ስመኝ ከፒያሣ
የኢትዮጵያ ፕሬስ የሚታወሰው ወይም የሚነሳበት ዘመን ቢኖር ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ ኢህአዴግ መላ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረበት ከግንቦት 20/1983 ዓ.ም እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ ምንም ያደረገው ነገር አልነበረም፡፡ ፀጥታ የነገሰበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ማለትም 1985 ዓ.ም ላይ የኤርትራ ሪፈረንደም የተፈቀደበት ጊዜ ነበር፡፡
ከዛ በኋላ ደግሞ በሙሉ ነፃነት ነገሮችን መግለፅ ተጀመረ፡፡
ታዲያ በነዚህ ጊዜያት ከወጡትና ስለኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት አለን ብለው መፃፍ ከጀመሩት መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ አንዱ ነው፡፡ እስክንድር ነጋ በምድረ አሜሪካ ይኖር የነበረ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ከደርግ ውድቀት በኋላ ነው፡፡ በቤተሰቦቹ ላይም ሆነ በእሱ ላይ ከፍተኛ እንግልት፣ ስቃይና በርካታ የንብረት ውድመት በደርግ መንግስት ደርሶባቸዋል፡፡ እሱና እናቱ በቀይ ሽብር ወቅት ከፍተኛ ጭፍጨፋ ፈፅመዋል ከሚባሉት አንዱ በሆነው ” ግርማ ከበደ” ከፍተኛ እንግልትና የንብረት ውድመት ሲያደርስባቸው ወደ አሜሪካ ተሰደዱ፡፡
እስክንድር በአሜሪካ በነበረበት ወቅት ደርግ ይፈፅማቸው ለነበሩ ያልተገቡ ተግባራት በሙሉ በአሜሪካ ይገኙ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን በደርግ መንግስት ላይ ጫና ይደረግ የሚል መርህ ባነገቡ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ቀርተው አያውቁም፡፡ ሁሌም ስለሀገሩ ያስብም ነበር፡፡ የእስክንድር ፍላጐት ሀብት ንብረትና ገንዘብ ሣይሆን የኢትዮጵያ እድገትና ለውጥ ማየት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሌላው ሀገር በተሻለ ለውጥ ማምጣት የምትችል ሀገር በመሆኗ ይህ ለምን መሆን አልቻለም ብሎ የሚናገር ጋዜጠኛም ነበር፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ከመጣም በኋላ “ኢትዮጲስ” የተባለ ጋዜጣን ከሟች ጋዜጠኛ ተፈራ አስማረ ጋር በመሆን አቋቋመ፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ ኢህአዴግ ዴሞክራሲን አስፍኛለሁ ያለበት ጊዜ ነበር፡፡ ዴሞክራሲ ያለገደብም ተብሎ ነበር፡፡ ከዚህ በመነሣት በርካታ ዜናዎች ማቅረብ ጀመሩ፡፡ በወቅቱ እነሱ የጀመሩት ጋዜጣ ዋጋ 75 ሳንቲም ቢሆንም ይዘውት የሚወጡት ዘገባ ከባድነት “ኢትዮጲስ” ጋዜጣ ሰባት ብር ድረስ ትሸጥ ነበር፡፡ የዛሬ 20 አመት ሰባት ብር የነበረውን ጥቅም ማንም ቢሆን የሚዘነጋው አይደለም፡፡
ታዲያ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ኢትዮጲስ ተቋረጠች፡፡ እነ እስክንድርም ታስረው ወጡ፡፡ ከዛ “ሀበሻ” የተባለ ጋዜጣ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ማሣተም ጀመረ፡፡ ይሁንና ግን ብዙም ሣይራመድ “ጐበዝ አምስት አመት ሞላ” የሚለው ዘገባ ችግር ፈጠረ፡፡
