Sunday, 17 March 2013

ሰንበት ምሳ፤ እንደ እድገቱ፤ ቢቀንስ እብደቱ… ! አቤ ቶክቻው

ማሳሰቢያ 1፤ ይህ ጨዋታ ባለፈው አርብ ለታተመችው ለልዕልና ጋዜጣ ታስቦ የተሰናዳ ነው!
ማሳሰቢያ 2፤ ፎቶግራፉን እንደው ባዶውን ከሚሆን ብዬ ያደረግሁት ነው…!
እንደምን ከረማችሁ ወዳጆች፤ ወዳጅ ያልሆናችሁም ጭምር እንዴት ናችሁ…! ለሁላችሁም ደህንነቱን እመኛለሁ፡፡ 
 
 ደህንነቱ ብል ግዜ ምን ትዝ አለኝ… መንግስታችን የየቤተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ፤ ለእያንዳንዳችን የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛ እና የደህንነት ሰራተኛ መድቦልናል የሚባለው ነገር እንዴት ነው…! አረ እንደው በስንቱ ነገር ተቸግሮ ይችለዋል… አሁንስ ይሄ መንግስት አንጀቴን በላው! የምሬን እኮ ነው አሁን ዘግይቶ በደረሰኝ ዜና እኮ የመስሪያ ቤታችን የበላይ ሃላፊዎች የሰዓት እና የስራ ብቻ ሳይሆን የት ገባህ የት ወጣህ የሚለውንም የሚቆጣጠሩ ደህንነቶቻችን መሆናቸውን እየሰማን ነው! ታድያ እንዲህ ሲያደርግ መንግስታችን ስለኛ “ከሚገባን በላይ፤ ከሚችለውም በላይ” መጨነቁን አያሳይም ትላላችሁ…  ቆይ እስቲ በዚህ ጉዳይ ላይ ሌላ ቀን እንመለስበት ይሆናል…
ለማንኛውም እነሆ ደግሞ በልዕልና ተከሰትን፤ በአንዱ ሲዘጋ በአንዱ መከሰት በመቻላችን የላይኛውን ገለታ ይግባህ ብለን እናመሰግናለን፡፡

እኔ የምለው ያቺ ለዘመናት ስንመካባት የነበረች 11.2 በመቶ ዕድገት እንደዋዛ አሽቆልቁላ 8.5 በመቶ ላይ ደረሰች አይደል እንዴ! መቼም እኛ ከሀገር ከወጣን በኋላ እና አቶ መለስ “ከተሰዉ” በኋላ ያልመጣ ለውጥ የለም፡፡
እውነቱን ለመናገር በዛን ሰሞን ዕድገቷ ከ11.2 በመቶ አልንቀሳቀስ ብላ ሳይ አንዳንድ ግዜ ሰዎቻቸን ከላያቸው ላይ ያጣበቋት በኮላ ይሆንን! ወይስ በባለቆቡ ሚስማር ከገላቸው ተመታለች… ያሰኘኝ ነበር፡፡ ከአናፂ ግምት ወጣ ስል ደግሞ በማይለቀው ንቅሳት (“ታቱ”) ተነቅሰዋት ይሆን ብለንም አስበን ነበር፡፡

ትዝ ይልዎ እንደሆነ ወዳጄ ለበርካታ አመታት የኢኮኖሚ እድገት ሲባል 11.2 በመቶ የሚል ቁጥር ግዴታ ይመስል ነበር፡፡ ደሞ ከሁሉ የሚገርመው ኢኮኖሚ እድገት እየተባለ መነገር በተጀመረ ግዜ የመጣው የኖሮ ውድነት የትም አይተነው አናውቅም ነበር፡፡ ያኔ አይደል እንዴ ታድያ ለአምላካችን እባክህን ጌታዬ የኢኮኖሚ እድገቱ ከፍ እንዳይል አንተ ጠብቅልን ብለን ስዕለት የተሳልነው…! ታድያስ…  እሱ አያልቅበት ስንቱን ነገር የሰማን ነውና ይህንንም እነሆ ሰማን፡፡ እናም “ዝቅ አለልን ዝቅ አለልን…” ብለን ዘመርን፡፡ ምክንያቱም ከፍ ባለ ግዜ ያመጣብንን ጦስ እናወቀዋለንና!

አንድ ወዳጃችን ልብ ብሎ ልብ እንዳስባለን፤ መንግስታችን የኢኮኖሚ እድገቱ ሲቀንስም ሲጨምርም የሚናገረው በኩራት ነው፡፡ አንድ ሰሞን ተቃዋሚዎች፤ “ይሄ እድገት የምትሉትን ነገር አለቅጥ እንጨምራለን ብላችሁ ህዝቡ በኑሮ ውድነት ሊያልቅ ነው… ታድያ እድገቱ ለማነው…” ብለው ቢጠይቁ፤ “ጫማ ጠበበን ብለን እግራችንን አንቆርጥም የፈለገ የዋጋ ንረት ቢመጣም የኢኮኖሚ እድገታችንን አንገታም…” እያሉ ሲንገታገቱ የነበሩት ባለስልጣናት አሁን ደግሞ “የኢኮኖሚ እድገት በመቀነሳችን የዋጋ ንረቱን ቀንሰነዋል እናም ህዝቤ ሆይ ደስ ይበልህ…!” እያሉን ነው፡፡ እንግዲህ በፊት የተነገረን ትክክል ከነበረ አሁን “እግራችሁን ስለቆረጥንላችሁ ደስ ይበላችሁ!” እንደማለት ነው ማለት ነው፡፡

