቻችን ውስጥ ኑሮን ከመሰረቱት ከጥላቻ እና ከበቀል ጭራቆች ጋር ትግላችንን ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ከእኛ ሀሳቦች፣ የማስፈጸሚያ መንገዶች እና ስልቶች ጋር ከማይስማሙ ወገኖቻችን ጋር ትዕግስት እና መከባበርን በተላበሰ መልኩ ልናስተናግድ ይገባል፡፡ በመርህ ደረጃ ምንጊዜም በመሬት ላይ መቆም አለብን፡፡ በሰላማዊ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ለውጥ እናምናለን፡፡ በዚህ መርህ መሰረት ከማንም ጋር ቢሆን ካለመስማማት ውጭ ካልሆነ በስተቀር ላለመስማማት መስማማት ይኖርብናል፡፡  በሌሎች ስኬቶች እና ስህተቶች ሳይሆን እኛ በምናበረክተው ጠቀሜታ ብቻ መገምገም እንዳለብን እናምናለን፡፡ የምንለውን በተግባር ላይ ለማዋል ምንጊዜም ቢሆን ጠንቃቃ መሆን አለብን፡፡ ይህም ማለት ከፍተኛ የሆነ የተያቂነት፣ የግልጽነት እና የሰለጠነ አካሄድ ስርዓትን መከተል ይኖርብናል፡፡ በእርግጥ ደጋፊዎቻችን የእኛን ልዩ ሆኖ መቅረብ፣ የበለጠ ታማኝነትን እና ቀጥተኛነትን ማሳየት እና ሀሳቦችን ለመቀበል ዝግጁ ሆኖ መገኘት እንዳለብን ከእኛ ይጠብቃሉ፡፡

የወደፊት ትግላችን፡ ኢትዮጵያ እንደ ዳዊት እና ህወሀት/ኢህአዴግ እንደ ጎልያድ
በኢትዮጵያ የሚደረገው የስርዓት ለውጥ በጣም አስቸጋሪ እና ታላቅ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ገዥው አካል ሰማያዊ ፓርቲን ለማዳከም እና ለመደምሰስ ሲል ያለውን ኃይል ሁሉ በመጠቀም ሌት እና ቀን እንደሚሰራ ለእኛ የሚሰወር አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው ገዥው አካል በሰማያዊ ፓርቲ አባላት ላይ በዘፈቀደ ከህግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር የማዋል፣ የእስራት፣ የማሰቃየት፣ የይስሙላ የህግ ሂደትን የማሳየት እና የግድያ ተግባራትን ሊፈጽም እንደሚችል ከግንዛቤ ማስገባት ይኖርብናል፡፡ ገዥው አካል በሰማያዊ ፓርቲ አባላት እንቅስቃሴ ላይ ህገወጥ እርምጃ ሊፈጽም እንደሚችል መተንበይ ማለት ነገ ፀሐይ ትወጣለች ብሎ እንደመተንበይ ይቆጠራል፡፡ ላለፉት 23 ዓመታት ገዥው አካል እየተከተለ ያለውን የአሰራር ተሞክሮ እናውቃለን፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት በምንም ዓይነት መልኩ አይፈሩም፡፡ የሰለጠኑ ወሮበላ ደብዳቢዎችን እና ጠመንጃዎችን አይፈሩም፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ አዲስ ዝርያ ያላቸው ኢትየጵያውያን/ት ወጣት መሪዎች እየተነሱ እና ለነጻነት እና ለዴሞክራሲ ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረጉ ያለበት ሁኔታ እየተፈጠረ ስለሆነ ባለው ገዥ አካል ካባ ስር ተደብቀው እና ተወሽቀው በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሸፍጥ በመስራት ላይ ያሉትን ወሮበሎች የሚፈሩ አይደሉም፡፡ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ውብሸት ታዬ፣ አንዷለም አራጌ፣ ኦልባና ሌሊሳ፣ በቀለ ገርባ፣ አቡባከር እና ሌሎች ብዙዎች በአስቀያሚነቱ በሚታወቀው በመለስ ዜናዊ የቃሊቲ የማጎሪያ እስር ቤት ወስጥ ታስረው በመማቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ መንፈሰ ጠንካራ ወጣቶች በስልጣን ላይ ያለው ገዥ አካል ትግላቸውን እንዲያቆሙ ቢያስፈራራ እና የማሸበር ድርጊቱን በግልጽ እና በስውር በየጊዜው ቢያካሂድም ለአገራቸው ነጻነት እና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ታጥቀው የተነሱት ወጣቶች ሊበገሩለት አልቻሉም፡፡ እምቢኝ አሻፈርኝ ለነጸነቴ ብለው ቃል በመግባት የጭቆናን አገዛዝ ከስሩ መንግሎ ለመጣል በጽናት ተነስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሰላማዊ ትግል ለውጥ ለማምጣት የምናምን ኢትዮጵያውያን/ት በሙሉ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን/ት ልብ እና አእምሮ መግዛት ይኖርብናል፡፡ የእኛ ስኬታማነት መለካት ያለበት በጽናት እና ቀጣይነት ባለው መንገድ ህዝቡን አስተምረን በማሳመን በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ለማምጣት በመረጡ ህዝቦች ብዛት ነው፡፡ በስልጣን ላይ ያሉት ኃይሎች ደግሞ ድላቸውን እና ምን ያህል ኃያል እንደሆኑ የሚለኩት በየውጊያ መስኮች ምን ያህል ኢትዮጵያውያን/ት እሬሳዎችን ለመዘረር እንደቻሉ በድንን በመቁጠር ነው፡፡ ይህ የአሁኑ የትግል ውጤት ቀደም ሲል የተተነበየ እና ተግባራዊ የተደረገ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ በአንድ ወቅት ጎልያድ የሚባል በጣም ኃይለኛ የሆነ ሰው ነበር፡፡ የብረት እና የነሀስ ቆብን ለስጋዊ ህይወቱ መሸፈኛ በማድረግ ጎልያድ በተራራው ላይ በመውጣት እብሪት በተቀላቀለበት መልኩ ቀን በቀን ህዝቡን ማስፈራራቱን ቀጠለበት፡፡ በአካባቢው ሁሉም በመፍራቱ ምክንያት ጎልያድን የሚገዳደር አንድም ሰው ጠፋ፡፡ ከዚያም አምላክን ብቻ እንጅ ማንንም የማይፈራ እና ሲያዩት ጥንካሬ የሚጎድለው የሚመስል ዳዊት የሚባል ኮሳሳ ወጣት እረኛ ከመንጋዎቹ መካከል ብቅ አለ፡፡ ዳዊት የወርቅ፣ የብር እና ሌሎች የከበሩ ሽልማቶችን ለማግኘት ሲል የመጣ ሳይሆን የራሱን ወገኖች ኩራት፣ ክብር እና እምነት ለመመለስ በማለም ከጎልያድ ጋር ፍልሚያ ሊያደርግ ወሰነ፡፡ 

 ዳዊት ጎራዴ፣ ጦር፣ መከላከያ ብረት ለበስ ልብስ እና የእራስ የብረት ቆብ ተሰጠው፡፡ ዳዊት  በወንጭፍ እና በ5 ጠጠሮች አማይነት ከጎልያድ ጋር ለመዋጋት መረጠ፡፡ ጎልያድ ባዶ ጩኸት እያሰማ እና በትንሹ ዳዊት ላይ የንቀት ስሜትን በማሳየት ዳዊት ሊገጥመው እንደማይቻለው እየተንጎማለለ ቡራ ከረዩ ማለት ጀመረ፡፡ ዳዊት ጎልያድን አገኘው እና ጎልያድ ምንም ነገር እንዳልሆነ በህሊና ሚዛኑ መዝኖ የተሸከመውን የእብሪት ቀልቀሎ በአንዲት ጠጠር