Monday 22 April 2013

ሲ.አ.ን ምርጫ ቦርድን ለ3 አመት ህፃን የምርጫ ካርድ መስጠቱን በማስረጃ አጋለጠ

April 22, 2013 

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ(ሲአን) ሚያዚያ 11 ቀን 2005ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) ዋና ጽህፈት ቤት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ እንዳልሆነ ማስረጃዎች አጋለጠ፡፡ ፓርቲው የሚያዚያ 2005ዓ.ም. የከተማ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ ላይ በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ለመወዳደር ወደ ምርጫው ቢገባም በቅስቀሳው ወቅት አባሎቹ ላይ ኢህአዴግ ከፍተኛ ማስፈራራት፣ እንግልት፣ እስርና ግድያ እየፈፀመ በመሆኑ አቤቱታውን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወዲያው ቢያሳውቅም መፍትሄም ሆነ ምላሽ ሊሰጥ ባለመቻሉ ከምርጫው ወጥቷል፡፡

በመግለጫው እንደተጠቀሰው በዞኑ ለሚገኘው ዳሌ ወረዳ ምክር ቤት ዕጩ ተዋዳዳሪ የሆኑት አቶ ተሸመ ሳታና ባካባቢው ባለስልጣናት ከምርጫው እራሱን እንዲያገል በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከሰጡ በኋላ በጥይት ገድለውት የውሃ ጉድጓድ ውስጥ በመጨመር የአስከሬን ምርመራ እንኳ እንዲደረግ አጥብቀን ብንጠይቅም ፖሊስ ቶሎ እንዲቀበር አድርገዋል ሲል የተፈፀመበትን ጠቁሟል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ዕጩ ተወዳዳሪ የመንግስት ሰራተኞች ከስራ እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፣ ህገወጥ የስራ ቦታ ዝውውርም ተፈፅሞባቸዋል ፣ በግፍ እንዲታሰሩ ተደርገው ተፈርዶባቸዋል፤
በሲአን ስብሰባ ተካፍላችኋል በሚል 3 ሴት ተማሪዎችና 4 ወንድ ተማሪዎች ለሁለት ዓመት ከትምህርት ገበታቸው ታግደዋል፣ ሌሎችም እስራት በመፍራትም መሰደዳቸውን በመግለጫው አስታውቀዋል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ምርጫ ቦርድ ለአንድ ድምፅ ሰጭ ሁለትና ከዛ በላይ ካርድ ማደል፣ ድምፅ መስጫ ወረቀት ከድምፅ መስጫው ቀን አስቀድሞ ለካድሬዎች ማደል፣ህዝቡ ለድምፁ ዋጋ በመስጠት አዋጁ በሚፈቅደው መልኩ የሰጠውን ድምፅ እንዳይጭበረበር ከምርጫ ጣቢያው 500 ሜትር ርቆ እንዳይጠብቅ የምርጫ አዋጅን በመፃረር ቀጥታ ወደ ቤታችሁ ግቡ በማለት የምርጫ ክልል ጽህፈት ቤት በማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ትዕዛዝ መስጠቱም ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ ያልተለያዩበትን ማስረጃ ዋቢ በማድረግ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አለመሆኑን ፓርቲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ ፓርቲው በመግለጫው ወቅት ለማስረጃ ካቀረባቸው በርካታ የፎቶና የቪዲዮ ማስረጃ በተጨማሪ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎችን ለጋዜጠኞች ይፋ ያደረገ ሲሆን ከቀረቡት መካከልም የ3ዓመት እና የ5ዓመት ህፃናት የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን፣ አንድ ሰው ሁለትና ከሁለት በላይ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን፣ ሚያዚያ 13 ቀን የሚደረገው የቀበሌ የድምፅ መስጫ ካርድ የምርጫ ቦርድ ማህተምና ፊርማ
ያረፈበት የድምፅ መስጫ ወረቀት ቀድሞ መውጣቱና መታደሉ፣ ከመደበኛው የተለየ የተጭበረበረ ድምፅ መስጫ ካርድ አዘጋጅቶ ማደል፣ ምልክት የተደረገበት የምርጫ ወረቀት በማደል ከኢህአዴግ ደጋፊ ውጭ ለሆኑ መራጮች ድምፅ እንዳይሰጡ የተበላሸ የመራጮች ካርድ መሰጠቱ፣ ምርጫ ቦርድ የፃፈው መራጮች ድምፅ ከሰጡ በኋላ ወዲያው ወደቤታቸው እንዲሄዱ ትዕዛዝ ያረፈበት ደብዳቤ፣ አንድ ለአምስት የተደረገ ጥርነፋ ለምርጫ ቃለ መሐላ የተፈፀመበት ሰነድ፣ የ አካባቢው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎች ኢህአዴግ አባል የሆኑበትንና የአባልነት መዋጮ ያዋጡበትን ሰነድን ጨምሮ በርካታ ማስረጃዎችን ማየት ችለናል፡፡ 

ፓርቲው በመግለጫው ምርጫው የይስሙላ ያለተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲ እና አብዛኛው ህዝብ ያልተሳተፈበት ምርጫ የየትኛውንም የምርጫ መስፈርት የማያሟላ በመሆኑ ምርጫው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡ በመጨረሻም በሀገራችን እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ሰፍኖ የዜጎች የግልና የቡድን መብት እንዲከበር በእንዲህ በተናጠል በሚደረግ ትግል ውጤት እንዳይመጣ ሲአን ተገንዝቦ 33ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ግንባር የሚፈጠርበትን ሁኔታ በአስቸኳይ አመቻችቶና የጋራ ትግል ስልት ቀይሶ ለሰላማዊ ትግል እንዲነሳ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

No comments:

Post a Comment