Saturday, 22 December 2012

የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር የተሳካ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ አካሄደ፣ “አለም አቀፍ ኮሚቴ” የሚባል እንቅሰቃሴ አለመኖሩን ገለጸ

ከኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ጎጠኛው የወያኔው ስርዓት በአገራችንና በህዝባችን ላይ ሲያደርስ የነበረውና እያደረሰ ያለው ግፍ ለስልጣን በበቃበት መንገድ መውረድ አለበት ብሎ ጠብመንጃውን ካነሳና መፋለም ከጀመረ አመታትን አስቆጥሯል።

የትጥቅ ትግል መራርና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ህይወት የሚጠይቅ ቢሆንም አያቶቻችን ያለምንም ዋጋ ውድ ህይወታቸውን ለአገርና ለህዝብ ፍቅር በመክፈል ያቆዩልንን የአርበኝነት አደራ ለመወጣት ከምንጊዜውም በበለጠ አጠናክረን የቀጠልንበት ደረጃ ላይ እንገኛለን ።

 በመሆኑም ይህን የአገርና የህዝብ ታሪካዊ አደራ ለመወጣት ብሎም ትግሉን በተፋጠነ መልኩ ለመቀጠል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ መጠቀም ይኖርብናል ሲል ሰሞኑን ያካሄደው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ውሳኔ አስተላልፏል። ከህዳር 28-30/2005 ዓ/ም የተካሄደው ድርጅታዊ ኮንፈረንስ ብዛት ያላቸው ድርጅታዊ አጀንዳዎችን የዳሰሰ ሲሆን፡ በዋናነት ወታደራዊ እንቅስቃሴው ድርጅቱ በ 2005 ዓ/ም አቅዶት የተነሳውና በያዝነው አመትም በአመርቂ ድሎች የጀመረ ቢሆንም ይበልጥ ሊጠናከር የሚችልበትንና ከፍተኛ ውጤት ሊመዘገብ የሚችልበትን ሂደት ተወያይቷል።

ድርጅታዊ ኮንፈረንሱ አስከትሎም የአገራችንና የህዝባችን ችግር ሊፈታ የሚችለው ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነን ስንታገል ነው በሚል መርህ ጥምረት ከፈጠርናቸው ድርጅቶች ጋር ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ስራ መሰራት እንዳለበትም ውሳኔ አስተላልፏል።

ሌላው ድርጅታዊ ኮንፈረንሱ አጽንኦት ሰጥቶ የተወያየበት ድርጅቱ በለም አቀፍ ደረጃ ድጋፍ ሊያገኝ የሚችልበትን ሁኔታ መቀየስ ሲሆን፡ እስካሁን ድረስ በተለያዩ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተገቢው ድጋፍ ያልተገኘበትንም ምክንያት በዝርዝር በመወያየት ውሳኔ አስተላልፏል።

በርግጥ ላለፉት አመታት የተለያዩ አለም አቀፍ የሆኑ ኮሚቴዎች የተቋቋሙ ቢሆንም በግለሰቦች አለመግባባት ምክንያት ከድርጅቱ ጎን መቆም የሚገባቸው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እንዲሰላቹና ከትግሉም እንዲርቁ አድርጓል። ድርጅቱ ይህ ኮንፈረንስ እስኪካሄድና ወደፊት የሚኖረው አሰራር ምን መሆን አለበት ብሎ ጥናት አካሂዶ እስኪ ወስን ድረስ የተወሰኑ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን <<የዘመቻ ደም መላሽ አስተባባሪ ግብረሃይል>>በሚል አቋቁመው መልካም የሚባል እንቅስቃሴ እያደረጉ መቆየታቸውን ኮንፈረንሱ በአድናቆት ያየው ሲሆን፡ የዘመቻ ደም መላሽ መተዳደሪያ ደንብ በሚያዘው መሰረት <<ይህ ግብረ ሃይል ስራውን የሚያቆመው ድርጅቱ ሌላ የአሰራር ሂደት ሲከተል ብቻ ነው >>የሚለውን መሰረት በማድረግ የወደፊቱ የአሰራር ሂደት እንዲቀየር ተወሰኗል።

ኮንፈረንሱ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የወያኔን እድሜ በማሳጠሩና ትግሉን በማፋጠኑ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጾ ያደርጉ ዘንድ ሁኔታዎች በቀጥታ ድርጅቱ ይህን ስራ ብቻ እንዲሰራ ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር በመገናኘት ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ሊያደርጉ እንዲችሉ ሲወሰን፡ የአሰራር ሂደቱም በየአገራቱ የሚቋቋሙ ቻፕተሮችም ቀጥታ ግንኙነታቸው ከድርጅቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ጋር ብቻ መሆኑ ተወሰኗል።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ከአሁን በኋላ በውጭው አለም የሚንቀሳቀስ<<አለም አቀፍ ኮሚቴ>>የሚባል እንቅሰቃሴ አለመኖሩን እያስታወቀ አገራችንንና ህዝባችንን ከዚህ ጎጠኛ ቡድን በማላቀቁ ረገድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእውቀቱ፥ በጉልበቱ ፥ በህይወቱና በገንዘቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርግ ዘንድ ድርጅታዊ ኮንፈረንሱ ጥሪውን አስተላልፏል።

አንድነት ሃይል ነው!!!

የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር

ታህሳስ 1 / 2005 ዓ/ም

No comments:

Post a Comment