በወንጭፍ ተኳሽነት ማስተንፈስ እንደሚችል በተግባር አረጋገጠ፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ በፍርሀት እና በጥላቻ የተሞላው ወያኔ/ኢህአዴግ እየተባለ የሚጠራው ጎልያድን ድል የሚያደርግ የኢትዮጵያ ዳዊት ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ኃቅን እና ኃቅን ብቻ ይዞ የተነሳ ለኃይለኞች ተገዳዳሪ ሆኖ የመጣ የፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡ ወያኔ/ኢህአዴግ የተባለው ጎልያድ ጠብ መንጃዎችን፣ ቦምቦችን፣ ታንኮችን፣ ከባድ መሳሪያዎችን እና የጦር አውሮፕላኖችን ሁሉ አግበስብሶ በመያዝ እስከ አፍንጫው ድረስ ዘመናዊ የጦር ትጥቅ የታጠቀ ሀሰትን የአቅጣጫው መመሪያ ኮምፓስ አድርጎ የተነሳ ቡድን ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በአሁኑ ጊዜ ብዛት ያለው ጨቋኝ የፖሊስ እና የደህንነት ካድሬዎችን ሰብስቦ ከያዘ ከአፍሪካ ተወዳዳሪ ከማይገኝለት ጎልያድ በተጻራሪ የቆመ ፓርቲ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የገንዘብ እርዳታ እና ብድር ከሚደረግለት እንዲሁም ከህዝብ የተዘረፈ ገንዘብ በማግበስበስ ኃይሉን ካጠናካረ ጎልያድ ጋር ለመገዳደር እና ድል ለማድረግ በተጻራሪ የቆመ ፓርቲ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የጥላቻ እና መለያየት መርዝን ከሚረጨው የጎልያድ ደም፣ ውሸትን እና ማጭበርበርን ከሚፈበርከው የጎልያድ አእምሮ፣ በተስፋ ማጣት እና በመከራ ውስጥ ተዘፍቆ ከሚዳክረው የጎልያድ መንፈስ፣ እና ህይወቱን እና አስትንፋሱን ከሚያጨልመው የጎልያድ ልብ በተጻራሪ የቆመ ዳዊታዊ ጽኑ መንፈስ የተሞላበት ፓርቲ ነው፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ ወንጭፍ እንዲሁም ፍቅር፣ እውነት፣ ተስፋ፣ ሰላም እና አንድነት የሚባሉ አምስት ጠጠሮችን ብቻ በመታጠቅ ከወያኔ/ኢህአዴግ ጎልያድ ጋር ለመፋለም ቆርጦ የተነሳ ፓርቲ ነው፡፡ በመጨረሻም ሰማያዊ ፓርቲ በወያኔ/ኢህዴግ ጎልያድ ላይ ድልን ይቀዳጃል፣ እናም ወያኔ ይድናል፣ በእርግጥም ይድናል፣ ምክንያቱም የሰማያዊ ፓርቲ ጠጠሮች ይፈውሳሉ እንጅ አይገድሉም፡፡ ከወያኔ/ኢህአዴግ ጎልያዶች በተጻራሪ ከቆሙት ከሰማያዊ ፓርቲ የኢትዮጵያ ዳዊቶች ጎን ተሰልፌ ለፕሮጀክቱ ግንባታ ስኬታማነት ለህንጻው ጥንካሬ ውኃ ማቀበል በመቻሌ ከፍ ያለ ክብር ይሰማኛል፡፡

ለሰማያዊ ፓርቲ ዕ(ድል) እንስጠው
በተለያዩ የሰማያዊ ፓርቲ የከተማ የስብሰባ አዳራሾች ስብሰባዎች ላይ በመገኘት “ጠቃሚ ንግግሮችን” ሳሰማ በመቆየቴ ልዩ የሆነ ክብር እና ሞገስ ተሰምቶኛል፡፡ እኔ እራሴን “ጠቃሚ ንግግር” አድራጊ አድርጌ አልቆጥርም፡፡ እራሴን የምቆጥረው እንደ አንዳንድ ታሪካዊ የሆኑ ወሳኝ ክንውኖች ሲከናወኑ በማየት ለማስረዳት ፈቃደኛ ሆኖ በመቅረብ “ምስክርነት” መስጠት ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከወያኔ/ኢህአዴግ ጎልያድ ጋር በሚያደርገው ትግል በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ት ለሰማያዊ ፓርቲ የውጊያ ዕድል እንዲሰጡ፣ የድጋፍ ዕድል እንዲያደርጉ  ለመጠየቅ እና በተስፋም ለማሳመን ምስክር ሆኘ ቀርቢያለሁ፡፡

