Friday 1 February 2013

ኦ! ጋዜጠኞች አሁንስ ለህሊናችሁ፡ፖለቲከኛዎችም!!

(ከዳንኤል ገዛኽኝ አትላንታ)

በኢትዮጲያ በአሁኑ ወቅታዊ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ጋዜጠኞች ከመቼውም ጊዜ በላይ ሃላፊነትን የተሸከሙበት ወቅት ነው። በዚህ መልኩ ሃላፊነትን ተሸክመው ያለፉባቸውን እና በሃላፊነታቸውም የተነሳ ያረፈባቸው ጠባሳ ሳይረሳ ማለት ነው። የአሁኑ ደግሞ ታሪካዊ አደራ እና ሞያዊ ግዴታቸውን የሚወጡበት ወቅት በመሆኑ ከመቼውም በላይ ሃላፊነቱን ከበድ ያደርገዋል። በተጉዋዳኝ ሃገራችን ኢትዮጲያን እንደ ካንሰር ልበለው እንደ ነቀርሳ ላለፉት ሃያ አንድ አመታት በአምባ ገነንነት ከያዛት ገዢ ሃይል ለመላቀቅ በሚደረገው መስዋ ዕትነት ጠያቂ የትግል ጎራ ተቀላቅላችሁ የፊቱን መሪ በመያዝ በመዘወር ላይ የምትገኙቱም ጉምቱ እንዲሁም ወጣት ፖለቲከኛዎችም እንደዚሁ ትልቅ ሃላፊነትን የሚጠይቀውን ቦታ ተሸክማችሁዋል።  ስለዚህ በሌሎች መንገድ “ፖለቲካ ውሸት ነው” በሚለው ስልት እና መርህ እንድትራመዱ የኢትዮጲያ የፖለቲካ ታሪካዊ ወቅታዊ ሂደት አይፈቅድላችሁም። ይህ የሚሆን ከሆነ እውነተኛ ለውጥ በሚመጣበት ጊዜ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላችሁዋል እና ለ እውነት መቆም ይጠበቅባችሁዋል።


