ሥርጉተ ሥላሴ
02.02.2013
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
02.02.2013
ታማኝ አወቀበት ….
ተፈጥሮበት
የተነሳለት ዓለማ – አስከበሮ አፈራለት
ትናት ዘርቶ – ዛሬን አፋፍቶ – አጎምርቶ – አሳመረበት፤
ነገን ለማብራት – በተግባር ቀለም ድሮ – ጽናትን ኮለበት።
ፍቅር ሰጥቶ ፍቅር – ለታሪክ ተቀበለበት
በቀለበት ተቋም፤ - አደራን ውል አዋዋለበት።
ታማኝ አወቀበት ….
ትውፊት አጽድቆ – ለዘመን ደረበለት
መሆን መቻልን – ለመቀነት ደረሰለት።
በፍቅር ስንቅ – ተስፋን አክበሮ ለራዕይ – ዳረለት
እንደ ትናንቱ ዛሬም ታማኝ … ታመነበት ….
በማስተዋል ድርሻን – በድርጊት አበቀለበት።
ሁለት እርእሰ ጉዳዮችን በአንድ የወግ ገባታ አጣምሬ ወይንም አጋብቼ ለማቅረብ አሰብኩ። ግን ይቻለኝ ይሆን? … ትታይ እሜቴ ብዕር … አዎን እኔ እርእሰ ተሰጥቶኝ መጻፍ
አልችልም። ሁልጊዜም እርእስ እምሰጠው መጨረሻ ላይ ነው። መጻፍ ለእኔ ከቧንቧ ውኃ እንደ መቅዳት እጅግ ቀላሉ ስራ
ነው። ለትምክህት አይደለም።
የመዳህኒትዓለምን ሥጦታ ለማክበር ነው። ችግሬና ብዙ ጊዜ የሚፈጅብኝ ግን እርእስ
ከመስጠቱ ላይ ነው። እስከ ወር የሚጠብቁ ጹሑፎች ይኖሩኛል … ጋዳ ነው አይደል?! ለእኔ እርእስን ዘው አድርጎ
ለጹሑፎቼ ቤተኛ ማደረግ … ዳገት ነበር። ዛሬ ግን ግድ አለና እርእሰ ጉዳዩን ካላይ ከአናቱ ጉብ አድርጌ እንተያይ
አልኩት። ተጠራጠርኩት እራሴን … ግን አልገርም? እችል ይሆን? እንጃ ነው እንጃ ጉድሽ ሥርጉተ …
ከሥነ-
ምግባሮች ሁሉ የከበረው ክብር ታማኛነት ነው። ለቃል !~ ለአደራ!~ ለዕምነት!~ ለሰንደቅዓላማ!~ ለዓላማ!~
ለህዝብ የግፍ ዕንባ! … ለትዳር ጓደኛ!~ ለሙያ ሥነ-ምግባር!~ ለዕውነት ፍሬ ነገር!~ ለህዝብ ፍቅር!~
መታመን
ለታማኝነት። መታደል። ሥጦታው የመዳህኒትዓለም ነው። መክሊቱ የአማኑኤል ነው። ሳይተላለፉ መፈጸሙ ደግሞ
የእያንዳንዱ ሰብአዊ ፍጡር መብትና ግዴታ ነው። እርግብ እንኳን ለፍቅረኛዋ ታማኝ ናት! ወንዱም እርግብ ለፍቅረኛው
ታማኝ ነው። የሰው ልጅ ግን ተዛነፍ ነው … ይመስለኛል።
እርግጥ ነው እግዚአብሄር የሰጣቸውን ጸጋና
በረከት አክብረው የሚከብሩ ወገኖች አሉ። ይህን ሳስብ ታማኝነት በምደረ በዳ ላይ አለመከተሙ ባሊህ የሚሉት ወገኖች
መኖራቸውን ሳስብ ደግሞ እጽናናለሁ። ታማኝነት — ከወደዱት ካደነቁት፤ ካከበሩት ጋር ነግሶ -ያነግሳል። ከብሮ-
