Saturday, 13 April 2013

ምርጫ እናካሂዳለን ሲሉ ሰማሁ ልበል? (አቡ ዘኪያ)

አቡ ዘኪያ
ከምድረ-አናቶሊያ

ምርጫማ ጥሩ ነው!
ምርጫማ ጥሩ ነው ጥሩ ነው ምርጫማ
“ድምፃችን ተሰርቋል” ካላላችሁማ!
ከቶ የት ይገኛል ምርጫን የመሰለ
ከውስጥም ከውጭም ታዛቢ ከሌለ
ተቃዋሚ ፓርቲ ጠፍቶልን ከአገሩ
ቢሆን “ጽቡቅ” ነበር ምርጫ በየወሩ!
ምርጫኮ ጥሩ ነው ክብሩ የገነነ
የምርጫ አስፈፃሚው የራስ ሰው ከሆነ!
እንደ ምርጫ አስደሳች የት ይገኛል እስቲ
በተለይ ከሌለ ተቃዋሚ ፓርቲ!!
 
“ከፀሐይ በታች” ከተሰኘው የሰለሞን ሞገስ የግጥም መድብል የተወሰደ
“ከሰው መርጦ ለሹመት ከእንጨት መርጦ ለታቦት”እንዲሉ ይሆነኛል ያሉትን ግለሰብ መርጦ ለሹመት ማብቃት በአፍሪካ የፖለቲካ ሕይወት ዉስጥ ነባር ባህል ነው::”አንድ ሰው አይፈርድም አንድ እንጨት አይነድም”የምትለዋ ብሒለ አበውም ዘመናትን ያስረጀች ነባሩንና አባት አደሩን የጋራ አመራር ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህላችንን ጠቋሚ አፍሪካዊ የፖለቲካ ፍልስፍና ነች::ለአብነት የአምሐራዎችን ሸንጎ የትግሬዎችን ባይቶ የኦሮሞ ጌድኦና ኮንሶዎችን የገዳ ስርዓት ያስታውሷል::

ሃያኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካ ስር-ነቀል ታሪካዊ ክስተቶችን ያስተናገደችበት ዘመን ነበር::መሰረታዊ የፖለቲካ ባህል ለውጥ አንዱና ቀንደኛው ስር-ነቀል ታሪካዊ ክስተት ነበር:: በስምምነት ላይ የተመሰረተው ባህላዊ አፍሪካዊ የመንግሥት ስርዓት(Traditional African Government by Agreement) ስፍራውን ለአውሮፓ በቀሉ ፉክክር ተኮር የፖለቲካ ስርዓት (Government by Competition) ለመልቀቅ የተገደደበት ዘመን ነበር ሃያኛው ክፍለ ዘመን:: የዛፍ ስር ስብሰባ በፓርላማ አባ ገዳዎች አባ
ዱላዎችና የጎበዝ አለቆች በሚኒስትሮችና ኮማንደሮች የቃል ሕግ በጽሁፍ ሕግ(ሕገ መንግሥት)ወዘተ ተተኩ::

ለሀገራችን ኢትዮጵያ የዘመኑን አውሮፓዊ የፖለቲካ ፋሽን መከተል የውዴታ ግዴታ ነበር::  የኢትዮጵያ “የስልጣኔ” አባት ተብለው የሚጠሩት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ነበሩ በሕይወታቸው የመጨረሻ ዓመታት ባንዱ የመጀመሪያውን ካቢኔ በመመስረት ኢትዮጵያን ከአውሮፓዊው የፖሊቲካ ስርዓት ጋር ያስተዋወቋት:: የአፄ ምኒሊክን አልጋ ወራሽ በመፈንቅለ መንግሥት አስወግደው አልጋ ወራሽ የሆኑት ራስ ተፈሪ መኮንን በ1911 ጃን ሜዳ ላይ መሀል ሰፋሪ በተሰኘው የቤተ መንግሥት ጦር በመታገዝ አስራ ሁለት አጋንንት ሆነው ተገኙ ያሏቸውን በአፄ ምኒሊክ የተሾሙትን አስራ ሁለት ሚኒስትሮች በማስወገድ የመጀመሪያውን የዘውድ ምክር ቤት ራሳቸው በመረጧቸው መኳንንት አባላት አቋቋሙ:: ምርጫና መረጣ ምክር ቤት፤ መካሪና አማካሪ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት ዉስጥ በገሀድ ብቅ ማለት ጀመሩ::

