Sunday 28 July 2013

ተጠርጣሪ ባለሥልጣናት ባለድርሻ የሆኑበት ‹‹ልማት በዕድገት›› የሚባል ድርጅት መገኘቱ ተጠቆመ

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከሚገኙት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኃላፊዎችና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር በተጠረጠሩበት ወንጀል ታስረው የሚገኙት የትራንዚት ሠራተኛ በነበሩት አቶ ማሞ ኪሮስ ስም የተቋቋመና የባለሥልጣኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች ባለድርሻ የሆኑበት ‹‹ልማት በዕድገት›› የሚባል ድርጅት መገኘቱን፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ለፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡


የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ሐምሌ 18 ቀን 2005 ዓ.ም. የባለሥልጣኑ ከፍተኛ ኃላፊ በነበሩት እነ አቶ ዳዊት ኢትዮጵያ የምርመራ መዝገብ በተፈቀደለት አሥር ቀናት ውስጥ ያከናወናቸውን የምርመራ ሒደቶች ለችሎቱ እንዳስረዳው፣ አቶ ማሞ ኪሮስ የትራንዚት ሠራተኛ ሆነው ሳለ ‹‹ያለቀረጥ በነፃ ያስገቧቸው›› በሚል የተጠረጠሩ 22 ኮንቴይነሮች ሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ ተይዘዋል፡፡ ተጠርጣሪውና በሌላ ምርመራ መዝገብ የተካተቱ የባለሥልጣኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ባለድርሻ የሆኑበት፣ ‹‹ልማት በዕድገት›› በሚል ስያሜ አክሲዮን ማኅበር አቋቁመው መገኘቱን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡

አዲስ የተቋቋመውን ድርጅት አቶ ማሞ በሥራ አስኪያጅነት በሚመሩበት ጊዜ ‹‹ለድርጅቱ›› እየተባለ የተለያዩ ዕቃዎች ያለቀረጥ መግባታቸውን የሚያሳይ ፍንጭ ማግኘቱንም መርማሪ ቡድኑ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ ድርጅቱን የሚገመግምና የሚመረምር ቡድን አቋቁሞ እየሠራ መሆኑንም ቡድኑ አክሏል፡፡
የምስክሮችን ቃል መቀበሉን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ አዳማ፣ አዋሽና ሚሌ የተጓዘው መርማሪ ቡድንም በአጠቃላይ የ18 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን አስታውቋል፡፡
ሁሉም ተጠርጣሪዎች ያከማቹትን ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን በሚመለከት ባለሙያዎችን በማሰማራት እየሠራ መሆኑንም ቡድኑ ገልጿል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ዳዊት ኢትዮጵያ፣ ማሞ አብዲ፣ አሸብር ተሰማ፣ ፍፁም ገብረ መድኅን፣ ማሞ ኪሮስ፣ አበበልኝ ተስፋዬና ኮነ ምህረቱ (በዋስ ተለቀዋል) ሲሆኑ፣ ሁሉም በግላቸውና በጠበቆቻቸው አማካይነት የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸውና በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡
ሌላው ፍርድ ቤቱ የተመለከተው በእነ አምባው ሰገድ አብርሃ (የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሕግ ማስከበር ኃላፊ)፣ አቶ ተክለአብ ዘርአብሩክ፣ ያዴሳ ሚደቅሳ፣ እሸቱ ግረፍ፣ ጌታሁን ቱጂ፣ መላኩ ግርማ፣ አስፋው ሥዩም፣ ጌታነህ ግደይ፣ ዮሴፍ አዳዊ፣ በእግዚአብሔር አለበልና ዘለቀ ልየውን የምርመራ መዝገብ ነው፡፡
ኮሚሽኑ በተሰጠው አሥር የምርመራ ቀናት ለጠቋሚዎች ይከፈል የነበረን አበል፣ ቀረጥ ያልተከፈለባቸውና በሕገወጥ ጥቅም መመሳጠር የገቡ ዕቃዎችን፣ ታክስ ዝቅ የማድረግ ሥራን በሚመለከት ሰነድ መሰብሰቡንና ምስክሮችን መቀበሉን አስረድቷል፡፡
በሁሉም ተጠርጣሪዎች ማለትም በዕለቱ በቀረቡት 18 ተጠርጣሪዎች ላይ ቀሪ ምርመራ እንደሚቀረው በመግለጽ፣ ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
እነ አምባው ሰገድ በራሳቸውና በጠበቆቻቸው አማካይነት የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ፣ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ለኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን አሥር ቀናት በመፍቀድ ለሐምሌ 29 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ethiopian reporter

No comments:

Post a Comment