ያስከብራል፡፤ ጸድቆ – ያጸድቃል። አብቦ – ያፈራል። አስብሎ – ያፋፋል። ንቁውና ቅዱሱ ታማኝነት ታታሪ ነው።
ወረተኝነትንና ስንፈና የረታ የድርጊት ንጉሥም ነው። ክህደትን የገደለ አርበኛ ነው። ግለኝነትን የገፈተረ ወንድ
ነው። ፍቅርን አንደ ታቦት የከበከበ ጻድቅ ነው። ታማኝነት ከአሉታ የጸዳ ብርቱ ክንድ ነው። ከአድሎና ከብክነትም
የራቀ ንጹሕ ሥነ- ምግባር ነው።
ምን ታይቷቸው የአርቲስት ታማኝ በዬነ ወላጆች „ታማኝ በዬነ“ ሲሉ እንደ
አወጡለት ሳስበው ይገርመኛል። እርግጥ ነው ሥምን ቅዱስ መላእክ ያወጣዋል የሚባለውም እውነት ነው። አፈ ታሪክ
አይደለም። በዘመናችን በትውልዳችን እያዬን ነው። አሁን ሥመ -ጥሩውን አርቲስት ቴውድርስ ካሳሁንና „ጥቁር ሰውን“
ስታዩት ጦርነት ሳይታወጅ ለድል የበቃ ተግባር የከወነ የአርበኝነት ልዩ ውሉ ይመስለኛል። ነብዩ አበበ ገላውንም
ስታስቡት የሰው ትልቁ ክቡር ነገር ገላው ነው። ገላው በግፍ ለተጠቀጠቀ፤ ለታረደ፤ ለታሰረ፤ ለተሰደደ ወገን ሁሉ
ጥብቅና ቆመ። እውነቱን ለመናገር የቀደሙት ቅኖች ስለነበሩ የልጆቻቸውን ሥም ሲያወጡም መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው
ስለመኖሩ ማመሳካሪ ቅርስ ትተው አልፈዋል።
ለ21ኛው ምዕተ ዓመት ትውፊት ደግሞ የትውልዱን እርግማን ሁሉ
ያሥተሰረዩ ጀግኖች ዘመናችን አፍርታለች። ከእነሱ ውስጥ አንዱ የሰብዕዊ ተሟጋቹ ታማኝ በዬነ ነው። ታማኝና ችሎቱ
በመሆን ሰንደቅዓላማው በድርጊት የተንቆጠቆጠ ነው። እኔ ታማኝን የማውቀው ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ በወጣበት
ዕለት በጎንደር ሲኒማ ባር ከጓደኞቼ ጋር ታድሜ ከነበረበት ወቅት ጀምሮ ነው። ያን ጊዜ አርቲስ ታማኝ በዬነ ከዓይን
ያውጣህ የተባለ ኣራት ዓይናማ የመድረክ ንጉሥ ነበር። መድረኳ ለእሱ የተፀነሰባት፤ የተወለደባት ብቻ አልነበረችም።
ለዛች ማዕልት ታማኝ የመድረክ ባለሟልና ቤተኛ ስለ ነበር ከዓይን ያውጣህ የተባለ ቀንበጥ ነበር።በዕለቱ አርቲስት
አሰፉ ደባልቄ፤ አርቲስት እናንዬ፤ ጋዜጠኛ አበበ በለው እና ሌሎችም የጎንደር የፋሲለደስ የባህል ኪነት አባላት
ሁሉ ከዛ የወጣትነት ውበት ጸዳል ጋር በሀገር ባህል ልብስ አምረው ብቅ ሲሉ ዋ! ጎንደር የሸበላዎች የቆንጀዎች
መፈጠሪያ ያሰኝ ነበር። ያለማጋነን እጅግ ቆንጆዎች ነበሩ። በምልሰት ስቃኘው … ያን ቀን የተሰማኝን ሐሤት መለካት
ሆነ መመዘን ከቶውንም አልችልም። ወጣትንት ፍቅርና ጤንነት። አለፈ እንደ ዋዛ …
አዎን አርቲስት ታማኝ
በዬነ እና እኔ ከስንት ዘመን በኋላ እሱ በመምህርነት እኔ ደግሞ በተማሪነት። እሱ በሰበአዊ መብት ተሟጋችነት
ተናገሪነት እኔ ደግሞ በአድማጭነት ታደምን። በሲዊዘርላንድ በጄኔባ ከተማ። አንድ ቀን ደግሞ አቤን ባዬው ምንኛ ደስ
ባለኝ ነበር። በምልሰት ከማሰበው ሐሤት ጋር የሚገናኙኝ እነሱ ሁለቱ ብቻ ናቸው። ስለምን? ጽናትን ጽላታቸው
ስላደረጉ ብቻ። ለሆዳቸው ስላላደሩ ብቻ። ለብዙኃኑ የዕንባ ጥሪ ከልጅነት እስከ እውቀት ስለ አመሳጠሩልኝ ብቻ።
በእውነቱ ትውልዱንም ስላሰፈሩ።
አዎን ሲዊዝዬን እጅግ እወዳታለሁ። በአንድ ወቅት እህቴ ከወደ አሜሪካ
መጥታ ገዳማዊ ከተማ ስትል ሾመቻት። እኔ ደግሞ የልቤ ስል ሸልምኳት። ሲዊዘርላንድ የሰላምና የጤና ሀገር ናት።
አዬሩ እራሱ ልዩ ነው። ሲዊዘርላንድ እያላቸው ዝቅ ብሎው የሚኖሩ ዜጎች የከተሟት ሀገር ናት። ሲዊዘርላንድ 26
ክፍለተ ሀገራት አሉት። ሲዊዘርላንድ አራት የሥራ ቋንቋንቋዎች ተስማምተው ሲነገሩባት በሰባት መሪዎችም ትመራለች።
በሲዊዘርላን የነፍስ ወከፍ ገቢ ከፍ ያለ ሲሆን በስደት ህይወት ግን የከፉ ገጠመኞች፤ እርስ በእርሳቸው የተተበተቡ፤
ሰንሰለታማ ፈተናዎችን የበረከቱባትም ሀገር ናት።
ሌላው ሲዊዘርላንድ የሚያስደስተው ነገር በትዳር
ምሰረታና ህይወት ውስጥ ኢትዮጵውያን አብዛኞቹ ፍጹም የሆነ የሰላም ሕይወት የሚያሳልፉበት ገነታዊ ምደር ናት።
በጋብቻ ጥያቄ ላይ እግዚአብሄር ከሰጠው ጋር መጋባት የወል መርህ ነው። ዘር የለም ጎሳ የለም፤ መንደር ጥያቄ
የለም። እንዲያውም አብዛኞቹ የተዋህዶ ልጆች በቅዱስ ቁርባንና በሥርዓተ -ተክሊል ነው የሚጋቡት። ነገር ግን
የሀገርን ዕንባ በመጋራት እረግድ ሲዊዝ ከገባሁበት 2001 ጀምሮ እስከ 2006 ድረስ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ
ሰምቼ ስለማላውቅ ይገርመኝ ነበር። ምን ኮሽ ከማይል ማህበረሰብ ውስጥ ገባሁ እያልኩ አንሰላስልም ነበር።
ከ
2006 ኋላ ግን ዓለምዓቀፍ በሆኑ የትግል እንቅስቃሴዎች ሁሉ ሲዊዘርላንድም ታዳሚ በመሆኗ ደስ አለኝ።
ታዲያላችሁ 2013 የመጀመሪያ ወሩን አሸሼ ገዳሜ እያለ ሸኝቶ ወርሃ የካቲትን ቤት ለ እንግዳ ባለበት ጣሸተ ማዕልት
ገና ከመባቻው በወጣትነት ዘመኔ የማውቀውን አርቲስት ያን ሸባላ ለግላጋ ወጣት ግራጫማ ጸጉር አብቅሎ አዬሁት –
በዓይኔ። ውስጡ ጨሶ የለ
የሰብዕዊ ተሟጋቹ አርቲስት ታማኝ በዬነ ወደ ስብሰባው አዳራሽ ሲገባ አዲስ
ነገር ነበር የገጠመው። እንዴት በሉ? እንዴት ማለት ጥሩ ነገር ነው። አንዲት የስብሰባው ታዳሚ ኡኡታዋን በረጅሙ
በመልቀቅ ከአንገቱ ተጠምጥማ ፍቅሯን፤ አድናቆቷን፤ ስስቷን፤ናፍቆቷን ስትገልጽ በህይወቴ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ
ስለነበር በአፍላው ደነገጥኩ በኋላ ግን ፍቅር የሚሉት የሥነ ምግባሮች ንጉሥ የትዕይንቱ ጥበብ ዕልፍ ስለመሆኑ
አመሳከርኩበት።
ሌሎች … በበርን የሚኖሩ አድናቂዎቹ ደግሞ ዜማ ፈጥረው፤ ፍሬ ቋጥረው፤ እሱን የፈጠረች
ማህጸን፤ እሱን የፈጠረ አብራክን ሲቀድሱና ሲያወደሱ፤ መታደል የሚለው ቃል ውስጤን ስለ መግለጹ ተጠራጠርኩት።ሌላው
መውድሳዊ ግጥሙ፤ ሳቁ፤ የደስታ ፈንጠዝያው እሱን ለማዬት ሽሚያው፤ ካኢሱ ጋር ፎቶ ለመነሳት ጥድፊያው ሁሉ ሳይ
ትውልዱ ታደሰ አልኩ።
ታማኛና ሰራዊቱ ዕልፍ ነበሩና … ፍቅር እንዴት ደግ ነገር ነው። ፍቅር እንዴት
ያምራል – ያሳምራል። ፍቅር እንዴት ያበራል … ከመላ ሲዊዘርላንድ ካሉ ክ/ሀገራት ችለው፤ አጋጣሚውም አግዟቸው
የተገኙት ወገኖች ሁሉ ፍቅራቸውን ቋጥረው፤ ፍቅራቸውን አስልተው፤ ፍቅራቸውን ታቦት አድርገው፤ እንዲሁም በአረንጓዴ
ቢጫ ቀይ ተውበው እኔም እኔም እያሉ ሲሻሙት … ምነው ተደግመህ ተወልደህ እንደ ገና ወጣት በሆንክልን በእውነት
ያሰኛል።
ለመሆኑ ታማኝ ስንት ወላጅ? ስንት ወንድምና እህት ይሆን ያለው? በቁጥር እንዳትተምኑብኝ …
አዳራ … ፍቅር የገዛቸው፤ ፍቅር የጣራቸው። ፍቅር ያስተዳደራቸው ዕልፍ ናቸው። መጠነ ብዙ ናቸው። ከሊቅ አስከ
ደቂቅ ታማኝ የሚሉት … በድንቋ በባዕታችን እስተዲዮ ውስጥ ሲገኝ እንኳን „ግባ ባለው ታማኝን“ ይባል የነበረው
ዛሬም በስደቱ ቀዬ የታማኝ የፍቅር መክሊት በርትህ አደባባይ ችሎት ላይ ቢውል ድንበር አልባም ነው። የእውነት
የማልያ ፍቅር ታውቃላችሁን? አዎን እሱ የዕናባችን ማልያ ነው።
የኢሰአት የገቢ ማሰባሰቢያ በሲዊዝ ጄኔባ – ውሎና ምሽት።
ፕሮግራሙን
ያዘጋጁት የሲዊዝ የኢሰአት አስተባበሪ ኮሚቲዎች ደፋ ቀና ሲሉ የሰነበቱበትን የፍቅር መስተንግዶ አህዱ ያሉት
