Tuesday 7 May 2013

አራት፦ ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም! የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዢንና ራድዮ

ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ሚያዝያ 2005
Professor  Mesfin Woldemariamእንደሚመስለኝ ከነፍጠኛነት ይልቅ ነገረኛነት ጥሩ የዴሞክራሲ መሠረት ሊሆን ይችላል፤ በእርግጥ ነገረኛነት ለኢትዮጵያውያን የባህል መሠረት አለው ቢባልም በነፍጠኛነት ስር እየታሸ ነው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ከነፍጠኛነት ጫና ስር ሲያመልጡና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመደራጀት ሲሞክሩ ሁሌም ነገረኛነት ያይላል፤ በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ በተለያዩ ከተሞች የኢትዮጵያውያን ማኅበሮች መሀከል ሕግንና ሥርዓትን ተከትሎ የተዋጣለት ማኅበር ብርቅ ነው፤ አብዛኛዎቹ እየተነታረኩ ሲከፋፈሉና ሲዳከሙ የሚታዩ ናቸው፤ የችግሩ መነሻም ሁልጊዜም ሥልጣን፣ ገንዘብና ዝና ናቸው፤ 


 ከነዚህ ሲያልፍም በኢትዮጵያዊነት መሠረት ላይ ብቻ የቆመውን ማኅበር የፖሊቲካ እምነት ወይም የጎሣ ቀለም ለመቀባት በመሞከር ነው፤ በኢትዮጵያውያን ማኅበሮች ላይ ሲታይ የቆየው ኋላ-ቀር አስተሳሰብ በውጭ በተቋቋሙ ቤተ ክርስቲያኖችም ላይ መታየት ጀመረ፤ ባህል ነዋ።
በዘመናችን የተከሰተው ነገረኛነት ከባህላዊው እሰጥ-አገባ ክርክር በጣም የራቀና የዘቀጠ ነው፤ ‹‹ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረከመጠምጠም መማር ይቅደምነገር ሳያውቁ ሙግት፣ ሳይጎለብቱ ትዕቢት…›› ወዘተ. በሚሉ የሕገ ኀልዮት መመሪያዎች የሚገዛ ሙግትም ሆነ ክርክር፣ ወይም ወግና ጨዋታ ከነገረኛነት የተለየ ነው ለማለት ይቻላል።

የዛሬው ነገረኛነት የአእምሮ ሥርዓተ-ቢስነት አለበት፤ እኩልነትን በትክክል ካለመረዳት የሚገኝ የአእምሮ ብልግና አለበት፤ ዱላ ከያዘ ጋር ነገረኛነት አይኖርም፤ ፍርሃት ያጠፋዋል፤ ሥርዓት የሚመጣው በዱላ ብቻ ነው ከተባለ ውርደት ነው፤ በአንድ በኩል በስደት ያሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በስደተኛነት እኩል ናቸው ከሚል መነሻ፣ በሌላ በኩል በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጭቁን አቅመ-ቢሶች በመሆናቸው እኩል ናቸው ከሚል መነሻ ይጀምርና ሌላው ልዩነት ሁሉ ድራሹ ይጠፋል፤ ስለዚህ ማንም በምንም ጉዳይ ቃላትን እየፈተለ እንደዘመኑ ዳንስ ብቻ ለብቻ መንቦጫረቅ የኢትዮጵያውያን የነገረኛነት ባህል ሆኖአል፤ በቅርቡ አንደሰማሁት በዚህ የቃላት መንቦጫረቅ (ፓልቶክ) አንደኛ ሶማሌያውያን፣ሁለተኛ ኢትዮጵያውያን፣ ሦስተኛ ኤርትራውያን ሲሆኑ ሌሎች አፍሪካውያን የሉበትም አሉ፤እውነት ካልሆነ እንርሳው፤ እውነት ከሆነ ግን ብዙ የምንማርበትና ራሳችንን የምናስተካክልበት ምክንያት ሊሆነን ይችላል፤ በቃላት መንቦጫረቅ ለጊዜው በእኩልነት ጸዳል የሚያሞቅ ቢመስልም የኋላኋላ ራስንም፣ማኅበረሰቡንም ይጎዳል።

የሶማልያውያኑንና የኤርትራውያኑን ባላውቅም ስለኢትዮጵያውያኑ ባጭሩ ምስክርነት መስጠት እችላለሁ፤ አብዛኛዎቹ የዘመኑ ኢትዮጵያውያን ፊደል ከቆጠሩ ራሳቸውን አዋቂዎችና ፈላስፋዎች አድርገው በአደባባይ ለማቅረብ አያፍሩም፤ ግን ያሳፍራሉ፤ ለአንባቢው ማስተላለፍ የሚፈልጉትን ራሳቸው ሳያውቁት ጀምረው ሳያውቁት ይጨርሱታል፤ በእንግሊዝኛ መጻፍ የማይችሉ ቢሆንም በአማርኛ ጽሑፋቸው እንግሊዝኛ የሚያውቁ ለማስመሰል የሚያደርጉት ጥረት ሀሳቡንም አጻጻፉንም ያወላግድባቸዋል፤ ለዚህ ብዙ ምሳሌዎችን ከየጋዜጣው ማሳየት ይቻላል፤ ግን አስፈላጊ አይደለም፤ ምክንያትም አለኝ፤ ካላበዙት አንድ ጥሩ ባሕርይን ያመለክታል፤ በድንቁርናም ቢሆን በጣም የሚያስደንቅ በራስ መተማመንን ያሳያል፤ እኔ አምስተኛ ክፍል ሆኜ (የዚያ ክፍል ጓደኛዬ የዓየር መንገዱ ግርማ መኮንን አሁንም አለ) 

