Tuesday, 4 June 2013

ኢትዮጵያ ተነስታለች ! (ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም)

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም ከነጻነት ለሃገሬ

The long youth march to freedom and dignity has begun in Ethiopia. It is beautiful. 
እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ግንቦት 20 1983 መለስ ዜናዊና ሽምቅ ተዋጊዎቹ ከላሽኒኮቭ ደግነው የጅ ቦንቦች ታጥቀው አዲስ አበባን ወረው ገቡባት፡፡

 ወደ ከተማው ሲገቡ ዴሞክራሲን እናመጣለን፤ ከግፈበኛው የወታደራዊ አገዛዝ እንላቅቃለን የሚል ቱልቱላ ነበር ቃል ኪዳናቸው፡፡ የከተማው ነዋሪም በመለስተኛ ጉጉት በተስፋ አስተናገዳቸው፤ ተቀበላቸው፡፡ ላለፉት 17 ዓመታትም በላያቸው ላይ ተጭኖ ከነበረው የጭቆና አገዛዝ ለመላቀቅ ተስፋ በማየታቸው እጅጉን ተጽናንተው ያ አረመኔያዊ አገዛዝ ወደ ታሪክ መቀመቅ መውረዱ ተስፋቸው ነበር፡፡

እንደ ኢትዮጵያ አቆጣተር ግንቦት 25 2005 ከ100000 በላይ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሴቶችና ወንዶች ወጣቶች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፤የሃይሞኖት ነጻነት ፤የሰብአዊ መብት፤ ሕገ መንግስቱ እንዲከበር እና እንዲተገበር በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ በሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ነበር፡፡ስለወጣቱ ሥራ አጥነት፤የዋጋ ግሽበት፤ ሙስና ከሃገሪቱ እንዲወገዱ በማለት ሰልፍ ወጡ፡፡ ሰልፍ የወጡት የእጅ ስልኮቻቸውንና መፈክሮቻቸውን ብቻ አንግበው ነበር፡፡ ስለ ነጻነት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ዘመሩ፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ሃገሬ››የሚለውን ዜማ ከዳር እስከ ዳር አስተጋቡት፡፡ ስለነጻነታቸው፤ ስለወላጆቻቸው፤ ስለ እህትና ወንድሞቻቸው፤ ስለ ሕዝቡ ነጻነት በሰልፍ በሰላማዊ መንገድ በጎዳናዎች ላይ ተመሙ፡፡ የማይረሳና ታሪክ የማይዘነጋው ትመት!

በኢትዮጵያ የጠነከረ የወጣቱ ሰላማዊ ሰልፍ ለነጻነትና ለክብሩ አሀዱ ተብሎ ተጀመረ፡፡ ውብ ነው! ቆንጆ ነው! ምክንያቱም ሰላማዊ ነበርና!! ውበት የሞላው ነበር ምክንያቱም መንስኤው የሃገር ፍቅር፤የአንድነት እርስ በእርስ ፍቅር፤የአንድ እናት ኢትዮጵያ ልጆች ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ‹‹ከእንግዲህ ባርነት በቃን፤ መገዛት በቃን መራብ መሰደድ በቃን፤ ግፍ መረረን፤ ውሸት ታከተን፤> በማለት በአንድነት በመዘመር የተካሄደ ሰልፍ ነበር፡፡ ይህ ዕለት ግንቦት 25 ኢትዮጵያ በላይዋ ላይ ከተመረገባት ክፉ ደዌ ለመላቀቅ፤ ከገባችበት የመገዛት ጉረኖ በልጆችዋ ክንፍ ተጠልላ የምትወጣበትን ያሳየ ትልም በመሆኑ በታሪክ የማይረሳ ዕለት ሆኖ ይዘከራል፡፡