ሰማያዊ ፓርቲን በሙሉ ልብ እደግፈዋለሁ፣ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ወጣቶች የአገራቸውን ዕጣፈንታ ለመወሰን እና ፍቅር የነገሰባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት ራዕይ፣ ኃይል፣ ብቃት እና ጽናት ያላቸው ብቸኛዎቹ ኃይሎች በመሆናቸው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት ወደ 94 ሚሊዮን ገደማ እንደሚሆን የሚገመት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ዕድሚያቸው ከ35 ዓመት በታች የሚሆነው 70 በመቶውን የሚሸፍነው የወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በብዛት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሰለባ ሆነው የሚገኙት ወጣቶች ናቸው፡፡ የፖለቲካ ጭቆና እና ማስፈራራት፣ ከህግ አግባብ ውጭ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር የማዋል እና እስራት፣ ማሰቃየት፣ ማዋረድ እና ደካማ የእስር ቤት አያያዝ ሰለባ የሚሆኑት በአብዛኛው በሚባል መልኩ ወጣቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስር በሰደደ የስራ አጥነት ወጥመድ ተጠፍረው እና የትምህርት እና ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን አጥተው የበይ ተመልካች የሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ለነጻነት እና ለስርዓት ለውጥ የሚያነሱት ጥያቄ በእራሱ ገላጭ ነው፡፡ ለውጥ ሰላማዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ይመጣል ነገር ግን ለውጡ ዘግይቶ እንደሚመጣ ባቡር ነው፡፡ ጥያቄ ሊሆን የሚችለው የኢትዮጵያ ወጣቶች ለውጡ ዕውን እንዲሆን የሚፈልጉት እየጨመረ በመጣው የኃይል አሰላለፍ ነው ወይስ በሰላማዊ መንገድ በሚደረግ ሽግግር ነው የሚለው ነው፡፡

ላለፉት ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ ሲደረግ በቆየው የሰብአዊ መብት ጥበቃ የትግል ሂደት የእራሴን መጠነኛ የሆነች ድርሻ ለማበርከት ሞክሪያለሁ፡፡ ሆኖም ግን ዘግይቸ የወሰድኩት ኃላፊነት ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ከእኔ ሳምንታዊ ትችቶቸ እና ንግግሮች ትምህርት አግኝተንበታል በማለት በኢትዮጵያ የአቦሸማኔው እና የአቦ-ጉማሬው ትውልድ ከመስማት የበለጠ ክብር የሚሰጥ ነገር አላገኝም፡፡ መምህር ከዚህ በላይ ምን ሊጠይቅ ይችላል?