እኔ እና ከእኔም በላይ የገዢው ፓርቲ ድርጊት ከጭፈራ ፓርቲ እኩል ደስ የሚያሰኘን ግለሰቦች ኢህአዴግዬ ሱፍ ገበርዲን ሲለብስም ራቁቱን ሲሄድም አንዴ አድናቂዎች ሆነን ተፈጥረናልና እያደረቀንም እናደንቀዋለን!
አረ ወዳጄ የኢኮኖሚ እድገቱ ሲቀንስ የአስተዳደር እብደቱ ደግሞ ብሶበታል የሚባለው ነገር እንዴት ነው… መቼም ከላይ እንዳልኩዎ… እኛ ከወጣን እና እርሳቸው “ከተሰዉ” በኋላ ያልመጣ ነገር የለም፡፡ እውነት ግን ብዙዎቹ ነገሮች “መለስ ተመለስ” የሚያሰኙ እየሆኑ ነውኮ፡፡

ከወደ መቀሌ ከሚሰማው የህውሃት መሰነጣጠቅ ወሬ ጀምሮ እስከ … አዲሳባው የጋዜጦች ህትመት ክልከላ ድረስ አቶ መለስ በስንት ጣዕማቸው… ያሰኛል፡፡ ለነገሩ የህውሃቱ መሰነጣጠቅ እንኳ የተለመደ ነው፡፡ እርሳቸውም እያሉ አይናቸው እያየ ቃ…ቃ…ቃ… ብሎ ሲሰነጠቅ እኛም ሰምተናል፡፡
አረ ከመስማትም አልፈን ከአሁን አሁን ምን ይፈጠር ይሆን… ብለን ስንጨነቅ ነበር የሰነበትነው፡፡ በተለይ ነፍሳቸውን እሱ እንደፈቀደ ያድርጋትና እርሳቸውን ክፉ ይነካብን ይሆን… ብለን አጥብቀን ስናስብ ነበር፡፡

ታድያ ያኔ ፀቡ የተነሳው ባድመ የእኛ ናት አይደለችም፡፡ በሚል እንደነበር ውስጥ አዋቂዎች ሹክ ብለውናል፡፡ በውጤቱም “እንኳንስ ባድመ አሰብንም እንከራከራለን” ያሉት እነ አቶ ገብሩ አስራት እና እነ አቶ ስዬ በኪራይ ሰብሳቢነት ሲገመገሙ፤ እነ አቶ መለስ ግን በፓርቲ ሰብሳቢነት ቀጥለው ነበር፡፡
ለማንኛውም አሁንም የህውሃት ሰዎች እየተጨቃጨቁ ብቻ ሳሆን እየተቦጫጨቁ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ ይሄንን ጉዳይ የሰሙ አንዳንድ አዛኝ ቅቤ አንጓቾች “አይዟችሁ በዚሁ ቀጥሉበት…” እያሉ ማበረታቻ እየሰጡ ነው፡፡ አሁን ቡድን ለይተው በልምምድ ላይ ያሉት የህውሃት ሰዎች ልምምዳቸውን ጨርሰው ፍልሚያውን አከናውነው አንዳቸው አንዳቸውን ድባቅ ከመቱ በኋላ የሚሰጠው መግለጫ ነው የናፈቀኝ፡፡ “የታላቁ መሪን ራዕይ ለማሳካት ስንል ተሰነጣጠቅናል!”

ባለፈው ግዜ አንድ ወዳጄ በእኔ ስም አንዲት ቀልድ ለወዳጆቹ ነገራቸውና ቀልዷ ዞራ ዞራ እኔው ዘንድ ደረሰች፡፡ ከዛ በጣም ሳቅሁ፡፡ መሳቄን የተመለከተ ሌላ ወዳጄ “እንዴ በራስህ ቀልድ እንደ አዲስ ትስቃለህ እንዴ…” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም አረ እኔ እንዲህ አይነት ቀልድ አላውቅም፡፡ ብል ግዜ በእኔ አሳብቦ ያወራው ወዳጄ ጋር አገጣጠመኝ እኔም …መቼ ነው ይሄንን ቀልድ ያወራሁት መቼም ሞቅ ሲለኝ የምለውን አላውቀውም ሞቅ ብሎኝ ነበር እንዴ… ብዬ መጠየቅ፤ ወዳጄም “እስቲ ተወኝ አለቃ ገብረሃና ያንን ሁሉ ቀልድ እርሳቸው አውርተውት መሰለህ እንዴ በእርሳቸው ስም የሚነገረው…” ብሎ ጥያቄዬን በጥያቄ መለሰልኝ፡፡ ከቀልዱ ይበልጥ ይሄኛው አሳቀኝ፡፡

