Wednesday, 20 February 2013

የታማኝ ጥሪ ለተቃዋሚ ኃይል መሪዎች – ታማኝነት ያፈራውን ህዝባዊ ፍቅር ተረከቡኝ ነው

“ህዝቡ መሪዎችን ተጣራ! … ሳትሰሙ ብትቀሩ ግን ግፍ ይሆናል! … እኔ ተራው ሰው ይህንን የህዝብ ጥያቄ የመሸከም አቅሙም ብቃቱም የለኝም! የመነጋገሪያና የመደማመጫ ጊዜያችሁ አሁን ነው! እባካችሁን?!” በማለት የተቃዋሚ ኃይሎችን እንደ ድርጅት የህዝብን ፍላጎት እንዲረከቡና እንዲመሩ ከሰበዕዊ መብት ተሟጋቹ ከአርቲስት ታማኝ በዬነ ጋር በተደረገው ቃለ ምልለስ ከኢሳት Feb 18, 2013 ከዕለታዊ ዜና ጋር አዛምዶ ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም ካቀረበው የተወሰደ።

“ህዝብ መሪዎችን ተጣራ!” መንገድ ጠራጊው ለአዲስ ምዕራፍ – ብሄራዊ የፍቅር ጥሪ አቀረበ!
ሥርጉተ ሥላሴ 19.02.2013
ወይ ጉዴ ዛሬ ደግሞ እንዴትና እንዴት አድርጌ ነው ላቀርበው ያሰብኩት ይሆን … እም! ስገርም
Artist Tamagne Beyene on ESAT Newsየሰብዕዊ መብት ተሟጋቹ አርቲስት ታማኝ በዬነ ከእኛም ሲዊዘርላንድ መጥቶ በነበረበት ጊዜ የተናገረው አንድ ኃይለ ቃል ነበር። „ …ሰው ጠፋና እኔ ሰው ሆኜ ለእኔ እንዲህ ትወድቃላችሁ ትነሳላችሁ …“ እኔ ይህን ሲል … እኔን! አፍር ልብላልህ አልኩኝ። እራሴ ሥርዓቱን በቪዲዮም እዬቀረጽኩት፤ በተጨማሪም በድምጽ መቅረጫም እዬቀዳሁት መሆኔን ዘንግቼ። ትናንትና ሳዳምጠው የእኔንም ድምጽም ቀድቶታል። የቀደሙት ሐዋርያትና ሰማዕታት „እኔ ትቢያ እኔ ታናሽ ስሆን ይሉ ነበር።“ ላቅ ያለ አብነት ነው። እንዲህ ዝቅ ማለት። እራስን ማዋራድ ~ ጸጋ ነው። እራስን ዝቅ ሲያደርጉ ህዝቡ የአንተ ሥፍራ ይህ አይደለም ብሎ፤ ቦታውን አደላድሎ፤ ወዶና ፈቅዶ የመረጠውን ከፍቅሩ ማህደር ያስቀምጣል። 


ለአርቲስት ታማኝ በዬነ ቦታውን የመደበለት፤ የደለደለለት ህዝቡ እራሱ ነው። በፈቃዱ ወዶና ደስ ብሎት ነው የሰጠው።
ስለዚህ ወንድሜ ታማኝ በዬነ በዚህ ሊሸማቀቅበት አይገባውም ባይ ነኝ። ከዚህች ቃል ኪዳናዊ ስጦታ ፈቀቅ ያለ ዕለት ግን ያን ጊዜ  ቢከብደው፤ ቢሳነው ይገባል እንጂ አሁንማ … ደስ ብሎት በሐሤት ሊቀበለው ይገባል። አክብሮ በተግባር ሊከበክበው ይገባል። የህዝብን ልዩ ሥጦታ ሊያስመቸውም ይገባል። አርቲስት ታማኝ በዬነ ግበረ – ሰላም አስገብቶ፤ ሊጋባ አሰልፎ፤ ወይንም ሽልንጓን ዘርዘር – መንዘር አድርጎ በነፍስ ወከፍ ስለአደለ አይደለም የህዝብን ፍቅር ተንበርክኮ እንዲህ የሚዘቀው፤ በነጠረ ድርጊቱ ብቻ ነው። ያገኘውን ህዝባዊ ፍቅርን በቅጡ ማስተዳደር የመቻል አቅሙ ሥልጡን በመሆኑ ነው። የሚታይ የሚጨበጥ ዕውነት አንጡራ ንብረቱ በመሆኑ ነው። ለህዝብ ዕንባ ታማኝና ቋሚ አገልጋይ በመሆኑ ነው።

እጅግ የማከብራችሁ የጹሑፌ ታዳሚዎች … ወደ እርእስ ጉዳዬ ከመግባቴ በፊት ግን ስለ አዬሁት ነገር ትንሽ ምስክርነት ቢጤ ብሰጥ መልካም ነው። ሙንሽን ውስጥ እንዲህ ቅልጥ ያለ የኢትዮጵውያን ህዝባዊ ስብሰባ ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያው ነው። የእስልምና እህቶቻችንም እንዲህ በብዛት ወጥተው ትግሉን ሲቀላቀሉ ሳይም ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው። በተረፈ ሙንሽን የታደለ ነው። ዓላማቸውን ጠንቅቅው የሚያውቁ፤ ከፍላጎታችው ጋር ያልተላለፉ፤ ፍላጎታቸውን ጽላታቸው ያደረጉ፤ የህዝብን መዋዕለ ሃብት ሆነ መክሊት በአግባቡ የሚመሩና የሚያስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን ብቃትን በአግባቡ ጥቅም ላይ በመዋል ረገድ አንቱዎች ያሉበት ከተማ ነው። እኔ በዓይኔ አይቻለሁ – መስክሬያለሁም። ሙንሽን የተግባር ጀግኖች ያሉበት ቦታ ስለሆነ ውጤቱ እንደ ሰማችሁትና እንዳያችሁት ሆኗል። ነገም …

አሁን ወደ የምወዳት ከተማ ወደ ፍራንክፈርት አማይን አብረን እንጓጓዝ። የትኬት አትጠየቁም። እሺ! አንድ ሚስጢር ላውጣ መሰል … ፍራንክፈርቶች ቀናተኞች ናቸው። ወንድሞቻችን ከሙንሽን እዬሄዱ ትግሉን ሲመሩ፤ ሲያስተባብሩና ሰያግዙ እኛ እያለን ስለምን? ሲሉ ከትግሉ ተቆርቋሪዎች አድምጫለሁ። ለምን ተበለጥን? ማለት ለመስዋዕትንት ከሆነ በጣም አዎንታዊ ነው። በተረፈ ቀደም ባለው ጊዜ ፍራንክፈርት አማይን የኢትዮጵያ ኮምኒቲው እራሱ ስንት በተግባር የተባ ክንውን ፈጽሟል መሰላችሁ። በአጎራባች ሀገሮች እዬተጠራ የልምድ ልውውጥም ያደርግ ነበር የፍራንክፈርቱ አማይን ዬኢትዮጵያ ኮሚኒቲ።
ፍራንክፈረት አማይን በ90ዎቹ አጋማሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኦነግ በስተቀር የተቃዋሚ ኃይሎችን በአንድ መድረክ አገናኝቶ ያነጋገረ፤ በአማራጭ ኃይሎች፤ በኢተፖድህ፤ በመህአድ፤ በመድህን፤ በአርበኞች ግንባር … ምሰረታ ሆነ የድጋፍ ኮሚቴ በማደራጀትና በመምራት ወግ ያለው ተግባራትን ሲከውንብት የቆዬ ነው። በዘመነ ቅንጅትም – ትንሳኤ ራዲዮ ፕሮግራምን ጨምሮ የበቃ ተሳትፎ እድርጓል። በኋላም ቢሆን የግንቦት ሰባት የተሳኩ ስብሰባዎችን በውጤት ለናሙናነት የበቃበት ከተማ ነው ፍራንክፈርት አማይን። የሚገርመው በማናቸውም ጊዜ ጀርመን ውስጥ የሚኖሩ የወያኔ አባላትና ደጋፊዎቻቸው በህዝባዊ ስብሳባ በመገኘት „እኛ ወያኔ ነን“ በማለት ሲያፋጥጡም  ፊት ለፊት በመፋለም አሳፍረው፤ አሸማቀው ይልኳቸው ነበር። ይህም ብቻ አይደለም ልክ አሜሪካን ሀገር ኮለንቮስ ኦሃዩ ባለው መልክ የእናት ልጆች ተለያይተው የነፃነት ትግሉን በመደገፍና በመቃወም አጋ ለይተው የሚፋለሙበት ከተማ ነው ፍራንክፈረት አማይንና አካባቢው።

