* ዶ/ር ነጋሶ….. <አማራም ቢሆኑ ውስጡ ገብቼ አንድነትን አጠናክራለው> የሚል አቋም አላቸው።
* ቡልቻ “አማራ” የሚለውን ቃል ተጠቀመ ብለው [አንድነቶች] ሊከፋቸው አይገባም። ታዲያ እኔ ምን ብዬ ልግለጣቸው? እዛ ያሉትን እኔ የማውቃቸው በአማራነታቸው ነው።
* በአንድነት ውስጥ ያሉ አማራዎች ግን የጀነራል፣ የሀገረ ገዢ፣ የአምባሳደር የአስተማሪና የሲቪል ሰርቪስ ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው።
* አፄ ቴዎድሮስም ቢሆን በጀግንነቱና ወንድነቱ እኛ ኢትዮያውያን ብቻ ሳይሆን መላ አፍሪካ ሊኮራ ይችላል። ነገር ግን እንደ ኦሮሞና ደቡብ ከእሳቸው ጋር አንተዋወቅም።
* አቢሲኒያ የሚባል ሀገር ነበር። ምናልባት ሶስት ሺው ከዚያ ጋር ተያይዞ ሊገለፅ ይችላል። የዛሬው ደቡብ፣ ምስራቅ ምዕራብ አቢሲኒያ አልነበረም።
* [አፄ ምኒልክ ወኪሎቻቸውን በመላክ] ዛሬ የምናውቃትን ኢትዮጵያን ፈጥረዋል።…..ነገሩ ሁሉ የሆነው በጉልበት ነው። በእርግጥ ጀርመንም፣ ጣሊያንም ይሄው ልምድ በመኖሩ በዚህ ላይ እኔ ቅሬታ የለኝም።
የቀድሞ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ፡፡
ሰንደቅ፡- በአሁኑ ወቅት የመድረክና የአንድነት ፓርቲ ግንኙነት እንዴት ይገመግሙታል?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- በመጀመሪያ ልዩነት የተነሳው አንድነት መድረክን እገመግማለሁ ብሎ መነሳቱ ነው። በእኔ እምነት አንድነት ፓርቲ መድረክን ሊገመግም አይገባውም። ምክንያቱም አንድነት እራሱ የመድረክ አንዱ አካል ነው። መድረክ በራሱ እንጂ በሌላ ፓርቲ ሊገመገም አይገባም። አንድ አባል ፓርቲ አፈንግጦ ወጥቶ ከውጪ እንደሌለ ፓርቲ መገምገም ትክክል አይደለም።
ሰንደቅ፡- ግምገማው መድረክ ይበልጥ እንዲሰራና እንዲሻሻል በማሰብ መካሄዱን የአንድነት ፓርቲ ሲገልፅ ቆይቷል። ከዚህ አንፃር ግምገማውን ከበጎ ጎን ማየቱ ተገቢ አልነበረም?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- በእርግጥ ትክክል ነው። ነገር ግን ብቻቸውን ሳይሆን ከቀሩት የመድረክ አባል ፓርቲዎች ጋር በመሆን ተመካክረው መገምገም ይገባቸው ነበር። አሁን የሌሎቹ ፓርቲዎች አስተያየት ባልተካተተበት ሁኔታ ነው ገመገምን ያሉት። ድምፃቸውም የተሰማው የገምጋሚዎቹ ብቻ ነው።
ሰንደቅ፡- የመድረክን እንቅስቃሴ በቅርብ የሚከታተሉ ሰዎች አንድነት መድረክን የገመገመው ከመድረክ ጋር አብሮ መቀጠል አዋጪ መስሎ ስላልታየው ነው ይላሉ፤ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- መድረክን ስናቋቁም እኔም ነበርኩ። ኦፌዴንን ይዤ ነው ከጓደኞቼ ጋር መድረክ ውስጥ የገባሁት። ወደ መድረኩ የገባነውም ተማክረን ነበር። የምክራችን የጀርባ አጥንት የነበረው ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በአንድነት እንድትኖር ከተፈለገ ወገኖቿን ሁሉ ይዛ መቀጠል አለባት። ይህ ማለት ቤት አለምሰሶ እንደማይቆም ሁሉ፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሁሉም ካልተባበሩ እና ካልደገፉዋት ኢትዮጵያ ሀገር ልትሆን አትችልም። እና በወቅቱ በዚህ ላይ መክረን፣ ዘክረን፣ ገብቶን፣ ሁላችንም አምነንበት ነበር። ኢትዮጵያ “ኢትዮጵያ” ተብላ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ታላቅ ሀገር ሆኗ እንድትኖርና እንድትከበር የሁሉም ሕዝብ ትብብር፣ አንድነትና መልካም ስሜት እንዲሁም ፍቅር መኖር አለበት። አለበለዝያ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አትኖርም። ስለዚህ መድረክን የመሰረቱት ፓርቲዎች አንድነትን ጨምሮ ይሄንን በደስታ ተቀብለው፤ “ያላችሁት ትብብር መቶ በመቶ አስፈላጊ ነው” ብለው መድረክን ጀመርነው። አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ተስፋ መድረክ ነው። አንድ ፓርቲ ተነስቶ ገንዘብ ከውጪ መጥለቶለት፣ ከመሬት ተነስቶ ምንም ቢያደርግ አይሆንለትም። ሁሉም ሕዝብ የደገፈው መንግስት ነው መቆም የሚችለው። ሕዝቡ የደገፈው ማለት የአብዛኛውን ሕዝብ ድምፅ ያገኘ ማለት ነው። በአምባገነንነት ቢሆን አይችልም። አምባገነንነት ከቀጠለ ነገም አንድ ሰው በግድ ልክ እንደ አፄ ቴዎድሮስ አይነት ተነስቶ ልግዛ ሊል ይችላል።
ሰንደቅ፡- አፄ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ አንድነት መድከማቸው በታሪክ ይነገራል። እርስዎ ይሄንን እንዴት ነው የሚረዱት?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- አፄ ቴዎድሮስ እኔ የምረዳበት መንገድ የተለየ ነው። አፄ ቴዎድሮስ ለእንግሊዟ ንግስት የሚፅፉትን ደብዳቤ ብታይ ለኢትዮጵያ አንድነት መቆማቸውን እንድትጠራጠር ያደርግሃል። አፄ ቴዎድሮስ የዛሬውን ምስራቅ፣ ደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚያውቁት አይመስለኝም። በእኔ እምነት በኢትዮጵያ ታሪክ እስከዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያን አንድ አደርጋለሁ ብሎ የተነሳ ፓርቲ አለ ብዬ አላምንም። ኢትዮጵያ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ፣ ጉራጌ፣ ኮንታ፣ ሀድያ፣ አፋር ፣ ሶማሌ፣ ትግሬ እያለ ኢትዮጵያ እስላም፣ ኢትዮጵያ ክርስቲያን ነች ካላለ ኢትዮጵያ አንድናት ማለት አይቻልም። አፄ ቴዎድሮስም ቢሆን በጀግንነቱና ወንድነቱ እኛ ኢትዮያውያን ብቻ ሳይሆን መላ አፍሪካ ሊኮራ ይችላል። ነገር ግን እንደ ኦሮሞና ደቡብ ከእሳቸው ጋር አንተዋወቅም። አቢሲኒያ ማለት ቀርቶ ደቡብን አጠቃሎ ኢትዮጵያ ከተባለች በኋላ ነው መተዋወቅ የጀመርነው።