መታሰብ ያለበት ጉዳይ በስልጣን ላይ ያሉት ባለጊዜዎች ይህን ሰላማዊ ሰልፍ ሲፈቅዱ ከበስተጀርባው ምን እንደደገሱ ማወቅ ያችቸግረኛል፡፡ባለፈው ጊዜ በግንቦት 7/1977 የምርጫ ካርዳችን ተዘረፈብን ብለው ሰላማዊ ሰልፍ ከወጡት ሰላማዊ ሰልፈኞች መሃል 193 ንጹሃን በግፍ በአደባባይ በአንጣጥሮ ተኳሦች ሲጨፈጨፉ 763 ሰላማዊ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡
እንደእውነቱ የገዢው መደብ አባላት ምንም ይምከሩ ምንም፤ ያሻቸውን ተንኮል ያውጠንጥኑ ቁም ነገሩ እሱ አይደለም፡፡ እውነታው በተጣመመ የተንኮል አስተሳሰብ አካሄድ የተፈቀደው ሰላማዊ ሰልፍ ለዕውነተኛና ሕዝባዊና ሀገራዊ ጉዳይ መከናወኑ ነው፡፡ እውነትን ለመተግበር መቼም ቢሆን አይረፍድም፡፡ ሃሰትን ለመተግበር ግን በጭራሽ ትክክለኛ ወቅት ብሎ ነገር የለም፡፡

እነዚህ በስልጣኑ ማማ ላይ ያሉት ከተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ትንሽ የተማሩ ይመስለኛል፡፡ ከወጣቱ ትውልዳችን ምንም የምንፈራው ነገር አይኖርም፡፡ ልጆቻችን ናቸው፡፡ የወደፊት ተስፋችን ናቸው፡፡ በምን ምክንያት ነው ልጆቻችንንና የፊት ተስፋችንን የምንፈራው?  ወጣቶቹ ልጆቻችን በሰላማዊ መንገድ በአደባባይ የወጡት እኮ ለችግራችን ሰሚ አጣን ብለው ነው፤ተረሳን በማለት ነው፡፡ ያሁኖቹ ዘመነኛ ገዢዎች እኮ በ1970ዎቹ ወደ ጫካ ሲገቡ ያስመረራቸው ጉዳይ አሁን ሰልፍ የወጡት ልጆቻችን የተሰማቸው ስሜት ስላደረባቸው ነበር፡፡ 

ያሁኖቹ ወጣቶች ሰልፍ የወጡት እኮ በተናጠልና በየአጋጣሚው ችግሮቻችን ብናነሳ ብንጥል ብንጮህ  ምሩታችንን ብናዜም ጨርሶ ሰሚ በመጥፋቱ በሕብረት ሆነን ሺህና አሰርት ሺህ ሆነን በሕብረት ነጻነትን ሰብአዊ መብትን ፍትህን ዴሞክራሲን እኩልነትን አንድነትን ብናዜም ብንጮህ ድምጻችን ከፍ አድርገን ብናስተጋባ  ማንንም በጉልበቱ ተመክቶ ጆሮ ዳባ ልበስ ያለን ሃይል ጆሮውን እንዲከፍትና እንዲያዳምጥ ማድረግ እንችላለን በማለት ተስፋ ኣደርገው ነው፡፡
ዕውነታው ወጣቱ ትውልድ ዛሬ ሕይወቱ እየተበላሸ፤ ራዕያቸው በመቃቃርና ተስፋ ቢስነት እየከሰመ መሄዱ ተሰምቷቸዋል፡፡ ስለዚህም በታጠቁ አነጣጣሪ ተኳሦች ከመገደል መሸሽን፤ ከደህንነት ወከባ መደበቅን፤ ከታጠቁ ሕሊና ቢስ ፖሊስ ተላላኪዎች መከለልን ሳይሆን ፍላጎታቸው መደመጥ መሰማት ነው፡፡ ኢትዮጵያ እኮ የወጣት ልጆቿ ሃገርና መኖርያ ነች!

ጌን ሻርፕ፤አልበርት አይነሽታይን ተቋም፤ የሰላማዊ ትግል አራማጅ ድርጅት መስራች፤ አምባገነኖች እንደሚያስቡትና እንደቅዠት እምነታቸው ያህል ሃይለኞች አይደሉም፤ሕዝቦችም ቅዠተኞቹ እንደሚያስቡት ያህል ደካሞች አይደሉም፡፡ አምባገነኖች መግዛት የሚችሉት የሚገዙት ሕዝብ፤ ሃይለኛና የማይነኩ ናቸው ብሎ ስለሚያስብ ብቻ ነው፡፡ አምባገነኑ ምንም ያህል ሃይለኛም ቢሆን ከሕዝቡ መጠነኛም ቢሆን ድጋፍን እስካላገኘ ድረስ ጨርሶ መግዛት አይችልም፡፡ ምናልባትም በመመርያ ድጋፍ ኖሮት ቢሆንም  ያም ቢሆን ተኖ ካለቀ የትየለሌ ነው፡፡ አሁን ያለውን ገዚ መንገስት የሙደግፉ በጣት የሚቆጠሩ አሉ፡፡ ያም ቢሆን ገዢው መንግስት ለውጥን ለመቀበል ፈቃደኛነቱ እስካልኖረ ድረስ ገዝቶ ለመኖር ያለው እድል መቀጨጩን ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡

ለውጥ አይቀሬ ነው፡፡ ሚዛናዊ የሆነ ለውጥ ደግሞ ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም ግን ለለውጥ ዘልአለማዊና የማይታለፉ እውነታዎች አሉ፡፡ ዶር ማርቲን ሉተር ኪንግ ‹‹ለውጥ አይቀሬ በሆነው ሽክርክሪት ላይ ሳይሆን ቀጣይነት ባለው ትግል የሚገኝ ነው፡፡ ስለዚህም ወገባችንን ጠበቅ አድርገን ለነጻነታችን መስራት መጣር ይገባናል›› ብለዋል፡፡ የኢጥዮጵያ ወጣቶች ቀበቷቸውን አጥብቀው በመታገል ላይ ናቸው፡፡ ስለዚህም፤በውይይት፤በግልጽነት፤በመግባባት፤በማሕበራዊ ምክክር፤ ከወጣቱ ጋር አብረን መቆምና ትግሉ ጎራ መግባት ይገባናል፡፡

ዕውነተኛው ለውጥ የሚጀመረው በየአንዳንዳችን ልብ ውስጥ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሃይለኛውም ሆነ ደካማው፤ በፖለቲካ አቋምና ስርአት ሊሆን አይችልም፡፡ ማንም የራሱን ሕሊና መለወጥ ያልቻለ በምንም መልኩ ጥላቻን ወደ ፍቅር፤ከቁጠኝነት ወደ መግባባት፤ከልዩነት ወደ አንድነት፤ከጥርጣሬ ወደ መተማመን፤ ከቅሬታ ወደ ይቅር ባይነት፤ ከቀላማጅነት ወደ ታማኝነት፤ ከተስፈንጣሪነት ወደ መለስተኛነት፤ ከመጀነን ወደ ሰብአዊነት፤ከዝምታ ወደ ራስን መግለጽ፤ከመሰላቸት ወደ ወደ መቻቻል ወዘተ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ሕሊናና ልብ በአንድነት መስራት አለባቸው፤ ምርጫ ከተባልን ግን ለልቦናችን መንገዱን ሁሉ ማስተካከል ግድ ነው፡፡ ለውጥ ለውጥን የምናመጣበት ምርጫ ነው፡፡

 ፕሬዜዳንት ኬኔዲ እንዳሉት፤ ‹‹ለውጥን ለመቀበል ፈቃደኛነት የሌላቸው፤ አመጽን አይቀሬ ተተኪ ያደርጉታል›› ምን ጊዜም ሰላማዊውን ጎዳና ምርጫችን እናድርግ፡፡  ላለፉት ዓመታት በእያንዳንዱ ሳምንት በኢትዮጵያ ሰላማዊ ለውጥ እንደሚቻል አስገንዝቤያለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በትንሳኤዋ እንደገና እንደምታበራ ተናግሬያለሁ፡፡ ይህም የሚፈጸመው በደፋር ጀግና ቆራጥ ልጆቿ ክንፎች ጠለላ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብልህ ወጣቶች፤ችሎታ ብልሃት ዘዴ እውቀት አንዳችም ጥርጣሬ የለኝም፡፡ በዚህም ብቃታቸው ሰላማዊውን ትግል ሳያቋርጡ እንደሚያካሂዱ እምነቴ የጸና ነው፡፡

