Wednesday, 12 December 2012

የኃይለ ማርያም የአስመራ መንገድ ከመለስ ይለይ ይሆን?

በየማነ ናግሽ

አንድ በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ወጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ‹‹ቶክ ቱ አልጀዚራ›› ከሚለው የአልጄዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ያደረጉትን ቃለ ምልልስ በድረ ገጽ ለማግኘት እየታገለ ነው፡፡ አልጄዚራ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲዘጉ ከተደረጉ ድረ ገጾች መካከል ነውና አልቻለም፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ ምልልስ የሰጡት ለጋዜጠኞቹ ብለው ነው? ወይስ በአገራቸው ሕዝብ እንዲነበብ እንዳይታይ ከማይፈቀደው ሚዲያ ጋር መነጋገራቸው ምን ይሉታል?›› እያለ ከጓደኞቹ ጋር በማጉረምረም ከአንድ ኢንተርኔት ካፌ ሲወጣ አየሁት፡፡

እውነት ነው፤ የአልጄዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባይዘጋም ዘመኑ ባመጣው የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ማዳመጥ ወይም ደግሞ ማንበብ ለሚፈልግ ሰው ግን አይቻልም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የተለያዩ አገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮችን አስመልክተው የ25 ደቂቃ ቃለ ምልልስ ያደረጉበት ከኳታር (ዶሃ) የሚሠራጨው የአልጄዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ድረ ገጽ ተዘግቷል፡፡ ቪኦኤ፣ ናዝሬት፣ ዓባይ፣ ኢትዮ ሚድያ፣ መርካቶና ሌሎች በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ትችቶችን የሚያስተናግዱ ድረ ገጾችም እንደዚሁ ተዘግተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሚዲያዎችን በማፈን፣ ጋዜጠኞችን በማሰርና በማዋከብ ግንባር ቀደም ከሆኑ አገሮች ስሟ እየተጠራ ሲሆን፣ በተለይ ግን ድረ ገጾችን ‹‹ጃም›› በማድረግ በቅርብ ጊዜያት ቀዳሚ ሳትሆን እንደማትቀር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከአልጄዚራ ጋዜጠኛዋ ዥ ዱተን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር ስለተፈጠረው ቀውስ፣ ዕርዳታ ለፖለቲካ ጥቅም ፍጆታ ስለመዋሉ፣ የመሬት ወረራ፣ በቅርቡ ስለተደረገው የሥልጣን ሽግግርና የዓባይን ግድብ በተመለከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ፈገግ እያሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በጋዜጠኛዋ ጥያቄዎች ሲቀርቡላቸው፣ በተለይ ደግሞ ግብፅንና ሱዳንን በተመለከተ ጋዜጠኛዋ ያቀረበችው ጥያቄ ከመረጃ እጥረት የተነሳ መሆኑን እያዋዙ ዘና ብለው ሲናገሩ፣ ከዚህ በፊት ለአገር ውስጥ ከሰጡዋቸው ማብራሪያዎች ብዙም ያልተለዩ ነበሩ፡፡


አዲሱ ነገር ኤርትራን በተመለከተ ነበር፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ስለሚደረገው የእግር ኳስ ጨዋታ ተጀምሮ በአገሮቹ መካከል ስላለው ግንኙነት ‹‹ስፖርትንና ፖለቲካን›› በመቀላቀል ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ ይገኝበታል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያና ኤርትራ በአፍሪካ ሻምፒዮንሺፕ የሚያደርጉት ጨዋታ በገለልተኛ ሜዳ እንዲካሄድ ጠይቃችኋል›› በማለት በተነሳ ጉዳይ፣ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ያባብስ ይሆን ወይ በማለት ጋዜጠኛዋ ጠየቀቻቸው፡፡ ‹‹እግር ኳስ ነው ያልሽኝ?›› እና ‹‹የትኛዋ አገር?›› በሚል ማጣጣል በሚመስል በጀመሩት ንግግር ስለተነሳው ጉዳይ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ነበር የገለጹት፡፡ ቀጠል አድርገው ግን፣ ‹‹ሆኖም ግን አስመራ ድረስ በመሄድ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ለመነጋገር ትፈልጋለህ ወይ የሚል ጥያቄ ብታቀርቢልኝ?›› በማለት ራሳቸው ቀድመው ላነሱት ጥያቄ ‹‹ምላሼ አዎ ነው›› ብለዋል፡፡

እሳቸው የተኩዋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ከሃምሳ ጊዜ በላይ እንነጋገር የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰው፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ግን በግትር አቋማቸው ምክንያት ተገቢ ምላሽ እንኳን አለመስጠታቸውን ነበር የተናገሩት፡፡ የመደራደር ጉዳይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት የመቼም ጊዜ አቋም መሆኑ የገለጹት ግን፣ ‹‹አካባቢያዊ ውህደት መፍጠር›› የሚል አዲስ አስተሳሰብ ሊሰጥ የሚችል አስተያየት ጣል አድርገዋል፡፡ የኃይለ ማርያም የአስመራ መንገድ ከመለስ የተለየ ይሆን? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡ 

መለስና ኢሳይያስ
ባለፈው ዓመት ከዋናዋ ሱዳን ተገንጥላ አዲስ አገር ሆኖ ከመጣችው ደቡብ ሱዳን ቀደም ብላ ወደ የዓለም አገሮችን የተቀላቀለች ኤርትራ ነበረች፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም የኤርትራውያን የነፃነት አባት ተደርገው ይቆጠሩ ነበር፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የቀድሞ የትግል አጋራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ አገርን አስገንጥለዋል በሚል በተቃዋማዎቻቸው የሚሰነዘርባቸው ተቃውሞ የፖለቲካ ኪሳራ አድርሶባቸዋል፡፡
ሁለቱም ታጋዮች ደርግን ከመጣልና የኤርትራ ነፃነትን ከመደገፍ ውጭ በምንም ዓይነት ፖለቲካዊ እሳቤዎችና ወታደራዊ ስልቶች የሚስማሙ አልነበሩም፡፡ እንደ ጓዶች ከሚቆጠሩ ይልቅ እንደ ባላንጣዎች የሚታዩ ናቸው፡፡

ደርግን ለመጣል ሙሉ ስምምነት ነበራቸው ቢባልም፣ አንዱ ከሌላው እየተደበቀ ከፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር በመነጋገር ችግራቸውን ለመፍታት የተደረጉ ሙከራዎች እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ሁለቱም መሪዎች ግን አንድ ስለመሆን ወይም ደግሞ የኤርትራን መገንጠል ለማስቆም ያደረጉት አንዳች ጥረት ለመኖሩ መረጃ አልተገኘም፡፡ ሁለቱም ባላንጣዎች አንድን አገር በጋራ መምራት የሚችሉ አልነበረም፡፡

የሁለቱም መሪዎች ባላንጣነት አንዱ የሌላው አለቃ ሆኖ ለመሥራት የሚያስችላቸው አልነበረም፡፡ ሁለቱም የበላይ አለቃ መሆን ነበረባቸው፡፡ በዚህም ሁለት አገሮች መፈጠር ነበረባቸው፡፡ ይህ በአብዛኛው ለሁለቱም መሪዎች ቅርበት የነበራቸው ውስጥ አዋቂ ፖለቲከኞች የሚያቀነቅኑት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የኤርትራን ነፃነት በተመለከተ ገና ከጠዋቱ ከትጥቅ ትግል ጊዜ ጀምረው የሚያምኑበት የፀና አቋማቸው ቢሆንም፣ ኤርትራ በኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ሥር ነበረች የሚለው ፖለቲካዊ ትንታኔያቸው እጅግ የበዛ ነቀፌታ እንዲሰነዘርባቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ ሆኖም ከውጭም ከውስጥም የሚደመጠውን ነቀፌታ የሚቀበሉ አልነበሩም፡፡

ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ
ኤርትራውያን እንደ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የደረሰባቸው ጭቆና ለአንዴና ለመጨረሻ ለመገላገል ነበር ለ30 ዓመታት ያህል ጦርነት ማካሄዳቸውን የሚናገሩት፡፡ የታላቋ ኢትዮጵያ ለሁለት መሰንጠቅ ግን ከመለያየቱ ጀምሮ ጤነኛ አልነበረምና የተጠበቀውን ያህል ሰላም አላስገኘም፡፡ የሁለቱም አገሮች ዳር ድንበር በውል ሳይካለል፣ በኢትዮጵያ የነበሩ የኤርትራ ተወላጆች የዜግነት ጥያቄ ግልጽ መፍትሔ ሳይደረግበት በይደር ነበር የቆየው፡፡

ሁለቱም መሪዎች መንግሥታቸውን በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ለማሳደር በሚያደርጉት ግስጋሴ ተፎካካሪነታቸው እየጨመረ የመጣው የኤርትራ መንግሥት ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛ በተጀመረበት ወቅት ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን የሁለቱም አገሮች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መልኩን እየቀየረ በመምጣቱ አንዱ በሌላው ላይ ማሴር ጀምረው ነበር ይባላልም፡፡ ይኼ ሁሉ የፈነዳው ግን በይደር በቆየው የድንበር ግጭት ወቅት ነበር፡፡ የድንበር ግዛት የይገባኛል ጥያቄ ዋነኛ ማዕከል ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ ሲጠቀስ በነበረው ባድመ ላይ በተደረገው ውጊያ ከሁለቱም አገሮች ከ70 ሺሕ በላይ ወጣቶች በጦርነቱ ተሰው ከዚያም ጉዳዩን በበላይነት ይዞት የቆየው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሁለቱንም አገሮች ወደ ሌላ ዘር ጦርነት የሚከት ፍርድ በመስጠት እነሆ “ሰላምና ጦርነት አልባ” እንዲሆን አደረገው፡፡ በአካባቢው ሰፍኖ የቆየው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሰላም አስከባሪ ኃይል ደግሞ ለቆ በመውጣቱ ዛሬ ወይም ነገ ይፈነዳል የተባለው ጦርነት ዋል አደር እያለ እዚህ ደርሷል፡፡

የመለስ መንገድ
ጦርነቱ በኢትዮጵያ ወታደራዊ የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ጠረጴዛ ዙርያ ድርድር ለመምጣት የቸኮሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ በዓለም አቀፉ የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ደስተኛ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያም የምትቀበለው አልሆነም፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰላም አላመጣም፡፡ ለችግሩም ምንም እልባት አላስገኘም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንደ አማራጭ ባቀረቡት ባለአምስት ነጥብ የእንደራደርና የሰላም ሐሳብ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በሚገርም ሁኔታ ከጎናቸው ማሰለፍ ችለው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ግን በዚሁ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የፖለቲካ አካሄድ በመበለጣቸው የባድመን ግዛት ብቻ ሳይሆን፣ አሜሪካን ጨምሮ ዋነኛ ወዳጆቻቸውንም ያስቀረባቸው ነበር፡፡ በዘ ሔግ ፍርድ ቤት ውሳኔ የተቆጣችው ኢትዮጵያም ወታደራዊ የበላይነቷ ወዳጅ አላሳጣትም፡፡ በአፍሪካ ቀንድ የሽብርተኝነት ሰለባ የሆኑት ምዕራባዊያን ከሁለቱም ባላንጣዎች አንዱን መምረጥ ነበረባቸው፡፡ የዓለም ፖለቲካ ባህል ነውና ደካማውን ለመምረጥ አልተገደዱም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን የሰላም ሐሳብ ተቀብለው ኤርትራ እንድትቀበል ጫና መፍጠር ጀመሩ፡፡ በዚህም የተነሳ ከጎረቤት አገሮች ጋር እንደ እብድ ውሻ ሲናከስ የነበረው የኤርትራ መንግሥት ከራሱ ሕዝብና ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጋር መጣላቱን ተያያዘው፡፡

በወቅቱ በሁለቱ አገሮች መሪዎች መካከል ከነበረው የቃላት ጦርነት ልውውጥ በተጨማሪ፣ የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያ አማፂ ኃይሎችን በመደገፍና በማስታጠቅ የተለያዩ የሽብር ተግባሮች መፈጸምን እንደ አንድ አማራጭ ይዞ ነበር፡፡ ቀጥሎም፣ በሶማሊያ የተቋቋመውን የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት በመደገፍ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጅሃድ እንዲያውጅ በማድረግ በፈጸመው የእጅ አዙር ጦርነትም ተሸንፏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በአንድ ወቅት ፓርላማ ቀርበው በሰጡት ማብራርያ፣ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ከተጀመረ የማይመለሱበትና እስከ መጨረሻ እንደሚሆን ዝተው ነበር፡፡ በቀጥታ ወታደራዊ ጥቃት ሳይፈጽም፣ የተለያዩ የእጅ አዙር ጥቃቶችን ማስፈጸም የተያያዘው የኤርትራ መንግሥት ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር በተረጋገጠው በአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ወቅት አዲስ አበባ ውስጥ ሊፈጽመው ተዘጋጅቶ በከሸፈበት ሙከራ ማዕቀብ እንዲጣልበት ምክንያት ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ ከዓለም የዲፕሎማሲ መነጠል (Isolation) የገጠመው ሲሆን፣ በአገር ውስጥ የሚያካሂደው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አፈና ታክሎበት፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከፍተኛ ትችትና ነቀፌታ ሲሰነዘርበት ቆይቷል፡፡