ከወራቶች በፊት የኢትዮጲያ የሽግግር ምክር ቤት በተቁዋቁዋመበት ጊዜ የምክር ቤቱ መስራች እና ሊቀመንበር ሆነው ብቅ ያሉትን ዶ/ር ፍሰሃ እሸቱን የሚተች አንድ ጽሁፍ ጽፌ ነበረ። ጽሁፌ የሚያጠነጥንበት ጭብጥ ዶ/ሩ ለአመታት በንግድ ከዘመኑ ሰዎች ጋር ተዛምደው ቆይተው በሁዋላም ተቃዋሚ ሆነው መምጣታቸውን እና ቀደም ሲልም ከአንድ መቶ ሃምሳ በላይ ጋዜጠኛዎችን ባሰባሰበው የዩኒቲ ድምጽ እና የ እለታዊ አዲስ ጋዜጣ የፕሬስ ተቁዋምን መስርተው ሲያበቁ ለስምንት ወራት ዘልቀው በሁዋላም ህውሃት ለሁለት መሰንጠቁን ጋዜጣዋ ብትዘግብ በማግስቱ ጋዜጣዋን ዘግተው ያንን ሁሉ ጋዜጠኛ መበተናቸውን ተችቼበታለሁ። በዚህ አላበቃሁም እንደ ምርጫ 97 ባለው ክስተት እና ሂደት ያልተሳተፉት እኚህ ዶ/ር ዛሬ ከየት ተገኙ ብያለሁ። በወቅቱ በጻፍኩት ጽሁፍ ብዙ ጸያፍ ስድቦች እና ወቀሳዎችን አስተናግጃለሁ። ሂደቱን በኔ መነጽር ሲታዘቡ የኖሩ ደግሞ ለሃሳቤ ድጋፍ ሰጥተዋል።
ዛሬ ግን ዶ/ር ፍሰሃን ልወቅስ እና ልከስ ሳይሆን ከሰሞኑ ያደረሱን ጽሁፍ አንጀቴን ቅቤ ስላጠጣው ላመሰግናቸው ነው። ዶ/ር ፍሰሃ በኢትዮጲያ የተቃውሞ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ከኛ ወዲያ ላሳር የሚሉ ፖለቲከኛዎችን አንገት የሚያስደፋ ሃሳብ በማንሳት የልበ ሙሉነት አስተሳሰባቸውን ቁርጠኝነታቸውን ያሳዩበትን መል ዕክት አስተላልፈዋል ዶ/ር ፍሰሃ። በዚህ መል ዕክታቸውም ከኛ ወዲያ…ባዮቹ ፖለቲከኛዎች እኛስ ማን ነን ? ብለው ራሳቸውን እንዲጠይቁ ውስጣቸውን እንዲፈትሹ የሚያደርግ ጥቁምታን ሰጥተዋል። በዚህ ሊመሰገኑ ይገባል። ዶ/ር ፍሰሃ ቁምነገር ማስተላለፍ ብቻም አይደለም “እኔ መሪዬን መርጫለሁ እናንተስ ?” ሲሉም በማፋጠጥ ሁሉንም ጠይቀዋል። በ እውነት ሊያስመሰግናቸው እና ሊያስደንቃቸው የሚገባ ሃሳብ ነው። ይህ ዶ/ሩ የመረጡት መሪ ጀግናው ጋዜጠኛ በ እስር የሚገኘው እስክንድር ነጋ ነው። አዎ እስክንድር የኛ ማርከስ ጋርቬይ…እስክንድር የኛ ማልኮልም ኤክስ…እስክንድር የኛ ማህተማ ጋንዲ…እስክንድር የኛ ማርቲን ሉተር ኪንግ እስክንድር ነጋ ጀግናው ጋዜጠኛ ለኛ ብዙ ብዙ ነው። እንዲሁ ወጣቱም ፖለቲከኛ አንዱአለም አራጌም። ምክንያቱም እስክንድር የተጉዋዘበትን መንገድ የመረጠ ፖለቲከኛም ሆነ ሊመራን በቁርጠኝነት የተጋ ባለመኖሩ እስክንድር ሊመራን ይገባል ብሎ መቀበል በእውነት ልባምነት ነው።

ይህ በ እንዲህ እንዳለ ወደዋናው የተነሳሁበት ጭብጥ ስገባ አሁን አሁን አብዛኛው በውጪ ሃገር የሚገኙ ሚዲያዎች ሃገራችን ላይ የተጫነውን እባጭ የወያኔ አገዛዝ በመታገሉ በኩል ማለትም እውነትን ለህዝብ በማድረስ የሚተጉት ትጋት አሌ የሚባል ባይሆንም ነገር ግን የተወሰኑ የተቃውሞ ሃሳብ አራማጅ ቡድኖችን በቻ በመነጠል ለነሱ ሽፋን በመስጠት የንግድ ማስተዋወቅ ፕሮሞሽን ያህል የማስተዋወቅ ስራ በመስራት እንደተጠመዱ እየታዘብኩ ነው። ለዚህም አስረጂዬ የተወሰኑትን ክፍሎች ሃሳብ እና አካሄድ እየተናጠቁ እና እየተቡዋጨቁ በማስተጋባት መጠመዳቸው ነው።
በመጀመሪያ በሃገር ቤት በመንግስት በተያዘው የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ማሽን ፈብራኪ በሆኑ የገዢው ሃይል ሚዲያዎች ውስጥ ያንን እንቶ ፈንቶ ወሬ በመለፈፍ ሃገር እና ህዝብን የሚያሳዝኑ ጋዜጠኛዎችን የምንተችበት አንዱ እና ዋናው ነጥብ “ለምን እውነት በመናገር ለህሊናቸው አያድሩም” የሚል ነው ከብዙ በጥቂቱ። እናም በትችታችን እና በወቀሳችን መሰረት እነዚህ ሰዎች ተሳክቶላቸው ለህሊናቸው ማደር ከጀመሩ ሊኖራቸው የሚችለው ምርጫ ጥቂት ነገር ነው።