ሰንደቅ፡- እንደ አንድ የፖለቲካ ልሂቅ “ኢትዮጵያ የሶስት ሺህ ታሪክ አላት” መባሉን አይቀበሉትም ማለት ነው?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- አቢሲኒያ የሚባል ሀገር ነበር። ምናልባት ሶስት ሺው ከዚያ ጋር ተያይዞ ሊገለፅ ይችላል። የዛሬው ደቡብ፣ ምስራቅ ምዕራብ አቢሲኒያ አልነበረም። እርግጥ እንደ ሕዝብ የሚጋራው ነገር ሊኖር ይችላል። አመጋገብ፣ ባህል፣ ኪነጥበብ፣ ወንዝ ይጋራል። ነገር ግን አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ አናውቅም። እኛ የምናውቀው ጎሳ ነበር። ሰሜኖቹ አፄ ቴዎድሮስ ታላቅ መሪ ነበሩ፤ ከአፍሪካም ለመጀመሪያ ጊዜ ፈረንጅን የተቋቋሙ ስለሆኑ በታሪካቸው እንኩራ ቢሉ ደስ ይለኛል። ነገር ግን አፄ ቴዎድሮስ እንኳንስ ከሰሜን አልፈው ቦረና ድረስ ሊደርሱ ቀርቶ ከጎንደርም አልፈው ሰሜን ሸዋም አይታወቁም ነበር። ይህ ሲባል ግን ሸዋን ለማስገበር ጥረት አላደረጉም ማለት አይደለም። ከአፄ ቴዎድሮስ በኋላ የመጡት አፄ ምኒልክ ከሸዋ ተነስተው ሀረር ድረስ ሄደዋል። ከዚያም በኋላ ጅማና ወለጋ ድረስ እሳቸውም ባይሄዱ ወኪሎቻቸውን፣ እነ እራስ ጎበናን በመላክ ዛሬ የምናውቃትን ኢትዮጵያን ፈጥረዋል። እና ከዚያ ጊዜ በኋላ ነው ኢትዮጵያ የተፈጠረችው። በዚያም ጊዜ ቢሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን በፍቅርና በደስታ ኢትዮጵያን ተቀላቀሉ ማለት አይደለም። ነገሩ ሁሉ የሆነው በጉልበት ነው። በእርግጥ ጀርመንም፣ ጣሊያንም ይሄው ልምድ በመኖሩ በዚህ ላይ እኔ ቅሬታ የለኝም። እንደውም ትክክል ነው።
ሰንደቅ፡- አንድነት ፓርቲ ኢትዮጵያን በብሔር፣ በጎሳ መከፋፈል ለሀገሪቱ አንድነት አደጋ ነው በማለት በብሔር መደራጀት ዲሞክራሲያዊ መብት ቢሆንም አደረጃጀቱ ግን አይጠቅምም የሚል አቋም አለው እና. . . .?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- ብሔር የሚለውን ነገር እንተው ማለት እንዴት ሊሆን ይችላል? ሲዳሞ “ሲዳሞ” መባሉን ይተዋል? አማራስ ቢሆን “አማራ” አልባልም ይላል? የሚል አይመስለኝም። ማንም ሰው ታሪኩንና ቋንቋውን ተከትሎ “እኔ እንዲህ ነኝ” ቢል ምን ችግር አለው። ችግር የሚሆነው “እኔ እንዲህ ነኝ” የሚለው ለመለያየትና ለመጣላት በር እንዲከፍት ያደረግነው ሲሆን ነው። መድረክ ቅይጥ ቢሆን ምን ችግር አለው። ልዩነታችንን አምነን በቆየን ቁጥር ጥንካሬአችንም አስተማማኝ ይሆናል። ልዩነታችንን ለወዳጅነት ካልተጠቀምንበት ጠላት እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል። ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አማራ ወዘተ የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት ነው። ኢትዮጵያ እንደ አንድ መኪና ብትመስላት መኪና ሊሽከረከር የሚችለው ሁሉም አካላቶቹ ሲሰሩ ነው። ኢትዮጵያም ወደፊት ልትራመድ የምትችለው ሁሉንም ሕዝቦቹን መጠቀም ስትችል ነው። ስለዚህ ቡልቻ “አንድነት አማራ አለ” እያሉ ከማኩረፍ ተቻችለን፤ ለምንስ እንዲህ አለ እያሉ በቅንነት እየፈተሽን ወደፊት መራመድ ይሻላል።
