Wednesday, 22 May 2013

ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በቤንሻንጉል ተፈናቃዮች ዙሪያ ተቃዋሚዎችንና ሚዲያዎችን ወቀሱ



ከቤንሻንጉል ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ጋር በተያያዘ ሕገወጥ ድርጊት ፈጽመዋል የተባሉ 35 ተጠርጣሪዎች ከመንግስታዊ ኃላፊነታቸው መባረራቸውን ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም አስታወቁ፡፡
ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር የመ/ቤታቸውን የ2005 የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ዛሬ ለፓርላማው ሲያቀርቡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለ3ሺ 248 ያህል የአማራ ተወላጆች መፈናቀል ምክንያት እንደሆኑ የተደረሰባቸው 35 ተጠርጣሪዎች ከያዙት ኃላፊነታቸው እንዲሰናበቱ መደረጉን ፤ከነዚህ ውስጥ በቂ መረጃና ማስረጃ የተገኘባቸው 12 ያህል ተጠርጣሪዎች ላይ በሕግ እንዲጠየቁ ክስ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡

በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም ከቤንሻንጉል ክልላዊ መንግስት ሕገወጥ በሆነ መልኩ ከተፈናቀሉ 3ሺ 248 የአማራ ተወላጆች መካከል 2 ሺ 412 ያህሉ ወደነበሩበት ቀዬ እንዲመለሱ ቀሪዎቹ 836 ያህል ሰዎች ደግሞ ድሮ ወደነበሩበት ቀዬ መመሳቸውን ለፓርላማው ሪፖርት አድርገዋል፡፡


እንደሚኒስትሩ ገለጻ እነዚህን ተፈናቃዮች መልሶ በማቋቋም ሂደት ላይ በክልሉ ከፍተኛ አመራር የሚመራ ቡድን በዞን፣በወረዳ፣በቀበሌ መዋቅር ያሉትን አመራሮችና በየቀበሌው በሚኖሩ ሕዝቦች ድረስ በመውረድ አመለካከት የማስተካከል ስራ እየተሰራ ሲሆን ንብረት የማስመለስ ስራም ተከናውኗል፡፡
በቤንሻንጉል ክልል በአማራ ተወላጆች ላይ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ጀምሮ ችግሮች መኖራቸውን ከክልል እስከማዕከል አቤቱታ ሲቀርብ እንደነበረ ያስታወሱት አንድ የፓርላማ አባል ፣ ችግሩ የተከሰተው በመጋቢት ወር ሳይሆን በየካቲት ወር መሆኑን፣ችግሩ ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ ለምን እንዳልተፈታ ጥያቄ አዘል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ችግሩ ሲከሰት የክልሉ መንግስት ብቻም ሳይሆን የፌዴራል መንግስት ያውቃል ብለው እንደሚገምቱና መፍትሄ ለመስጠት ለምን እንደዘገዩ ጠይቀዋል፡፡

ዶ/ር ሽፈራው ለዚህ ጥያቄ በሰጡት መልስ ሁሉም ነገር ከአንድ ደቂቃ በፊት ሊሰራ እንደሚችል ይታወቃል በማለት በተዘዋዋሪ ችግሩን ለመቅረፍ መዘግየት እንደነበር ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ አይይዘውም የመ/ቤታቸው ተልዕኮ ግጭትን መፍታት ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ መከላከል መሆኑን በመጥቀስ መረጃዎች ሲገኙ እንዲህ ዓይነት የመከላከል ስራዎች
እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል፡፡
ዶ/ር ሽፈራው የቤንሻንጉል ተፈናቃዮች ጉዳይ በአገር ውስጥም በውጪም ያሉ የትምክህትና የጸረ ሠላም ኃይሎች መጠቀሚያ ሆኖ መክረሙን በመጥቀስ በእነሱ ምክንያት የወሰድነው ምንም ዓይነት እርምጃ የለም ብለዋል።

እነሱ ነገሩን በማጦዝ “20 ሺ የአማራ ተወላጆች ተፈናቀሉ፣አንድ አይሱዚ ሙሉ ሰው ገደል ገባ” እያሉ አዛኝ መስለው ሲቀሰቅሱበት መክረማቸውን ክፉኛ በማውገዝ እኛ ከሁለቱ ክልሎችና ከሕዝቡ ጋር በመሆን ችግሩን ፈትተነዋል ሲሉ አክለዋል።
ዶ/ር ሺፈራው ይህን ይበሉ እንጅ ተፈናቃዮች ንብረታቸው እንዳልተመለሰላቸው፣ ችግሩም እንዳልተፈታና ግጭት ይፈጠራል ብለው በስጋት ላይ እንዳሉ ኢሳት ባለፈው ሳምንት ተፈናቃዮችን አነጋግሮ መዘገቡ ይታወሳል።
source: ኢሳት ዜና:-

No comments:

Post a Comment