አንድም ባላቸው የሞያ ብቃት ወይንም ክህሎት በሃገር ውስጥ በገለልተኛ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ የራሳቸውን ስራ መስራት። ገለልተኛ ስራ በመስራታቸው ብቻም ሳይሆን ከመንግስት የሃሰት የፕሮፓጋንዳ ፍብረካ ስራ ራሳቸውን በማራቃቸው እስራት እና ወከባ ካልገጠማቸው ማለት ነው። ካልሆነም ህሊናን በመምረጥ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ቸል በማለት በሌላ ማህበራዊ የጋዜጠኝነት መንገድ መራመድ። ይህንን ስል ህውሃት ለሁለት በተከፈለበት ወቅት የመንግስት ሚዲያዎችን ትተው በአንድ ጊዜ መልቀቂያ አቅርበው የተሰናበቱ ስምንት ጋዜጠኛዎችን ማስታወስ ይቻላል። ምንም እንኩዋን በዚሁ ምክንያት ፓርቲያችንን በአስቸጋሪ ወቅት የከዱ ተብለው እስራት ባይገጥማቸውም መስራት እስኪያቅታቸው ድረስ ሃገር ውስጥ በስራቸው አበሳ ቢቆጥሩም።
በሌላ በኩል ከሃገር በመሰደድ ነጻ ሞያዊ ግዴታቸውን መወጣት። የሆነው ሆኖ ግን ነጻነት ፍለጋ ተሰዶ የራሱን ነጻነት ለፖለቲካዊ አጀንዳ እና አመለካከት ጥገኝነት አስገዝቶ ደሞዝ የሚጠብቅ ጋዜጠኛ ግን የዋልታ ኢንፎርሜሽንን እና የአዲስ ዘመን ጋዜጠኛን ለመክሰስም ሆነ ልመውቀስ የሞራል ብቃት አለው ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነጻነት ፈልገው አህጉር አቁዋርጠው የተሰደዱ ጋዜጠኛዎች በነጻነት ሃገር ሚና መለየት መጀመራቸውን እየታዘብኩ ነው። መቼም አካፋን አካፋ የማለት ባህላችን አልዳበረም እና አንዳንድ ኩነቶችን በግርድፉ ለማለፍ ብገደድም አንዳንድ ነገሮችን ግን ይህንን ሃሳቤን ለማቀርብለት ህዝብ በሚገባው መልኩ ማለት የሚገባኝን ያህል እላለሁ።

