Wednesday 22 May 2013

“ከሌባ ስብስብ መሃል ጎበዝ ሌባ ይወጣል እንጂ አዲስ ነገር አይኖርም”


የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ

ፍኖተ ነፃነት፡- ለፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ ማተሚያ ማሽን ለመግዛት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ከሚደግፉ ኢትዮጵያዊያን ጋር ለመገናኘት ወደ አሜሪካ አቅንተው ነበር፡፡ በአሜሪካ ቆይታዎ ከአንድነት ደጋፊዎች ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንዴት ይመዝኑታል?
የተከበሩ አቶ ግርማ፡- ዋሽንግተንና ሜሪላንድ የመሳሰሉን ሳይጨምር አንድ አስር ቦታዎች ከደጋፊዎች ጋር ተገናኝቻለሁ፡፡ 


የሄድኩበት አላማ ሁለት ነው፣የአሜሪካ መንግስት እንዴት እንደሚሰራ ለማየት እንድንችል ለተወሰኑ የአፍሪካ ሰዎች እድል በመስጠቱና እግረ መንገድም የፍኖተ ነጻነትን ማሽን የመግዛት አላማ ከሚደግፉ ኢትዮጵያዊያን ጋር ለመገናኘት ነበር፡፡ ለእኔ ያደረግኳቸው ውይይቶች በጣም ጠቃሚ ነበሩ፡፡ ከአገሩ ውጪ የሚገኙ የአገራችን ልጆች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለመረዳት የሚያስችል ነው፡፡ እንደ ፖለቲካ ድርጅትም ሰዎቹ በምን ሁኔታ እንደሚገኙ ማወቅና እንዴት ሊደግፉን እንደሚችሉ መረዳት ወሳኝ በመሆኑ ውይይቱ በጣም አስፈላጊ ነበር፡ ፡ አንዳንድ ሰዎች የተገኘሁባቸውን መድረኮች ስኬታማነት በተሰበሰበው ገንዘብ ሊለኩት ይፈልጋሉ፣ ነገር ግን እኔ እንደዚያ መመልከት አልፈልግም፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- በየመድረኮቹ ይቀርቡልህ የነበሩ ጥያቄዎች በዋናነት በምን ላይ የሚያተኩሩ ነበሩ፣የተደረገልዎት አቀባበልስ? 
የተከበሩ አቶ ግርማ፡- የተደረገልኝ አቀባበል በእውነቱ የጠበቅኩት አይነት አልነበረም፡፡ ብዙዎቹ ቦታዎች ላይ የተደረገልኝ አቀባበል ደማቅ ነበር፡፡ በአብዛኛው ይቀርብልኝ የነበረው ጥያቄ ሰላማዊ ትግልን የሚመለከት ነበር፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሰላማዊ ትግል አዋጪ አይደለም የሚሉ ሰዎች አጋጥመውኛል፡ ፡ የሰላማዊ ትግልን ሙጥኝ ማለታችንን ከፍርሃት የሚያገናኙ ሰዎችም ነበሩ፡፡ ሰላማዊ ትግል ለኢትዮጵያ ከመቼውም ግዜ በላይ አስፈላጊ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጡ ሽግግሮች በህግ ስርዓት እንዲሆኑ አርአያ መሆን ይገባናል በማለት እናምናለን፡፡ ጥያቄዎቹን የሚያነሱት ሰዎች ይህ መንግስት በሰላማዊ ትግል ይወድቃል የሚል እምነት የላቸውም ታዲያ በምንድን ነው የሚወድቀው በማለት ስንጠይቃቸው ግን ምላሽ የላቸውም፡፡ብዙዎቻችን ግን ህዝቡን እያሳሳትነው ነው ነጻ እናወጣሃለን እንለዋለን፡፡ ትልቁ ነገር ግን ህዝቡ መብቱን እንዳያስነካ ማነሳሳት ነው፡፡ 