አንድ የሳይንስ አስተማሪ የካቶሊክ መነኩሴ መሬት ትዞራለች ብለው ማስረጃዎቻቸውን ሲደረድሩ እኔ እጄን አውጥቼ ‹‹መሬት አትዞርም፤ ዳዊት ወአጽንአ ለምድር ዲበ ማይ ይላል፤ ብዬ ድርቅ አልሁ፤ እግዚአብሔር ያሳያችሁ፤ እኔ ገና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነኝ፤ አስተማሪዬ ያላቸው እውቀት ለእኔ እሳቸው ከመጡበት አገር ከካናዳም ይርቃል፤ በዚያ ላይ እሳቸው መነኩሴ ናቸው፤ ዳዊትን በየቀኑ ይደግማሉ፤ ስለሃይማኖትም ቢሆን እኔ ከሳቸው ጋር አልወዳደርም ነበር፤ አስተማሪዬ ዝም ብለው ይስቁብኝ ነበር፤ በፈተና ጊዜ ግን ዳዊትን ጠቅሼ አልመለስሁም! ባልለወጥ የትምህርት ነገር በአምስተኛ ክፍል አብቅቶልኝ ነበር፤ እንዲህ ያለውን አጉልና ባዶ በራስ መተማመን በቶሎ ካልቀጩት አእምሮን ያባልጋል፤ በጥሩ መልኩም ቢሆን ነገረኛነት አይወደድም፤ ዳኛቸው ወርቁ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የወጣው ክርክሩን ሊቀበሉት ያልፈለጉ ሰዎች ‹‹ነገረኛ›› (እንደአቶ ሐዲስ ዓለማየሁ ‹‹ጉዱ ካሣ››) ተብሎ ነበረ።

አፍ ዳገት አይፈራም ሲባል የአነጋገሩን ትክክለኛነት ለመለካት ሳይሆን የተናጋሪውን አለመፍራትና አለማፈር ለመግለጽ ነው፤ አሽከር በአንደበቱ ውሻ በጅራቱ ሲባልም መናገር ወደላይ እያዩ ለመቀባባት ወይም ለማረጋገጥ ነው እንጂ ይዘቱ ከእውነት ጋር የማይገናኝ ይሆናል፤ ነገረኛ ማለት ደረቅ፣ እውነቱን ለቅቆ ለስለስ የማይል፣ ችኮ-መንቻካ ማለትም ይሆናል፤ ባለሥልጣኖቹ ለመስማት የሚፈልጉትን ብቻ እየመረጠና እያዋዛ ሳይሆን ለሱ የሚታየውን ደረቁን እውነት ይዞ የሚናገር ማለት ነው፤ በግልምጫ፣ በቁጣ፣ በጥቅም፣ ሳይሸነፍ የሚኖረው ነገረኛ ይባላል፤ ባህላችን ነገረኛነትን የሚያጥላላው ለኔ እንደሚመስለኝ ጠመንጃ-ያዥነትን ለማስከበር ነው፤ ሎሌ የሚኖረው መሣሪያ ወይ አንደበት ወይ ጠመንጃ ነው፤ ሎሌ በአንደበቱ ሲናገርም ሆነ በጠመንጃው ሲተኩስ ለጌታው ሲል ለመግደል ወይም ለማቁሰል ነው፤ የራሱ ዓላማም ሆነ ኢላማ የለውም።

ጠመንጃ-ያዥና ጠመንጃ-ያዥ ሲጫረሱ የሚያደርሱት ከባድ ጥፋት ለሰላማዊው ሕዝብም፣ ለአገርም  ይተርፋል፤ ነገረኛነት የዚያን ያህል አይጎዳም፤ በተጨማሪም ወደሠለጠነና ሥርዓት ወዳለው እሰጥ-አገባ ክርክር ለመድረስ ከጉልበተኛነት ከመነሣት ይልቅ ከነገረኛነት መነሣቱ መንገዱን ቀና የሚያደርገው ይመስለኛል፤ ነገረኛነት በአጉል እኩልነት ላይ የቆመ ቢሆንም የዱላ ፍርሃት የለበትምና ይሻላል፤ ደግሞም ትምህርት እየተስፋፋ ሲሄድ አጉል ነገረኛነት ለዝናብ እንደተጋለጠ ጨው እየቀለለ ይሄዳል፤ ስለዚህም አጉል ነገረኛነት የሚያስጠላ ቢሆንም ብንታገሠውና ብናርመው ከመደባደብ የተሻለ አማራጭ በመሆኑ ይጠቅመናል፤ እየተራረምን በዚህ መንገድ ብንሄድና ብንለምደው፣ የእውቀትን ጎዳና አገኘነው ማለት ነው፤ ለብዙ ችግሮቻችን መፍትሔዎችን ማግኘት እንችላለን ማለት ነው።

No comments:

Post a Comment