አንዳንድ ድረ-ገጾች የተወሰኑ ጸሃፊዎችን ጽሁፍ ላለማስተናገድ የማሉ ያህል እስኪመስሉ እድሉን አይሰጡም። አንዳንድ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ደጋግመው መድረክ የሚሰጡት ለተወሰኑ ሰዎች ነው። በዜና እወጃቸው ላይም እንደማጠናከሪያ ሃሳብ ደጋፊ አስተያየት ሊሰጡ የሚገባቸውን ሰዎች አይናችሁ ላፈር ያሉ ያህል አያስታውሱዋቸውም። በዚህ ረገድ የአኙዋክ ጀስቲስ መስራች አቶ ኦባንግ ሜቶ ለነጻ ሚዲያዎች አላርጂክ ናቸው የተባሉ ያህል ለብቻቸው ስደተኛውን በተመለከተ የማይገቡበት ሃገር የማይሄዱበት ስፍራ የለም ነገር ግን እኚህ ሰው በስራቸው በርካታ ስደተኛዎችን እየታደጉ ሳሉ ነገር ግን የሚሰሩትን ስራ በተመለከተ ሚዲያዎች ከ እሳቸው የሚላኩላቸውን ጽሁፎች እንኩዋን ሲዘሉ ይስተዋላሉ። በተመሳሳይ በሰው ሃገር እንደጨው የተበተኑ አስታዋሽ ያጡ ስደተኛዎችን ያለማንም ጎትጉዋችነት በግላቸው ከኑሮዋቸው ላይ አንስተው የሚደጉሙበኢትዮጲያዊነታቸው የበኩላቸውን የሚያደርጉቱ የቨርጂኒያዎቹ እነከባዱ በላቸው…ወይዘሮ ሶስና ሌሎችም ያልጠቀስኩዋቸው ጥቂት ሰዎች አሉ ሚዲያው ግን ስራቸውን ተግባራቸውን ማበረታታት ብቻም አይደለም ሌሎችም ኢትዮጲያውያን የበኩላቸውን እንዲያደርጉ የሚገፋ ስራ አይሰራም ለምን ይሆን ? የስደቱ ችግር…ስደተኛውን ማስታወስም በራሱ እኮ የሃገራችን ብልሹ አስተዳደር ውጤት የሆነውን አብይ ጉዳይ ማንሳት መሆኑን ማንም የሚዲያው ባለሞያ ያጣዋል አለልም። ኦ ጋዜጠኛዎች እባካችሁ እባካችሁ።
ሌላው እንደ አራያ ከሚጠቀሱ ሰዎች መካከል እንደ ቀድሞዋ ሞዴሊስት…የፊልም ተዋናይት…የ እርዳታ ድርጅቶች አስተባባሪ እና በአለም ለተበተነው የ ኢትዮጲያ የቀድሞው ሰራዊት እና ስደተኛ እንደ እናት በመሆን የበኩልዋን ስታደርግ የኖረችዋን ወ/ሮ የሃረር ወርቅ ጋሻውን አንድም ቀን ሚዲያዎች አስታውሰዋት አይውቁም። በእርግጥ የሃረር ወርቅ በአንድ ወቅት ኤርትራ በመገኘት ከሰፊው የ ኤርትራ ሚዲያዎች ጋር ቆይታ አድርጋለች ከፕረዚዳንቱ ጋርም ተገናኝታለች ታዲያ ይሄ ምኑ ይሆን ክፋቱ ?
ምናልባትም እርስዋን ፖለቲከኛዎች ሊጠሉዋት ይችሉ ይሆናል ለዚያውም ጥቂቶች ነገር ግን ጋዜጠኛዎች እቺን ኢትዮጲያዊት ስለቀደመው ስራዋ መድረክ ሊሰጡዋት አይገባም ?። እዚህ ጋር አንድ ነገር ልበል ጋዜጠኛዎችን የ ኤርትራውን ሃይል ሻዕቢያ አትበሉ ማለት እና ከ ኤርትራ መንግስት ጋር በሆነ ወቅት የተገናኘ ሰው መድረክ አለመስጠት እስቲ ሁለቱን ጉዳዮች አመዛዝኑዋቸው። እርግጥ ነው የ እርትራ ጉዳይ አብ ሲነካ …እንዲሉ ሊሆን ይችላል። በተጎዳንበት የ እትዮጲያ ወቅታዊ ጉዳይ ፖለቲካ ጨዋታ…ጌም ነው የሚለው አባባል የሚሰራ አይመስለኝም።