ባለፉት ጊዚያት የሰብአዊ መበቶች ጥበቃ ድጋፍ እንድናደርግ እና ለግለሰብ መብቶች ክብር መጠበቅ በሚል እሳቤ ለአንባቢዎች ጥያቄዎችን፣ ልመናዎችን እና ተማጽዕኖዎችን በተደጋጋሚ ሳቀርብ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁን አንባቢዎቸን የምጠይቀው በእርግጥም የምማጸነው በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት ከሁሉም በኢትዮጵያ ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ከሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች የበለጠ ያስጠብቃል የሚል እምነት ለምጥልበት በኢትዮጵያ ወጣቶች ለተገነባው ለሰማያዊ ፓርቲ ድጋፋችሁን እንድታደርጉ ነው፡፡

እኔ ሰማያዊ ፓርቲን ስለደገፍኩት ብቻ አንባቢዎቸ እንዲደግፉት አልፈልግም፣ ሆኖም ግን ለሀገራቸው ራዕይ ባላቸው የአቦሸማኔዎቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች የተሞላው የሰማያዊ ፓርቲ ስብስብ እራሱ ለሀገሪቱ ከሚያስገኘው ጠቀሜታ አንጻር ብቻ በአእምሯቸን የፍርድ ሚዛን ተመዝኖ ሊደገፍ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲን ለመደገፍ ከውሳኔ ላይ በደረስኩበት ወቅት ጥቂት ጥያቄዎችን አንስቸ ነበር፡፡ እነዚህም 1ኛ) በሰላማዊ መንገድ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት በእውነት ሙሉ እምነት አለኝን? 2ኛ) በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ለማምጣት ሙሉ እምነት አለኝ ካልኩ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ካለው ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የትኛው የፖለቲካ ፓርቲ ነው ይህንን ዓላማ በተሻለ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ ወደ ተግባር ሊቀይረው የሚችል? 3ኛ) እንደዚህ ያለውን ለውጥ የኢትዮጵያ ወጣቶች የፈጽሙታል የሚል እምነት ካለኝ እነርሱን ለማገዝ ምን ማድረግ እችላለሁ?

በውጭ የምንገኝ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት በሙሉ ሰማያዊ ፓርቲን በተለያዩ መንገዶች ልንደግፈው እንችላለን፡፡ አቅሙ ያላቸው የተቻላቸውን ያህል በገንዘብ ሊደግፉ ይችላሉ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ድርጅታዊ ስራውን በተቀላጠፈ መልክ ለመስራት እና ብዙሀኑን የወጣት ክፍል ለመድረስ ለሚያድርጋቸው ጥረቶች ብዙ ገንዘብ ይፈልጋል፡፡ ሌሎችም ከእዚህ ያላነሱ ለሰማያዊ ፓርቲ ድጋፍ ልናደርግባቸው የምንችልባቸው መንገዶች አሉ፡፡ ስለሰማያዊ ፓርቲ ማወቅ እና ሌሎችን ማስተማር ታላቅ ጠቀሜታ ያላቸው ድጋፎች ናቸው፡፡ ለሰማያዊ ፓርቲ በሁሉም መስኮች ያተኮረ የፖሊሲ ትንተና እና ልማትን ያካተተ የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምሁራን እና የአካዳሚው ማህበረሰብ በዚህ ረገድ ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲን የተስፋ፣ የአንድነት እና የሰላም መልዕክቶች ለሌሎች መረጃው ለሌላቸው ወገኖቻችን ማሰራጨት ከሌሎች ድጋፎች ሁሉ የበለጠ ጠቃሚ ድጋፍ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲን ከሚሰነዘሩበት የውሸት ውንጀላዎች እና ክሶች እንዲሁም የፍርሀት እና ጥላሸት የመቀባት ዘመቻዎች መከላከል ጠቃሚ ድጋፍ ነው፡፡ የሞራል ድጋፍ መስጠት እና ለሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት ከፍተኛ የሆነ የማበረታቻ ድጋፍ ማድረግ ሌላው ታላቅ ድጋፍ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲን ማድነቅ ማንም ኢትዮጵያዊ/ት ጀግና አርበኛ ሊያደርገው/ልታደርገው የሚገባ ታላቅ ድጋፍ ነው፡፡

የግል ምልከታ
ከሰማያዊ ፓርቲ የድጋፍ ስብስብ ወጣቶች ጋር መስራት ለእኔ የሚያስደንቅ ልምድ ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት በሳምንታዊ ትችቶቸ እና አልፎ አልፎ በማደርጋቸው ንግግሮች የኢትዮጵያ ወጣቶችን ለማስተማር፣ ለማሳወቅ እና ብዙሀኑን ወጣቶች ለመድረስ የተቻለኝን ያህል ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ እንዲጠናከር እና ከፍ ወዳለ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ጥረት ሲያደርጉ ለቆዩት እና አሁንም በማድረግ ላሉት ወጣት ፕሮፌሽናሎች፣ የንግድ የስራ ፈጣሪዎች/ኢንተርፕሪነሮች እና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በአማካሪነት ደረጃ ተመድቤ እያገለገልኩ በመሆኔ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሰማያዊ ፓርቲ የድጋፍ ስብስቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተጠናከሩ መምጣት የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ወጣቶች ተባበሩ በፍጹም እጅ እንዳትሰጡ የሚለውን እምነቴን የበለጠ እንዲቀጣጠል አድርጎታል፡፡
ስለሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ስለይልቃል ጌትነት ያሉኝን የእራሴን ጥቂት ምልከታዎች ላካፍላችሁ፡፡ ባለፉት ስምንት ዓመታት ከበርካታ የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የንግድ እና የማህበረሰብ መሪዎች ጋር በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ተገናኝቻለሁ፡፡ ብዙዎቹ እነዚህ መሪዎች የሚያስደምሙ ስብዕናዎች አሏቸው፡፡ ለማንኛውም የፖለቲካ መሪ ባህሪ ዋና የስብዕና ማረጋገጫ ነው የሚል አመለካከት አለኝ፡፡

ይልቃል የፕሮፌሽናል እና የቤተሰቡን ፍላጎት በመግታት ለኢትዮጵያውያን/ት ወገኖቹ ነጻነት በማለም በኢትዮጵያ ሰላማዊ የለውጥ ሽግግር ለማድረግ ሌት ከቀን የሚታትር ወጣት መሀንዲስ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱን ምርጫ ለመወሰን ታላቅ ስብዕናን እና ግላዊ የመንፈስ ጥንካሬን ይጠይቃል፡፡ በጉብኝት ጊዚያችን የይልቃልን ዘርፈብዙ ባህሪያት ለመመልከት ችያለሁ፡፡ የመርህ ሰው መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ለማምጣት በሚል እየተከተለ ያለው ምዕናባዊ ሀሳብ እንጅ አሁን ካለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ በተግባር ሊውል እንደማይችል እና ይህ አካሄድ ከውድቀት እንደማያድን የሚፈታተኑ ጥያቄዎች ቀርበውለታል፡፡ እርሱም የክርክር ጭብጦቹን በሚያሳምን መልኩ አዘጋጅቶ ኃይል የደካሞች መሳሪያ መሆኑን፣ ማንም ቢሆን በጉልበት እና በኃይል ተጠቅሞ ልብን እና አእምሮን ሊቀይር እንደማይችል አጽንኦ በመስጠት ለማሳመን ጥረት አድርጓል፡፡ 

ኢትዮጵያ የክልሊስታንስ (የክልሎች) አወቃቀር እንደያዘች መቀጠል ያለባት ትክክለኛ የፖለቲካ መስመር መሆኑ ታምኖበት መስተካከል ያለበት ነገር ቢኖር “የብሄሮችን እና የብሄረሰቦችን” መብት ከማስከበር ላይ ነው የሚል ሌላ ፈታኝ አስተያየት ቀርቦለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የግለሰብ መብቶች ሲከበሩ እና ጥበቃ ሲደረግላቸው የቡድን መብቶችም በዚያው ልክ ይከበራሉ ጥበቃም ይደረግላቸዋል የሚለውን መርህ በማንሳት በሚያሳምን ሁኔታ ለማብራራት ሞክሯል፡፡ በሌላም በኩል መብት ደፍጣጩ ገዥ አካል እርሱን እና ሌሎችን በሰማያዊ ፓርቲ አመራር ላይ ያሉትን ሰዎች መብት ቢደፈጥጥ፣ ቢያስር፣ ቢያሰቃይ እና ቢገድል ምን ዋስትና አለ የሚል ሌላ ፈታኝ አስተያየት ቀርቦለት ነበር፡፡ እርሱም ሲመልስ ይህ ይፈጸማል በሚል እንደማይፈራ ምክንያቱም እርሱና ሌሎች የሰማያዊ ፓርቲ የአመራር አባላት ይህንን ፓርቲ ገና ከመጀመሪያው አልመው ሲመሰርቱ ትክክለኛውን ነገር ለመስራት ለአገራቸው እና ለወገኖቻቸው ነጻነት ሲባል ማንኛውንም መስዕዋትነት ለመክፈል ዝግጁነታቸውን አረጋግጠው እንደሆነ በማስገንዘብ በሙሉ ልብነት ይህ አያስፈራንም ብሏል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ በወጣቱ እና በቀድሞው ትውልድ መካከል የልዩነት መስመር በማስቀመጥ ልዩነትን ሲያራምድ የቆየ ነው በሚል ትንተና እና ጩኸት የቀረበለትን ሀሳብ ይህ የሀሰት ውንጀላ ነው በማለት አስተባብሏል፡፡ እንደ መርህ ስንወስደው በትውልዶች መካከል የስራ ክፍፍል መኖር አለበት በማለት ጉዳዩን ግልጽ አድርጎታል፡፡ የኢትዮጵያ የቀድሞው ትውልድ አባላት አማካሪዎች እና ድጋፍ ሰጭዎች በመሆን ወሳኝ ሚና መጫወት ያለባቸው ሲሆን ወጣቱ ትውልድ ደግሞ ከባዱን ሸክም ለማንሳት በየመንገዶች መደብደብ እና እየተያዘ በእስር ቤቶች ታስሮ እየማቀቀ ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ዓላማ ከግብ ማድረስ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የመጨረሻውን ወሳኙን ለውጥ ለማምጣት ፍላጎቱ፣ ጽናቱ፣ ብቃቱ፣ ኃይሉ እና የፈጠራ ችሎታው ያለው በኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ወጣቶች ትከሻ ላይ ነው ብሏል፡፡ “አሜን!” ብያለሁ፡፡ ይልቃል የእርሱ ፓርቲ ከሌሎች የገዥውን አካል ከሚቃወሙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር “ህብረት” በመፍጠር ለመታገል ጥረት  ለምን እንደማያደርግ ከባድ ወቀሳ ተሰንዝሮበታል፡፡ በምላሹም የእርሱ ፓርቲ ከሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አብሮ እየሰራ እና እያስተባበረ እንዳለ ሆኖም ግን ከሌሎች የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መሰረታዊ የሆኑ የፖሊሲዎች፣ የእስትራቴጂዎች እና የስልቶች ልዩነቶች ስላሉ “ህብረት” የመፍጠር እንቅስቃሴውን ፈታኝ ያደርገዋል ብሏል፡፡ አያይዞም በውጭ የምንገኘው የዲያስፖራ አባላት በአገር ውሰጥ ያሉትን የተቃዋሚ ኃይሎች ለምን ህብረት ፈጥረው በአንድነት አይታገሉም በማለት በተደጋጋሚ በመተቸት ከመውቀስ ባለፈ በውጭ የምንገኘው የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት እራሳችን ህብረት በመፍጠር በአንድነት በመስራት በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን አምባገነንነት በመታገል ለሌሎች በሀገር ቤት ላሉት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አርዓያ ሆናችሁ አታሳዩም በማለት ጥያቄውን በጥያቄ በመመለስ ይህ ጉዳይ ሁልጊዜ የሚገርመው መሆኑን ገልጿል፡፡

ይልቃል ትንሽ ተክለሰውነት ያለው ወጣት ነው፡፡ በቀረቡለት ከአንድ በላይ የሆኑ ቀጥተኛ ፈታኝ ጥያቄዎች ሁሉ በሰለጠነ መንገድ ተገቢውን መልስ እና አስተያየት ሰጥቷል፡፡ በእውነት ለመናገር ይልቃል እውነተኛ ስልጡን አንጋፋ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል፡፡ በየሄደበት ቦታ ላገኛቸው ወገኖቹ ሁሉ ቅንነት እና አድናቆት የተሞላበት አቀራረብን አሳይቷል፡፡ በየደረሰበት ሊያናግሩት የሚሞክሩትን ወገኖች ሁሉ በጥሞና እና በትዕግስት ሲያዳምጣቸው ነበር፡፡ ሆን ተብሎ ስሜትን የሚፈታተኑ ጥያቄዎች በቀረቡለት ጊዜም በተረጋጋ እና ከስሜታዊነት በጸዳ መልኩ ምላሾችን ሲሰጥ ነበር፡፡ ወደ እውነታው ለመድረስ በሚደረገው ግንኙነት ሁሉ ያለምንም ስሜታዊነት በትዕግስት ከማዳመጥ እና ከመመለስ በስተቀር ተቃራኒውን ሲያሳይ አልተስተዋለም፡፡ እራሱን “የፓርቲ መሪ” ወይም ደግሞ ልዩ የሆነ ሰው አድርጎ አላቀረበም፡፡ በቀላሉ ሊገኝ የሚችል እና በህዝብ እና በግል ጉዳዮቹ በሚደረጉት ግንኙነቶች ሁሉ ቀናነት እና ግልጽነትን ሲያሳይ ነበር፡፡

የይልቃልን ስብዕና አድንቂያለሁ፡፡ ብዙዎችን ቦታዎች ስንጎበኝ በነበረበት ጊዜ የአቦሸማኔው እና የጉማሬው ትውልድ በየከተሞቹ የስብሰባ አዳራሾች ሁሉ ጢም ብሎ እስኪሞላ እናገኛቸዋለን በማለት ላሳምነው ሞክሬ ነበር፡፡ ከመድረኩ ጀምሮ እስከ ታዳሚው መቀመጫ ድረስ ከእያንዳንዱ የጉማሬው (የቀድሞው ትውልድ) አባላት ጎን የአቦሸማኔው (የወጣቱ ትውልድ) ተቀምጦ ይመለከት ነበር፡፡ የትኞቹ የአቦሸማኔዎች እና የትኞቹ ደግሞ የጉማሬው ትውልድ አባላት እንደሆኑ እንዳመለክተው ጠየቀኝ፡፡ በፍጹም መለየት አልቻልኩም፡፡ የቀድሞው ትውልድ አቦሸማኔዎች ከወጣቱ ትውልድ አቦሸማኔዎች አጠገብ ተቀምጠው ይታዩ ነበር፡፡ በጣም ጠቃሚ ትምህርት ተምሪያለሁ፡፡ የወጣቱ ወይም የቀድሞው ትውልድ መሆን ማለት የአዕምሮን ሁኔታ እንደ የአእምሮው ባለቤት ስብዕና ሁኔታ የማመሳል ያህል ነው፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ አቦሸማኔ ትውልዶችን ለመደገፍ በመውጣት በየስብሰባ አዳራሾች ሁሉ ለተገኛችሁ የወጣቱና እና የቀድሞው ትውልድ አቦሸማኔዎች ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋናየን አቀርባለሁ!

ለሰማያዊ ፓርቲ ዕ(ድል) እንስጠው! 
የሰሜን አሜሪካ የሰማያዊ ፓርቲ ድጋፍ ኮሚቴ
የ.ፖ ሳ.ቁ. 75860
ዋሽንግተን ዲሲ፣ 20013
ኢሜል፣ info@semayawiusa.org
እርዳታ ለማድረግ፣ http://www.semayawiusa.org/donate/
እርዳታ በቼክ፣ በገንዘብ ማዘዣ፣ በተከፋይ ወይም ደግሞ ሰማያዊ የሰሜን አሜሪካ ድጋፍ የሂሳብ አካውንት በቀጥታ ገቢ በማድረግ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል፡፡
አመሰግናለሁ…
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ጥር 13 ቀን 2006 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment