ከመስፍን ነጋሽ
የአፍሪካ ኅብረት የወላጁን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ዕድሜ ጨምሮ 50ኛ ዓመቱን በመዲናችን
ሊያከብር ነው፤ ወይም እያከበረ ነው። ኅብረቱ በአብዛኞቹ አፍሪካውያን ሕይወት ውስጥ ይህ ነው የሚባል ቦታ የሌለው
በመሆኑ የእርሱን የሃምሳ አመት ጉዞ በስፋት በመገምገም አልጠመድም። ሆኖም በጥቅሉ ሲታይ የኅብረቱ ጉዞ የአባላቱ
ነጸብራቅ ነው፤ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት ወደኋላ የሚሔድ። ተስፋ የለውም አይባልም፤ ቢያንስ ያማሩ ሕጎችና
ስምምነቶችን ከነተቋሞቻቸው የሚያልሙ በርካታ ስምምነቶችን አዘጋጅቷል፤ አጸድቋል። ሆኖም ግምሹ ያህል ስምምነቶችንና
አዋጆች እንኳን በተግባር አይውሉም፤ በገዛ አጽዳቂዎቻቸው ይሻራሉ።
መንግሥታቱ በየአገራቸው ራሳቸው ያወጡትን ሕግ
እንደሚጥሱ ሁሉ በአፍሪካ ኅብረት ያጸደቁትን ስምምነትም ከቁብ አይቆጥሩትም። ኅብረቱ ተስፋ የሚያጭሩ ጅምሮች
ቢኖሩትም ተማምነው ተስፋ የሚጥሉበትም ወደመሆንም አልደረሰም። ለማንኛውም ዕድሜ መቁጠር በዕድሜው ከተሰራበት ነገር
ጋራ ባህሪያዊ ግንኙነት ስለሌለው፣ የሃምሳኛ ዓመት በዓሉ መከበሩ የሚያከራክር አይደለም።
ድርጅቱ ልደቱን በተወለደባት መዲናችን ማክበሩ ነገሩን የበለጠ ቅርብ ሳያደርግልን አይቀርም። ቀዳማዊ ኅይለ ሥላሴን እና መለስ ዜናዊን ለኅብረቱ ያበረከተችው ኢትዮጵያ በ50ኛው ልደት የምትወከለው በሃይለማርያም ደሳለኝ ነው። ሃይለማርያም ገና ተማሪና ተመሪ ናቸው እንጂ የአገር መሪ አልሆኑም። አጋጣሚው እንደ አገር መሪ ራሳቸውን ለማቅረብ ትልቅ እድል ይሰጣቸው ይሆናል። ሆኖም ችለውና ጨክነው ራሳቸውን ከመለስ ጥላና ኮፍያ አስወጥተው መድረክ ላይ የሚቆሙ አይመስለኝም። ንጉሱንና መንግስቱን ወቅሰው፣ የቀድሞ አለቃቸውን አወድሰው አንድም የሚታወስ ነገር ሳይናገሩ ከወረዱም ለሚቀጥለው ልደት የመዘጋጃ ጊዜ አያገኙ ይሆናል። መልካም እድል እንመኝላቸዋለን፣ ከፋም ለማም የአገራችን ”መሪ” ናቸውና ጎልተው ቢወጡ ክብሩ ለእኛም ነው። ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በአብዛኛው የኢትዮጵያ ገጽታ ሲል የኢሕአዴግ ገጽታ ማለቱ ስለሆነ ኢትዮጵያ ለድርጅቱ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ለመዘከር ብዙ ደክሞ የሚያቀርበው ነገር ካለው የምናየው ይሆናል። እዚህ ላይ ”የቀኀሥ ሐውልት በኅብረቱ ግቢ ይቁም አይቁም” የሚለውን ውዝግብ ለአፍሪካ ኅብረት ለራሱ ትተን፣ በዚህ ትልቅ አኅጉራዊ አጋጣሚ ንጉሡና በየዘመኑ የነበሩት ዲፕሎማቶቻችን (ዲፕሎማትነት በደም ጥራት ብቻ የሚቀላቀሉት የቤተሰብ ጽዋ ከመሆኑ በፊት) ያደረጉትን ክልላዊና አኅጉራዊ አስተዋጽኦ የሚያስታውስ አንዳች ዝግጅት ይዘጋጅ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ማሰብ አይከለከል!
የኅብረቱ ልደት አከባበር ከአገራችን ፖለቲካ ጋራ ተገናኝቶ እንዲታይ የሚያደርግ ነገር የለም፣ በቅርቡ ”ሰማያዊ ፓርቲ” ካቀረበው ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ በቀር። ስለዚህን ጥሪ ከማተቴ በፊት አጋጣሚው በአህጉሪቱ በየአቅጣጫው ያለው ችግርና ተስፋ በብዙ ሰላማዊ ሰልፎች ሊገለጽበት የሚገባ እንደነበር ማስታወስ አለብኝ። አህጉሯ አፍሪካ፣ ድርጅቱ የአፍሪካ ኅብረት፣ አስተናጋጇ ኢትዮጵያ ሆነው እንጂ በዚህ ትልቅ አህጉራዊ በዓል ወቅት ሰልፍ መጠራቱ በራሱ ለንግግር የሚበቃ ትልቅ ጉዳይ ባልሆነ ነበር። ሲሆን ሲሆን፣ በዚህ ሰሞን የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገሮች ያሉትን አምባገነኖች፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ወዘተ የሚቃወሙ ሰልፎች በመዲናችን በተካሄዱ ነበር። ለማንኛውም የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች ብጤ ሆኖብን አሁን የራሳችንንም ጉዳይ በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለጽ ማሰብና ማቀድ ራሱ ብርቅ ሆኖብን እያማጥን፣ እያመነታንና እየተሟገትን ነው፤ ረጅም እድሜ ለውርስ አስፈጻሚዎችና ለአውራሹ፤ (ሌጋሲ አማርኛ የለውም ማለት ነው?)።
”ሰማያዊ ፓርቲ” ሚያዝያ 25 ቀን ስለሰልፉ ባወጣው መግለጫ እንዲህ ብሏል፤ ”...ድምፃችንን ለማሰማት ከግንቦት 15 - 17 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ጥቁር ልብስ በመልበስና ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ፅ/ቤት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ከላይ ያነሳናቸውና ሌሎችም ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ ሰማያዊ ፓርቲ ለመጠየቅ ወስኗል፡፡ በመሆኑም እነዚህ ጥያቄዎች እንዲመለሱ የሚፈልግ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሲቪክ ማህበራትና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በእነዚህ ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡”