ሰንደቅ፡- በእርግጥ እርስዎ የአንድነት ፓርቲን “የአማራ ፓርቲ” ያሉበት መነሻ ምንድ ነው? ለዚህ አባባልዎት ማረጋገጫ አቅርቡ ቢባሉ ምን ሊያቀርቡ ይችላሉ?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ስለአማራ ብሔር ምንም መጥፎ ነገር አልተናገርኩም። ያልኩት ምንድነው መድረክ ውስጥ አንዳንድ ፓርቲዎች የገንዘብ ጉልበት አላቸው፤ ምክንያቱም አሜሪካን ሀገር ያለ ኢትዮጵያዊ አማራም ሆነ ኦሮሞ እንዲሁም ሲዳማና ትግሬ የኢትዮጵያ ፓርቲ አንድ ይሁኑ በሚል በአጋጣሚ አንድነት ፓርቲ ስላወቁ ለአንድነት ፓርቲ ገንዘብ ይልካሉ። እና እኔም በጽሁፉ “አንድነቶች ገንዘብ አለን ብላችሁ አትቁሙ ፤ ከሌሎቹ ተደባለቁ፣ ባገኛችሁት ገንዘብ ሁላችንንም ያሳተፈ ስብሰባ እንጥራ፣ በጋራ ቢሮ እንከራይ ብያለሁ። ምክንያቱም የመድረክ አባል ፓርቲዎች እንደ አንድት ገንዘብ የላቸውም። እናም አንድነቶች የምታገኙትን ገንዘብ ለአንድታችን አውሉ ብያለሁ። ምክንያቱም መድረክ ብቻ ነው የኢትዮጵያን ወገኖች ያሰባሰበው፤ ሰው በአግባቡ አልተገነዘበውም እንጂ መድረክ ኃይለኛ ስራ ነው የሰራው። ማንም ተነስቶ ሰልፍ ቢጠራ ዋጋ የለውም።
ሰንደቅ፡- መድረክ ለአራት ዓመታት ቢቆይም አባል ፓርቲዎቹ በፌዴራሊዝም እና በመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ላይ መስማማት ባልቻሉበት ሁኔታ እንዴት መቀጠል ይችላሉ?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- ተሳስተሃል። በኢትዮጵያ ሁለትን ብሔራዊ ቋንቋ ይኑር ብሎ መድረክ ተስማምቷል። መድረክ መሬት አይሸጥም ብሎ ተስማምቷል፣ መድረክ የፌዴራሊዝም የመንግስት አስተዳደርን እንደሚቀበል አረጋግጧል። ለዚህ ሁሉ የተፃፈ ሰነድ አለ። አሁን አንዳንድ የአንድነት ሰዎች በአቋራጭ ሌላ ነገር እያደረጉ ነው። አዝናለሁ ሁሉም ወዳጆቼ ናቸው። ነገር ግን እኔ የምናገረው ለአንድነታችን፣ ለጥንካሬያችንና ለአሸናፊነታችን አንድ መሆን አለብን በማለት ነው። ቡልቻ “አማራ” የሚለውን ቃል ተጠቀመ ብለው ሊከፋቸው አይገባም። ታዲያ እኔ ምን ብዬ ልግለጣቸው? እዛ ያሉትን እኔ የማውቃቸው በአማራነታቸው ነው። ይሄን ቃል መናገሬም አማራን ለመውቀስ አይደለም። እንደውም አንድነቶች በመድረክ ውስጥ መኖራቸው በጣም ጥሩ ነው። ደቡቦች እና ኦሮሞዎች በአገዛዝ ውስጥ አልነበሩም። በአንድነት ውስጥ ያሉ አማራዎች ግን የጀነራል፣ የሀገረ ገዢ፣ የአምባሳደር የአስተማሪና የሲቪል ሰርቪስ ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። በተዋረድ የገዢዎች ልጆች ናቸው። እና እነዚህን ሰዎች በመድረክ ውስጥ ልንጠቀምባቸው ይገባል። ቢሰድቡን እንኳ ችለን ወደነሱ መቅረብ ይገባናል። እና አማራ ነን የምትሉ ሰዎች አባካችሁ መድረክን አታዳክሙ በማለቴ “አማራ” የምትል ቃል በመግባቷ ትርጉሙ ተዛብቷል። የከተማ ሊህቃን ያልኩትም ትክክል ነው። ይሄ ደግሞ ሊያስከፋቸው አይገባም። በዚህ አገር የከተማ ሊህቃን ከሚባሉ አንዱ እኔም ልሆን እችላለሁ። በዚህ ለምን ይከፋሉ ፤ አልጠላዋቸው፣ አልቀናሁባቸው እና ገዢ ተገዢ እያልን መናናቁን ትተን ለሀገራችንና ለራሳችን ማሰብ አለብን። አፄ ኃይለስላሴ ትክክለኛዋን ኢትዮጵያ እየገለፁ ቢመሩ ኖሮ የሀገራችን አንድነት ከብረት በላይ በጠነከረ ነበር።
