Wednesday, 22 May 2013

ከኢህአዴግ ተፈጥሮ የሚመነጨውን ሙስና ሥርዓቱን በመለወጥ እንጂ ዓመታትን ጠብቆ ከፍተኛ ባለስልጣናትን በማሰር መግታት አይቻልም!!!

May 22, 2013

Unknown
ከ33ቱ ፓርቲዎች የተሰጠ መግለጫ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆኑት የፌደራል ዋናው ኦዲተርና የፌዴራል የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሚያዚያ 22 እና ግንቦት 6 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም በቅደም ተከተል ሪፖርቶቻቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
በዋናው ኦዲተር የቀረበው የ2ዐዐ4 ዓ.ም በጀት ዓመት ኦዲት ሪፖርት በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ ከሕግ ውጭ የተፈፀሙ ጉድለቶችን ሲዘረዝር ወደ 1.4 ቢሊዮን ብር አለመወራረዱን፣ 353.6 ሚሊዮን ብር ደንብና መመሪያ ያልተከተለ ግዥ መፈፀሙን 3.5 ቢሊዮን ብር ባልተሟላ ሰነድ ወጪ መሆኑንና ከዚህም ውስጥ መከላከያ ባልተሟላ ሰነድ 3.2 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ይገልፃል፡፡ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ ብር 212.5 ሚሊዮን መጠቀማቸውንም ያሳያል፡፡

የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በበኩሉ በመንግሥት ባለስልጣናት የተፈፀመውን የመሬት ወረራ፣ በግብርና ታክስ አሰባሰብ ረገድ የሚፈፀመውን ሙስናና በኮሚሽኑ ስለተወሰደው ርምጃ ወዘተ የሚገልጽ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ የኮሚሽኑ ሪፖርት ሌላው ክፍል ያተኮረው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሁለት ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ፈጽመውታል ባለው የሙስና ድርጊት ነው፡፡ አቶ መላኩ ፋንታ (በሚኒስትር ማዕረግ) የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተርና ምክትላቸው፣ አቶ ገብረዋሕድ ወልደጊዮርጊስና ሌሎች በፈፀሙት ሙስና በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ክስ ለመመስረት መዘጋጀቱን ኮሚሸኑ ገልጿል፡፡

የሁለቱም ተቋማት ሪፖርቶች በዝርዝር ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር በይዘት አዲስ አይደሉም፡፡ የዋናው ኦዲተር (መስሪያ ቤት) ላለፉት በርካታ የበጀት አመታት ቁጥራቸው እጅግ በበዛ የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የመንግሥት በጀት ከታለመለት ዓላማ ውጭ በከፍተኛ መጠን እየባከነ መሆኑን ፓርላማው ጉዳዬ ባይለውም ያላመላከተበት ዓመት የለም ለማለት ያስደፍራል፡፡ ይህን ይዘት ያለው ሪፖርት ለዓመታት ከመደጋገሙ የተነሳም የዋናው ኦዲተር በመንግሥት መስሪያ ቤቶች የመንግሥት በጀት እየተመዘበረ ነው የሚለው ሪፖርት የተለመደ ሆኗል፡፡ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽንም ከተቋቋመበት ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ (በሪፖርቶቹም ሆነ በጋዜጣዊ መግለጫዎቹ) የመንግሥት ባለስልጣናትን (በአብዛኛው ትንንሾቹ አሳዎች የተባሉትን) በጥቂቱም ቢሆን በሙስና ሲከስና ሲያስቀጣ መቆየቱ የተለመደ ሆኗል፡፡ ሙስናው ግን ተባበሰ እንጂ አልቀነሰም፡፡