መብቱን ሌሎች ሳይሆኑ ራሱ ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ነጻ ማውጣት የፖለቲካ ፓርቲዎች ስራ አለመሆኑ መታወቅ ይኖርበታል ከዚህ አንጻር ትልቅ ክፍተት እንዳለ ተረድቻለሁ፡፡ ፓርቲዎች ዋና ስራቸው አገርን የሚመሩ ሰዎችን ማፍራት መሆኑ ቀርቶ አመጽ ቀስቃሾችና አነሳሾች አድርጎ መውሰድ እየተለመደ መጥቷል፡፡ይህ የግንዛቤ ችግር ነው ብዬ እወስደዋለሁ፡፡ፓርቲዎች የጋዜጠኝነት ወይም የሲቪክ ማህበራት ስራን እንዲሰሩ መጠበቅ የለባቸውም፡፡አንዳንድ ጊዜ ድንበሮችን እያለፍን የምንሰራቸው ስራዎች አሉ፡፡ለምሳሌ ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣን መውሰድ ይቻላል፡፡ጋዜጣውን ማሳተም የጀመርነው ሚዲያው በመታፈኑ እንጂ ጋዜጣውን ማዘጋጀት የእኛ ሃላፊነት ሆኖ አይደለም፡፡በየሳምንቱ የምናደርገው ውይይትም የእኛ ጉዳይ ሳይሆን በዋናነት ሲቪክ ማህበራት ሊሰሩት የሚገባ ነበር ነገር ግን ይህንን የሚሰሩ ሲቪክ ማህበራት ባለመኖራቸው ክፍተቱን ለመሙላት እየሰራን እንገኛለን፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- እንደሚያውቁት ከ1997 በፊት በተለይ በውጪ አገራት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሰላማዊ ትግሉን በመደገፍ ረገድ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደርግ ነበር፡፡የምርጫው ውጤት መገለጹን ተከትሎ በተፈጠሩ ነገሮች የተነሳ የሰላማዊ ትግል አዋጭ አይደለም የሚሉ ቡድኖች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ ዜጎች እንዲህ አይነት ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ መንግስት አስተዋእጾ አላደረገም?

የተከበሩ አቶ ግርማ፡- ትግሉ ፍሬ እንዲያፈራ እኮ ከመነሻው መንግስት አይፈልግም፡፡ገዢው ፓርቲ ለአርባና ሰላሳ አመታት መግዛት እንደሚፈልግ ነግሮናል፡፡እኛ ከእነርሱ እንዲህ አይነት ነገር ይመጣል ብለን አንጠብቅም፡፡ከዚህ ይልቅ እኔ የማይመቸኝ በየጊዜው ቅንጅት እያልን የምንዘፍናት ዘፈን ናት፡፡በ97 የተፈጠረው ነገር መንግስት አሸንፋለሁ በሚል ትእቢት ተሞልቶ ለተቃዋሚዎች የተሻለ ሁኔታን ፈጠረ ህዝቡም
እንዲህ አይነት ነገር ሲፈጠርለት በትክክል ምን እንደሚፈልግ አሳየ፡፡ነገር ግን የነበረው ነገር ሁሉ የተደራጀ አልነበረም መንገስት የተቃዋሚ አመራሮችን ጠራርጎ እስር ቤት ሲያወርድ ህዝቡ ተመልሶ ወደ ነበረበት ገባ ፡፡

ይህ የሚያሳየን የተቀናጀ ነገር አለመኖሩን ነው፡፡ትግሉ የሚቆም ሳይሆን ቀጣይነት የሚኖረው መሆን አለበት፡፡ አንድ ሚልዮን ሰው የሚሳተፍበትን የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ሀምሳ ሰው በማሰር አይኮላሽም፡፡ለምሳሌ የሙስሊሞቹን አይነት እንቅስቃሴ ተቃዋሚዎች ለምን መፍጠር አልቻሉም ይባላል፡፡ሙስሊሞቹ በየሳምንቱ አርብ የሚገናኙባቸው መስጊዶች አሏቸው እኛ ይህንን ለማድረግ መገናኛ ቦታዎችን መፍጠር አለብን እንደምታውቁት አንድነት አምስት መቶ ሃምሳ የምርጫ ወረዳዎችን በመለየት በአሁኑ ሰዓት ህዝቡን የማገኝበት መድረክ ይሆነኛል በማለት እየሰራ ይገኛል፡፡ የእኛ መስጊዶች የሚሆኑት እነዚህ ናቸው ማለት ነው፡፡
እንደዚህ አይነት ቦታዎችን መፍጠር ካልቻለን አገር አቀፍ እንቅስቃሴ መፍጠር አንችልም፡ ፡ መንግስት ከ97 ምርጫ በኋላ ባወጣቸው ህጎች አማካኝነት ትልቅ ሚና የነበራቸውን ሲቪክ ማህበራትና ሚዲያዎች ከጨዋታ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- በአንድ የውይይት መድረክ ማኪያቶ ወይም ቢራ እየጠጣን መታገል እንፈልጋለን በማለት መናገርዎ ጉርምርምታ ስለመፍጠሩ ተወርቷል፡፡ምን ማለትዎ ይሆን?
የተከበሩ አቶ ግርማ፡- ብዬ አላውቅም ግን ቢራና ማኪያቶ የሚከለክለኝ ነገር ግን የለም፡፡ቢራና  ማኪያቶ እንደማልለምን ካረጋገጥኩ በኋላ ነው ፖለቲካ ውስጥ ገብቼ መጫወት የጀመርኩት፡፡ ደግሞም እኮ ሱባኤ አይደለም የምገባው ነገር ግን እንዲህ አይነት ነገር ተናግሬ አላውቅም ሌሎችም እንዲህ አሉ በመባሉ ይደብረኛል