ሐምሌ 9 ቀን 1923 የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ታወጀ:: በቀጣዩ ዓመትም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤትና የሕግ መምሪያ ምክር ቤት ተብለው የተሰየሙ ሁለት ምክር ቤቶች ያሉት ፓርላማ (bicameral parliament)ተመሰረተ:: ‹‹ሕዝቡ ራሱ መምረጥ እስከሚችል ድረስ የምክር ቤቶቹ አባላት በንጉሡና በመኳንንቱ ይመረጣሉ›› በሚለው ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ መሰረትም የሁለቱም ምክር ቤቶች አባላት የተመረጡት በንጉሠ ነገሥቱ ነበር::

በፋሽስት ኢጣሊያ ወራራ ሳቢያ የመበተን እጣ የገጠመው የመጀመሪያው ፓርላማ ለዳግም ትንሳዔ የበቃው በ1935 ነበር:: ሁለተኛው ፓርላማ እንደፊትኛው ሁሉ ባለ ሁለትዮሽ ምክር ቤት ነበር:: የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላትም በንጉሠ ነገሥቱ ይሁንታ የተመረጡ ነበሩ:: በሁለቱ ፓርላማዎች መካከል የነበረው መለስተኛ ልዩነት ከቀድሞው በተለየ መልኩ የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላት በንጉሠ ነገሥቱ ሳሆን በሀገር ሽማግሌዎች የተመረጡ ባላባቶች መሆናቸው ነበር:: የሁለቱ ምክር ቤት አባላትም ለአስራ አምስት ተከታታይ ዓመታት በአባልነት ቆይተዋል::

በሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ተጽዕኖ ሳቢያ ንጉሠ ነገሥቱ ነባሩን ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ተገደዱ:: በ1948 ተሻሽሎ በወጣው ሕገ መንግሥት መሰረትም ሕዝቡ በየአራት ዓመቱ እንደራሴዎቹን ራሱ የመምረጥ መብት እንዳለው ተደነገገ:: ያን ድንጋጌ ተከትሎም ከ1948 እስክ የካቲት 1966 ሕዝባዊ አብዮት ድረስ ባሉት ዓመታት አምስት የፓርላማ ምርጫዎች ተካሂደዋል::

መስከረም 2 ቀን 1967 ንጉሠ ነገሥቱን ከዙፋን አውርዶ ስልጣን ላይ የወጣው ወታደራዊ ጁንታ ፓርላማውን በትኖ በምትኩ ከተለያዩ የሠራዊቱ ክፍሎችና መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ 60 ግለሰቦችን ያቀፈ ከአንድ ዓመት በላይ በሕይወት ያልቆየ አንድ የመማክርት ጉባዔ መሰረተ:: ከመማክርት ጉባዔው ፍጻሜ በኋላ ለአስራ አንድ ዓመታት ያለ አንዳች ምክር ቤትና ሕገ መንግሥት ሀገሪቱን የመሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም የስልጣን እድሜ ፀሐያቸው እያሽቆለቆለች ባለችበት ወቅት ሕገ መንግሥት ቢጤና በኢሰፓዎች ጠቋሚነትና አስመራጭነት የተመረጡ 835 አባላት ያሉት አንድ ግብዳ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰኘ ምክር ቤት እንካችሁ ማለታቸው ይታወሳል::

ግብዳው ብሔራዊ ሸንጎ “የሕዝብ” ብሶት በወለዳቸው ከሲታ ብሶታዊያን ከተበተነ ሁለት አሰርት አለፈው:: ከደርግ ውድቀት ወዲህ አራት አወዛጋቢና አስተዛዛቢ ብሔራዊና የአካባቢ ምርጫዎች ተከናውነዋል:: እነሆ አሁን ደግሞ አምስተኛውን የአካባቢና የአዲስ አበባ መስተዳድር ምርጫ ለማካሄድ በዋዜማ ላይ እንደሚገኙ ከወደ ገዥዎቻችን መንደር ሰማን::
የአካባቢ ምርጫ እንደ ዋነኛው ብሔራዊ ምርጫ በቀጥታ ለመንግሥት ስልጣን ባያበቃም ቅሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብን የልብ ትርታ የሚያዳምጡበትና ወደ ቤተ መንግሥት ለሚያደርጉት ጉዞ ስንቅ የሚሸምቱበት የፖለቲካ ገበያ ነው:: ይሁን እንጅ ባለፉት አራት የአካባቢ ምርጫዎች እንዳደረጉት ሁሉ ዋነኛ ተቃዋሚዎች አሁንም ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን ይፋ አድርገዋል:: ምክኒያቱም ግልጽና ግልጽ ነው:: የሀገርና ሕዝብ ኃብት በተለይም የመገናኛ ብዙኃን ከዓመት እስከ ዓመት የገዥው ፓርቲ ፕሮፓጋንዳ ማሰራጫና የምርጫ ማስፈጸሚያ በሆኑባት፣ገልተኛ የምርጫ ቦርድ በሌለባት፣ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ወንጀል በሆነባት፣ መራጮች በገዥው ኃይል ካድሬዎች በሚዋከቡባት፣ የምግብ ለስራ ፕሮግራም ወደ ምግብ ለምርጫ ፕሮጀክትነት በተቀየረባት ባጭሩ የፖለቲካ ምህዳሩ በጠበበባትና የምርጫ ውድድር ሜዳው ወጣ ገባ በሆነባት ሀገር ዉስጥ ነጻ ፍትሃዊና እንከን አልባ ምርጫ ማድረግ ስለማይታለም ነው::

ከላይ ባጭሩ ለማሳየት እንደተሞከረው ባለፉት 81 ዓመታት ሀገራችን በርካታ ምርጫዎችን አስተናግዳለች:: እንዳለመታደል ሆኖ አንዳቸውም ነጻ ፍትሃዊና እንከን አልባ አልነበሩም:: ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረው የሕዝባችን የነጻ ፍትሃዊና እንከን አልባ ምርጫ ጥያቄ እስከ አሁን ምላሽ አላገኘም:: ሕዝባችን ነጻ ፍትሃዊና እንከን አልባ ምርጫ ይሻል:: በነጻ ፍትሃዊና እንከን አልባ ምርጫ ብቻና ብቻ ነው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው:: ነገር ግን እንዴት ነው ለውጥ በሌለበት ነጻ ፍትሃዊና እንከን አልባ ምርጫ የምናየው? እንዴትስ ነው ነጻ ፍትሃዊና እንከን አልባ ምርጫ በሌለበት ለውጥ የምናየው? ማየት የምንፈልገውን ዓይነት ምርጫ ለማካሄድ ለውጥ ያስፈልገናል:: '

ነገር ግን አሁን በሀገራችን ዉስጥ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለውጥን ማየት የማይታሰብ ነው:: አሁን በሀገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሳይለወጥም ምንም ዓይነት ነጻ ፍትሃዊና እንከን አልባ ምርጫ ማድረግ አይታለምም:: ያለ ነጻ ፍትሃዊና እንከን አልባ ምርጫም ሰላማዊ ለውጥ አይታሰብም:: በመሆኑም ስልጣን ለባለቤቱ ማለትም ለሕዝቡ እስኪመለስ ድረስ መታገል የግድ ነው:: ከሰላምዊ የትግል ስልቶች አንዱም በእሁዱ ምርጫ መሰል ልግጫ በመራጭነትም ሆነ በተመራጭነት ከመካፈል ራስን ማግለል ነው::
በሰለሞን ሞገስ ዉብ ስንኞች የጀመርኳትን ጦማሬን ከወራት በፊት ይህን ምርጫ አስመልክተው የደሴ ሙስሊሞች የገጣጠሟት ነች ተብላ በፌስ ቡክ በተሰራጨች አጠር ያለች ግጥም ልቋጭ:-

እኛ የለንበትም…
አንመዘገብም
አንወጣም አንመርጥም
ኢሕአዴግና ደርግ
ደርግና ኢሕአዴግ
አህያና ፈረስ፤ፈረስና በቅሎ
ቀልቀሎ ስልቻ፤ ስልቻ ቀልቀሎ
ሁሉም የጋማ ከብት ማን ከማን ተሽሎ
መምረጥስ ማየትን “ማየት”ዝም ብሎ!
ማን ነበር “ዝምታ ከጩኸት በላይ ይሰማል”ያለው?
መዓ ሰላማህ!

No comments:

Post a Comment