በሐገሪቱ የመንግሥት ባለስልጣናት በሙስና የመዘፈቃቸው እውነታ መባባሱን በብዙ ረገድ ማመልከት ይቻላል፡፡ የመንግሥት ጆሮና ሕጋዊ ርምጃ የተነፈጉ የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከዓመት ዓመት የሚሰሙ የበጀት ብክነትን የሚያመለክቱ ሪፖርቶችና የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በትንንሾቹ አሶች ላይ የሚመሰርታቸው ክሶች ሙስና መባባሱን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ገዢው ፓርቲና መንግሥት ቁርጠኛ ርምጃ መውሰዱ ቀርቶ ይፋ መግለጫ ለመስጠት የተቸገሩበትና የተባበሩት መንግሥታት አካላትን ጨምሮ አለም አቀፍ ተቋማት ባለፉት አስር ዓመታት ከ12 ቢሊዮን ዶላር (24ዐ ቢሊዮን ብር) የሚበልጥ ገንዘብ በሕገ-ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ መውጣቱን የሚገልፁ ሪፖርቶች ስለሙስና መባባስ ተጠቃሽ አስረጅዎች ናቸው፡፡ መንግሥትም በአደባባይ የኛ (የመንግሥት) ሌቦች ብሎ መናገሩ ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ በንግድና ኢንቨስትመንት ዓለም ከሚታሰበው (ከሚገመተው) ውጭ በአንድ ጀምበር ከምንም ተነስተው ራሳቸውን ቤተሰቦቻቸውንና ዘመዶቻቸውን በሀብት ማማ ላይ ያወጡትን ጥቂት ሚሊየነሮች እና ቢሊዮነሮች የመንግሥት ባለስልጣናትን መከረኛውና ጎስቋላው ሕዝብ ለይቶ ያውቃቸዋል፡፡ ‹‹የሙስና ሠፈር›› ሕንፃዎችን፣ የንግድ ድርጅቶችንና ቪላዎችን የማን እንደሆኑ ሕዝቡ አንድ በአንድ ያውቃል፡፡ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ‹‹የሙስና ሰፈሮች›› መብዛታቸውን ማን ከሕዝቡ ሊደብቅ ይችላል?

ይህ እየሆነ ኢህአዴግ ‹‹ዛሬም ሙስናን እየተዋጋሁ ነው›› ቢልም ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ ሆኖበታል፡፡ ኢህአዴግ የከበደው ራሱ የፈጠረውን የሙስና ምንጭ ራሱ ማድረቅ የማይችል በመሆኑ ነው፡፡ ዜጎች በብቃትና በነፃ ውድድር ለኃላፊነት የሚበቁበትን ሥርዓት ከመዘርጋት ይልቅ የፖለቲካ ታማኝነታቸውን ብቻ ዋና መመዘኛ ማድረግ የሙስና ምንጭ መፍጠር ነው፡፡ ነፃ የዳኝነት ሥርዓት አለመዘርጋት ለሙስና በር መክፈት ነው፡፡ የፕሬስና የሚዲያ ነፃነትን ማፈን፣ የመንግሥታዊ ተቋማትን ነፃነት መንፈግ፣ የሙስና ምንጭ መፍጠር ነው፡፡ ምክንያቱም ያለ እነዚህ ተቋማት ተሳትፎ ሙስናን መከላከልም ሆነ መግታት አይታሰብምና ነው፡፡
ከዚህም በመነሳት ኢህአዴግ ሙስናን በቁርጠኝነት ለመዋጋት ተፈጥሮው አይፈቅድለትም ለማለት ይቻላል፡፡ ኢህአዴግ የሚተማመነው በነፃ የዳኝነት ሥርዓትና በነፃ ሚዲያ አይደለም፡፡ በነፃ መንግሥታዊ ተቋማትና በነፃ ሲቪል ማህበራት አይደለም፡፡ በነፃና ፍትሓዊ ምርጫም አይደለም፡፡