ስለሆነም ፍራንክፈርት አማይን እጅግ ድንቅ፤ አንጋፋ፤ ሰፊ የተግባር ልምድ ያካበቱ ወገኖች የሚገኙበት ነው። እራሱ 25ኛው የብር እዮቤል የኢህአፓ በዓል የተከበረው እዛው ፍራንክፈርት አማይን ላይ ነበር። የኢተፖድህ ሁለተኛ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤንም ያስተናገድ ፍራንክ ፈርት አማይን ነበር። በሱዳን የነበሩ ኢትዮጵውያን ወገኖቻችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ኤን. ሲ. ኤች አር ሲበይን እስከ ተባበሩት መንግስታታ ጽ/ቤት ድረስ የተፋለሙት ትንታጎች ደመላሽ ይመራው የነበረው የድርሻችን እንወጣ የወጣቶች ማህበር ነበር። የሟቹ የአባ ጳውሎስ የተቃውሞ ቦንብ የፈነዳውም ፍራንክፈርት ቅድስተ ማርያም ላይ ነበር ….
የመጀመሪያው የአውሮፓ እግር ኳስ ጥንስስ ጨዋታ የተካሄደው ፍራንክፈርት አማይን ውስጥ ነበር። አውሮፓ አቀፍ  „ „ራዕይ“ መጽሄት ዝግጅትና ስርጭት ፍራንክፈርት ላይ ነበር … እንዲያውም „ራዕይ“ መጽሔት አንደኛ ዓመቱን ሲያከብር አውሮፓ አቀፍ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ተካሂዶ የነበረው ወርክ ሾፕና ፓናል ዲስከሽን ለዘመኑ ልዩ ጌጥ ነበር።  እና ለፍራንከፈርት አማይን ልጆች ለኢሰአት ባይታወር ሲሆኑ እንደ ልብ አምላኩ ንጉሥ ዳዊት „የቤትህ ቅናት በላኝ“  ብለው መነሳታቸው ወሸኔ ነው። ማለፊያም ነው። ወንድሜ ታማኝ ከዕቅዱ ውስጥ ያልነበረውን ፍራንክፈርት አማይን እንዲሳተፍና በቦታውም ተገኝቶ ሰብሉን ለመሰብሰብ መወሰኑ የተገባ ብይን ነው። „አያሰፍሩኝም!“ ብሏል። እኔም እደግመዋለሁ። አዎን! ፍራንክፈርትና አካባቢዊው ፈጽሞ አያሰፈሩህም። ለነፃነት ትግሉ ሲሉ የአንድ እትብት በሥጋም የሚገናኙ ልጆች ተፋተው የሚኖሩበት ከተማ ነውና …. በሃዘን በደስታ ጨርሶ አይገናኙም።

እኔ እንደማስበው ብቻም ሳይሆን በጣም በእርግጠኝነት ልናገር የምፈልገው ፍራንክፈረት አማይን ውጤቱም ቢበልጥ እንጂ አያንስም። ሃይድልበርግ፤ ማንሃይም፤ ካልስሮ ምን አልባትም ሽቶትጋርዶች ወደ ሙንሽን ካልሄዱ፤ እንዲሁም ከፈረንሳይ ከኢጣሊያን ያሉ ወገኖችም ወደ ዛ ሊያመሩ ይችላሉ ብዬ አስባለሁና …
እራሱ ፍራንከፈርት አማይን አንዱ መንደር ብቻ እንኳን ሲሰላ የትዬለሌ ነው። እንኳንስ ኩታ-ገጠም ሁነቶች ሲዳሰሱ።  እንደ እኔ እጅግ ተቆርቋሪ ወንድምና እህቶች ያሉበት አካባቢ ስለሆነ ውጤቱ ዝቀሽ ነው። ለአሁን ለአርቲስት ታማኝ በዬነ ጉዞና ተልዕኮም ብቻ ሳይሆን ሃብትን በቋሚነት በማነጽ ረገድም ይህ የአሁኑ መጠነ ሰፊ ህዝባዊ ስብሰባ ትግሉን ሊያግዙ የሚችሉ የበቁ ተግባራት ይከውንበታል ብዬም አስባለሁ። ሰፊ መሰረት ሊያስጥል የሚችል ይሆናል ብዬም እገምታለሁ።

አሁን ደግሞ ወደ አምሰተረዳም ልውሰዳችሁ ዬት እንደ ደረሱ አላውቅም። ብቻ በማናቸውም አውሮፓ አቀፍ ስብሰባዎች በራሳቸው ወጪ፤ በተሟላ ካሜራ ለታሪክ ዶክመንቴሽን ይሰሩ የነበሩ የአእምሮ ጋዜጣ አዘጋጆች ከሀገር ከወጡም በኋላ መልካም ተግባር ሲከውኑ ነበር። እና ስለ አምስተረዳም ሲነሳ እነሱ ሁልጊዜ ትዝ ይሉኛል … ማለት ተሳትፎው በሁሉም ዘርፍ ከዬአካባቢው ነበር። ነፍሱን ይማረውና የኢቶጲሱ ያ ጀግና ጋዜጠኛ ሟቹ ተፈራ አስማረም ነፍሱን ይማረውና ወደ ለንድን ከማቅናቱ በፊት በርካታ ተግባራትን ከውኖበታል። እንዲሁም ሌሎቹም …  ዬሲዊዲን ተሳታፊዎች ነበሩት … ራዲዮኑም በዬስብሰባዎች እዬተገኘ ይዘግብ እንደ ነበር አስታውሳለሁ።

ያው ሰብሰብ ያለው፤ ከወን ያለው ነዶ የሚበተነው በተቃዋሚ ኃይሎች የውስጥና የውጭ የቅራኔ አያያዝ ድክመት ምክንያት፤ ኃይሉ በዬጊዜው ካለአግባብ ይባክናል እንጂ። እርግጥ ነው አሁን አሰባሳቢው የፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን ነፃው ሚዲያ ኢሰአት ነውና መሰንበትን ለማሰብ የሚቻል ይመስለኛል። በተረፈ  ኩታ ገጠም ሀገሮች በተለይ ጀርመን፤ ሆላንድና ሲዊድን እጅግ የተቀራራበ፤ የተዋህደ ተግባር ሲከውኑ የቆዩ ብቻም ሳይሆን የጋራም ታሪክ ያላቸው ናቸው። እርግጥ በዬወቅቱ አናቱና ዓውራው ጀርመን ነበር። በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን ከእስልምና እህቶች አንዲት ነፍስ ከባላቤቷ ጋር አብራ ሙሉዑ ተሳትፎ ታደርግ ነበር። ዛሬ ግን ሙንሽን ላይ ያዬሁት የእስልምና እምነት ተከታይ እህቶቻችን በመጠን ላቅ ብለው መገኘት እፁብ ድንቅ የሆነ የሰማይ ታምር ነው። ዋው! እንዴት ደስ እንዳለኝ አትጠይቁኝ። ብርቅ ስለሆኑብኝ በተደጋጋሚ ነበር ያዬሁት።

ወደ ቀደመው ይላሉ አባቶቻችን … ከኢሰአት ትርፋማ ጉዞ የተገኘው ዕንቁ ጉዳይ የታማኝ ሀገራዊ ጥሪ ነው„ታማኝነትንና ህዝባዊ ፍቅርን ተረከቡ ነው።“ ይገርማል። አሁን ማን ይሙት? የትኛው ሰው ነው መዳፌ ውስጥ ላይ የሚገኘውን መጠነ ሰፊ የለማና የፋፋውን ህዝባዊ ፍቅርን ተረከቡኝ የሚለው? ፍልሚያው ያለው እኮ ከዛ ላይ ነው። እውነት ከዚህ ላይ ያለው የአርቲስት ታማኝ ፍጹም ታማኝነት ደግሞ ከዘመኑ ያፈነገጠ ሆነብኝ።  „ህዝብ ለእኔ የሰጠኝን ፍቅር ተረከቡኝና ከዕንባ ታደጉን ነው“ የሚለው። እንዴት ውብ ነገር ነው?! እንዴትስ ለዘመናት የሚቀር ትውፊት ነው እያሰተማረን ያለው?! እንዴትስ ያለ የበቃ የሐዋርያነት ተግባር ነው? ይገርማል። ይደንቃል። ያሰተምራል። ይመረምራል። ይፈውሳል። ያለማጋነን መድህንነት ነው።  ታማኝ  በታማኝነት የቆረበ አይደለ – ለዛውም በዚህ ዘመን ለኮፒራይት ልባችን ድብን በሚልበት፤ የግለኝነት ሞተር መንፈሳችን አንጠልጥሎ እንደ አሻው በሚዘውርበት ዘመን … …“ ህዝባዊውን ፍቅርተረከቡኝ!“ አለ። ዋው! ታማኝና ዕሴቱ ልዩ ሥጦታችን ናቸው። ቀለማም፣ ቅዱስ፣ ቅናዊ መንፈስ … ም!