„የሲዊዝ ተሳትፎ በኢሳት አንባ“ በሚል አጠር ያለ ሪፖርት በማቅረብ ነበር። ስብሰባውን ለዬት ያደረገው ደግሞ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች ካህናት ተገኝተው ቡራኬ መስጠታቸው ብቻም ሳይሆን ከእስልምና እምነት
ተከታዮችም ውክል መሰጠቱ ማዕልቱን ፍጹም ውበት ሰጥቶታል።
ዋው! ከዚህ በኋላ ምን ሆነ መሰላችሁ
….መቼም ዘመኑ የወጣቶችም ነው ማለት ይቻላል … ከሴቶችም ጎራ ታክሎበት በጥምረት ጋዜጠኛ ገሊላ መኮነን ያቀረበቸው
ዕንባ ያራጫ „ኢትዮጵያ በፍሰኃ ዘመኗ፤ የፍሬዎቿን ሁለገብ ብቃትና ክህሎትን መነሻው በማደረግ በምለሰት ቃኘት
አድርጎ፤ ውድ እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለፈችበትን የመሰናክል ዘመናትን አስነብቦ፤ ዛሬ ያለውን የማህጸኗን የደም
ዕንባና የሱባዬ ወቅት በእርምሞ ያመሳጠረው ትዕይንት የላቅ ነበር። ብቁ ነበር። የሰለጠነ ነበር። አንድ ብቻዋን
ከ300000 ዘመናት ታሪካዊ ሁነት እስከ ሰንደቅዓላማ እስር ቤት ድረስ አመሳጠረቸው። በስንት ዘመኔ ዓይኔና
ትዕይነት በሥርዓተ ተክሊል ተጋባ መሰላችሁ። ይባርካት። እዬበሉ እዬጠጡ እንዳይሆን አብራችሁ መርቁ። የእኛ ውበታችን
እኮ ብዙ ነው። በምርቃት ወተትም ጭምር ነው ያደግነው።
ሥነ- ጥብብ አማረባት … ሙዚቃው ባንዱ የመጣው
ከጣሊያን ነበር። ሁሉን የሰጠው ደርባባ … ኢትዮጵያን አምጥቶ መዳፋችን ላይ ከነውበቷ በ80 አጋባልን። ወላድ
ትውለድ … ጥበብ ይደግ ይመንደግ። አሁንም መርቁ … እያኮኮምኳችሁ ነው። የጄኔባን ህዝበ ጠቀም የወገን ጥሪ ቀን
ፍሬና ሰብሉን እያቆላመጥኩ እያከሰከስካችሁ ነው … አቤት! ስንት አንገት – ስንት የንብ አውራ የመሰለ ሽንጥና ዳሌ
ሲውነከነክ … አየሁ መሰላችሁ … አማራችሁ ይሆን? ይላክላችኋል። ግን ባህሬያችሁን ካሳመራችሁ ብቻ …
ማዕደ-
መስተንግዶው በሁሉም ዘርፍ ማለፊያ ነበር። የጾታ ልዩነት ሳይኖር በርካቶቹ ታድመውበታል። ወይ ጉድ! የሲዊዝ
ሴቶች ጉደኞች ናቸው፡፤ የሴት አረቂዎች …. አቤት ሲያስደስቱ …. የቀራቸው የለም ጠላውን ጠጁን … ምግቡን
አትጠይቁኝ የእናት ቤት ማጀት ሙላት በሙላት። ሌላ ምን ቀረኝ? እህ … እኔን ይርሳኝ ቡና አለሙን አዬላችሁ።
ፍንጃሉ ከነረኮበቱ ጉብ ብሎ ምን በመሰሉ በሀገር ባህል ልብስ በተዋቡ ልጆቿ ኢትዮጵያም ደምቃና አብባ መጥታ ጄኔባ
ላይ ጉብ አለችላችሁ- ከነመንበሯ። ማን ጌታ አለባት?! ልጆቿ ይኑሩ እንጂ። እነሱ ከባህላቸው ዝንፍ አይሉ –
የጸደቁ!
ሁሉ ነገር እዬተዋዛ ሰውነትም ዘና እያለ ሲሄድ አርቲስት ታማኝ በዬነ አመጣው፤ በመረጃ አስደግፎ
ሰቆቃ፤ ግፍ፤ ትእቢት፤ እና የህዝብ ፍዳ … በተጨባጭ በማብራራት „ፍዳን እያዩ እንዳላዩ ሆኖ መርገጥ፤ መጠቅጠቅ
… ወይንስ ፍዳን ከሥር ለመንቀል ትግሉን በሁሉም ዘርፍ ማገዝ? … በሚል እጅግ በሚመስጥ፤ ህሊናን በሚያፋጥጥ
ቅኔዊ ስልት አዋህዶ ፍርድና ድኝነቱን አቶ ህሊና አሰኘው። አወና! እኔስ ምን አደርኩ በማለት ከራሳችን ህሊና ጋር
እንድንነጋገር ችሎቱን በሚዛን አዋቀረልን። እሰቡት አኔ ለእኔ አጀንዳ ስሆን፤ አስሉት እኔ ለእኔ ተናጋሪ ስሆን፤
እሰቡት – እኔ በእኔ ውስጥ አደባባይ ሲውል – ሲወስን ስበይን ሲተችም … እንዲህ ነበር መንፈስን አባብሎና
አቆላምጦ በመግራት ሰራዊቱን ለተግባር ያሰማራው የሥነ -ጥበቡ ጄኒራል …
ጠረገው መንገዱን።
አስተካከለው ወጣ ገባውን። አስማምቶ – አላሳልሶ „ የሚዲያ አስፈላጊነት ለነጻነት ትግሉ የ ኢ ሰ አትን ተጨባጭ
የተግባር ውጤት በመሰታግብር አስተጻምሮ አዋዶም“ የመጣበትን ተልዕኮ ገለጸ። የሲዊዝ ልጆችም ህሊናቸው የዳኘላቸውን
እጅግ የበቃ ተግባር ከወኑ። በጨረታው ብቻ ከ20000.00 የሲዊዝ ፍራንክ ያለነሰ ተሰበሰበ። ፉክክሩ፤ ውድድሩ፤
እልኹ ሁሉ በራሱ ሐሤት ቀላቢ ነበር።
ተሳትፎው – በረዱ፤ ብርዱ፤ ዝናቡ፤ ጉዞው ሳያደከመው ፍቅሩን
በተግባር ፍቅር አቅልሞ ኢሰአትን አከበረው። ታውቃላችሁ አይደል ሲዊዝ ትንሽ ሀገር ናት። በዛ ላይ የተገኘው ሰው
አንስተኛ ነው ማለት ባይቻልም ሁሉም አልተገኝም ። ነገር ግን የሁሉንም ጥቂቶች ኃላፊነቱን በተሟላ ሥነ -ምግባር
ተወጡት። ይገርማል አንዲት ሴት ብቻዋን የወር ደሞዝተኛ 1000.00 የሲወዝ ፍራንክ ስትሰጥ ማዬት ዕፁብ ነው።
የጸሎት አጥር ለሰጪ … ያስፈልጋልና በጸሎት እሰቡ … ሂሩተ – ገብርኤልን … እና ሌሎችንም። አብነቱ የትምህርት
ተቋም ነው።
በአጠቃላይ ጥቂት ሰው ስላችሁ የመጠው ሰው ትንሽ ነበር ብላችሁ እንዳታሰሉት። በቂ ወገን
ተገኝቷል። የአርት አፍቃሪ፤ የኢሰአት አድናቂ፤ የታማኝ ናፋቂ እንደ አመጣጡ …. የጀግንነት ውሎውን በደማቅ
ተግባር ከውኖ ልክ ከምሽቱ ሰባት ሰዓት አካባቢ በድል፤ በፍቅር፤ በፍሰሃ የታማኝነት ውሎው ኢትዮጵያዊነትን አዝምሮና
ዘምሮ ተጠናቀቀ። ታማኝም በመታመን ቆረበ።
ዛሬም እንደትናቱ ታማኝነቱን ለህዝባዊ ፍቅር እንዲሰግድ
የፈቀደው አርቲስት ታማኝ በዬነ በፈካ ገጽ ፍጹም በሆነ ወገናዊ ፍቅር እኩል በሆነ የአያያዝ ጥበብ የተነሳለትን
ዓላማ ከግብ ለማደረስ ቆርጦ ተነሳ፤ አፈራም። ስብሰባውን የአዘጋጁት የሲዊዝ የኢሰአት አስተባበሪ ኮሚቴዎችም
ድካማቸው አሰበለ። ፍቅር ምንኛ ጥሩ ነው። ቅንነት ምንኛ ደግ ነው። ይኽው በስንት ዓመቴ ከታማኝ ጋር እኔም ለዓይነ
ሥጋ በቃሁ … ተመስገን!
አራት ዓይናማው መንገዳችን ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው!
እልፍ ነንና እልፍነታችን በተግባር እልፍ እናድርገው!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
No comments:
Post a Comment