ፍኖተ ነፃነት፡- የፍኖተ ነጻነት ጋዜጣን ማተሚያ ማሽን ተሳክቶላችሁ ብትገዙ መንግስት ምን ሊያደርግ ይችላል የሚል ጥያቄ እንደቀረበልዎም ሰምተናል ምላሽዎ ምን ነበር?
የተከበሩ አቶ ግርማ፡- ይህንን እኮ መመለስ ያለባችሁ እናንተ ናችሁ እኔ እሰጥ የነበረው ምላሽ ግን እሞታለሁ ከሚል ስጋት የተነሳ ሰው ሳይተኛ እንደማይቀር ነበር፡፡ሊወርሱት ይችላሉ ወይም ያዘርፉታል የሚል ስጋት ያላቸው ሰዎች አሉ ነገር ግን ይህንን በመፍራት ማድረግ ያለብንን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አንልም፡፡ ጋዜጣችንን ያትሙ የነበሩ ማተሚያ ቤቶችን በስልክ እየደወሉ አስፈራሯቸው እንጂ ማተሚያ ማሽኑን አልወሰዱባቸውም፡፡ ስለዚህ ለእኛ ደውለው ከአሁን በኋላ አንዳታትሙ ቢሉን ፈርተን አንቀመጥላቸውም፡፡ሊወርሱት ወይም ሊሰርቁን ይችላሉ እናም ይህው ሌባ መንግስት ነው ብለን አናሳያቸዋለን፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- በስራ አጋጣሚም ይሁን ለፖለቲካ ስራ ወደ ተለያዮ አገራት ሲያመሩ ከየአገራቱ የፓርላማ አባለት ጋር ተገናኝተው ሲወያዮ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ መሆንዎን ሲሰሙ ምን ይላሉ?
የተከበሩ አቶ ግርማ ፡- ይህንን ብንተወው ነው የሚሻለው፡፡የሚመለከቱኝ እንደብርቅዬ ነገር ነው ፡፡ስለ እኔ ብቸኛ የተቃዋሚ ተወካይ በፓርላማ መሆኔን ሲሰሙ የምናወራበት ነገር ሳይቀር እየተለወጠ ብቸኛው መወያያ የምሆነው እኔ ነኝ፡፡ እየመጡ እየነካኩኝ ምናምን ነው የሚያወሩኝ እንደ ልዮ ነገር ነው የሚመለከቱኝ፡፡ እንዲህ በመሆኑ የምደሰት የሚመስላቸው ሰዎች ካሉ ተሳስተዋል ይህ አያስደስትም ፡፡ ምናልባት የገዢው ፓርቲ ማንነት በዚሀ ተጋልጦ ይሆናል ነገር ግን የሚጋለጠው እርሱ ብቻ አይደለም አገርም ትገመታለች፡፡ እኔ አንድ የፓርቲ ተወካይ ብቻ በመሆን ፓርላማ ከምገባ ለመንግስት የሚሻለው የአንድ ፓርቲ አመራር ሆኜ እዛ ብገባ ነበር፡፡እንዳለመታደል ሆኖ ግን እነርሱ በዚህ ሊማሩ አልፈቀዱም አሁን የተደረገውን ምርጫ በአጠቃላይ ስለ ማሸነፋቸው እየተናገሩ ነው፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- እርስዎ ወደ ውጪ ባመሩበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስድስት ወራት ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡ ብዙዎች እርስዎ በፓርላማው የሚያቀርቡትን አስተያየት ለመስማት ፈልገው ነበር፡፡እንዴት ነው ሪፖርቱ የሚቀርብበትን ወቅት ባለማወቅዎ ነው ወይስ ሪፖርቱ ያለ ጊዜው እንዲቀርብ በመደረጉ ነው?