በነገራችን ላይ ይህንን ስል ሚዲያዎች የማህበራዊ ገጽ ቁዋሚ ተሳታፊዎች አንዳንድ ሰዎችን ማወደሳቸውን እና ማድነቃቸውን በሌላ መልኩ ነው የምመለከተው። ምክንያቱም እነዚህ ጥቂትተሙዋጋቾች ልበላቸው ታጋዮች የቤተሰባቸውን ጊዜ እና ወሳኝ ጉዳዮች ወደጎን በመተው የሚያደርጉት ተጋድሎ ከአድናቆት እና ከውዳሴም በላይ ውዳሴ ያስፈልጋቸዋል። ምክንያቱም በርካታዎች ደጃፋቸውን ዘግተው ባሉበት፤ ሌሎችም ሆድ አደሮች አሳፋሪ ስራ በሚሰሩበት እንደ ፕሮፌሰር አለማርያም፤ እንደ ብርቅዬው የኢትዮጲያ የቁርጥ ቀን ልጅ እንደ ታማኝ በየነ አይነቶቹ መድረክ አይደለም ዙፋን ቢሰጣቸው የትኛው ኢትዮጲያዊ ይከፋው ይሆን ? በበኩሌ ሰው ማለት ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋለት የሚባለውን ብሂል የምቀበለው ታማኝን ሳየው ነው። አስታውሳለሁ በምርጫ 97 የሰሜን አሜሪካ የቅንጅት ቅስቀሳ ወቅት ከታማኝ በየነ ጋር የነበሩ በርካታዎች ነበሩ። ባንዲራ ለብሰው ባንዲራ አሸርጠው፤ መፎክር እያሰሙ እየፎከሩ እየሸለሉ የነበሩ፤ ነገር ግን ዛሬ የት ናቸው ? የምናውቅ እናውቃለን። ሆዳቸውን ወደው የተቀላቀሉትን ማንሳት ፈልጌ ሳይሆን ቤቴ፤ንብረቴ…ሃብቴ፤ገንዘቤ እያሉ ከምኑም ሳይሁኑ ዳር የቀሩቱን ነው። ስልዚህ መድረክ ለሚገባቸው መድረክ መስጠት ግዴታ ነው። ነገር ግን እንደ የሚመለከታቸው ሁኔታ መድረክ የተነፈጉ ሰዎችን ግን ማስታወስ እና ሙያዊ ጌዴታን መወጣት የናንተ የጋዜጠኛዎች ግዴታ ነው። ስለዚህ ጋዜጠኛዎች ታሪካዊ እና ሃገራዊ ግዴታችሁን ተወጡ እንጂ በጎጥ በወዳጅነት እና በፖለቲካዊ እምነት መቀራረብ ጭቦ አትስሩ።

አንዳንድ ጊዜም ጭራው እና ጫፉ ባልተለየ ጉዳይ መወደስ እና አድናቆት አትደርድሩ። አንድ አመት ሊደፍን ምንም ያህል አልቀረውም ስለ ዘፋኙ ቴዎድሮስ ካሳሁን የቴዎድሮስ ንቃቃቶች በሚል አንድ ጽሁፍ ጽፌ ነበረ። አብዛኛውን ስለቴዎድሮስ የ ኢትዮጲያ ህዝብ የሆነለትን እና ቴዲ በምትኩ የመለሰውን ምላሽ አስነቤብያለሁ በተመሳሳይም የቴዲን የሙዚቃ ስልት አድንቄያለሁ። ነገር ግን ትላንትም ዛሬም እኔ ስለ ቴዲ የምለው ቴዲ ጥቅም አስገኚ ዘፈኖች እና ስሜትን ማሸነፍ የሚችሉ ስራዎች መስራት የሚችል ኮመርሺያል ዘፋኝ እንጂ የነጻነት ፋኖ ወይንም ታጋይ አድርጌ እንድስለው የሚያደርገኝ እውነት የለም።
ማንም የራሱን እምነት በየትኛውም ጉዳይ ላይ መያዝ ይችላል በሚለው ሃሳብ ማለቴ ነው። ቴዲ አውቆ ይሁን ሳያውቅ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚሰራቸው ስህተቶች በርካታ አድናቂዎቹን በተለይም በሃገሪኛ የሙዚቃ ስራዎቹ የተሳቡ ተከታዮቹን ስሜት ሲያደፍረስ አስትውላለሁ። ዝርዝር ውስጥ አልገባም በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ የፈጸመው ስህተት በቂ ነው ይህንን ለማለቴ። ዘፋኙ ወደ ደቡብ አፍሪካ የተጉዋዘው በአንድ የወያኔ ካድሬ ፕሮሞተርነት ሆኖ ሳለ የብሄራዊ ቡድናችንን ለመደገፍ ነው የምጉዋዘው ብሎ በአደባባይ ዋሽቶዋል። ለዚህ ማስረጃው ፕሮሞተሩ አቶ አለም የወያኔ ካድሬ መሆኑ ብቻም ሳይሆን በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ምርጥ የኢትዮጲያ ልጆች በቴዲ ዝግጅት ላይ ለመገኘት ቲኬት ቢገዙም ከበር እንዲባረሩ ተደርገዋል።

