Wednesday 7 November 2012

አንዲት አስተያየት፤ አቶ ኦባማ ለወይዘሪት ኢትዮጵያ ምኗ ናቸው!?

አቤ ቶክቻው
ዛሬ የወዳጃችን ሰላማዊት በቀለ ፌስ ቡክ ላይ እንዲህ አይነት ነገር አነበብኩ። እውነትም ብዬ እኔም ቀጠልኩበት፤
የአክሱም ሀውልት ለደቡብ ምኑ ነው? አሉ መለስ! በቅርቡ የሚሞት የሚቀርባቸው ሰው ካለ “የአክሱም ሀውልት ለደበቡ ብዙ ነገሩ ነው። ምክንያቱም አክሱም ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነውና!” ብሎ ይንገርልኝ። በቅርቡ የሚሞት የሚቀርባቸው ሰው ከሌለ ግን እኔ ራሴ ስሞት ሄጄ እነግራቸዋለሁ። እዛም ደግሞ ሞተው ካልጠበቁኝ…!
የአሜሪካ ምርጫ በባራክ ኦባማ አሸናፊነት ተጠናቋል። ተቀናቃኛቸው አቶ ሮምኒ እንኳን ደስ አልዎት ብለዋቸዋል። እኛም እንኳን ደስ አለዎት እንበላቸው፤ በቅንፍም (ይሄ ነገር ቀላል ያስቀናል እንዴ…!?) ብለን እንቅና…!
ግን የኦባማ መመረጥ አለመመረጥ ለኢትዮጵያ ምኗ ይሆን!? ምናልባት ጠይምነታቸው እኛን ስለሚመስል ካልሆነ በስተቀር ከአሜሪካ ጥቅም ውጪ ለእኛ ቀና ደፋ ይላሉን!? አይሉም። እውነት እውነት እላችኋለሁ ነጩ ሮምኒም ሆኑ ጠይሙ ኦባማ የአሜሪካ ጉዳይ እንጂ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደማይገዳቸው አስመልክቶኛል!
“አስታውሳለሁ…. መቼ ረሳለሁ” የዛሬ አራት አመት የባራክ ኦባማ ምርጫ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ዘንድ የቤተሰብ ጉዳይ እስኪመስል ድረስ በእያንዳንዱ ጎጆ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። እኔን ጨምሮ በርካቶችም ኦባማ ሆይ አንናፍቅሃለን! ብለናቸው ነበር።
ኦባማ እንደናፈቅናቸውም መጡ። ግን ምን አደረጉልን!?
ጠቅላይ ሚኒስትራችንን በሰላም ከተቀመጡበት ቤታቸው “የግብርና ምርት አሳድገሃል እና ልምድህን ለሌሎች አካፍል” ብለው ጠርተዋቸው ጠቅላያችን ምንም ሳይጠረጥሩ ሄደው ለሞት በቁ! ከዚህ ውጪ ምን አደረጉልን….!?
ዛሬም ከምርጫው በፊት በነበሩት ቀናት እና አሁንም ከድሉ በኋላ በአዲሳባ የሚገኙ ኤፍኤም ራዲዮኖች እና ፌስ ቡክ ወዳጆቻችን ሁሉ ስለ ኦባማ አብዝተው እየተጨነቁ እና እየተደሰቱ ነው።
ይኸው አቶ ኦባማ ተመርጠዋል…! ደግመን እንጠይቅ አቶ ኦባማ ለወይዘሪት ኢትዮጵያ ምኗ ናቸው!?
ይልቅስ የአዲሳባ ምርጫ መቼ ነው!?
የራሳችን ኦባማ ናፈቀኝ! ብልስ…!?

No comments:

Post a Comment