የካናዳው ‹‹ቃሌ የኢትጵያውያን የውይይት መድረክ›› ከጎናችሁ ነን ብሎናል
29ኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመታገል ባለ አስራ አምስት ነጥብ የመግባቢያ ሰነዱ ላይ ነገ ተወያይተው
እንደሚያፀድቁት የተገለፀ ሲሆን አገሪቱንና ኢትዮጵያውያንን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፓርቲዎቹ ሰብሳቢ
አስታወቁ፡፡ የመግባቢያ ሰነዱ የህዝብ የበላይነት እንዲሁም ዲሞክራሲያዊ መብቶች የተከበረበት ዘላቂ ህገ መንግስታዊ
የመድብለ ፓርቲ ድሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባትን ዓላማ ያደረገ እንደሆነና ውይይቱ ፓርቲዎቹን ወደ አንድ ፓርቲነት
ሊያመጣቸው እንደሚችል ተገልጿል፡፡ የመድረክ የስራ አስፈፃሚ አባልና የፓርቲዎች ሰብሳቢ አቶ አስራት ጣሴ ለአዲስ
አድማስ እንደጠቆሙት፤ ለሃያ ዘጠኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመግባቢያ ሰነዱ የተበተነላቸው ሲሆን ፓርቲዎችም በባለ 15
የመግባቢያ ነጥቦች ላይ በመስማማታቸው፣ በነገው ዕለት ውይይት አድርገው በሰነዱ ላይ ለመፈራረም ተዘጋጅተዋል።
የመግባቢያ ሰነዶቹ በዋናነት የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅሞች የሚነኩ ጉዳዮችንና መንግስት በሚወስዳቸው የሀገርና
የህዝብ ጥቅም በሚጎዱ እርምጃዎች ላይ የጋራ አቋም መያዝ፣ የመግባቢያ ሰነዱን የሚፈርሙ ፓርቲዎች አባላት
ከመንግስትም ሆነ ከገዥው ፓርቲ የሚደርስባቸውን የተለያዩ ህገወጥ ርምጃ በጋራ መታገል፤ ምርጫን በተመለከተ የጋራ
ስትራቴጂ መቀየስ፤ ፓርቲዎቹ በሚያደርጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ሁሉ በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ወጥነት ያለው አቋም
መያዝና ትግላቸው ለማቀናጀት እንዲችሉ የህዝቡን የአንድነት መንፈስ የሚያጐለብቱ እርምጃዎችን በጋራ መውሰድ፣ አፍራሽ
የመከፋፈል የማጋጨት እርምጃዎችን መከላከል፣ ትብብሩን ወደ ላቀ የፓርቲ አደረጃጀት ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል
የጋራ አቅጣጫ መቀየስ እና ሌሎች አገራዊና ህዝባዊ ነጥቦች ላይ በጋራ ለመስራት ያለሙ ሲሆን ለዚህም አብይ ኮሚቴና
የተግባር ኮሚቴ እንደሚዋቀር ታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሃያ ዘጠኙ ፓርቲዎች አመራር አባላት በካናዳ አገር ከሚገኘው ‹‹ቃሌ የኢትጵያውያን
የውይይት መድረክ›› ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይና የፖለቲካ ሁኔታ ላይ በፓልቶክ ውይይት ያደረጉ ሲሆን መድረኩ
በማቴሪያል፣ በፋይናንስና በዲፕሎማሲ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ሰብሳቢው አስታውቀዋል፡፡ የካናዳው ‹‹ቃሌ
የኢትጵያውያን የውይይት መድረክ›› በምታደርጉት ሰላማዊ ትግል ከጎናችሁ ነን ብሎናል ብለዋል – አቶ አስራት፡፡
መድረኩ ይሄን ስያሜ ለራሱ የሰጠው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር የነበረችውን የወ/ሮ ብርቱካን
ሚደቅሳን ‹‹ቃሌ›› ዝግጅት ለማስታወስ ይሆናል ያሉት አቶ አስራት፤ አንድነት ፓርቲ ከዚህ በፊት በየወሩ “ቃሌ
የጥበብ ምሽት” በሚል የሻማ ማብራትና የውይይት መድረክ ያካሂድ እንደነበርና አሁን ግን ‹‹ቃሌ ምሽት››ን ቀይሮ
‹‹የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ምሽት›› በሚል በየወሩ የሻማ ማብራትና ውይይት እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment