የሕግ ባለሙያ፣ ባለሀብትና አርቲስት የሆነው አበበ ባልቻ ተከስሶ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሔዷል፡፡ አበበ ባልቻ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሊሔድ የቻለው ባለፈው ሐሙስ ሌሊት ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ሸገር ሕንፃ ስር በሚገኘው ዩጎቪያ ክለብ በመዝናናት ላይ ነበር፡፡ በቦታው ለእረፍት ከኖርዌይ የመጣውና በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኖርዌያዊ የሆነው ሐሰን መሐመድና የወንድሙ እጮኛ እየተዝናኑ ነበር፡፡ ከሐሰን ጋር የነበረችው ሴትም አበበ አስናቀን ሆኖ በሚጫወትበት የሰው ለሰው ድራማ ታደንቀው ስለነበር ወደ እሱ በመሄድ አብራው ፎቶ ለመነሳት ትጠይቃለች፡፡ አበበም ፈቃደኛ በመሆን አብሯቸው ይነሳል፡፡
ትንሽ ቆይቶ ግን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ መበሳጨት ይጀምራል፡፡ ከዚያም ወደ ሰዎቹ በመሄድ ከሐሰን ላይ ፎቶ ያነሳበትን አይፎን 5 ይቀበለውና መሬት ላይ በመጣል በእግሩ ይሰባብረዋል፡፡ ከልጁም ጋር ለመደባደብ መተናነቅ ሲጀምር የክለቡ ጠባቂዎች ይገላግሏቸዋል፡፡
ሞባይሉ የተሰበረበት ሐሰን አበበን እንዲሁ ሊለቀው ስላልፈለገ ወደ ሕግ ሊወስደው ሲጥር እሱ ባልጠበቀው ሁኔታ ጠባቂዎቹ አበበን ከቤቱ ያወጡታል፡፡ የአበበን መውጣት ያወቀው ሐሰን ግን ከአበበ ጋር አብሮ ይዝናና የነበረውን አርቲስት ሰለሞን ቦጋለን በመያዝ “አንተ ስለሆንክ ያስመለጥከኝ አንተን ወደ ሕግ እወስድሃለሁ” በማለት ይዞት አቅራቢያው ወደሚገኝ ካራማራ ፖሊስ ጣቢያ ይሄዳሉ፡፡ ጣቢያ ደርሰውም ጉዳዩን ያስረዳሉ፡፡ ስለ ሁኔታ የተጠየቀው ሰለሞንም ድርጊቱ መፈፀሙንና በማግስቱ አበበን እንደሚያቀርበው ተናግሮ የአበበንም ስልክ ለፖሊሶች በመስጠት ይለቀቃል፡፡
በማግስቱም ከሳሾች በንብረት ማጉደል ክስ መስርተው ለአበበ በወኪሉ አማካኝነት መጥሪያ በመስጠት ይመለሳሉ፡፡ አበበም ፖሊስ ጣቢያ በመቅረብ ሁኔታ መፈፀሙን እንደማያስታወስ ግን ምናልባት በትከሻው ገፍቶት ወድቆ ሊሆን እንደሚችል ይናገራል፡፡ አቃቤ ሕግና ፖሊስም እነ አበበ ጉዳዩን በሰላም እንዲፈቱት በማግባባታቸው አበበ ለሰበረው ሞባይል 18 ሺህ የኢትዮጵያ ብር እንዲከፍል በመወሰኑ ተያይዘው ወደ ቢሮው በመሄድ ቼክ ፈርሞ ለሐሰን በመስጠቱና ይቅርታ በመጠየቁ ችግሩ ሊፈታ ችሏል፡፡ (የዚህ ወሬ ምንጭ ኢትዮጲካ ሊንክ የተሰኘው የአዲስ አበባ ሬዲዮ ነው)
No comments:
Post a Comment