አርቲስት ታማኝ በዬነ ደቡብ አፍሪካ ላይ የነበረውን ሁኔታ አስመልከቶም ኢሰአት ላቀረበለት ጥያቄ እንዲህ ሲል ነበር የመለሰው “እኔ መንገድ ጠራጊ፤ ደልዳይ ነኝ“ ሲል ተደምጦ ነበር። አሁን ደግሞ „እኔ መሸከም አልቻልኩም! ይህ ህዝብ ቆሞም ተንበርክኮም እዬለመናችሁ ነውና እባካችሁ ተደማመጡ! ኃብታችሁንም ተረከቡ አለ። ለዛውም የከበረውና የበቃውን የሥነ ምግባር ልዑልን ፍቅርን ተረከቡኝ!“ ነው የሚላቸው የተቃዋሚ ኃይሎችን መሪዎችን። እስኪ ይህን አብነትነትህን፤ አደራህን ለመወጣት ሁሉም ደጋፊህ፤ አድናቂህ በተግባር እንዲሆንበት አምላክ ይርዳን። አሜን!
እኔ እንደማስበው በፖለቲካ ድርጅቶች አንድነትና ውህደት መሰባሰብ፤ ልዩነትና መፈራቀቅ፤ እንዲሁም መለያዬት የተፈጠረው ጦርነት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያለነሰ ነው። ጠቅልለው ወደ ወያኔ የገቡት መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ እንበላቸውና … የኛ በምንላቸው እነሱም አለን ለሚሉት ግን ይህ ቅንነትን ስንቅ ያደረግ የህዝባዊ ፍቅር ርክክብ ዓዋጅ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ማዕልት ሁላችነንም ናፍቆናል። አዎን! የአርቲስት ታማኝ በዬነ ብሄራዊ ጥሪ እንደ ባላንጣ መተያዬት በነበር … ነበር … ብቻ እንዲዘለል ነው ፍላጎቱ ….

ነበርን እንደ ነበር ለታሪክ ትቶ፤ አሁን ግን በግል እንኳን እዬተገናኙ የፖለቲካ መሪዎች፤ አባላቶቻቸውም ሆነ አካላቶቻቸው ይህን የህዝብ ጥሪ በጸጋ ተቀብለው በሥርዓት መምራትና ማስተዳደር ይኖርባቸዋል። በኢሰአት ስብሰባዎች ላይ የሚታደመው ወገን አብዛኞቹ በትግሉ ውስጥ የቆዩ ናቸው። አስተባበሪዎቹ ደግሞ የአንደኛው ወገን የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ወይንም ተቀላቅለው፤ ወይንም ተዋህደው ሊሆንም ይችላል። የሆነ ሆኖ ተሳታፊው ኢሰአትን ፈልጎ ሲሄድ፤ ግልምጫ – መገለል – ፊት መነሳት – ባይታዋርነት ሊደርስበት እንደሚችል አምናለሁ ያዬሁት ነውና።
ግን ነገር ግን ተሳታፊው ፊት ለፊቱ የተጋረደውን የልዩነት ጋራ ንዶና አሽንፎ፤ ህሊናውንም አባብሎና አሳምኖ ለመሰዋእትነቴ የማንም ፈቃድ አያስፈልግኝም፤ እኔ ለሀገሬ አንባሳደር ነኝ፤ ብሎ እንዲህ ተሞ ሲሄድ፤ መሄድ ብቻ ሳይሆን ልዩ ታሪክ ፈጽሞ፤ ልዩ ታሪክ ሲሰራ ከላይ ያሉት የፖለቲካ መሪዎችም ከታችኛው ክፍል በመማር እራሳቸውን ቆንጠጥ እድርገው፤ ቢያስፈልግም ገስጸው የትግሉን ባህሪ ለውጥ እድርገው ለአዲሱ ዘመን የሚስማማ በሙሉ ሥነ ምግባር ፍቅርን ማወጅ አለባቸው። በሰነድ ለምደነዋል – በመሆን ይጋቡ …