ፓርቲው ያነሳቸው ጥያቄዎችም ሆኑ የመሰብሰብና ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን በተግባር የማስከበር ጉዳይ አዲስ ጥያቄዎች አይደሉም፤ ሁሉም ተቃዋሚዎች (ግለሰቦችም ድርጅቶችም) የሚጋሩዋቸው ናቸው። ሆኖም ”ሰማያዊ ፓርቲ” ላቀረበው ጥሪ የሚሰጠው ምላሽ የጉዳዩን ያህል ሁሉንም ለማስተባባር የቻለ መስሎ አይታይም። ለምን ሲባል ግማሹ ”ሰማያዊ ፓርቲ” ነገሩን አስቀድሞ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋራ ሊመክርበት ይገባ ነበር ይላል፤ ሌላው ደግሞ ሰልፉ ኢሕአዴግን የሚያጋልጥ ሳይሆን የሚጠቅም ነው ይላል። ሦስተኛው ክርክር መንግሥት ሰልፉን አይፈቅድም፣ ቢፈቅድም ብዙ ወሰኖች ሊያበጅ ይችላል (ለምሳሌ ሰልፉን ከእይታ በራቀ ቦታ አድርጉ፣ ወይም የሚመጣው ሰው ቁጥር ይወሰን ወዘተ የሚል ቅድመ ሁኔታ ይጥላል) የሚል ነው። ሌሎችም ክርክሮች ይኖሩ ይሆናል፤ አላየኋቸውምና አስተያየት ልሰጥባቸው አልቻልኩም።
በፓርቲዎቹ መካከል ያለውን ግልጽና ስውር ውድድር አሳንሰን ሳንመለከት፣ ነገሩ ረዘም ያለ ጊዜ ተሰጥቶት፣ ሐሳቡ ከአንድ ፓርቲ የመጣ ቢሆንም በውይይት ሌሎቹም የራሳቸው አድርገውት ቢሆን የተሻለ ይሆን እንደነበር መከራከል ተገቢ ነው። እውነትም ይህ ቢሆን ጥሩ ነበር። እርግጥ ፓርቲዎቹ አስቀድመው ስላወቁ ብቻ ሰልፉ የተሻለ ውጤት ይኖረዋል ማለት አይደለም። ሆኖም በዚህ ወቅት ቢያንስ ጥቂት ፓርቲዎች በጋራ ያዘጋጁትና የጠሩት ሰልፍ ቢሆን በዝግጅቱም ሆነ በውጤቱ ጥሩ ነበር። ለማንኛውም ይህ አልሆነም። ጥያቄው ይህ ስላልሆነ ሰልፉን መደገፍ የለብንም ወይ የሚል ሆኖ ይታየኛል።
ሁለተኛው ትችት ደግሞ ሰልፉ ቢፈቀድ እንኳን የኢሕአዴግን/መንግሥት ሰብአዊ መብት የሚያከብርና ሰለፍ የሚፈቅድ በማስመሰል ከተቃዋሚው ይልቅ ጨቋኙን የሚጠቅም ሊሆን ይችላል የሚል ነው። ይህ ግምት በጣም ሐሳባዊ ነው፤ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፤ አሁን ማረጋገጫ የለንም። በሰልፉ ምን ያህል ሰው እንደሚገኝ፣ ምን እንደሚሆን ወዘተ መናገር አንችልም። ስለዚህ በውጤቱ ኢሕአዴግን ይጥቀም አይጥቀም አናውቅም። ከዚያም በላይ ግን ይህን መሰል ጥሪዎችና ሙከራዎች ያላቸውን መሠረታዊ ፋይዳ ገደል የሚከት ነው። በዚህ ላይ እመለስበታለሁ።
መንግሥት ሰልፉን እንደለመደው በውሃ ቀጠነ ይከለክላል ወይም ውጤቱን ለማኮሰስ የተለያዩ ገደቦችን ይጥላል የሚለው ክርክር በእውነትም ሊሆን የሚችል ነው። ልምዳችን ይህን ያረጋግጥልናል። ሆኖም ይህም ቢሆን ሰልፉን ላለመደገፍ የሚያበቃ ምክንያት ሆኖ አልታየኝም። ይህ ክርክር ዜጎች መብታቸውን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ እንዲጠይቁ ከማበረታታት ይልቅ በውልና በእርግጥ የማናውቀውን ”አመቺና አስማማሚ” ሁኔታ ቁጭ ብለው እንዲጠብቁ የሚጣራ ነው። ይህ ስህተት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ትችቱ የልምዳችን እስረኞች መሆንን የሚደግፍ ይመስላል፤ ትናንት ተክልክሏል፣ አልተቻለም ማለት ዛሬ አይቻልም ማለት አይደለም።
ሦስቱም ትችቶች በጋራ የሳቱት ወይም የረሱት አንድ ትልቅ ቁም ነገር አለ (እመለስበታለሁ ያልኩት)፤ ይኸውም ይህን መሰል ሙከራዎችና ጥሪዎች ዜጎች መብታቸውን በሁሉም አጋጣሚዎች እንዲጠይቁ የማበረታታቱ፣ ፍላጎትን በተግባር የመቀስቀሱ፣ ፈጠራን የማጎልበቱ ጥቅም ነው። ሙከራው የሚጀምረው ደግሞ በመጠየቅ ነው። ለዚህ ነው ጥያቄው በዚህ ወቅት መቅረቡ በራሱ ጥሩ ነው ብዬ የማምነው። ጥሪው ተሳክቶ ሰልፍ ተካሄደም አልተካሄደ ጥያቄው መቆም የለበትም። ቀድሞ ነገር ይህን መሰል ጥሪዎች በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን የሚቻል ሆኖ ሲገኝ በየክልሉ ከተማና ወረዳ ሁሉ መጠየቅ አለበት፤ ስብሰባውና ሰልፉ ባይፈቀድ እንኳን ይህን የሚጠይቁ ዜጎችን ማግኘትና ማሰባሰብ በራሱ አቅም ይፈጥራል። የእነዚህ ጠያቂ ሰዎች ቁጥርም የግድ መቶና ሺህ መሆን የለበትም፤ መቁጠሪያ ቁጥር ከአንድ ይጀምራል።
ይህ ዜጎችን በራሳቸው ላይ የማሰልጠን (empower) ጥቅም ሰልፉ በአንድ ፓርቲም ይጠራ በ10 አይለውጥም። ይህ ጥቅም ሰልፉ መካሔድ የሚችለው በ200 ሰዎች ሰንዳፋ ከተማ ውስጥ ነው ቢባል እንኳን አይቀርም፤ 200 ሰዎች ይሰለፉና ድምጻቸውን ያሰሙ። የግድ ከሺህና ከአስር ሺህ መጀመር አለበት እንዴ? ይህ ጥቅም በሰልፉ መካሔድ ኢህአዴግ/መንግሥት የሚያገኘው ነጥቢ ቢኖርም አይቀርም። ቀድሞውንስ ኢሕአዴግ የህዝብን መብት እስካከበረ በዚህ ተግባሩ ቢጠቀም ምን አለበት? አምባገነኑ መንግሥት አንድ ሰልፍ በስምነት ዓመቱ ስለፈቀድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ስም ይለወጣል ብሎ ማሰብ (መስጋት) የዋህነት ነው። ጅምሩ እውነተኛ ከሆነ ደግሞ ከተስፋው እንካፈላለን። ኢሕአዴግ/መንግሥት በፈለገው ስሌት ሰልፉን ቢፈቅድ ተቀብሎ በአግባቡ መጠቀም ይገባል። የሰላማዊ ትግል የመጀመሪያ ነጥብ የተገኘውን እድል በአግባቡ መጠቀም ነው፤ እድሉ ጠባብም ይሁን ሰፊ፣ በአጋጣሚም ይገኝ በእቅድ እድሎችን መጠቀም በድምር ውጤቱ በመጨረሻ የሚጠቅመው ገዢዎችን ሳይሆን ለነጻነት እታገላለሁ የሚለውን ወገን ነው።
ስለዚህም የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪው ሲሆን ሊተባበሩት የሚገባ፣ ይህ ቢቀር ደግሞ ጥያቄውን የምናደንቅበት ነው እላለሁ። ዜጎች ሰልፉን ይደግፉ ሲባል ግን ”ሰማያዊ ፓርቲ” ትልቅ ሐላፊነት እንደነበረበትና እንዳለበት ሳይረሳ ነው። ፓርቲው ነገሩን ካሰብኩበት ቆይቻለሁ ቢልም ለምን በዚያ ቀን ይፋ ማድረግ እንደፈለገ አልገባኝም፤ ሟቹ ጠ/ሚ ”ቀኑ ሐሙስ ስለሆነ ነው” እንዳሉት አይነት መልስ ካልተሰጠ በቀር። ቀድሞ ከታሰበበት ቀድሞ ይፋ ማድረግ፣ ቀድሞ ጥቂት ፓርቲዎችን ቀርቦ ማነጋገር ወዘተ አይቻልም ነበር? ካልተቻለ ለምን? ፓርቲው ለመዘጋጀት ለራሱ ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ (እንዳሉት ከሆነ) ይህንኑ ጊዜ ምነው ለሌሎቹ ፓርቲዎች ማሰቢያና መዘጋጃ መስጠት አቃተው? (ልብ በሉልኝ፣ ቀደም ሲል ጥያቄው በአንድ ፓርቲም ቢቀርብም ማገዝ/መተባበር ይገባል ብዬ ”ቀድሞ ካልተነገረን የለንበትም” የሚሉትን ተችቻለሁ።) ይህ ቀድሞ ማስታወቅ ለገዢው ፓርቲም የመዘጋጃ ጊዜ እንደሚሰጠው የታወቀ ነው፤ በጥሩም በመጥፎም። ቀድሞ በመጥራት ብዙ ሰው ይመጣል ተብሎ ታምኖና ተገቢው ስራ መሬት ላይ ተሰርቶ ካልሆነ በቀር ከቀኑ 3 ቀን በፊት እቅዱን ገልጾ መንግስትን የመዘጋጃ ጊዜ መንፈግ አይቻልም ነበር ወይ የሚል ጥያቄም ገጥሞኛል። ለማንኛውም ”ሰማያዊ” ሌሎቹን ፓርቲዎች ከሌላው ሕዝብ በእኩል ጊዜ በላከላቸው ጥሪ የሚጋብዛቸው በምን እንዲረዱት ነው? ደጋፊዎቻቸውንን አባሎቻቸውን በሰልፉ ተሳተፉ እንዲሉ ነው ወይስ ሌላ በዚህ አጭር ቀን ሊደረግ የሚችል ነገር አለ?
ስለሰልፉ ቀድሞ ከታሰበበት በሰልፉ አደረጃጀት ላይ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብሎ መገመት ይቻላል ማለት ነው። የተደረገውን ዝግጅት ቀኑ ሲደርስ ፓርቲው በሚወስዳቸው አቋሞችና እርምጃዎች የምናየው ይሆናል። ይህን ሁሉ ስል በሰልፉ ዝርዝሮች ላይ (ጥቁር ልብስ በመልበስና ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ፅ/ቤት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ) አስተያየት ሳልሰጥ ነው። ሌሎቹ ፓርቲዎች የሚሰጡት ድጋፍ አይነትና መጠን፣ አብሮ በባለቤትነት ከማዘጋጀት በመጨማሪ፣ በእነዚህ የሰልፉ ታክቲኮችና ስትራቴጂዎች ላይ በሚወስዱት አቋምም የሚወሰን ነው። ስለዚህ ”ሰማያዊ” ከሌሎቹ ፓርቲዎች ሊያገኝ የሚችለውንና የሚገባውን እገዛ ሲገመግም እንዚህንም ከግምት ማስገባት ይኖርበታል። በአጠቃላይ ግቡ ላይ መስማማትና በዝርዝር አፈጻጸም ላይ መመሳሰል ለየቅል ናቸው።
በመጨረሻ፣ የዚህ ሰልፍ ውጤት ምንም ይሁን ”ሰማያዊ”ን ጨምሮ ፓርቲዎች ጥሩ የመነቃቂያ ትምህርት እንድትወስዱበት፣ የመራራቂያ ሳይሆን የመቀራረቢያ አጋጣሚ አድርጋችሁ እንድትጠቀሙበት እመኛለሁ። በቀረውስ፣ ብኖር ኖሮ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ብቻ ሳይሆን ኅብረቱን ራሱን የሚመለከቱ ተቃውሞዎችም ነበሩኝ። ለነገሩ፣ እርሱም ቢሆን መንግሥት ”እንግዶችን ማስቀየም” የሚል አዲስ የአሸባሪነት ወንጀል ካልፈጠረ ነው።
No comments:
Post a Comment