ግንቦት 25 ቀን፤ በታሪክ መዝገብ የኢትዮጵያ ወጣቶች ቀለመ ደማቅ የሆኑትንና ያሸበረቁትን የዘር፤ የሃይሞነት፤ታሪካዊ  ክንፎቻቸውን ዘርግተው በውህደት የወጡበት ቀን ትባላለች፡፡ በድምጾቻቸው ተናገሩባቸው፡፡ በዴሞክራሲ፤በሰብአዊ መብት፤በነጻነት፤ ነጋሪት ጉሰማ እየተመሩ ተመሙ፡፡ ከእምግዲህ የኢትዮጵያን ወጣቶች ማዳከም ከንቱ ምኞት ነው፡፡ ልትመቷቸው፤ ልታጥሏቸው ይቻላችሁ ይሆናል፡፡ ግን እንደወደቁ ማቆየት ግን ከንቱ ውዳሴ ነው፡፡ የማይቻል ሙከራ ነው፡፡ ከወደቁበት እየተነሱ ሲንገዳገዱም እየተደጋገፉ በመነሳት ትግላቸውን ይቀጥላሉ፡፡

 የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት፤ ‹‹ገዢውን መንግስት በተደጋጋሚ የታሰሩትን ሰላማዊ ሰዎች የተለጠፈባቸውን የፈጠራ ታርጋ አውልቆ እንዲፈታቸው አጥብቀን ጠይቀናል፤በሃይሞኖቶች ማሀል ጣልቃ እንዳይገባ አሳስበናል፤ እነዚህ ጥየቄዎች እስካልተመለሱ ድረስና በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ውስጥ ለውጥ ካልታየ፤ ተጨማሪ የሰልፍ ጥሪዎች አድርገን እንወጣለን፤ በሰላማዊ መንገድ እንቀጥላለን፤ሠላማዊ ትግሉ ፍትሕ በጠራ ሰማይ ላይ እንደምታበራው ጸኃይ ብርሃን እስኪሆን ድረስ ቀጣይ ነው፡፡›› በማለት አሳስቧል

ኢትዮጵያ ተነስታለች !
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንጸባራቂ ማዕድ ትነሳለች ትገናለች
ከፈላጭ ቆራጭ ስርአት ተላቃ
የግድበ አፍሪካ ምድር እንደሚበራው የበጋ የንጋት ፍንጣቂ
በአፍሪካ ምሽት ሰማይ እንደምትበራው የጨረቃ
ብርሃን አንቂ ኢትዮጵያ ትንሳኤዋ ያበራል ትገናለች::
ኢትዮጵያ ከራስ ደጀን ጉብታ ጫፍ ትንሳኤዋ ይታያል
እስከ ኪሊማንጃሮ ዘልቆ ይጠራል
ከፖለቲካው አረንቋ መታወቂያነት
እስከ ሀገራዊ ኩራት በልዩነት
ኢትዮጵያ አስከብራ የሁሉንም ማንነት ትነሳለች::
በአፍሪካ ምድር የነጻነት ብርሃኗን ትረጫለች
የሊቃውንት ሃገር ኢትዮጵያ ከመንደርተኛ አዋቂዎች በላይ ተንብያ
ህዝቦቿ ተሰባስበው ተዋህደው ተፋቅረውና ተግባብተው
ሰብአዊነትን ወግነው አንድነትን መቻቻልን አንግበው
ኢትዮጵያ ትነሳለች ትገናለች::
ኢትዮጵያ የነግህ የአፍሪካ ተስፋ
በትንሳኤዋ የረገጧትን የጨፈለቋትን  አልፋ
ቅጥፈታቸውን ጭካኔያቸውን ሙስናቸውን
ያን ያለፈ ዘመናቸውን ከነምኞታቸው ገንዛ በብረት ሳጥን
የሕግ የበላይነትን አስከብራ፤ኢትዮጵያ እንደ ጸሃይ ታበራለች::
በምድሯም ሰላም እስከ ዘልዓለሙ እንዲሰፍን ታደርጋለች
የኢትዮጵያ ትንሳኤ በማይደፈሩት ሃቀኛ ወጣቶቿ
ከፍ ትላለች ተደግፋና ተሞሽራ በልጆቿ
ኢትዮጵያ እስከማዕዜኑ ትገናለች
ለወጣቱ ትውልድም  የዘልአለም ቤቱ ትሆናለች::

*የተቶረገመው ጽሁፍ (translated from):
http://open.salon.com/blog/almariam/2013/06/02/ethiopia_has_arisen

No comments:

Post a Comment