ቅዱስ ሲኖዶስ ያካሄደው ስብሰባ ውጥረት የተሞላበትና የመንግስት ግልጽ ጫና የታየበት መሆኑን የቤተክህነት ምንጮች ገልፁ
ጥር ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
 
 ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሀዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በአዲስ አበባ በትናንትናው እለት ያካሄደው
 ስብሰባ ውጥረት የተሞላበትና የመንግስት ግልጽ ጫና የታየበት መሆኑን የቤተክህነት ምንጮች ገልጸዋል::
 
 መንግስትም አቡነ መርቆሪዎስ መንበራቸው ላይ ተመልሰው ማየት እንደማይፈልግ በአቶ አባይ ጸሀዬ በኩል ግልጽ አቆሙን ያንጸባረቀ በመሆኑ የዕርቁ ጉዳይ ፍጻሜ ላይ መድረሱን ለማወቅ ተችሎል::
 
 በውጭ የሚገኙ አባቶች በዛሬው እለት በሎስ አንጀለስ በጀመሩት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ብጹዕ ወቅዱስ 
አቡነ መርቆሪዎስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ በትላንትናው እለት ከካናዳ ሎስአንጀለስ ገብተዋል::
 
 ትላንት በአዲስ አበባ በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ለተገኙት አባቶች አቶ  አባይ ጸሀዬ በግልጽ 
እንዳስታወቁት አቡነ መርቆሪዮስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ ማለት መንግስቱ ሀይለማሪያም ይመለስ ከማለት ተለይቶ 
አይታይም ማለታቸው ተሰምቶል::
 
 መንግስት  አቡነ መርቆሪዎስ ቢመለሱ ግድ እንደሌለው ነገር ግን ፓትሪያርክ ሆነው ማየት እንደምይፈልግ አቶ አባይ ጸሀዬ አረጋግጠዋል::
 
 ስለሆነም የ 6 ኛውን የፓትርያርክ ምርጫ ሂደት እንዲያፋጥኑ እንዳሳሰቦቸውም መረዳት ተችሎል::
 
 አንዳንድ ከመንግስት ጋር የሚሰሩ ጳጳሳት በተለይም ብጹዕ አቡነ መቃሪዮስ አቡነ መርቆሪዮስ የሚመለሱ ከሆነ እኛም 
አክሱም ላይ የራሳችን ሲኖዶስ እናቆቁማለን በማለት ቤተክርስቲያኒቱን በግልጽ በዘር መስመር ለማስቀመጥ ሀሳብ 
መሰንዘራቸውን የተገኘው ዜና ያብራራል::
 
 ዕርቁን የሚደግፉና አቡነ መርቆሪዎስን በመንበር ማየት 
የሚፈልጉ ጳጳሳት ቁጥር እየጨመረ የመጣ ቢሆንም መንግስት አቆሙን በግልጽ ማስቀመጡን ተከትሎ የመንግስት  ፍላጎት 
ባገናዘበ መልኩ ስብሰባው እንዲጠናቀቅ እየተጠበቀ ነው::
 
 
 
          
      
 
  
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
No comments:
Post a Comment