 ኢህአዴግ የሚተማመነው ከእሱ ጋር ሆነው ምርጫ በሚያጭበረብሩ መካከለኛና ከፍተኛ ካድሬዎቹ ነው፡፡ ምርጫ ሲጭበረበር ‹‹ምርጫው ነፃና ፍትሓዊ ነው›› ብለው በሚመሰክሩ ‹‹ልማታዊ›› ባለሀብቶቹና ይህንኑ በሚያስተጋቡት ‹‹ልማታዊ›› ጋዜጠኞቹ (የፕሮፓጋንዳ ሰዎቹ) ነው፡፡ ዛሬ በእነዚህ ላይ ጨክኖ በቁርጠኝነት ፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ በተለይ በከፍተኞቹ ላይ ቢያፋፍም በቀጣይ ምርጫ ለማጭበርበር አጋር ከየት ይገኛል? ሙሰኛ ካድሬዎችና ‹‹ልማታዊ›› ባለሀብቶች ኢህአዴግን ይፈልጉታል፡፡ ኢህአዴግም እንዲሁ ይፈልጋቸዋል፡፡ ሕዝብንና አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት የፖለቲካ ቁማር ለመጫወት ሲል ግን ከመንጋ ሙሰኞች መካከል በጣት የሚቆጠሩትን የመስዋዕት በግ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ዘዴ በዙፋኑ ላይ ለመቆየት ይሻል፡፡ ለኢህአዴግ ፖለቲካና ሙስና መጣመሩ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡

ኢህአዴግ የሁል ጊዜ ጭንቀቱ በሆነው የዙፋኑ አጀንዳ በተጠመደበት ሁኔታ ከላይ እስከታች የተዘረጋው የሙስና ሰንሰለት ሀገሪቱን ክፉኛ እየጎዳት ነው፡፡ ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ሙሰኞቹ ባለስልጣናትና ተባባሪዎቻቸው ወደ ውጭ ባንኮች እያሸጋገሩ ነው፡፡ የሕዝቡን ማህበራዊ ሕይወት ለማሻሻል (ለምግብ ምርት፣ ለጤና አገልግሎት፣ ለንፁሕ ውሃ፣ ለመኖሪያ ቤት፣ ጥራት ላለው ትምህርት. . . ) መዋል የነበረበት ገንዘብ እየተዘረፈ የሕዝብ ጉስቁልና እየጨመረ ነው፡፡ በሙስና የተገኘ ሀብት ፍትሕን ለማዛባት እየዋለ ዜጎች ሰብአዊ መብቶቻቸው እየተጣሱ ነው፡፡ ሀገሪቱ 12 ሚሊዮን ዜጎችዋን በቋሚ ረሀብተኛነት (በምግብ እጥረት ተጠቂነት በሚባለው) ለለጋሽ አገሮች በረሀብተኘነት አስመዝግባ፣ ለሴፍቲኔት ምጽዋት ከስራቸው ወድቃለች፡፡ በራሳቸው አቅምና በነፃነት ለመሻሻል የሚጥሩ ነጋዴዎችና በለሀብቶች የእድሉ በር ተዘግቶባቸዋል፡፡ ዜጎች በሐገራቸው መንግሥታዊ አስተዳደርና የፍትሕ ሥርዓት ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ ሙስና ለፍትሓዊ የሀብት ክፍፍል ጠንቅ በመሆኑ ዜጎች በአደገኛ ሁኔታ አንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃና ሦስተኛ ደረጃ ወዘተ ዜጎች ሆነው ተከፍለዋል፡፡ ይህም ከሙስና ለሚመነጩ ወንጀሎች ሀገሪቱን አጋልጧል፡፡
ከዚህ አጠቃላይ ቀውስ ለመወጣት የሚቻለው ኢህአዴግ ‹‹ሙስናን እየተዋጋሁ ነው፡፡›› በሚለው የማስመሰያ ፕሮፓጋንዳ ሳይታለሉና ሙስናው የሥርዓቱ ብልሹ አስተዳደር ውጤት መሆኑን በመረዳት በኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ ሥርዓት እንዲገንባ የሚደረገውን ሕዝባዊ ትግል በሙሉ ልብ በመቀጠልና በማስፋት ነው፡፡
ከ33ቱ ፓርቲዎች የተሰጠ መግለጫ
ግንቦት 13 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment