Friday, 12 April 2013

የብርሃኑ ደቦጭ የምኞት ትችት

ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም

(ልዕልና ጋዜጣ)
የብርሃኑ ደቦጭ የምኞት ትችት
ብርሃኑ ደቦጭ (የታሪክ ተመራማሪ) ስለመክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ ለመተቸት ተነሣና እሱን ሲያጉላላው የቆየውን ነገር ሁሉ ጻፈ፤ እንዲያውም ገና ሲጀምር ስለመክሸፍ ያለበትን ሁሉ አልነካውም በማለት ይናገራል፤ መጽሐፉ ስለመክሸፍ ነው፤ ብርሃኑ ደቦጭ የመክሸፍን ነገር አይወደውም ይመስለኛል፤ ስለዚህ ለምን አልተወውም? መጽሐፉን ትቶ ወደኔ! እኔን ሲደቁሰኝ ቢውል እንደመክሸፍ አልጠጥርበትም! እንግሊዝኛን በአማርኛ ፊደል መጻፍ የሚችል መሆኑን አወቅሁለት።


መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክን ብርሃኑ ደቦጭ የተጠቀመበት በአእምሮው ውስጥ መውጫ አጥተው ሲጉላሉ የነበሩ ሌሎች በጭራሽ ያልተያያዙ ቅንጭብጫቢዎችን ለመዘርገፊያ አጋጣሚ ማግኘቱ ይመስላል፤ የጠቃቀሳቸውንም ነገሮች ፍሬ-ነገራቸውን አልነገረንም፤ በዚህ ዓይነት ጽሑፍም ሊነግረን አይችልም፤ ፍሬ-ነገሩን ሊነግረን ያልቻለውን ነገር እያነሣ ማለፍ ብቻ እውቀትን አይጨምርም፤ እንዲያውም የአስመሳይነት ስሐተት ውስጥ ይከታል፤ ለምሳሌ እኔን ‹‹በማርክሲስት የሚያስፈርጀውን ገጽታ ይላበሱና …›› ይላል፤ አሁን ይህ ለምን ያገለግላል? ከየት አምጥቶ ነው የሚለጥፍብኝ? ተልእኮው ያነጣጠረው በመጽሐፉ ላይ እንዳልሆነ የሚያሳዩ ብዙ እንደዚህ ዓይነት ምልክቶች አሉ፤ ይኸው ይበቃኛል።

1. የደርግ የጽሑፍ ተቆጣጣሪ (በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና በለንደን ታሪክ የተማረ የታሪክ ተመራማሪ ካድሬ ነበር) አሁን ለትችት በቀረበውና ባልተተቸው መጽሐፍ ረቂቅ ላይ ‹‹የቷ ኢትዮጵያ? የማን ኢትዮጵያ?…) እያለ ጽፎ እንዳይታተም ከለከለ፤ ዛሬ ደግሞ ብርሃኑ ደቦጭ መጽሐፉ ከታተመ በኋላ ‹‹የመስፍን ኢትዮጵያ›› ብሎ ለጠፈባት! ‹‹በመጽሐፉ ከተነሡት ጉዳዮች የክሽፈት ታሪክ ስለተባሉት ጉዳዮች፣ የአርበኞችና የባንዳ ሚና ታሪክ አዘጋገብ እና የአድዋ-ማይጨው-ጅጅጋ ትርክት በዚህ አስተያት ያልተካተቱ መሆናቸውን ከወዲሁ መግለጽ እወዳለሁ፤..›› ያልተመቸውን እየተወና የፈለገውን እየለወጠና እያጎበጠ ስለመጽሐፉ መተቸት ምን የሚሉት አዲስ ፈሊጥ ነው?