እስክንድር መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያነበው ዘንድ ሀበሻን ይጠብቋት ብሎ የጋዜጣውን ማስታወቂያ በካርቶን ይዘው የሚዞሮ ወጣቶችን መድቦ ነበር፡፡ ይሁንና እስከ እነሱ ጭምር በድጋሚ ታሰረ፡፡ ወጣቶቹ ሲፈቱ እስክንድር ግን በማረሚያ ቤት ቀረ፡፡
የእስክንድር ቀኝ እጅ የተሰበረውም በዛ ጊዜ ነበር፡፡ እስክንድር ከተፈታ በኋላም ዳግም ታስሯል፡፡ እንደውም በ1987 አብሯቸው ከታሰራቸው መካከል የግብፁን ፕሬዝዳንት ሁሴኒ ሙባረክን ለመግደል ሙከራ ያደረጉና በቁጥጥር ስር ከዋሉ አሸባሪዎች ጋር ነበር፡፡ እዚህ ላይ የምገልፀው ነገር ቢኖሩ እስክንድር ነጋን እኔ እንደማውቀው ነው፡፡ ከዛ በኋላ ወይም ከረጅም ጊዜ እስር በኋላ ግን ተፈቶ እስክንድር ነጋ ወደ ጋዜጣ ሕትመት ሲመለስ “ምኒልክ” የተባለውን ጋዜጣ ይዞ ብቅ አለ፡፡ ምኒልክ ጋዜጣ መቼም በሀገሪቱ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ በህትመት ግንባር ቀደም የነበረ ጋዜጣ ነበር፡፡
እስክንድር ነጋ የተለየ ነገር ወይም ባህሪ አለው፡፡ ይህ ባህሪው ደግሞ ስለገንዘብና ጥቅም የሚያስብ ሰው አልነበረም፡፡ በወቅቱ ጋዜጦች በኪሳራ ከጨዋታ ሊወጡ ሲሉ የሚደጉም የለኝም ብሎ ለመጣ ሁሉ የሚሰጥ ሰው ነበር፡፡ እኔ እስክንድርን ከተዋወኩበት ጊዜ ጀምሮ ሁሌም እሱን ማወቅ ያጓጓኛል፡፡ ምክንያቱም ከእሱ የሚወጡት ሀሣቦችና ቃላት የተለዩና በውስጣቸው እውነትነት ያላቸው ነበሩና፡፡ እስክንድር ስለገንዘብ ጥቅም ወይም ተንደላቆ ስለመኖር የሚያስብ ሰው ፈፅሞ አይደለም፡፡ የየትኛውንም ሰው ሀሣብ ይቀበላል በፅሞናም ያዳምጣል፡፡
የትልቅነት መለኪያው ደግሞ ምንም ሣይሆን ሰዎችን ማዳመጥና መስማት መቻል ነው፡፡ እስክንድር በጋዜጦቹ ላይ በርካታ ነገር ይፅፋል፡፡ አንድም ጊዜ ቢሆን ግን ምስሉን ለጥፎ እኔ እስክንድር ነጋ ነኝ ብሎ አያውቅም፡፡ ከዛ ባለፈ ደግሞ “ሀበሻ” ጋዜጣ ከታገደበት በኋላ በስሙ ያወጣው ጋዜጣ የለም፡፡ ፎቶውን ሣይሆን ስሙን አውጥቶ የፃፋቸው ፅሁፎች ቢኖር የማስታውሰው የደርግ ባለስልጣናትን በሚመለከት በሚወጡ ፅሁፎች ላይ ነበር፡፡ ከዛ ውጭ ግን በሰራው ስራ በሕዝብ እንዲወደዱ እወቁኝ እወቁኝ እያለ በአደባባይ የወጣ ወይም ደረቱን ነፍቶ ይህ ይሁን ያለ ሰው አይደለም፡፡
እስክንድር የተለየ ቦታ ያለው ሰው ነው፡፡ አንድ ታሪክ ልንገራችሁ ይህን ታሪክ ግን ስም ሣልጠቅስ ባወራው እመርጣለሁ፡፡እስክንድር አሁንም በስራ ላይ ላለ ጋዜጣ ባለቤት እባክህ እከሌ የተባለን ባለሰልጣን ለማነጋገር ፈልጌ ሪፖርተሬን መላክ ፈለኩ እናም አስጨርስልኝ አለው፡፡
ይህ ሰውም ባለስልጣኑን ሲያናግር ባለስልጣኑ ሪፖርተሩ ሣይሆን ራሱ እስክንድር ነጋከመጣ ቃለመጠይቁን እሰጠዋለሁ አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት እስከንድር ሣይሄድ ቀረ፡፡ እኚህ ባለስልጣን ታዲያ አሉ ወይም ተናገሩ በተባለው ቃል “እስክንድር የገንዘብ ችግር እንደሌለበት አውቃለሁ የሚሰራው ለጥቅም ወይም ለፖለቲካ ፓርቲ አይደለም፡፡ አላማው ምን እንደሆነ እሱን አግኝቼ ማናገር እፈልጋለሁ” ሲሉ ገለፁ፡፡
የእስክንድርን መንፈስ ስናስበው ታዲያ በዚህች ሀገር ላይ እውነተኛው ዴሞክራሲ መስፈን አለበት ከሚል አንፃር በመነጨ የሚሰራ እንጂ አትራፊ ጋዜጠኛ ወይም የሕዝቡ የልብ ትርታ ይሄ ነው ብሎ ምስሉን ለጥፎ የሚነግድ አይደለም፡፡ ርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ በሀገሪቱ ከታተሙ ነፃ ጋዜጦች እስክንድር ነጋ የሚሰራባቸውን ጋዜጦችን በቁጥርና በጥራት የሚደርስ አልነበረም፡፡ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ እስከንድር ሻይ እንጠጣ ብሎ ኪሱ ሲገባ ገንዘብ ሣይዝ ረስቶ የሚወጣ ሰው ነው፡፡ ስለገንዘብና ስለዝና አይኖርም፡፡ በእሱ ስር የሚሰሩ ሰራተኞች ግን የበለጠ እንዲጠቀሙ ያደርጋል፡፡
እስክንድር ተቸገርኩ ላለው ሰው ሆዱ የማይጨክንና የሚራራ ደግ የሚባል ጋዜጠኛም ጭምር ነው፡፡
የእስክንድር ጋዜጣ ነው ከተባለ ጋዜጣ አዙሪዎች ለማውጣት አይፈሩም፡፡ ምክንያቱም እስክንድር ጋዜጣ አደረብኝ የሚል አዙዋሪ በሙሉ ይመለስለታል፡፡ ጋዜጣ አዙዋሪ የሌላውን ለማውጣት መጠን ያበጃል በእስክንድር ጋዜጣ ላይ ግን ቢመለስብኝስ ብሎ አይፈራም፡፡ 12 ሰአት ካለፈ በኋላ እድሜ ለእስክንድር ብሎ ቤቱ ይገባል፡፡ ጠዋት አምጥቶ ይመልሳል፡፡ አዟሪ በሙሉ ሌላ አሣታሚ አልመልስ ካለው እስክንድር እንኳን እየመለሰ ሲል ሁሉም ለእሱ ክብር ሲል መመለስ ጀመረ፡፡
እስክንድር የየትኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ አባል አይደለም፡፡ አልነበረምም፡፡ ሁሌም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ይወቅሳል፡፡ ይናገራል፡፡ ምኒልክ ጋዜጣ በነበረበት ጊዜ በመጀመሪያ የተጋጨው ከኢ/ር ኃይሉ ሻወል ጋር ነበር፡፡
የግጭቱ መንስኤ ደግሞ የፓርቲያችሁ አቋም ይሄ ነው ለምን ሆነ በሚል ነው፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ ለኢህአዴግ ስጋት ፈጥሮ የነበረው ፓርቲ “ቅንጅት” በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እስክንድር አንድም ቀን ተገኝቶ አያውቅም፡፡ በእነሱ አሰራር ወይም አካሄድ ላይ ቅሬታ ካለው ግን ይናገራል፡፡ ኢ/ር ኃይሉ ሻወል በልጃቸው አማካይነት ተቃውሞውት ወደ ክስ አመራለሁ ብለው ያውቃሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በውስጣቸው ያለውን ችግር ይገልፃል፡፡ ሌላው ይቅርና አቶ ልደቱ አያሌውን ማንዴላ በተባሉበት ወቅት ሣይቀር የእሣቸው አካሄድ ላይ በድፍረት ቅሬታውን የገለፀ ሰው ቢኖር እስክንድር ነጋ ነው፡፡
ዘመን ሲቀየር ሕዝብ ሊቀየር ወዳጅም ሊከዳና ሊርቅ ይችላል፡፡ እስክንድር ነጋ ግን ዛሬ አብጠው ሲሰሩ ከማያቸው አንዳንድ ጋዜጠኞች የእሱ ምክርና ድጐማ የሌለባቸው አሉ ብሎ ለመናገር ይከብዳል፡፡ ይህቺ ሀገር ጋዜጠኛ አፈራች እስክንድር ነጋን ብል የማፍርበት ሰው አይደለም፡፡ ሁሌም የምኮራበት ሰው ነው፡፡ ከላይ እንደገለፅኩት እስክንድር የማንም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለም፡፡ ሁሌም “ምርጫ 97″ የሚለውን መፅሐፍ ሣስበው አለም የእሱን የእውቀት ደረጃ እንዲለካ እፈልጋለሁ፡፡ ከእሱ በኋላ እሱን አጣጥመው የማያውቁት ተነስተው ታሪክ ለመስራት ቢሞክሩ እነሱን በወንፊት አጥልሎ ማንነታቸውን ለማወቅ ይከብዳልና፡፡
የማያውቁት አገር አይናፍቅም እንደሚለው ዘፈን እስክንድር ነጋን ያየ ዛሬ በሌሎች ያልተጣራና ያልተረጋገጠ ተግባር ሊደመም አይችልም፡፡ የፅሁፌ ሳጠቃልል እስክንድር ነጋ በኢትዮጵያ የነፃ ፕሬስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለውና ስለእውነት ብቻ የሚናገር ምርጥ ጋዜጠኛ መሆኑን ምስክርነቴን በመስጠት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment