“የሙስና መርከብ” በሚል ስያሜ የሚጠሩት አሉ። ከተቋቋመ ጀምሮ
አንድም ቀን ስለንብረቱ መጠን ለህዝብ ተገልጾ አያውቅም። ከአገሪቱ ባንኮች ትልቁ ተበዳሪ ነው።የወጋጋን ባንክ ትልቁ
ባለድርሻ ነው። በአንዳንድ ከፍተኛ የንግድ ተቋማት ውስጥ የንግድ ሽርክና እንዳለው ይታማል። የወርቅ ማዕድን
ፍለጋው ሰምሮለታል። የግል አስመጪዎችን በመፈታተን አነካክቶ ጥሏቸዋል። አገሪቱ ላይ የገነባው የንግድ ኢምፓየር
በበርካቶች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል። በሌሎች ክልሎች በተመሳሳይ የተቋቋሙትን የንግድ ተቋማት በመደፍጠጥ በፖለቲካው
የበላይነቱ ሳቢያ ልዩ ተጠቃሚ በመሆኑ አይወደድም። ይህ ታላቅ የህወሃት የንግድ ግዛት ኤፈርት ነው።
የትግራይ ህዝብ “ያንተ ነው” ስለሚባለው ታላቅ የንግድ ኢምፓየር
የሚያውቀው ነገር እምብዛም የለም። አስራ ሶስት ሰፋፊና ስትራቴጂክ ኩባንያዎችን ያቀፈው ኤፈርት በቅርቡ የእህት
ኩባንያዎቹን ቁጥር እንደሚጨምር ምልክቶች አሉ። ኤፈርት ትግራይን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰራ በስፋት
ይነገርበታል። ከዚሁ ከሚታማበት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ይሁን በሌላ ወ/ሮ አዜብ በድንገት ይፋ ያደረጉት ምስጢር
አነጋጋሪ ሆኗል።
ወ/ሮ አዜብ መስፍን ኤፈርት ቀውስ ውስጥ እንደነበር በማስታወስ
ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የባለቤታቸውን የአቶ መለስን ማንነት የሚያጋልጥ አስገራሚ
መረጃዎችን ሰጥተዋል። “ኢትዮጵያ ህዳሴ ባለቤትና ባለራዕዩ መሪ” በመባል በራሱ በህወሓትና በመላው የኢህአዴግ ሰዎች
“የሚመለኩት” አቶ መለስ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ በጎሳና በቀበሌ ደረጃ ወርደው የሚያስቡ “የጎሰኛነት አባት”
መሆናቸውን ባለቤታቸው አሳብቀዋል። ትግራይን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ መታሰቡን ምንጮቹን በመጥቀስ የስዊድን
የኢትዮጵያ ሬዲዮ ከዓመት በፊት የዘገበውን ምስጢር ወ/ሮ አዜብ ይፋ አድርገውታል።
ከሃዘን ያገገሙ የማይመስሉት ወ/ሮ አዜብ ትግራይን በመነጠል
የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ አቶ መለስ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ዕቅድ ነድፈው እንደነበር ይፋ ሲያደርጉ ትግራይን
ያጥለቀልቃሉ ስለተባሉት ኢንዱስትሪ ዓይነቶች ዝርዝር ግን አልተናገሩም። የስዊድን የኢትዮጵያ ራዲዮ ከዓመት በፊት
ኤፈርት በትግራይ የምግብ ማቀናበሪያ ፋብሪካዎችና እጅግ ግዙፍ የሚባል የፒቪሲ ጥሬ እቃ ማምረቻ ፋብሪካ በመክፈት
ትግራይን በመነጠል የኢንዱስትሪ ከተማ የማድረግ እቅድ እንዳለው ምንጮቹን በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል። (ፒቪሲ
በጣም ተፈላጊ የሆነ እና እጅግ በርካታ ለሆኑ የእርሻ፣ የኮንስትራክሽን፣ … ሥራዎች በቀጥታ ወይም እንደግብዓት
የሚውል ነው)
ኤፈርት ቀውስ ውስጥ እንደነበር፤ በ2004 ግምገማ ተካሂዶ
ከነበረበት “ክራይሲስ” እንደወጣና በበጀት ዓመቱ 357 ሚሊዮን ብር የትርፍ ግብር መክፈሉን ያስታወቁት ወ/ሮ አዜብ