2. እንደተማረው የተለያዩ የርእዮተ-ዓለማዊ አመለካከቶችን ስሞች ጠቅሶ የእኔ መጽሐፍ አንዱም ውስጥ አልገባልህም ስላለው አልተመቸውም።

3. ከክብረ ነገሥት የተጠቀሰው ብርሃኑ ደቦጭን አላስደሰተውም፤ ምናልባትም ጊዜው ያለፈበት ብሎ ይሆናል፤ ጊዜ ስላለፈባቸው መጻሕፍት በሌላም ቦታ ተናግሮአል፤ የመስፍን አዲሱ መንገድ ‹‹በብዙ መልኩ ጊዜ ያለፈባቸው መጻሕፍት›› መጥቀስ ነው ይላል፤ መጻሕፍት፣ በተለይም የታሪክ ፍልስፍና መጻሕፍት ጊዜ የሚያልፍባቸው እንዴት ነው? የብርሃኑ ቸግር ስለሁነት ያነበበውን ስለአስተሳሰብ፣ ስለአመለካከት ያደርገዋል፤ ምናልባት በፊዚክስ ጊዜው ያለፈ መጽሐፍ ሊኖር ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን የቶይንቢ ‹‹የታሪክ ጥናት›› የተሰኙትና ሌሎችም ጊዜያቸው መቼም አያልፍም፤ የመጻሕፍትን ባሕርይና ዋጋ ለፈተና ከመጥቀማቸው ውጭ ማየት ካልተቻለ የብርሃኑ አመለካከት በዓለም ያሉ ቤተ መጻሕፍትን ያራቁታል፤ በኋላ የተነገረው የተሻለ የሚባልበት ሁኔታ ስላለ በኋላ የተነገረው ሁሉ የተሻለ ነው ማለት አጉል አስተሳሰብ፣ ወይም በብርሃኑ ቋንቋ ‹‹ፋውል›› ነው።

4. ‹‹የአንድ አገር ታሪክን ለማጥናት የአገር ተወላጅነትን ግድ የሚያደርግ›› ይህ አስተሳሰብ የኔ አይደለም፤ እሱ ለራሱ ዓላማ የደነቀረው ነው፤ እኔ ያልሁት ‹‹…ባዕድ የሆነው የሌላ ሕዝብ ታሪክን ሲጽፍ ሁለት ምክንያቶች አሉት፤ አንዱ ለእንጀራ ነው፤ ሁለተኛው የእውቀት ፍላጎት ነው፡›› የቱ ላይ ነው ብርሃኑ ‹‹ግድ›› የሚለውን ያነበበው? ብርሃኑ ታሪክን የሚያጠናው ለእንጀራ ብቻ መሆኑን ሳይናገር አስረዳን! እኔ ያልሁት ‹‹የውጭ ሊቃውንቱ ጥናት ልዩ ጥቅም ቢኖረውም ባይኖረውም ለራሳቸው ሲሉ የሚያደርጉትን ጥናት በጭራሽ ልንቃወም አንችልም፤ የምንቃወመው እነሱ እኛን እነሱ እንደፈለጉ አድርገው ሊቀርጹን የሚያደርጉትን ሙከራ ነው፤ እኛም እንደጥቁር ሰሌዳ የእነሱን ነጭ ጠመኔ የባሕርይ አድርገን መቀበላችንን ነው፡፡›› ብርሃኑ ደቦጭ ይህንን የመቃወም መብት አለው፤ የራሳችን ሰዎች ብቻ መጻፍ ግዴታ ነው አላልኩም፤ ብርሃኑም እንኳን ይህንን አይልም፡፡ እንደገናም ‹‹ታሪክን ማጥናት የሚገባው የአገር ተወላጅ ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰባቸው …›› ይላል፤ ይህንን ሐረግ በእኔ መጽሐፍ ውስጥ ላገኘ ሰው አምስት መቶ ብር እሰጣለሁ፤ የምሬን ነው! ብርሃኑ የራሱን እምነት ለማራመድ እኔን ምክንያት ያደርጋል፤ በብርሃኑ አመለካከት አንድ ስዊድናዊ ስለኢትዮጵያ ሲጽፍና ሌላው ከአንደኛው የኢትዮጵያ ጎሣ ሲጽፍ ያው ነው፤ ይህ የእሱ አመለካከት ይሆናል፤ እኔ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ጎሣዎችን ሁሉ አንድ አድርጎ የሚያመሳስላቸውና ከስዊድናዊው ወይም ከሌላው የውጭ አገር ሰው የሚለያቸው ነገር አለ ብዬ አምናለሁ፤ ይህ ለእኔ ይታየኛል፤ ለብርሃኑ አይታየውም፤ ልዩነታችን ነው።

5. በጽሑፉ መጨረሻ ላይ ብርሃኑ ንዴቱ እየባሰበት ሄዶ ከመጽሐፉ ወጣ፤ ከመጽሐፉ ትችት ተሰናበተና ወደዘለፋ ገባ፤ ምክንያቱ አልገባኝም፤ ተለውጦአል ይለኛል፤ ለውጡን አይናገርም፤ የማያስፈልግ ሙግት፣ ከዚያም ከዚህም እየቀነጫጨበ የሚማታበት ልምጭ ይሰበስባል፤ አንዱ ስለታደሰ ታምራት የጥናት ዘመን (1270-1527) የሳትሁ አስመስሎ ወደዘለፋ የገባበት ነው፤ በትክክልና በቀና መንፈስ ላነበበ የሚከተለውን ብያለሁ፤– ‹‹ምንም እንኳን የታደሰ መጽሐፍ የጊዜ ገደቡ ቢያበቃም በመጨረሻው ምዕራፍ አጼ ምኒልክን ከአጼ ዓምደ ጽዮን ጋር በማመሳሰል በአሥራ አራተኛው ምዕተ-ዓመት ዓምደ ጽዮን ‹ክርስቲያን ኢትዮጵያን‹ እንዳስፋፋ ሁሉ ሁሉ አጼ ምኒልክም ይህንን የመስፋፋት ተግባር ፈጸሙ ፤ … ፕሮፌሰር ታደሰ ከግራኝ ወረራ ቀደም ብሎ ዝርዝር የታሪክ ጥናቱን ከአቆመ በኋላ፣ አራት መቶ ሃምሳ ዓመት ያህል ጭው ባለ ዝምታ ዘሎ ወደአጼ ምኒልክ ዘመን ተስፈንጥሮ ይገባል፤ ይህንን ጭው ያለ የአራት መቶ ሃምሳ ዐመት የጊዜ ገደል አልተሻገረውም፤ ለዚህ ዋናው ምክንያት ታደሰ መስፋፋት በሚል ርእስ የጻፈውን ሁሉ የሚያስተባብልበት ታሪክ የሚገኘው በዝምታ ሊዘልለው በሞከረው አራት መቶ ሃምሳ ዓመት ውስጥና …›› ብርሃኑ ደቦጭም እዚያ ገደል ውስጥ ሆኖ ነው ዘለፋውን የሚያሰማው! አንድ ዓረፍተ ነገር ይዞ ለነቀፋ ከመቸኮል ሁሉም አንብቦ መገንዘብ የተሻለ ክብርን ያመጣል።

6. ሌሎች ከባድ ከባድ የሆኑ የአገር ጉዳዮች በብርሃኑ ጽሑፎች ውስጥ አሉ፤ እነዚህ ውስጥ አልገባም፤ ዋናው ምክንያቴም ብርሃኑ እንዳለው ‹‹የመስፍን ኢትዮጵያ›› የሌሎቹ በተለይ የወጣቶቹም ካልሆነች እኔን ከሌላው ይበልጥ አይነካኝም፤ ብርሃኑ ደቦጭ ከማን ጋር ተማክሮ እንደሆነ የመጨረሻ ጥይት የሚል ውሳኔ ላይ የደረሰው አላውቅም፤ መገመት ቢችል ዝናሬ ገና ሙሉ ነው! ያለጥርጥር የብርሃኑ ደቦጭ ጽሑፍ ያነጣጠረው መጽሐፌ ላይ ሳይሆን እኔ ላይ ነው፤ ምክንያቱን አላውቅም፤ ስለዮሐንስና ስለምኒልክ ባለው ውዝግብ እኔን ወደምኒልክ ገፍቶ ከዮሐንስ ሊያርቀኝ ይሞክራል።

7. የታሪክ ተመራማሪው ብርሃኑ ደቦጭ ርእሱን ብቻ ያመለከተውን የመጽሐፉን እምቡጥ አልነካውም፤ ወይ ደስ አላለውም፤ ወይ ግራ ገብቶታል፤ እንዲህ ያለ የመጽሐፍ ትችት አይቼም አላውቅም፤ በግድ መጻፍ አለብህ ካልተባለ በቀር ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ የሚባልለት ጽሑፍ ነው፤ ባይጽፈው ይሻለው ነበር፤ ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ክፉኛ ይወርዳል።

No comments:

Post a Comment