የተከበሩ አቶ ግርማ ፡- ሪፖርቱ የቀረበው የጊዜ ሰሌዳውን ጠብቆ አይደለም፡፡አንድ የሚያሳምን ምክንያት ሊሆን የሚችለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለት ወር በፊት መጥተው የነበረ መሆኑ ነው፡ ፡እኔ በግሌ እንዲያመልጠኝ ከማልፈልጋቸው የፓርላማ ስብሰባዎች አንዱ ነበር ነገር ግን መሄድ ስለነበረብኝ በወቅቱ በፓርላማው መገኘት አልቻልኩም፡፡ተመልሼ ከመጣሁ በኋላ ከገረሙኝ ነገሮች አንዱ ሪፖርቱን በማግኘት ለማንበብ ሞከርኩ ሌላ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ሪፖርቶች ከመቅረባቸው ቀደም ብሎ የፓርላማ አባላቱ አንብበው ጥያቄዎችን እንዲያነሱ እንዲደርሳቸው ይደረጋል፡፡እናም ሪፖርቱ እንደተቀመጠልኝ በማሰብ ሳጥኔን ከፈትኩ ሳጥኔ ውስጥ አልገባም፣ምናልባት አለመኖሬን ሲያውቁ ቢሮ ልከውልኝ ይሆናል ብዬ ቢሮ ሄጄ ፈለግኩ እዚያም አልመጣልኝም፤ ከዚያም ማባዣ ክፍል ሄጄ ለምን ሪፖርቱን አልላካችሁልኝም ስላቸው ሪፖርቱ እንዳልተበተነ
ነገሩኝ፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- የፓርላማ አባላቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርቱ ሳይደርሳቸው ሪፖርቱ ቀረበ እያሉን ነው?
የተከበሩ አቶ ግርማ ፡- እኔ ብኖር ኖሮ እንዲህ አይደረግም ወይም ለኢትዮጵያ ህዝብ ሪፖርቱ ሳይቀርብልኝና ሳልዘጋጅ እንድጠይቅ መደረጌን እናገር ነበር ፡፡አንድ መሆኔን ብቻ ሳይሆን መመልከት ያለብን አንድ ሆኜም
የምሰራውን ነገር ነው፡፡በፓርላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይጠይቁ የነበሩ የፓርላማ አባላት ጥያቄዎቹን ለዚያውም የተጻፈ እያነበቡ መጠየቃቸው እንድገረም አድርጎኛል፡፡እነዚህ ሰዎች ጥያቄውን የጠየቁት እዚያው ነው
እንዳይባል ከመጀመሪያው ስማቸው እየተጠራ ነው እንዲጠይቁት የሚደረጉት፣ሪፖርቱ ደርሷቸዋል ከተባለም እንዳልተበተነ ማባዣ ክፍሉ ተናግሯል፡፡በአጭሩ ለፓርላማ አባላቱ ጥያቄ እያዘጋጀ የሚበትን አካል አለ ማለት
ነው፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- የአሜሪካ መንግስት እነ አንዷለም አራጌና እስክንደር ነጋ ለፈርድ ቤት ያቀረቡት ይግባኝ ውድቅ ተደርጎ እስሩ እንዲፈጸምባቸው መደረጉን በመቃወም ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥቷል መግለጫው በቀጣይ በአሜሪካና በገዢው ፓርቲ መካከል በሚኖረው ግኑኝነት ላይ ተጽእኖ ያሳርፍ ይሆን?
የተከበሩ አቶ ግርማ ፡- በእርግጥ የአሁኑ ጉዞዬ አላማ የአሜሪካ መንግስት እንዴት እንደሚሰራ ማየትን የሚጨምር ነበር፡፡ ከዲፕሎማቶች ጋር በተገናኘሁበት ወቅትም ያወራነው ስለዚህ ጉዳይ ነው፡፡በተረፈ እንዲህ አይነት ነገሮች በመደበኛነት ባይሆንም መነሳታቸው አይቀርም፡ ፡በግል ባነሳናቸው ውይይቶች የኢትዮጵያ መንገስት ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ላይ እየወሰደ የሚገኘው ነገር እያሳሰባቸው እንደመጣ ይነግሩኛል፡፡መሰመር ያለበት ጉዳይ ግን አሜሪካኖች ተጫኑም አልተጫኑም ትልቁ ትግል መደረግ የሚኖርበት በእኛው ነው፡፡ 

