ነብር… መንግስት… አቤ ቶክቻው!!
ሰሞኑን "ከሀገራችን ውጡ" ተብለው ከሀገራቸው እና ከቤታቸው የተባረሩ ሰዎችን ጉዳይ ሳስብ፤ መንግስታችን አስሮ
የሚያንገላታቸውን ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች ጉዳይ ሳስብ፤ በየቀኑ ባህር አቋርጠው የሚሰደዱ ወግኖቻችንን ሳስብ…
ሳስብ ሳስብ ሳስብ… በዛን ሰሞን ወዳጃችን ሰለሞን ሞገስ ያወጋን ጨዋታ ትዝ አለችኝ፤ እንደሚከተለው ትቀርባለች፤
በአንድ ወቅት በቻይና ውስጥ እንዲህ ሆነ አሉ፤
ሴትዮዋ በአንድ ጫካ ጥጋት ላይ ከሁለት ጨቅላ ልጆቿ ጋር ቁጭ ብላ እየዬ እያለች ታለቅሳለች፡፡ በአካባቢዋ አንድም
ሰው አልነበረም፡፡ ልቅሶዋ እጅግ በበረታ ጊዜ ግን አገር አቋርጦ የሚያልፍ አንድ መኪና ድንገት አጠገቧ ቆመ እና
ከውስጡ ሰዎች ወረዱ፡፡ እዚህ ቦታ ሰው ይኖራል ብለው አላሰቡም ነበርና ሰው ማየታቸው ሲያስገርማቸው፤ የእናቲቱ
ለቅሶዋ ደግሞ እጅግ አስጨነቃቸው፡፡
"ምን ሆነሽ ነው እዚህ ብቻሽን ተኮራምተሸ የምታለቅሺው…" አሏት፡፡
ጭራሽ ሀዘኗ በረታ! የሆነችውንም ዘርዝራ ስትነግራቸው እየተንሰቀሰቀች ነበር፡፡
"የጫካ ነብር ባሌን በላብኝ፤ የእርሱ ሀዘን ከልቤ ሳይወጣ ትልቁ ልጄን አሁን ነጠቀኝ አሁንም ትንሽ ቆይቶ መምጣቱ አይቀርም…" ስትል ተንሰቀሰቀች፡፡
ነገሩ በጣም ያስጨነቃቸው መንገደኞች፤ "ታድያ እዚህ ቁጭ ብላችሁ ሞታችሁን ከምትጠባበቁ ለምን ወደ ከተማ አትወጡም…?" አሏት፡፡
እርሷም፤ "ከተማማ መንግስት አለ!" አለቻቸው፡፡
ከነብር ይበልጥ ተናካሽ እና ተንኳሽ ከሆነ መንግስት ይሰውረን፡፡
No comments:
Post a Comment