ይህን ቢያደርጉ ወያኔ እያለ የሌለ ነውና ዘነዘናውን ይቀራል። የሚበጀው ነገር ወደ ኋላ በሚስቡ፤ በሚጎትቱ ጉዳዮች ላይ ጊዜን ከማባከን፤ አዕምሮን ከማቁሰል ወደ ፊት በማዬት የህዝብን ፍዳን፣ ስቃይን፣ መከራን፣ ስደትን፤ ሞትን፤ እስራትን፤ ራህብን በማሰብ ለዚህ ሲባል እራስን ዝቅ አድረጎ ወደ ዬሚያስማማ መስመር መጥቶ ትግሉን መምራት መቻል ብልህንት ይመስለኛል። ብልጥነትም ነው። ትርፋማነትም ነው። እስኪ ዛሬስ ይሁንባቸውና ወያኔን በብልጠትና በብልህነት ይብለጡት።
የኢትዮጵያ እስልምና እምነት ተከታዮችና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ወያኔን እኮ ቅስሙን እንኩት አድርገው ሰባባሩት። ደራጎን አፈረ ከሰረ … ተከሰከሰ። ይህ አስተምህሮት ለተቃዋሚ የፓለቲካ ድርጅቶችም ቢሰራ እንዴት ባማረብን ነበር። መንገዱም እኮ … እንደ እኔ የሰለጠነ ነው። ጠላት የማይፈልገውን አድኖ መፈጸም፤ … ጠላትን ካለ ባሩድ ማንደድ ነው። እያገላባጡም በጥቃት መንገርገብ ነው። ለድልም ያበቃል።

እርግጥ ነው ከቅንጅት መራራ ስንብት በኋላ አንድነትና ግንቦት ሰባት በተቻላቸው ተንቀሳቅሰው ትግሉን አሟሙቀውት ነበር። የዬሀገሮች የኮሚኒቲ ራዲዮ ጣቢያዎች፤ ድህረ ገጾች፤ የመወያያ መድረኮችም፤ ሀገር ድረስ መሰማት የሚችሉ ራዲዮኖችም ጭምር የበኩላቸውን አስተዋፆም አድርገውበታል። በዚህ ዙሪያም ያለው ኃይል፤ የሚፈስው አንጡራ ኃብት፤ ቀላል አይደለም …
የሆነ ሁኖ ግን ሚዲያ እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ፓርቲ ሊያታግልና የነፃነት ትግሉን ሊመራ ፈጽሞ አይችልም። የሚዲያ ሚና፤ ኃላፊነቱና ተግባሩ የነቃውን የህሊና ክፍል መንፈስን አለስልሶ በገዢው ፓርቲ ላይ ሙሉ በሙሉ መንፈስን ማሸፈት ብቻ ነው። በመረጃ የተደገፉ እውነቶችን ህዝቡ እንዲያውቅ በማድረግ የህዝብን የመረጃ የማግኘት ሙሉ መብት በተግባር ማረጋገጥ ነው። ሃቅን መነሻውና መድረሻው ላደረገ መረጃ ከወያኔ ደጅ የዕብለት መረጃ ፍርፈሪ ህዝብ ቆሞ እንዳይለምን የህዝብን የመረጃ ባለቤትነት መብቱን እቤቱ፤ እደጁ ድረስ በመገኘት በተግባር ማስጌጥ ነው። ወያኔ የሚፈጥራቸው አፈናዎችና የነፃነት እግርብረቶችን በብዕር ሰይፍ ብትንትናቸውን ማውጣት ነው። ኢ ሰ አ ት ይህን መጠነ ሰፊ ኃላፊነት በብቃት ይወጣ ዘንድ ነው የሰብዕዊ መብት ተሟጋቹ የአርቲስት ታማኝ በዬነ ጉዞና ድካም። ይህ የሰላ፤ የለሰለሰ መንገድ ደግሞ የበቃኝን፤ የእንቢተኝነትን የፋሙ ፍላጎቶችን ይፈጥራል – ያነጥራል። ግን እንቢታና በቃኝ መሪ ያስፈልጋቸዋል … „ተደማመጡ! ጊዜው አሁን ነው። ግፍ ይሆናል። ተደራጁና ምሩኝ ይላል ወገናችሁ። እባካችሁን?“ ብሏል መንገድ ጠራጊው „ፈረስ ያደርሳል እንጂ …“ ጨርሱት እኔም ጨረስኩ።

አራት ዓይናማው መንገዳችን ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው!
እልፍ ነና እልፍነታችን እልፍ እናድርገው!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

No comments:

Post a Comment