አብዛኛዎቹን ኢትዮጵያዊያን እንቅልፍ ስለሚነሳው የባህር ወደብ ጉዳይ ማንሳት ባይቻልም፣ የኤርትራ መንግሥትና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ግን በአካባቢውም፣ በአኅጉርም፣ በዓለም አቀፍ መድረክም ከፖለቲካ ጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሎ ነበር፡፡ በወቅቱ የቀረበው የሰላም ሐሳብ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ቀልብ ለመሳብ እንጂ ከልብ የመነጨ አልነበረም ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡ ይኼ ሁሉ የፖለቲካ ጨዋታ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መንገድ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የኃይለ ማርያም መንገድ
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሕይወት ሳሉ ኤርትራን ከዓለም ዲፕሎማሲ መነጠል ቢቻላቸውም፣ ከኤርትራ በኩል በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ግን የሚያስቆም አልነበረም፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት በአፋር አካባቢ በቱሪስቶች ላይ በተፈጸመው የማገትና የግድያ ተግባር የተማረረው የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ላይ የፖሊሲ ለውጥ ማድረጉን አበሰረ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተደረገ ስለተባለው ለውጥ ሰፊ ማብራርያ ሰጥተው ነበር፡፡ በተለይ ተመጣጣኝ ወታደራዊ ዕርምጃ የመውሰድ ፖሊሲን በተመለከተ፡፡

የተደረገው የፖሊሲ ለውጥም በተወሰነ ደረጃ በተግባር የታጀበ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ኤርትራ ግዛት ውስጥ በመዝለቅ ወታደራዊ ጥቃት ፈጽመው መውጣት ችለዋል፡፡ በባድመ አካባቢ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ በተወሰደው የማገት ዕርምጃ ምክንያትም ተጨማሪ ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ የኢትዮጵያ መንግሥት ተገዶ ነበር፡፡

ሰሞኑን ከአልጄዚራ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ግን፣ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር መነጋገር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ሥልጣን ከጨበጡ ሦስት ወራት ያልሞላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ “የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ራዕይ አስፈጽማለሁ፤” በማለታቸው ከአንዳንዶቹ ትችት ቢጤ ቢቀርብባቸውም፣ አሁን በኤርትራ ጉዳይ ላይ በሰጡት አስተያየት ግን ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ራዕይም ወጣ ያለ ይመስላል እየተባለላቸው ነው፡፡ “ወደ አስመራ በመሄድ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ትቀመጣለህ ወይ? ትነጋገራለህ ወይ? ብለሽ ከጠየቅሽኝ መልሴ አዎ ነው፤” ሲሉ ተደምጧል፡፡

“ለእኛ ዋነኛ ጉዳያችን ድህነትን መዋጋት ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ አካባቢያዊ ውህደት መፍጠር፡፡ ሁለታችን ይህንን ማድረግ ከቻልን ምርታማ እንሆናለን፤” በማለትም አክለው ተናግረዋል፡፡ ድህነትን በተመለከተ በአብዛኛው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አስተያየት አሁንም በመለስ አቋሞች ላይ ያጠነጠነ ቢመስልም፣ “ውህደት መፍጠር ከቻልን” የሚለው ግን አዲስ ‹‹መላ›› ይመስላል፡፡ ‹‹ውህደት መፍጠር›› የሚለው ንግግር አቶ መለስ አንስተውት የማያውቁት ርዕሰ ጉዳይ ሲሆን፣ አንድ አዲስ ምዕራፍ አመላካች ሊሆን ይችላል የሚል ትንታኔ እየተሰጠበት ነው፡፡

ምናልባትም ሐሳባቸው በአቻቸው በፕሬዚዳንት ኢሳያስ ተቀባይነት የሚያገኝ ከሆነ፣ ከአሥር ዓመታት በላይ የዘለቀው የሁለቱም አገሮች “ሰላምና ጦርነት አልባው” ግንኙነት መልኩን በመቀየር አዲስ ታሪክ ያስመዘገባል እየተባለ ነው፡፡ አገራቸው ውስጥ ባለው ሁኔታ ተቀባይነት ያጡትን ፕሬዚዳንት ኢሳያስም ምናልባት ከገቡበት ጥልቅ አዘቅት ውስጥ ሊያወጣቸው ይችላል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም፣ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የበለጠ ተቀባይነት ለማግኘት ሊጠቀሙበት የሚገባ የፖለቲካ ካርድ ሊሆን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

No comments:

Post a Comment