(ግንቦት 16 ቀን 2005 ዓ.ም. / May 24, 2013)
የኢትዮጵያ
ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ከተመሠረተ 2007 እ.አ.አ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የሚያዋስናትን የምዕራቡ ድንበራችን
እርዝማኔው 1600 ኪ/ሜትር የጎን ስፋቱ ከ30 እስከ 60 ኪ/ሜትር የሚሆነውን ከፍተኛ የተፈጥሮ ሃብትና ልዩ ልዩ
ብርቅየ የዱር አራዊትና አውዋፍ የሚገኙበት አንጡራ ለም የድንበር መሬታችንን ፀረ-ኢትዮጵያው ወያኔ የገዥ ቡድን
ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት በምስጢር መደራደሩን ፤ ከዚያም በኋላ መስጠቱን ለሕዝብ በማጋለጥ በተከታታይ ሰፊ
መግለጫዎች ማውጣቱ፤ ለልዩ ልዩ የዜና አውታሮች ቃለ-ምልልሶች መስጠቱ እና የተለያዩ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ማካሄዱ
የሚታወስ ነው። ከዚህም በላይ፤ ይኽኑን አሳሳቢ የድንበር ጉዳይ በተመለከተ ስፋትና ጥልቀት ያለው ታሪካዊ ሠነድ
እንደሚያዘጋጅ ቃል መግባቱ የሚታወቅ ነው።
በዚሁ ቃል-ኪዳን መሠረት፣ ከሁለት ዓመት በላይ ሰፊ የጥናትና
ምርምር ሥራዎችን ሲያካሂድ ቆይቶ፤ ይህኑን ዓብይ ጉዳይ በተግባር ለማዋል እንዲችል፤ የድንበሩ ኮሚቴ ከፍተኛ አካል
የሆነው ምክር ቤት ግንቦት 10 እና 11 ቀን 2005 ዓ.ም. ( May 18 and 19, 2013 ) ታላቅ ጉባዔ
በሲሊቨር ስፕሪንግ ከተማ፣ ሜሪላንድ፣ አሜሪካ (Silver Spring, Maryland, USA) አካሂዷል።
ጉባዔው
የተከፈተው የሀገራችንን ዳር- ድንበር ለማስጠበቅ በድንበሩ ላይ በቆራጥነት ከወራሪው የሱዳን ጦርና ከወያኔ ሠራዊት
ጋር እልህ አስጨራሽ ተጋደሎ በማድረግ ሲታገሉ የተሰውትን ወገኖቻችንንና ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የድንበር
ኮሚቴ ምክትል ሊቀ-መንበር የነበሩትን ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሊቀ ማእምራን አበባው ይግዛውን በማስታወስ የአንድ ደቂቃ
የሕሊና ፀሎት በማድረግ ነበር።
በዚህ ታሪካዊ ጉባዔ ላይ ድንበሩን በተመለከተ በእውቅ ኢትዮጵያውያን
ጠበብቶች የተዘጋጁ በተለያዩ ርእሶች ያተኮሩ ሰፊ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል። እነዚህም፥ 1ኛ/ ታሪካዊ ጥናት 2ኛ/
ዓለም-አቀፍ ሕጎችና ውሎች 3ኛ/ ምጣኔ ሃብት (ኢኮኖሚ)፣ ማሕበራዊ ሁኔታዎችና ብሔራዊ ደህንነትና ሉዓላዊነት
እና4ኛ/ የካርታ ጥናቶች ናቸው።
ምክር ቤቱ በእነዚህ ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ በሰፊው ተወያይቶ በአንድ ድምጽ
በማጽደቅ፤ ጥናታዊ ጽሑፎቹ ተቀናጅተው አንድ ወጥ የሆነ ለሀገርና ለወገን የሚሆን ታሪካዊ ሠነድ በቅርብ ወራት
ውስጥ እንዲዘጋጅ ወስኗል።
ሁላችንም እንደምናውቀው፤ ወያኔ ገዥ ቡድን ሽንጡን ገትሮ ለሱዳን ሕዝብና
መንግሥት የሚሟገትለትና የሚከራከርለት የቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ ሻለቃ ቻርልስ ጉዊን በግሉ ብቻውን የከለለውን የድንበር
መሥመር መሠረት በማድረግ ነው። ይሁን እንጅ፤ ቀደምት የኢትዮጵያ መንግሥታት ሻለቃ ቻርልስ ጉዊን ያሠመረውን
የድንበር መሥመር በጭራሽ ተቀብለው አያውቁም።
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የሚያዘጋጀው ታሪካዊ ሠነድ በርከት ያሉ ታሪካዊ ማስረጃዎችን ያሰባሰበ በመሆኑ፥
1ኛ/ የሻለቃ ቻርልስ ጉዊን ድንበር ከለላ መሥመር ሕገወጥ መሆኑን በተጨባጭ ውድቅ ያደርገዋል፤
2ኛ/ ፀረ-ኢትዮጵያው ወያኔ ለሱዳን በስጦታ ያስረከበው ዳር- ድንበራችን የኢትዮጵያ መሆኑን ያረጋግጣል፤
3ኛ/
የመሬት ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳ ከሆነ፤ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ሳይሆን ኢትዮጵያ በሱዳን ላይ ልትጠይቀው የምትችል
ሰፊ ለም መሬት እንዳላት ጥናቱ ያካትታል፡፡ ይህ ታሪካዊ ሠነድ በአማርኛና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ
እንደተጠናቀቀ፤ ለጉዳዩ ባለቤት ለሆነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ እናሳውቃለን።
ለወደፊቱ የሀገራችንን የግዛት
አንድነትና ሉዓላዊነት የሚያስከብር፤ ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ኢትዮጵያዊ መንግሥት ሲመጣ፤ ፀረ-ኢትዮጵያው ወያኔ
ለሱዳን የስረከበውን የሀገራችንን ምዕራባዊ ዳር-ድንበር ለማስመለስና ለማስጠበቅ ይህን ሠነድ ከሌሎች ጥናቶች ጋር
አያይዞ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡
ይህ ታሪካዊ ሠነድ ተጠናቆ እንዳለቀ፤ አወዛጋቢ የሆኑትን ሌሎች የሀገራችን ድንበር ውሎችና ስምምነቶች እንዲጠኑ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
የኢትዮጵያ ዳር-ድንበር በቋራጥ ልጆቿ ተጋድሎ ይከበራል!
ኢትዮጵያ ለዘላለም በነፃነትና በክብር ትኑር!
No comments:
Post a Comment