መንግሰትን ሌሎች እንዲያንበረክኩት መጠበቅ የለብንም፡፡ መጫን ያለብን እኛው መሆን አለብን፡፡ በደርግ ዘመን አባቴ ‹‹አንድ ልጅ ከዚህ ቤት በወታደሮች በሃይል አይወሰድም ልጆቼን የሚወስዱት እኔን ገድለው ነው››ይል ነበር፡፡በዚያ ወቅት እኮ ቤተሶዎች ልጆቻቸውን በብሄራዊ ውትድርና ሰበብ ይነጠቁ ነበር፡፡ እንዲህ አይነት እምቢ የሚል ሰላማዊ ታጋይ ማፍራት ይኖርብናል፡፡ ፊሪዎች ከሆንን አንድ ነገር ማድረግ አንችልም፡ ፡እናንተ ፈሪዎች ስለ መሆናችሁ አላውቅም ብትሆኑ ኖሮ እዚያ ግቤ አትገቡም በእንዲህ አይነት እሳትም አትጫወቱም፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- በቅርቡ እንግዲህ መንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎቹ ላይ ከስራ የማንሳትና የእሰር እርምጃ ወስዷል፡፡ ጸረ ሙስናም በፓርላማ በኮሚሽነሩ አማካኝነት ባቀረበው ሪፖርት ከፍተኛ ምዝበራ ስለ መፈጸሙ ተናግሯል፡፡ ሰሞነኛው እርምጃ መንግስት በሙስና ላይ ቆርጦ ስለመነሳቱ የሚያሳይ ነው ወይስ የተለመደው የፖለቲካ ጨዋታ ነው?

የተከበሩ አቶ ግርማ ፡- እኔ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተስፋ ከሚያደርጉ ሰዎች አንዱ መሆኔን ከዚህ ቀደም ተናግሬያለሁ፡፡ የፖሊሲ ለውጥ እንኳን ባይኖር የሹፌር ለውጥ የተወሰነ ለውጥ እንደሚፈጥር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው የሚያስቡ ደግሞ አሉ፡፡ ሹፌሩ ለውጥ ያመጣባቸዋል ብዬ ከማምንባቸው ነገሮች አንዱ ተቋማትን በህግ በተሰጣቸው መብት መሰረት እንዲሰሩ ያደርጋሉ በማለት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች፣እንባ ጠባቂ፣ጸረ ሙስና፣የፌደራል ኦዲተርና ሌሎችም በነጻነት መስራት ከቻሉ በትክክል የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስልጣን ማየት እንችላለን፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እነዚህ ነገሮች አያስፈልጓቸውም የሚፈልጉትን ነገር በስልክ መጨረስ ይችሉ ነበር፡፡ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ከዚህ መቆጠብ አለባቸው፡፡ 

ጸረ ሙስና ያደረገውን ነገር ማበረታታት አለብን ይህንን የምናደርገው ሰዎቹን ስለምንጠላቸው አይደለም፡፡ የግድ መደረግ ስላለበት ነው፡፡ የፖለቲካ ጉዳይ መሆኑም መዘንጋት የለበትም ፡፡ በሚኒስትር ደረጃ የሚገኝ ሰው በሙስና ተዘፍቆ መገኘቱ ለምንግሰት ጥሩ ነገር አይደለም፡፡ በዚህ ኢህአዴግ መጠየቅ አለበት፡፡ ሌባ የሾመው እኮ እርሱ ነው፡፡
ፍኖተ ነፃነት ፡- እነ መላኩ ፈንታ ከመታሰራቸው ቀደም ብሎ መቀሌ ላይ ህወሃት ስብሰባ ማድረጉንና እንዲታሰሩ ስለ መወሰኑ ተነግሯል ከዚህ በመነሳትም የባለስልጣናቱ መታሰር ከሙስና ባሻገር ሌላ መልእክት እንዳለው ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ፣በዚህ ላይ የወሳኝነቱን ሚና ከሀይለማርያም ይልቅ ለህወሃት የሚሰጡ ቀላል ቁጥር የላቸውም በዚህ ይስማማሉ?

