Thursday, 2 May 2013

የህማማት ማሰታወሻ ‹‹ህዝቤን ልቀቅ!›› እስክንድር ነጋን ልቀቅ!… ተመስገን ደሳለኝ

የህማማት ማሰታወሻ  ‹‹ህዝቤን ልቀቅ!››  እስክንድር ነጋን ልቀቅ!...

ይህ ሳምንት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ‹‹ሰሞነ ህማማት›› ተብሎ በፀሎትና በስግደት ይከበራል፡፡ ይህ የሆነው ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ በሀሰት ተወንጅሎ ለስቅላት ተላልፎ የተሰጠበት፣ በሰው ልጅ ከሚደርስ ስቃይ፣ መከራና ግርፋት ሁሉ የከፋውን የተቀበለበት ሳምንት በመሆኑ ነው፡፡
 
…የፖለቲካ ተንታኝና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሀይማኖት ጥብቅ አማኝ ነው፤ የሀይማኖቱን ትእዛዛቶች በጥብቅ ያከብራል፤ ሁሉንም አፅዋማትም ይፆማል፡፡ ዛሬ በግፍ ታስሮ በሚገኝበት የቃሊቲ ወህኒም ሆኖ እንኳ የኩዳዴን ፆም ከመፆም አልሰነፈም (በነገራችን ላይ እስክንድር የሚገኝበት ‹‹ዞን ሶስት›› ፈርሶ እንደገና ሊሰራ ስለሆነ እስረኞቹ ወደሌላ ቦታ ሊዘዋወሩ እንደሆነ ተነግሯቸዋል)
እስክንድር የተወለደው ጥቅምት 27 ነው፡፡ ይህ ዕለት ደግሞ ለእምነቱ ተከታዮች የ‹‹መድሐኒያለም ዕለት›› እየተባለ የሚከበረበት ቀን ነው፡፡ እርሱም ቢሆን ምንጊዜም ጠዋት ወይም ማታ ከስድስት ኪሎ ዩንቨርስቲ ከፍ ብሎ በሚገኘው ‹‹ምስኪያዙና መድሐኒያለም ቤተ-ክርስቲያ››ን የፈለገ አያጣውም፡፡

…የፊታችን ሀሙስ (ሚያዚያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም) የእስክንድር ነጋ ይግባኝ ‹‹ለመጨረሻ ጊዜ›› ተብሎ ተቀጥሯል፡፡ ዕለቱ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ‹‹ፀሎተ ሀሙስ›› ታስቦ የሚውልበት ቀን ነው (አይሁዳውያን ኢየሱስ ክርስቶስን አሳልፈው ሰጥተው ሲያበቁ ስለሁከት፣ ስለመግደል በወሀኒ ታስሮ የነበረውን በርባንን ‹‹ፍታልን!›› ያሉበትን እና የሐዋርያትን እግር ዝቅ ብሎ በትህትና ያጠበበትን ለማስታወስ ነው ቀኑ ‹‹ፀሎተ-ሀሙስ›› ተብሎ የተሰየመው)
…በድህረ ምርጫ 97 ለእስር ከተዳረጉ ጋዜጠኞች መካከል እስክንድር ነጋ አንዱ ነበር፡፡ የተፈታውም በ‹‹ይቅርታ›› ሳይሆን ፍርድ ቤቱ ‹‹ነፃ ነህ!›› ብሎ አሰናብቶት ነው፡፡ ቀኑም የ‹‹ፀሎተ-ሀሙስ›› ዕለት ነበር፡፡ …የከነገ በስቲያ ሚያዚያ 24 ግጥምጥሞሽስ ምን ያሰማን ይሆን?
የሆነ ሆኖ የመፅሀፍ ቅዱስ ቃል ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት እግዚአብሄር ሙሴን እንዲህ እንዳለው ይነግረናል፡-
‹‹እኔ እግዚአብሄር ነኝ፤ ከባርነት አወጣችኋላሁ፤ ከተገዥነታቸውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ በታላቅ ፍርድም እታደጋቸኋለሁ፤ አምላክም እሆናቸኋለሁ፡፡›› (ኦሪት ዘጸአት ም.6 ቁ.6-7)
በወቅቱ ብዙ ሺህ ንፁሃን፣ ፈርኦን በተባለ ጨካኝ ንጉስ ስር ይሰቃዩ ነበር፡፡ እናም ከዕለታት አንድ ቀን እግዚአብሄር ሙሴን ወደ ፈርኦን ላከው፡፡ ሙሴም ቤተ-መንግስቱ ውስጥ ድረስ ዘልቆ በዙፋኑ ለተቀመጠው ፈርኦን እንዲህ ሲል የአምላኩን መልዕክት ነገረው፡-
‹‹እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡- በፊቴ ለመዋረድ እስከመቼ እምቢ ትላለህ? ያገለግለኝ ዘንድ ህዝቤን ልቀቅ!››
…በምንወዳት ሀገራችን ኢትዮጵያም እስከዛሬ ድረስ ያየነው ስርዓቱና ምንደኞቹ ንፁሃንን በሀሰት ከሰው፣ በሀሰት ምስክርና በሀሰት ማስረጃ ወደ ጨለማ (ወህኒ) ሲወረውሩ ነው፡፡
በመላ ሀገሪቷ የነገሰውም የህግ የበላይነት አይደለም፤ የፈርኦን የበላይነት እንጂ፡፡ ፈርኦኖች ደግሞ ምን ጊዜም ከመከራ እንጂ ከታሪክ ተምረው አያውቁም፡፡ መልካሚቷን ምክርም ሊሰሙ አይወዱም፡፡ ስለዚህም ብቸኛው አማራጭ በአደባባይ ተሰባስበን፡-
 
‹‹በፊታችን ለመዋረድ እስከመቼ እምቢ ትላለችሁ? ሀገራቸውን ያገለግሉ ዘንድ ወንድምና እህቶቻችንን ልቀቅ!››
‹‹እስክንድር ነጋን ልቀቅ!
በቀለ ገርባን ልቀቅ!
አንዱአለም አራጌን ልቀቅ!
ርዕዮት አለሙን ልቀቅ!
ውብሸት ታዬን ልቀቅ!
የሱፍ ጌታቸውን ልቀቅ!
አቡበክር አህመድን ልቀቅ!
ብዙ… ብዙ ሺህ ንፁሃንን ልቀቅ!››
እያሉ መጮኹ ኢያሪኮን ለማፍረስ ያልተመለሰው የጭቁኖች ጩኸት መነቃነቅ የጀመረውን ስርዓት ለመፈረካከስ ብቸኛው ምርጫችን እንደሆነ ዛሬም ደግሜ እናገራለሁ፡፡
‹‹ልቀቅ! ልቀቅ! ልቀቅ!››

No comments:

Post a Comment