September 8, 2013
በማእከላዊ ቆይታው አሰቃቂ ጊዜ አሳልፏል!
በእስር
ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደ ክስ የተመሰረተበት ከጋዜጠኝት ስራው ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የቀድሞ የሙስሊሞች
ጉዳይ መጽሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተርና አዘጋጅ የነበረው ሰለሞን ከበደ ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ከቤቱ ወደ ስራ
ቦታው ሲሄድ ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በማእከላዊ ለአራት ወራት ያህል አሰቃቂ ምርመራ ተደርጎበታል፡፡
በምርመራ ወቅት
በቀን ከ12 ሰዓታት በላይ በተለያዩ ገራፊዎች ተፈራራቂነት ቶርች ሲደረግ ከመቆየቱም በላይ ለተደጋጋሚ ጊዜያትም
ራሱን ይስት እንደነበር ታውቋል፡፡ ጋዜጠኛ ሰለሞን በምርመራው ወቅት በድብደባም ሆነ በሌላ መልኩ ሊያስጠይቀው
የሚችል ምንም ወንጀል ባይገኝበትም ክስ ተመስርቶበት አሁን በቂሊንጦ ወህኒ ቤት ይገኛል፡፡
ጋዜጠኛ
ሰለሞን ሰለሞን በእነ አማን አሰፋ የክስ መዝገብ የተከሰሰ ሲሆን የክሱ ጭብጥም ‹‹የከተማ ጂሀድና መላውን ሙስሊም
ያካተተ ጂሀድ ማቀጣጠል›› የሚል አሳፋሪ ውንጀላ ነው፡፡ በመንግስት ክስ ከተማ ጂሀድና የትጥቅ ትግል በመምራት፣
በማደራጀትና በማቀጣጠል የተከሰሰው ሰለሞን በዚህ ውንጀላ መነሻነትም የማእከላዊ ገራፊዎች ሰለሞንን ደጋግመው
‹‹የጦር መሳሪያዎችን የት ነው የደቅከው?›› ሲሉ ይገርፉት ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹ለወታደሮች ስልጠና
ትሰጣለህም›› ተብሎ የማእከላዊ ገራፊዎች እረፍት የማይሰጥ አሰቃቂ ቶርች ፈጽመውበታል፡፡ ከአራት ወራት አሰቃቂ
አስር በኋላም በሰኔ 2005 ክስ ተመስርቶበታል፡፡
ሰለሞን ከበደ ላይ መንግስት ክሱን ከመሰረተ በኋላ
ለሁለተኛ ጊዜ ክሱን ከልሶ ያቀረበ ሲሆን በዚሁ በተከለሰው ክስ ላይም ሰለሞን የተከሰሰው በጋዜጠኝት ስራው መሆኑን
ተመልክቷል፡፡ ክሱ ‹‹… ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ከሽብር ቡድኑ አባላት ጋር በመገናኘትና በአወሊያና በየመስጂዶቹ
የተጀመረው አመጽ እንዴት መቀጠል እንዳለበት በመወያየት ለአመጽ የሚያነሳሱ ጽሁፎችን በየወሩ በመጽሄት በተለያዩ
ርእሶች ሲያወጣ ቆይቶ በመጨረሻም ይህንኑ በማሰባሰብ ‹‹የኢትዮጵያ ሙስሊም የት ጋር ነው?›› በሚል ርእስ አመጽ
ቀስቃሽ ጽሆፎችን በማሰባሰብ መጽሀፍ በማሳተምና በማሰራጨት…›› በሚል በግልጽ በሙስሊሞች ጉዳይ መፅሄት ላይ ይሰራ
በነበራቸው የጋዜጠኝነት ስራዎች መከሰሱ አውን ሆኗል፡፡
መንግስት ደጋግሞ ‹‹ጋዜጠኞች በሙያቸው በሰሩት
ስራ አልተከሰሱም አይከሰሱም›› ሲል የቆየ ቢሆንም ሰለሞን ከበደ በዚሁ የጋዜጠኝነት ስራው ተከሷል፡፡ የመፅሄቱ ዋና
አዘጋጅ የነበረው ዩሱፍ ጌታቸው በተመሳሳይ መልኩ በመፅሄቱና በቢ.ቢ.ኤን ሬዲዮ ላይ ያቀርባቸው በነበሩ ዘገባዎች
ምክንያት ክስ ተመስርቶበት ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ዳኢዎችና ኡለማዎች ጋር ከ14 ወራት በላይ
በእስር ላይ ይገኛል፡፡ የጋዜጠኛ መብት ተሟጋች የሆኑ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸውና ሰለሞን ከበደ
ከእስር እንዲለቀቁ ተደጋጋሚ ጥሪ ለመንግስት አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ጋዜጠኞችን በማሰር መጥፎ
ስም ማትረፏ የሚታወቅ ሲሆን በአፍሪካም ከኤርትራ ቀጥሎ ብዙ ጋዜጠኞችን ያሰረች አገር እንደሆነች አለም አቀፍ
ሪፖርቶች ያመላክታሉ፡፡
No comments:
Post a Comment