የተከበሩ አቶ ግርማ ፡- ባህርዳር ላይ ስብሰባ እንደሚደረገው መቀሌ ላይ ሊደረግ ይችላል፡፡ ሌላው እኔ ህወሃቶች ሌሎችን ማሽከርከር የሚችሉበት ቁመና ላይ ናቸው ብዬ ለማመን እቸገራለሁ፡፡ እንደውም እነርሱ ራሳቸውን ከሌሉቹ እኩል ለማድረግ እየሰሩ የሚገኙ ይመስለኛል፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- ራሳቸውን እኩል ለማድረግ ሲሉ በተለይ የብአዴኖችን እየጎሉ መምጣት ለመምታት እንዲህ አይነት እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋሉ የሚባለው?
የተከበሩ አቶ ግርማ ፡- ብአዴን ከጎላ እኮ ከእርሱ እኩል ያልሆነው ጫና ሊፈጥርበት አይችልም፡ ፡ሙስና የሚባለውን ነገር ኢህአዴግ ለመታገል ከተነሳ ተቃዋሚዎች ብንሆን እንኳን መደገፍ ይኖርብናል፡፡ ሚዲያዎችም ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ በሙስና የታሰሩትን ሰዎች ሳይ ወደ አእምሮዬ የሚመጣው የመጣው የመጀመሪያ ነገር ሌሉችን በተለይም ነጋዴዎችን ሌቦችና ሙሰኞች እያሉ ሲዘልፉ መቆየታቸው ነው፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- በእስሩ ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ሰዎች ሌላ የሚያነሱት መከራከሪያ ጸረ ሙስና ትልልቆቹን አሳዎች ሳያጠምድ ትንንሾቹ ላይ ሲያተኩር መቆየቱንና ከዚህ ቀደምም በእነ ስዬ ላይ የተወሰደው እርምጃ የበቀል አይነት መሆኑን ነው፡፡
የተከበሩ አቶ ግርማ ፡- ጸረ ሙስና እስከ ዛሬ በነበረው ስራው ከፓርቲ መገልገያነት ነጻ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን የአሁኑን ጉዳይ ከእነ ስዬ ጋር ማገናኘት አይገባንም፡፡ እነዚህ ሰዎች በአብዩታዊ ዴሞክራሲ ፍቅር ወድቀው ሌሎችን ሲያስጨንቁ የነበሩ ናቸው፡፡የፖለቲካ ልዩነት እንዳላቸው እኛ እስካሁን ድረስ ምንም አልሰማንም፡፡ጥፋት አጥፍተው አይ እንዲህ ስላልን ነው ማለት ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም፡፡መውጣት የነበረባቸው መጀመሪያ ነው፡፡

ፍኖተ ነፃነት፡- ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ባህር ዳር ላይ አድርጎት በነበረው ዘጠነኛ ጉባኤ ሙስናን እንደሚዋጋ መናገሩ አይዘነጋም ነገር ግን ተቺዎች ኢህአዴግ ሙስናን የሚዋጋ ከሆነ ራሱን ያጠፋል ይላሉ፣ለዚህ የሚያነሱት ነጥብ ድርጅቱ አባላቱን የሚሰበስብበት መንገድ ከጥቅም ጋር የተቆራኘ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ጸረ ሙስና ኢህዴግንም መመልከት አይገባውም ይላሉ?

የተከበሩ አቶ ግርማ ፡- አለበት እንጂ ከሌባ ስብስብ መሃል ጎበዝ ሌባ ይወጣል እንጂ አዲስ ነገር አይኖርም፡፡ እያንዳንዱ ሰው ለምን በኢህአዴግ ወስጥ እንደሚቆይ ብናጣራ ለፓርቲው ብለው የምናገኛቸው ሰዎች በጣም ጥቂት ይሆናሉ ፡፡ በመሰረቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በፍቅር እንድትወድቅለት የሚያደርግህ አይደለም፡፡ አሁን ኢህአዴግ በመሆናቸው ብቻ ስራ ያገኙ ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ባይሆኑ ኖሮ ይህንን ስራ አያገኙትም ስለዚህ ከድርጅቱ ጋር እንዲጣበቁ ያደረጋቸው ጥቅም መሆኑን ለመገንዘብ አያስቸግርም ይህ ደግሞ ትልቅ ሙስና ነው፡፡

No comments:

Post a Comment