በዚህ መግለጫቸው ኤፈርት በእርሳቸው አመራር ያስመዘገበውን ትርፍ ይፋ በማድረግ የቀድሞውን ሃላፊ አቶ ስብሃት ነጋ
ለማሳጣት ያለሙ መስለዋል።
“በተዘዋዋሪ የህዝብ ንብረት ናቸው” ሲሉ የገለጿቸው የኤፈርት
እህት ኩባንያዎች ለአስራ ሰባት ሺህ ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ወ/ሮ አዜብ አመልክተዋል። መስፍን ኢንጂነሪንግ
በሶስት፣ አልሜዳ ጨርቃጨርቅ በአምስት እጥፍ እንደሚያድግ፣ መሰቦ ሲሚንቶ የማስፋፊያ ስራውን በማጠናቀቁ ለበርካታ
ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ያስታወቁት ወ/ሮ አዜብ ሱር ኮንስትራክሽን የያዘው አዲስ ፕሮጀክት ሲጀመር አስር
ሺህ ለሚሆን ሰራተኞች ስራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል። ወ/ሮዋ የተፈጠረውን የስራ እድልና ሰራተኛ ብዛት ለይተው
በክልልና በብሄር ግን አልገለጹም።
ኤፈርት የሩብ ዓመት የስራ እንቅስቃሴውን ሲገመግም በአቶ መለስ
“መሰዋት” ምክንያት ኤፈርት ውስጥ ከፍተኛ ሃዘን ሰፍኖ ስለነበር በተወሰነ ደረጃ የስራ መፋዘዝ ቢከሰትም በተያዘው
የበጀት ዓመት 16.57 ቢሊዮን ብር የሚገመት ምርት ገበያ ላይ ለማቅረብና 1.7 ቢሊዮን ብር ትርፍ ለማግኘት
መታቀዱን የወ/ሮ አዜብ መግለጫ ያስረዳል።
ኤፈርት በቅርቡ ይፋ ከሚያደርጋቸው ፋብሪካዎች መካከል ለፒቪሲ
ምርቶች ግብአትነት የሚያገለግለውን ጥሬ እቃ የሚያቀናብረውን ፋብሪካ እንደሚሆን ይገመታል። ሪፖርተር ባለፈው ዓመት
እንደገለጸው ፋብሪካው የኤፈርት አስራ አራተኛ እህት ኩባንያ ሊሆን እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል። በቻይና
ባለሙያዎችና ቴክኖሎጂ የሚገነባው ይህ ፋብሪካ ለግንባታው ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ ይደረግበታል። ማምረት ሲጀምር
ለአገር ውስጥ የፒቪሲ አገልግሎት የሚውለውን 40 ሺህ ሜትሪክ ቶን ጥሬ እቃ በማምረት ለአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች
ብቸኛ አቅራቢ ይሆናል።
ከሼኽ
መሐመድ ሁሴን አላሙዲ ግዙፍ የንግድ ተቋም ሚድሮክ ግሩፕ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የንግድ ስትራቴጂ የሚከተለው
ኤፈርት በአሁኑ ወቅት ያሉት ቁልፍ የንግድ ተቋማት መሰቦ ሲሚንቶ፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል፣ ባባ ዳይሜንሽናል ስቶን፣
ሱር ኮንስትራክሽን፣ ኤክስፕረስ ትራንዚት፣ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ አዲስ ፋርማሲዩቲካል፣ ጉና ትሬዲንግ፣ ሂወት
አግሪካልቸር፣ ሼባ ታነሪ፣ ኤክስፔሪየንስ ኢትዮጵያ፣ አልመዳ ጨርቃ ጨርቅና ኢዛና ናቸው፡፡
ዜናውን ተከትሎ አስተያየት የሰጡ የደቡብ፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ
የፓርቲ የንግድ ተቋማት በክልላቸው እንኳ መነገድ ያልቻሉ የሙስና ተቋማት ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።በከባድ የሙስና ድብታ
ውስጥ ወድቀው እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብ በማሳፈር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። የአማራው የልማት ድርጅት አንድ
ሚሊዮን ብር እርዳታ አገኘሁ በማለት እነ ህላዊ ዮሴፍ ሸራተን ከበሮ ሲያስደበድቡ መስማታቸው እንዳሳዘናቸው የገለጹት
አስተያየት ሰጪ “ብአዴን ከአፈጣጠሩ ጀምሮ አሳፋሪ ሰለሆነ ልንታገለው ይገባል። ከብአዴን ጋር መቀጠል ወደፊት ብዙ
ዋጋ የሚያስከፍል ችግር ላይ ይጥለናል” ብለዋል።
አቶ አስገደ ገ/ስላሴ ከህወሃት መስራቾች መካከል አንዱ ናቸው።
ትግል ሲጀመር የነበሩትና ስለኤፈርት በመጠየቃቸው መባረራቸውን የሚጠቁሙት አቶ አስገደ ከፍትህ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት
ቃለ ምልልስ ስለ ኤፈርት የተናገሩትን ቃል በቃል አቅርበነዋል።አቶ አስገደ የአረና ትግራይ አባል ናቸው።
ፍትህ፡-እርሶ በአመራርነት እየሰሩበት
ያለው አረና ፓርቲ በትግራይ ህዝብ ዝም ነው የተደራጀው፡፡ ታዲያ በትግራይ ህዝብ ስም የተቋቋመው ኤፈርት
የሚያስገባው ገቢ የት እንደሚውል ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሆነ እና እንዳልሆነ ያደረጋችሁት ጥረት አለ?
አቶ አስግደ፡- መጀመሪያ ነገር አረና ምንም እንኳን ብሔራዊ ፓርቲ ሆኖ ቢመሰረትም
ለትግራይ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ አንድነት የሚታገል ፓርቲ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ወደ ጥያቄው ስንመለስ ይህንን
ጥያቄ እንኳ እኛ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ ቀርቶ ተራው ህዝብ ሳይቀር የሚያነሳው ነው፡፡ እኔ በግሌ እስከ 1993
ድረስ የኤፈርት ሰራተኛ ነበርኩ፡፡ በዋናነት ከህወሓትም ከስራዬም እንድወጣ ያደረኝ ከ84ዓ.ም ጀምሮ ይሄንን ጥያቄ
ስለማነሳ ነው፡፡ እናም አረና በተለያየ መድረክ ላይ ጉዳዩን ያነሳዋል፡፡ ነገር ግን ከነሱ ጋር ፊት ለፊት ቀርበን
ለመከራከር መድረኩን አላገኘንም፡፡ በራሳችን መድረክ ግን እንደ አጀንዳ እያነሳነው ነው፡፡ … ይሄ ገንዘብ ለልማት
አልዋለም…፣ … በዚህ ገንዘብ የትግራይ ህዝብ ሳይሆን 45 የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ለምን ፈላጭ ቆራጭ ይሆናል?…፣
…ገቢ እና ወጪው በውስጥ እና በውጭ ኦዲተር ይመርመር… እያልን ደጋግመን አንስተናል፡፡ በአሁኑ ወቅት የትግራይ
ህዝብ ይሄ ንብረት የማነው? እያለ ቢጠይቅም መልስ የሚመልስለት ግን አላገኘም፡፡ እነሱም ተልባ ቢንጫጫ በአንድ
ሙቀጫ እያሉ ከማፌዝ ውጭ መልስ አይሰጡትም፡፡
ፍትህ፡-ግን እኮ ኤፈርት ሲቋቋም
እርሶን ጨምሮ አቶ ገብሩ አስራት፣ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ፣ አቶ ስዬ አብርሃ እና የመሳሰሉትን አመራሮች
እንደነበራችሁበት የሚጠቅሱ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች … እናንተም ህወሓት ውስጥ በነበራችሁበትም ጊዜ ቢሆን
የኤፈርት ገቢ ለህዝቡ አይውልም ነበር… ሲሉ ይወቅሳችኋል፡፡ ታዲያ ይህ ሁኔታ እናንተንስ ተጠያቂ አያደርጋችሁም?
