Friday, 15 March 2013

መድረክ መነቃነቅ ጀመረ

በዘሪሁን ሙሉጌታ

የስድስት ፓርቲዎች ግንባር የሆነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በሀገሪቱ የፖለቲካ እንቅሰቃሴ ፈጠን ወዳለ እንቅስቃሴ ለመግባት መዋቅሮቹን ማነቃነቅ ጀመረ።

የግንባሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ባለፈው ሰኞ ባካሄዱት ስብሰባ የግንባሩ አራት የተግባር ኮሚቴ አባላት የመዋቅር ለውጥ በማድረግ የራሳቸውን ዝርዝር እቅድ ይዘው እንዲቀርቡ አዟል።

ለግንባሩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት የግንባሩ አራት የተግባር ኮሚቴዎች በስራቸው ንዑስ የስራ ኮሚቴዎችን በማዋቀር፣ በዋና ጽ/ቤቱም ቋሚ ባለሙያዎችን በመቅጠር ጭምር የግንባሩን የጽ/ቤት የእለት ተዕለት ስራ ለማከናወን ወስኗል።

ግንባሩ ከአንድ ወር በፊት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ በአባል ፓርቲዎች መካከል ያለው የመተማመን ደረጃ እየተሻሻለ በመምጣቱ ስራዎችን በጋራ የማንቀሳቀስ ሁኔታ ተጀምሯል። በመጪው አርብ በድጋሚ በሚካሄደው ተጨማሪ ስብሰባ የግንባሩን ስራ ይበልጥ ለማቀናጀት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ እቅዶች እንደሚቀርቡ ተገልጿል።

ግንባሩ በቅርቡ የራሱን ድረገጽ መክፈቱ እንዲሁም ልሳን የማዘጋጀቱንም ተግባር ልዩ ትኩረት መስጠቱ እንዲሁም ግንባሩን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሰፋ ያሉ የገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴዎች ላይ እንደሚሰማሩም ምንጫችን ጠቁሟል።

ቀደም ሲል ‘‘መድረክ ተኝቷል’’ የሚል ወቀሳ ከአንዳንድ የፓርቲው አመራር አባላት በግልፅ ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል። በግንባሩ ውስጥ ሥራውን በተግባርና በአመለካከት ደረጃ የሚያጓትት አካል እንዳለም ምንጫችን ያመለከተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግንባሩ ወደ ስራ ሲገባም ስራውን የሚያጓትተው እና የሚያፋጥነው አካል እንደሚለይም ታውቋል።

መድረክ ከሁለት አመት በኋላ የሚካሄደው የ2007 ሀገር አቀፍ ምርጫ ዋናው ግቡ መሆኑን የጠቀሰው ምንጫችን በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ውስጥ በስድስቱ ፓርቲዎች መካከል በሚፈጠረው የጋራ መግባባት ከግንባር እስከ ውህደት ሊደርስ የሚችልባቸውን አማራጮች እንደሚፈትሽ የጠቆመ ሲሆን ግንባሩ አሁን እየፈጠረ ባለው አዲስ መዋቅር አዳዲስ ጠንካራ ሰዎች ይፈጠራሉ የሚል ተስፋ ይዟል።

ግንባሩ ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንዳለበት ተደጋግሞ ቢገልፅም፤ የበጀት እጥረቱ መድረኩ ስለስራ ያጋጠመ ችግር መሆኑም የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል። በቀጣይ ሳምንታትም ግንባሩ ያዘጋጀው ማኒፌስቶ በመገናኛ ብዙኋን እና በዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ይፋ እንደሚደረግም ምንጫችን ጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት ስድስት ፓርቲዎች በግንባር ያዋቀረው መድረክ በ2002ቱ ምርጫ ከኢህአዴግ በመቀጠል ብዙ መራጭ ማግኘቱ አይዘነጋም።

Source: Sendek Newspaper

No comments:

Post a Comment