ሰንደቅ፡- በነገሮዎት ላይ አፄ ኃይለስላሴ “የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው” ስለሚባለው ነገር የሚያውቁት ነገር አለ?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- እንደው በዋዛ የሚነገር እና ቁም ነገር የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ የማንንም ደም መርምሮ የሚያውቅ ሰው የለም። ሕዝቡ እንደሚያምነውና እንደሚያውቀው የራስ መኮንን ጉዲሳ ልጅ ናቸው ይባላል። አቶ ጉዲሳ ደግሞ ዶባ ሰሜን ሸዋ ውስጥ የሚነሩ ኦሮሞ ናቸው። እና አፄ ኃይለስላሴ ኦሮሞነት አለባቸው ይባላል። ኦሮሞነት ስላላቸው የኦሮሞን ታሪክና ባህል አላቸው ማለት ግን አይደለም።
ሰንደቅ፡- አፄ ኃይለስላሴ ኦሮሞኛ ቋንቋ ይናገሩ ነበር?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- እኔም አነጋግሬአቸው አውቃለሁ። አፄ ኃይለስላሴ ኦሮሞኛ ቋንቋ በደንብ ይችላሉ። ነገር ግን ሀረር እንደኖሩ አማራዎች ነበር ኦሮምኛን የሚናገሩት። ይሄ ደግሞ የጠራ ኦሮምኛ አልነበረም።
ሰንደቅ፡- አንድነት ፓርቲን ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንደሚመሩት እያወቁ፣ በስራ አስፈፃሚ እና በብሔራዊ ምክር ቤት ውስጥ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መኖራቸውን እያወቁ “አንድነት ፓርቲን የአማራ ፓርቲ ማለትም የእነ ዶ/ር ነጋሶን ሞራል መጉዳት አይሆንም?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- የአንድነት ፓርቲ የአማራ ፓርቲ ናቸውና እንጥላቸው ነው ያልኩት? ይሄስ ቢባል ምን አለበት (Identification) ያስፈልጋል። ማንም ሰው ማንነቱ መታወቅ አለበት። ዶ/ር ነጋሶ እኔ በማምነው ሁኔታ ወደ አንድነት የገቡት በእርግጥ እሳቸው የሄዱበትና እኔ የምሄድበት የአንድነት መድረክ የተለየነው። እሳቸው አማራም ቢሆኑ ውስጡ ገብቼ አንድነትን አጠናክራለው የሚል አቋም አላቸው። እኔ ደግሞ በብሔራችን የፈጠርናቸው ፓርቲዎች ስላሉ እነሱን ይዘን እንግባ ያልኩት። እና ዶክተር ነጋሶ በውስጡ ገብቼ ሲሉ እኔ ከውጪ ወደውስጥ በሚል ስለሆነ ሞራላቸው የሚጎዳ አይመስለኝም።
ሰንደቅ፡- እንደሚያውቁት ባለፉት ሃያ ዓመታት በአማራ ሕዝብ ስም የመላው አማራ ሕዝብ ደርጅት (መዐሕድ) ውጪ ሌላ ፓርቲ በሕዝቡ ስም ሲመሰርት አይታይም። የክልሉ ተወላጆችም በአመዛኙ በኢትዮጵያዊነት ስም በሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ውስጥ ሊሳተፉ ይስተዋላል። እርስዎ ይሄንን ነገር አይተውታል?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- እውነትህን ነው። ይሄ ዝንባሌ ጎድቶናልም ጠቅሞናልም። ጉዳቱ እንደ የአማራ ስብስብ ፈንጠር ብለው “እኛ ነን መሪ” ብለው ባለመነሳታቸው ጥሩ ስራ ሰርተዋል ማለት ይቻላል። ነገር ግን “በሁሉም ነገር እኛ ነን ቀዳሚ” ብለው ፓርቲ መስርተው ቢነሱ የቀረው ሕዝብ ይሸሻቸዋል። የአሁኑንንም ያል አይጠጋቸውም። በወለጋ፣ በሲዳሞ፣ በሀረር አይመርጡም። እንደዚህ ካሉ ወደድሮ ገዢ መደብ እንመለሳለን። ስለዚህ ብልጠታቸውን