አቶ አስግደ፡- ምን መሰለህ ኤፈርት ገና ሲቋቋምም የአገሪቱን ህግ ተከትሎ እና አክብሮ
እንዳልተቋቋመ ግልፅ ነው፡፡ ለዚህም መሰለኝ አንድ ጊዜ የህዝብ ነው ይሉታል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የህወሓት ነው
ይላሉ፡፡ ተሸፋፍኖ ነው ያለው፡፡ እናም በወቅቱ ድርጅቱ ህግ አክብሮ አለመስራቱን መቃወም እና ማረም ነበረባቸው፡፡
በዚህ ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ በደረጃችን እኛም የምንጠየቅበት ካለ ልንጠየቅ እንችላለን፡፡ ሆኖም በወቅቱ ልንናገር
የምንችልበት አንደበት የለንም ነበር፡፡ አፈና ነበረብን፤ በተለይም ለታጋይ ከባድ ነበር፡፡ ስለዚህም በየደረጃው
ሊጠየቅ የሚገባ ሊጠየቅ ይችላል፡፡ ምክንያቱም 20 ዓመት ሙሉ ከኤፈርት ለማህበራዊ አገልግሎት የዋለው አንዲት
ትምህርት ቤት በ17 ሚሊዮን ብር ተሰርቷል፡፡ ማን ይጠቀምበታል እንጂ አንድ የአካል ጉዳተኞች ህንፃ 11 ሚሊዮን
ብር የሚፈጅ አውጥተው ሰርተዋል፡፡ በዋጅራትም አራት ሚሊዮን ብር የሚፈጅ አንድ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እየሰሩ
ነው፡፡ ወደ 4 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚሆንም ለአካል ጉዳተኞቹ እንደተሰጠ ይነገራል፡፡ ከዚህ ውጭ በቢሊዮን
የሚቆጠረው ገቢ የት እንደሚገባ አይታወቅም፡፡ ይሄ ገንዘብ ለግድብ ቢውል የተከዜን መጋቢ ወንዞች እየገደቡ የተሻለ
ስራ መስራት ይቻል ነበር፡፡
በተያያዘ ዜና ሰንደቅ 8ኛ ዓመት ቁጥር 374 ረቡዕ ጥቅምት 28
ቀን 2005 አንድ ሚሊዮን የመጠጉ የትግራይ ተወላጆች የተሳተፉበት ስብሰባ መካሄዱን በመጠቀስ ባስነበበው ዜና
በክልሉ ይበልጥ ተግባራዊ እንዲደረግ ከታቀደው ፖለቲካዊ አደረጃጀት በተጨማሪ በተያዘው ዓመት 750 ሺህ አርሶ
አደሮች በመስኖ እንዲያለሙ፣ በክልሉ 50 በመቶ የሚሆነው መሬት እንዲታረስና ከግብርና ምርት በተጨማሪ ከ40 እስከ
50 ሚሊዮን ኩንታል አትክልትና ፍራፍሬ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል። ለዚህ እቅድ ተግባራዊነትም ሁሉም አርሶ አደር
ማዳበሪያ እንዲጠቀም መመሪያ መውረዱንም አመልክቷል።
No comments:
Post a Comment