Friday, 13 September 2013

ኢትዮጵያ ከ2ኛ የዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠረች ሀገር ናት!” – ኢሳይያስ አፈወርቂ

File photo of Eritrean President Isaias Afewerki in Sana'a
የባሰ አታምጣ! ነው የሚባለው። መቼም የኤርትራ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋዜጣዊ መገለጫ በሰጡ ቁጥር ግርግር ሳይፈጥሩ፤ ጎረበት አገር በውስጠ ወይራ ሳይጎነትሉ፤ ምዕራባውያን መንግሥታት ግልጽና በማያሻማ ቋንቋ ሳይወርፉና ሳይዘነጥሉ፤ ብዙሐን ፈገግ ሳያሰኙ፤ በአንጻሩ ደግሞ የተማረውን ክፍል ሳያስለቅሱና እርር ድብን እስኪል ድረስ ሳያደርጉ አልፉ ማለት ዘበት ነው።

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ይህ ሁሉ ለማድረግም ሆነ ሁሉን ለማዳረስ ደግሞ የረጅም ሰዓት ሽፋን አያስፈልጋቸውም። በአስርና አስራ አምስት ደቂቃ ውስጥ መርፌ የሚያስፈልገውን መርፌ ወግተው ጸበል መርጨት የሚያስፈልገውን ጸበልን ረጭተው ሁሉን ነካክተውና አዳርሰው ጋዜጠኛ በጊዜ ማሰናበትም ተክነውበታል።

ፕሬዛዳንት ኢሳይያስ ከሌሎች አፍሪካዊያን መሪዎች ተለይተው የሚታወቁበት እልል ያለ የለየለት ጸባይም አላቸው። ይኸውም፥ የአገር ውስጥ ጋዜጠኛ በሳቅ አቁስለውና አስፈንድቀው መልቀቅ የሚያውቁበትን ያክል የነጭ ዘር ያለበት የባህር ማዶ ዜጋ ጋዜጠኛ ደግሞ “ይሄ ያንተ የፈጠራ ድርሰት ነው፣ እኔ ምን አውቅለሃለሁ?፣ አላውቅም!፣ ውሸት!፣ ይህ የላኩህ/ሽ የቀን ቅዥት ነው!፣ አሁንስ የሰለቸኝ ነገር ቢኖር የእናንተ ቀደዳ ነው!” በሚሉ ተራራና አንዳንድ ጊዜም ክብረ ነክ የሆኑ አጫጫር ቃላቶች በመሰንዘር ብርሃን ይመስል የነበረ ፊት አጥቁረውና እርር ኩምተር አድርገው፣ አበሳጭተው፣ አንገት አስደፍተው፣ አሳጥተውና አማረው በመጣበት የማሰናበት ጸባይ አላቸው።
ሰለ ክፉም ሆነ ደግ አመላቸው ከዚህ በላይ መሄዱ አስፈላጊ አይደለምና ወደ ጉዳዬ ልመለስ። ፕሬዛዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት መባቻ ምክንያት በማድረግ እ.አ.አ መስከረም 06/2013 ከአገር ውስጥ የዜና አውታሮችና መገናኛ ብዙሐን በትግርኛ ቋንቋ ባያደረጉት ረጅም ቃለ መጠይቅ ነባራዊ የኢትዮ ኤርትራ በተመለከተ “የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ መጨረሻ ምንድ ነው? መፍትሔውስ?” ሲል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ለመሆኑ እነ ማን ናቸው?” በማለት እንደ ሱማሌ … ነገሩን ጣልጣል ካደረጉት በኋላ ሰሚ ጆሮ ጭው የሚያደርግ አዲስ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ትንተና በመስጠት የሰጡት ምልሽ “በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ምንም የሚፈጥረው ስሜት አይኖርም” በማለት አቶ ኢሳይያስ በሚገባ ሳያስቡበት በድንገት ከአፋቸው አምልጧቸው የተናገሩት ቃል ሳይሆን በሚገባ ተሰልቶና ታስቦበት “ምን ያመጣሉ?!፣ የትስ ይደርሳሉ?!፣ ቅር ካላቸውም ቅራሬ በእኔ ሂሳብ፣ ከደረሱበት ደግሞ ለምን አፍንጫቸው ቀቅለው አይበሉም?!” በሚል በማን አልብኝነት በትዕቢትና በንቀት መንፈስ የተነገረ ለመሆኑ ተርጓሚ አያስፈልገውም። የፕሬዝዳንቱ ሙሉ ቃል እንደወረደ እንደሚከተለው ይነበባል፥
“ኢትዮጵያ ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ተከትሎ የተፈጠረች ሀገር ናት።
ያም ሆነ ይህ ሌላ ሰው የፈልገው ሊል ይችላል ይህች ኢትዮጵያ በመባል የምትታወቀው ሀገር ግን ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ተከትሎ የመጣ የዓለም ሥርዓት ሥርዓቱ ራሱ በሚመርጣቸው ገዢዎች ይጠቀምባት ዘንድ የፈጠራት ኃይል ናት።” (የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ)
እግዚአብሔር ያሳዮት! ታሪክ አጣቅሶ “ኢትዮጵያ በምኒልክ የተቆረቆረች ሀገር ናት” በማለት የተናገረ ውጉዝ ከመ አርዮስ!! እየተባለ በትልቁም በትንሹም ሲወገዝና ሲገዘት አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ደግሞ ኢትዮጵያ የምታክል አገር ሳይሰቀጥጣቸው ጭራሽ የ65 ዓመት ጎልማሳ አድርገዋት ቁጭ አሉ። ጎበዝ፥ 2ኛው የዓለም ጦርነት ማለት እኮ በአሜሪካና የሶቭየት ኅብረት አሸናፊነት የተጠናቀቀ ከ1932 – 1937 ዓ.ም የተካሄደ እጅግ ታላቅ አለም አቀፍ ጦርነት ሲሆን ሰባ ሚልዮን የሚገመት የዓለማችን ሕዝብ የበላ የትናንት ታሪክ ነው። ፕሬዛዳንት ኢሳይያስ ይህም ሳያንሳቸው ጃንሆይም ሆኑ ጓድ መንግሥቱ የውጭ ኃይሎች ስራ አስፈጻሚዎች፣ ተላላኪዎች፣ አሻንጉሊቶችና የይስሙላ መሪዎች ናቸው አሉን። ሀገሪትዋም (ኢትዮጵያ) የተመሰረተችው ለልዩ ተልዕኮ በውጭ ኃይሎች ምክርና ዕቅድ የተጠፈጠፈች ሀገር ናት በማለት ይባስ ባይተዋሮች አደረጉን።
እኔ የምለው “የኢትዮጵያ ዓይንና ጆሮ ነኝ” በማለት በቀንም በሌሊት ለፍፎ የማይደክመው ሁከተኛ ልሳን ኢሳት የት ገባ? ኧረ አገር ስትዘለፍ ኢሳት ምን አለ? “በኢትዮጵያ 66% በሚሆኑ ቤቶች መጸዳጃ ቤት አልባ ናቸው” አለ! በማለት እንደማይቀልዱብኝ ተስፋ አደርጋለሁ። “ነቢይ” ታማኝ በየነስ ከወዴት አለ? አልሰማ ይሆን እንዴ? ወይስ የስታንፎርድ ጥይት በሳስቶ እንዳስተኛው እንደተጋደመ ነው? ምህረቱን ይዘዝልህ ለማለትም አልተቻለም እኮ። ሲገኝ አይደል። ቃሉ በአቶ ኢሳይያስ ፈንታ አንድ የትግራይ ክልል ተወላጅ ተናግሮት ቢሆን ኖሮ ግን አንዲትዋን ቃል በእልፍ እየተባዛች፣ እየተሰነጠቀች፣ እየተሸረፈችና እተረሸራረፈች፣ እየተመነዘረችና እየተዘረዘረች ምድር ትሸከመው ዘንድ እስከማይቻላት ድረስ ይጮህ ነበር። አርቲስት ታማኝም እንደሆኑ ነገሩን በሚገባ ለማያያዝ፣ ለማንደድ፣ ለማቃጣጠል፣ ለማራገብና ሕዝብ ከሕዝብ ጋራ ለማናከስ እንዲሁም ለማጨራረስ ከፊትና ከኋላ በነገር አያያዡ በኢሳት ታዥበበው ከአገር አገር ይዞሩ ነበር። ነጋሪት እየተጎሰመ፣ እምቢልታ እየተነፋ፣ ከበሮ እየተደለቀ፣ የክተት አዋጅ ታውጆም የትግራይ ክልል ተወላጅ ባለባት ሁሉ ቁም ስቁልን ያይ ነበር።
አርቲስት ታማኝ በየነ ግልጽ በሆነ ቋንቋ የትግራይ ሕዝብን “የእንቁላል ነጋዴ” በማለት አፋቸውን ሲያላቅቁና አንድ የራሱ ባህል ወግና ልማድ ያለውን ሕዝብ ሲሰድቡና ሲያንቋሽሹ “ምን አልክ አንተ …” በማለት አጸፋውን የመለሰላቸው የትግራይ ክልል ተወላጅ አላያየሁም አልሰማሁም። አቶ ጀዋር መሃመድ የተባሉ ግለሰብም እንዲሁ በቅርቡ “አማራ ትናንት ወንድሞቼ ሲጨፈጭፍና ሲገድል የነበረ ጨቋኝ” ነው በማለት አፋቸውን ሞልተው ሕዝብን ሲወነጅሉም በተመሳሳይ አቶ ጀዋርን መልስ የሰጣቸው ሰው አልሰማሁም። ከዚህ ሁሉ ግን እንደ ሌላው ወገኑ የመናገር መብቱን ሳይቀር ተገፎ የሰቀቀን ኑሮ የሚገፋ የትግራይ ሕዝብ እጅግ ያሳዝነኛል።
እንግዲያውስ በኢትዮጵያዊነታችን መሰባሰብ ቀርቶ ሁሉም በየፊናው ከየአቅጣጫው “የዘር” ሐረጉን እየቀጠረ እየተጠራራ ሲሰባሰብና ሲደራጅ፤ የአባቶቹ ባህል ሲያጣጥምና ነኝ በሚለው ጎጣዊ ማንነት ሲኮራ ሲበጣጠስና ሲዝናና የትግራይ ሕዝብ ደግሞ እንደ ሌላው ሕዝብ በትግራዋይነቱ የሚኮራበት የአባቶቹ ታሪክ ለማወቅና ለመማር የማይሰባሰብበት ምክንያት ምንድ ነው? ሰዎች ነን በሚሉት ጎጣዊ አስተሳሰብ ሳያፍሩ ሳይሸማቀቁና ሳይፈሩ ኩራት እየተሰማቸው መሰባሰብ ከተቻላቸውና በአደባባይ መድረኮች በማዘጋጀት እርስበርስ ለመነገጋር፣ ለመመካከር፣ ለመተናነጽና ለመያያዝ ከበቁ የትግራይ ሕዝብ በትግራዋይነቱ ኩራት እየተሰማው የማይሰበሰብበት የእርስ በርስ የመመካከሪያና የመነጋገሪያ መድረኮችም በማዘጋጀት የማይወያይበት ምክንያት ምንድ ነው? በራሱ ቋንቋ ብሂልና ለዛ የራሱ የቴሌቭዥን ጣቢያ በመክፈት የማይዝናናበትና የጠላቶቹን አፍ የማይዘጋበት ምክንያት ምንድ ነው? ማንን ተፈርቶ ነው ይህ ሕዝብ ቁልቁል እንዲወርድ እየተፈረደበት ያለው? ለምንድ ነው ይህ ሕዝብ ያለ ኃጢአቱ እየተለጠፈበት እንዲገለልና እንዲነጠል እየተገፋ ያለው? ሌላው እንዳሻው ሲገለባበጥና እንደተመቸው ሲሆን የትግራይ ሕዝብ ሹክታ ያሰማ ቅጽበት ከየአቅጣጫው በሚወረወረው ፍላጻ እንዲቆስል እየተደረገ ያለው ለምንድ ነው? ጥበብ በጎዳና ላይ ትጮሃለች!
ከነተረቱ “እናትዋን የማታውቅ አክስትዋን ትናፍቃለች” ነው የሚባለው ደግሞስ የትግራይ ብሔር ተወላጅ ጠላት – በጥፋት መስመር ራሱን ያሰማራ የኤርትራ መንግሥስት ደግሞ እንደ ወዳጅ እሽሩሩ እየተባለ ሲያጠፋ የሚወደስበት አሰራርስስ ምን ይሉት ኢትዮጵያዊነት ነው? ኤርትራ ሌላው ይቅር “ኢትዮጵያዊ ጀግና” ተብለው የሚወደሱ አጼ ምኒሊክ በሀገር ክህደት፣ በአረመኔነትና በነፍሰ ገዳይነት ወንጀል “Wanted!” በማለት የምትፈልጋቸው የክስ መዝገብዋን ያልዘጋች አገር መሆንዋን እየታወቀ ዛሬ ደግሞ ፕሬዝዳንትዋ ሉዓላዊት የሆነች ሀገር (ሀገራችን ኢትዮጵያ) በጠራራ ጸሐይ ሲገሸልጥዋትና በረጅም ምላሳቸው ሲሸልትዋት በቃላቸው የማይጠየቁበት ምክንያት ምንድ ነው?
ኤርትራ ምድሪቱ ያፈራቻቸው ጀግኖችዋን ባወሳችና በዘከረች ቁጥር አጼ ምኒሊክ በኤርትራ ተወላጆች የፈጸሙትና አደረሱት የሚሉትን አሰቃቂና ዘግናኝ የአጼው ነውራም ድርጊት “ታሪክ የማይረሳው በደልና ግፍ!” በማለት ሳታሰማና አቤት ሳትል አታልፍም። ጥጉ፥ ይህን ጸሐይ የሞቀው ሐቅ ለጊዜው ተዳፍኖ በተጨማሪም የኢሳትም ሆነ የአርስቲስ ታማኝ በየነ ዝምታ የአማራ ብሔር ተወላጁ የሆኑትን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አሥመራ ከተማ መከተምና ከኤርትራ መንግሥት እጅና ጓንት ያደረገ ታሪካዊ ወዳጅነት ኖሮ ሳይሆን “የጋራ ጠላት” ተብሎ የተፈረጀው የትግራይ ሕዝብ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለማክሰም፣ ለማንበርከክ፣ ስመ ዝክሩ ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት፣ ለመደምሰስና ዘሩ ለመጨረስ ለመሆኑ የግንቦት ፯ አደረጃጀትና የድርጅቱ መሪዎች በትግራይ ሕዝብ ያላቸው ስር የሰደደ ጥላቻ እንዲሁም የሻዕቢያ መንግሥት የዘመናት ሕልም በሚገባ ማወቅን ይጠይቃል። ኢየሱስን ተስማምተው የሰቀሉ አካላትም ቢሆኑም እኮ የሚያስማማ ነገር ኖሯቸው ሳይሆን ሁለቱም በየፊናቸው ንጽሑን ሰው ኢየሱስ በተሳሳተ ሸውራራ መነጽር ስላዩትና እንዲህ ማስተማር ከቀጠለም ማናችንም አይቀርልንም ሲሉ በደርሱት የተሳሳተ ድምዳሜ ነበር ሰቃዮቹ ታሪካዊ ደምነታቸውን ለጊዜው አዳፍነው የንጽሑን ደም ለማፍሰስ የተጣደፉ።
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

No comments:

Post a Comment