አደንቃለሁ። “የመላ አማራ” ተብሎ ፓርቲ ሲቋቋም ሰው ሁሉ ተሳቀቀ። ምክንያቱም ሸዋ ላይ አማራውና ኦሮሞው ተደባልቋል። እናም ፓርቲው ብዙም አልገፋበትም። አሁንም ደግሜ የምናገረው “አማራ” አትበል ቢሉኝም የድሮ ገዢ መደብ ልጆች ዛሬ ለእኛ ጠቃሚ ናቸው ብዬ አምናሁ። ለምን ብትል የገዢ መደብ ልጆች በመሆናቸው እውቀት ቀምሰዋል ይጠቅሙናል። አሁንም ከነሱ ጋር መስራት አለብን። ስለዚህ ገንዘብ ስላገኙ ብቻ ብቻቸውን መሮጥ የለባቸውም። አለበለዚያ አንድነት ፓርቲ ብቻቸውን ኢትዮጵያን ሊመስል አይችልም። አሁን ባለው፣ ድሮም በነበረው ነባራዊ ሁኔታ አንድነት አሁን ባለው አደራጀት ኢትዮጵያን መለወጥ አይችልም።
ሰንደቅ፡- ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ብሔር የተገነባች አንድነቷም ዲሞክራሲያዊ አንድነት መሆን ይገባዋል የሚሉ ከሆነ ለምን የኢህአዴግን ፕሮግራም አይደግፉም?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- አልደግፍም! ለምን ብትለኝ ኦህዴድን ምሳሌ ልጥቀስ ኦህዴድ ከኦሮሞ ሕዝብ ነው የተገኘው? የኦህዴድ መሪዎች በራሳቸው ፈቃድ ተነስተው የተደራጁ አይደሉም። ኤርትራ ለመዋጋት ሄደው የተማረኩ ናቸው። ስልጣን የላቸውም። ከሕዝብ የፈለቁ አይደሉም። በእርግጥ ከመንግስቱ ኃይለማርያም ጊዜ ትንሽ ይሻላሉ። ታክስ የመሰብሰብ ስልጣን አላቸው። በክልሉም ወንጀለኛን መያዝ ይችላሉ። የኦሮምኛ ቋንቋ የሚተላፍ ቴሌቭዥን ከፍተዋል። እና የኢህአዴግ ፕሮግራም ጥሩ ሆኖ ሳለ ወደ አንድ ጎን አጋደለ። ህወሐት ያለውን ኃይል፣ ሐብትና ጉልበት ሌሎቹ የላቸውም። ሰልፍ ለማሳመር የተቀመጡ ናቸው። ክህወሃት ውጪ ያሉ ድርጅቶች ታክስ ለመሰብሰብ፣ ወንጀለኛን ይዞ ፍርድ ቤት ለማቅረብ፣ የተለመደውን መንግስታዊ ስራ ይሰራሉ። ጉልበት ግን የላቸውም። መንግስቱ ወይም ስርዓቱ የሚመራው ህወሃት በመሆኑ የኢህአዴግ ፕሮግራምን እንዴት ትደግፈዋለህ?
ሰንደቅ፡- በመጨረሻ የእርስዎ ባለቤት ግብፃዊ መሆናቸው ይነገራል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ግብፅና ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ባለው የህዳሴው ግድብ ላይ አለመግባባት ተፈጥሯል። ይህ ጉዳይ በእርስዎ ቤተሰብ ላይ ምን ስሜትን ፈጠረ?
ቡልቻ ደመቅሳ፡- ባለቤቴ ሙሉ በሙሉ ግብፃዊት አይደለችም። አባቷ የትግራይ ሰው ሲሆኑ እናቷ የግብፅ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ናቸው። መቼም ባልና ሚስት የሚያወራውን ለሌላ ሰው አይነገርም፤ ምስጢር ነው። በአባይ ጉዳይ ያለን አስተያየት ግን አንድ ነው። ግብፆች መገንዘብ ያለባቸው ኢትዮጵያ ወንዙን መጠቀም የፈለገችው ከወንዙ ላይ ቆንጥራ ነው። ምናልባት እኛ የምንወስደውን ውሃ ግብፅ የምታባክነውን ሊሆን ይችላል። እኛ ውሃውን ለሃይል ማመንጫ እንጂ ለመስኖ አይደለም። ኢትዮጵያ መብቷን መጠቀም ከፈራች ትጠፋለች። ስለዚህ የቅኝ ግዛት የውሃ ስምምነቱን ሁላችንም እየተቃወምን የግብፅን ሕዝብ ሳንጎዳ መጠቀም አለብን።
No comments:
Post a Comment