በፍቃዱ ዘ ኃይሉ
ከስድሰት
ወር በፊት እሠራበት የነበረው የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለግድቡ መዋጮ የፈለግነውን ያክል ገንዘብ
የምናዋጣበት ባዶ ቅጽ ላከልን። ብዙዎቻችን የወሩን ሦስት አራተኛ በጥልፍልፍ ብድር የምናሳልፍ በመሆኑ ገሚሶቻችን
በትሕትና ማዋጣት እንደማንችል ስንገልጽ ቀሪዎቹ ደግሞ “መቶም፣ ሁለት መቶም በዓመት ክፍያ ይቆረጥብን” ብለው
ፈረሙ። ይህ ያላስደሰታቸው አለቆች ከቆይታ በኋላ 50% ደሞዛችንን በዓመት ክፍያ እንድናዋጣ የተጻፈበት ቅጽ
ሊያስፈርሙን ሲያመጡ የፈቃደኝነታችን ሥርዓተ ቀብር ተከናወነ። እኔ አልፈርምም አልኩኝ።
የድኅረ ምረቃው ት/ቤት
ም/ፕሬዚደንት ቢሮዬ ድረስ መጥቶ ተማፀነኝ – “የተቋማችን ስም ይጎድፋል” በማለት። እኔም አልኩት “ወር በገባ
በ10ኛው ቀን ከሚያልቀው ደሞዜ ላይ የማዋጣው ገንዘብ የለኝም፣ ከቻሉ የገቢ ግብሬን ይጠቀሙበት – ለማይወክለኝ
ግንቦት 20 ድግስ ርችት የሚተኩሱበትንና ከአፌ ነጥለው የወሰዱትን ታክስ መጀመሪያ ባግባቡ ይጠቀሙበት። አሁን ግን
አዋጣ ከምትሉኝ ልቀቅ ብትሉኝ እመርጣለሁ። በእኔ ገንዘብ እየተሠራ ኢሕአዴግ ራሱን በኢቴቪ ሲያሞግስ ማየት
አልችልም” ብዬ ተንጣጣሁ። አስብበት ብሎ ቅጹን አስቀምጦልኝ ሄደ።
30 ደቂቃ ቆይቼ ሄድኩና “አሰብኩበት ግን አላዋጣም” አልኩት።
ነገሩ
በዚህ ያበቃ መስሎኝ ሳለ የዛሬ ስድስት ወር ገደማ በግል ጉዳዬ ተቋሙን ልለቅ ሳመለክት እና ‘ክሊራንስ‘ ሳዞር
የሕዳሴው መዋጮ ቀሪ አምስት መቶ ምናምን ብር አለብህ ተባልኩ። “I was like ‘what?!’” ይሉ ነበት
ፈረንጆቹ ቢሆኑ። ድንግጥ አልኩ። “ያ አሲዳም ደሞዜ ወትሮም ከብድር ከፋይነት የትም አላደረሰኝ። ለካስ በየወሩ
እየተቀነጠበ ነበር የባሰ መቅኖ ያጣብኝ” አልኩና ባሳቤ “በማን ፈቃድ ቆረጣችሁት?” አልኳት ሒሳብ ሠራተኛዋን።
የሆነ ዶሴ ፈልፍላ አወጣችና “አቶ በፍቃዱ …. እስካሁን ስላልተቆረጠባቸው … ከዚህ ወር ጀምሮ …” ደብዳቤው
እንደቃለጉባኤ ያለ ሲሆን ከግርጌው ፊርማዎች ሰፍረውበታል።
ም/ፕሬዚደንቱ ቢሮ ብስጭቴን ይዤ ሄድኩ። “እኔ
የለሁበትም” ተባልኩ። የፋይናንስ ኃላፊውጋ ሄድኩ “ተቋሞች በሙሉ የሠራተኞቻቸውን ደሞዝ አምሳ በመቶ ለማዋጣት
ስለተስማሙ ሁሉም ሠራተኛ ግዴታ ማዋጣት አለበት ተብሎ ተወስኗል” አለኝ። “በገዛ ደሞዜ ማን የመወሰን ሥልጣን
አለው? የኔ ደሞዝ የመንግሥት ፓሊሲ ለማውጣት የማይተገበረው የድምፅ ብልጫ ለምን ይተገበርበታል?” በማለት
አማረርኩ። በጩኸት “እከሳችሀኋለሁ” እያልኩ ዛትኩ።
ከዚያ በኋላ ግን አንደኛ “አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ”
መሆኑን እያወቅኩ ለማን እከሳለሁ? ሁለተኛ መቼም ጉዳዩ የአገር ጉዳይ ነው፣ እስኪ ከፕሮፓጋንዳ ተርፏቸው ከሠሩት
ይሥሩበት በማለት ቀሪውን ከ‘ፕሮቪደንት ፈንዴ‘ ላይ ከፍዬ ለቀቅኩ። ምናልባትም ከከሰስኩ ተቋሜን ሳይሆን መከሰስ
የሚገባውን የምከስበት ቀን ይመጣል!
ይህ ከሆነ ጀምሮ ያተረፍኩት ነገር ብስጭት ነው። ከጉሮሮዬ ነጥዬ
ያዋጣሁት እኔ እያለሁ፣ “አባይን የደፈረ ጀግና” ሌላ ነው። እኔ ካሁን አሁን ግድቡ አለቀ ብዬ በጉጉት እጠብቃለሁ፣
የግድቡ ፅንሰት እየተባባሉ በገንዘቤ ደግሰው ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፣ ይጨፍራሉ። ይህንንም በኢቴቪ ያስተላልፋሉ።
No comments:
Post a Comment