ይሄንን ቴዲ አያውቅ ይሆን ?…። እናም ጋዜጠኛዎች እባካችሁ ቸኩሎ ማወደስ ቸኩሎ መስቀል ይቅርብን እንደመስቀሉ ማውረዱ ይከብዳል እና። በመሰረቱ ያወደሰ ብዕር መተቸት ማየስ ባያዳግተውም ግን ያስቸግራል። እንም በበኩሌ ለሃገሬ የሚዘምረውን ድምጻዊ በፊትም መርጫለሁ አሁንም በድጋሚ እመርጠዋለሁ የቁርጥ ቀን ልጃችንን ሻምበል በላይነህን። የከያኒነቱ…የአክቲቪስትነቱ ጉዳይ እንዳለሆኖ እግር በ እግር እየተከተለ የወያኔን ሚስጥር በመረጃ የሚያጋልጠውን ታማኝ በየነን እንደዚሁ ሁልጊዜም በኢትዮጲያ የወሳኝ ወሳኝ ጊዜ ብላቴናነቱ በአስር ጣቴ ፈርሜ በአስር እጄ አጨብጭቤ መርጬዋለሁ። በጋዜጠኝነቱ ለተወሰነ የፖለቲካ ቡድን ድጋፍ በመስጠት ከአንዱ ወደ አንዱ መለጠፍን እንደ ስልት የተያያዙትን ሁሉ በሚያሳፍረው አካሄዱ አምባገነኑን መለስ ዜናዊን በአለም አደባባይ ያሳፈረውን ጋዜጠኛ አበበ ገላውን በመናገር ነጻነት ፈር ቀዳጅ በፊት አውራሪነት ድሜጼን ለግሸዋለሁ። አደጋ ውስጥ ባለችው አንዲት የ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለድፍን ሃያ አመታት እንደ ታላቅ መንፈሳዊ አባት በዝምታ ውስጥ ቆይተው በጥምቀት ዋዜማ ቃለ- ምዕዳናቸውን ያሰሙንን ብጹዕ ወ ቅዱስ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘ ኢትዮጲያ አቡነ መርቆሪዮስ ለኔ መንፈሳዊ ተጋድሎዋቸውን እየተጋደሉ ያሉት አባት ለኔ የሃገሬ ፓትሪያርኬ ናቸው። እናም ሚዲያው ጋዜጠኛው ጉዳያቸውን ዳር እስከ ዳር ሊያናኘው ይገባል ባይ ነኝ። እናም ኦ ጋዜጠኛዎች ስራችሁን ያለ ጭቦ በሃቅ ተወጡ።

ስለዚህ የዶ/ር ፍሰሃን አባባል ተውሼ እኔም የምመርጣቸውን በዚህ አጋጣሚ ስመርጥ ኦ ጋዜጠኛዎች ይሄ ከናንተ አይጠበቅም እና ለቁዋንቁዋ ለዘር ስፍራ በመስጠት ቡድንተኛ አትሁኑ መድረካችሁን ለሁሉ ክፍት  መናገሪያ አደባባያችሁን ለሚገባቸው ሁሉ ስጡ። ፖለቲከኛዎችም እንደዚያው የኔ አማራጭ…የኔ ሃሳብ ብቻ አትበሉ። በተጉዋዳኝ የፖለቲካ ድርጅታችሁን እናንተ ብቻ እንደ የግል ተንቀሳቃሽ ንብረት አታድርጉ። ዛሬ ስልጣን ካላጋራችሁ ዛሬ ሃላፊነትን ካላካፈላችሁ ነገ ጸሃይ ሲወጣ ጎጠኛዎችን ስታሸንፉ እንዳንጠረጥራችሁ ዛሬ ለነገው ስንቅ የሚሆን የዲሞክራሲያዊነት መሪነት ምልክታችሁን አሳዩን እላለሁ

አበቃሁ ሰላም።__

No comments:

Post a Comment