እና ታድያ አቶ መለስም የእርሳቸውን ራዕይ ለማስቀጠል ተብሎ እተወሰደ ያለውን እርምጃ እና እርግጫ ቢመለከቱ ሙት አይስቅም እንጂ ከት ብለው የሚስቁ ነው የሚመስለኝ፡፡
ልብ አድርጉልኝ ፍትህ ጋዜጣ ላይ እና ፍኖተ ነፃነት ላይ እንኳ የታላቁን መሪ ራዕይ ለማስፈፀም ተብሎ የደረሰው አስተዳደራዊ አበሳ፤
ፍትህ ያለምንም ፍትህ ተዘጋች፡፡ እሺ ይሁን ተባለ እና አዲስ ታምስ መፅሄት ሆና መጣች፡፡ አዲስ ታምስም በአዲሳባ ብሎም በኢትዮጵያ ምድር እንዳትታይ ተሰዋች፡፡ ፍኖተ ነፃነትም የመታተም ነፃነት አጣች፡፡ ይሄ ሁሉ የእርሳቸውን ራዕይ ለማስፈፀም ነው እንግዲህ…! አረ እንኳንም ሞቱ እንጂ ታመው አልጋ ይዘው ቢሆን ኖሮ ይህንን ሲሰሙ በሳቅ መሞታቸው አይቀርም ነበር፡፡

ፍትህ… አሁን ደግሞ በሌላ ስም መጥታለች…! እውነቱን ለመናገር የፍትህ ጋዜጣ ባልደረቦች እያደረጉ ያለው ነገር ድሮ እነ አቶ በረከት ስምኦን ኢህሃፓ እያሉ ሲያደርጉ ከነበረው ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ ይሄንን ለማረጋገጥ መስቀል አደባባይ አጠገብ ያለው የሰማህታት መታሰቢያ ሙዝየምን መጎብኘት በቂ ነው፡፡ በዛን ጊዜ ኢህሃፓ ሃሳቧን ከህዝቡ ዘንድ የምታደርስበት በድብቅ የሚሰራ ማተሚያ ማሽን ይገኛል፡፡ ደርግ በህትመት ላይ የሚያደርገውን አፈና ለመቋቋም ማሽኗ የከፈለችውን መሰዋትነት አፍ ቢኖራት እና ራሷ ብታወራው ይ¯ል ነበር፡፡ የእነ አቶ በረከት ኢህሃፓ እንደዛም ሆኖ ስላልቻለ ቀጥታ ራሱን ኢህዲን ብሎ ጫካ ገባ…!

ታድያ በፍኖተ ነፃነት እና በፍትህ ላይ እየሆነ ያለው ከዚህ በምን ይለያል፡፡ በእውኑ ይህንን ለማስረዳት እንደነ አቶ በረከት የግድ ጫካ መግባት አለብንን…! ብንልስ ጫካው የታለ…! ብለን ቀልደን አዲስ መስመር ላይ እንውረድ፡፡
እና ወዳጄ እንደ ኢኮኖሚ እድገቱ ሁሉ አስተዳደራዊ እብደቱም ቀነስ ቢል ለሁላችንም ጥሩ ነበር፡፡ መብራት ለጅቡቲ የምትሸጥ ሀገር ልጆች በመሃል አዲሳባ በኩራዝ ሲያጠኑ ይሄ ህዝብ አስተዳዳሪዎቹ ችግሩን የማያዩለት አዳራቸው የት ቢሆን ነው… ያስብላል፡፡ ሌሎች ችግሮች አንሰው በመሃል አዲሳባ ከውሃ አቅም እንኳ በቀን ሶስቴ መጠጣት ብርቅ ሲሆን ይሄ  አስተዳደራዊ እብደት ነው፡፡

ለየሃይማኖት ተቋሞች መሪ እኔ ልሹምላችሁ ብሎ አበሳ ማየት እና ሃይማኖታችሁን እኔ ልምረጥላችሁ ብሎ ግርግር መፍጠር “ከሚገባው በላይ ከሚችለውም በላይ” አስተዳደራዊ እብደት ማሳየትን የሚያመለክት ነው፡፡
ወዳጃሞች ተሰባስበው ራት ሊበሉ በሄዱበት ሆቴል ሰዎቹ የኢህአዴግ አባል ስላልሆኑ “ራት መገባበዝ አትችሉም” ብሎ መከልከል ይሄ ትልቅ እብደት ነው፡፡ ስለዚህ ጮክ ብለን እንናገራለን…
“እንደ ኢኮኖሚ እድገቱ ሁሉ አስተዳደራዊ እብደቱን የሚቀንስ ባለሞያ ይፈለግ!” አለበለዛ በዚሁ ከቀጠለ መንግስታችንን ራቁቱን ግፋ ካለ ደግሞ በግልገል ሱሪ አደባባይ እንዳናየው ያሰጋል!

ቸር ያሰማን!
አማን ያሰንብተን!

No comments:

Post a Comment