Monday 6 May 2013

"አባይ ማደሪያ የለው ደሞዝ ይዞ ይዞራል…"አቤ ቶክቻው!!

"አባይ ማደሪያ የለው ደሞዝ ይዞ ይዞራል…"የምትለው አባባል ከተፈጠረች እነሆ ሁለት አመት አለፋት፡፡ ግዜው ይሮጣል፡፡ ሶስት፣ አራት፣ እና አምስት አመትም እዝችው አጠገባችን ቁጭ ብለው የምናወራውን እየሰሙ ነው፡፡
ከሶስት አመት በፊት መንግስታችን የትራንስፎርሜሽን እቅድ የሚባል ወደ አስማት ቀረብ የሚል ዕቅድ አውጥቶ "ወተት በቧንቧ በየቤቱ እናቀብላለን" አይነት ነገር ሲነግረን ይቺ ነገር የየትኛው "እንትን" ውጤት ትሆን ብለን ስንጨነቅ ሰንበተን ነበር፡፡ ከዛ ወድያው ትራንስፎርሜሽኑን አባይ አጥለቀለቀው፡፡ ከዛስ…. ከዛማ ትራንስፎርሜሽን ተረስታ አባይ አባይ ይዘፈን ጀመር፡፡ ከዛስ…. ምን ከዛስ አለው… አባያችን ከእያንዳንዳችንን ኪስ ውስጥ ዘው ብሎ ገባ….ታ!

ሰላም ወዳጄ እንዴት ሰነበቱልኝ አውዳመቱ እንዴት አለፈ… እንኳንስ አውዳመቱ እና ስንቱ አያልፍም የተባለ ክፉ ቀን አልፏል… አሉኝ እንዴ! አዎ ጥሩ ነገር ብለውኛል፡፡ ቀጥሎም ገና ብዙ ቀኖች ያልፋሉ ዕድሜውን የሰጠን ሰዎችም ቁጭ ብለን እንታዘባለን፡፡ ስለዚህ ዕድሜውን ይለምኑ…! በቅጡ ካወጋን እኮ ሰነባበትን መሰል…! አንዳንድ ወዳጆቼም "በአነስተኛ እና ጥቃቅን ፅሁፎች አደከምከን እኮ" ሲሉ በውስጥ መስመርም በአደባባይም ተግሳጽ ልከውልኛል፡፡ ሰዉ ቀላል ተናጋሪ ሆኗል እንዴ…!

ለማንኛውም ዛሬ በአባይ ጉዳይ ላይ ትንሽ እናውጋ ብዬ ተከስቻለሁ…! ይቺ ፅሁፍ ለላይፍ መፅሄት እና እና ለ abetokichaw.com ድረ ገጽ ተብላ የተሰናዳች መሆኗንም እናገራለሁ፡፡ ከላይ በተንደረደርኩት መሰረት ስቀጥል እባክዎን ወዳጄ አብረውኝ ይዝለቁ ብዬ በመጋበዝ ነው፡፡

ለአባይ መዋጮ መዋጮ መባል የተጀመረ ሰሞን እኔ እሰራበት የነበረ የትምህርት ተቋም ከመንግስት ከፍተኛ አካላት ከፍተኛ ቁጥጥር ተጥሎበት ነበር፡፡ ቁጥጥሩ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአግባቡ ግልጋሎት ለህዝቡ እንዲሰጡ ተብሎ የተወሰደ ነበር፡፡ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች እና አለቃችን በዚህ ቁጥጥር የተነሳ የእለት እንጀራችንን እንዳይቆጣጠር፣ እንዳይወሳሰብ፣ ብሎም እንዳይቋረጥ ተጨንቀን፡፡ ተጨንቀንም፤ መስሪያ ቤታችንን በማፀዳዳት ስንተጋ በነበረበት ወቅት፤ የአባይ መዋጮ ነገር እየጠነከረ መጣ… እናስ… እናማ አለቃችን መጀመሪያ የስራ ሃላፊዎችን ሰበሰበ ሰብስቦም ሰራተኛው በሙሉ የአንድ ወር ደሞዙን ለአባይ እንዲለቅ የማሳመን ስራ እንዲሰሩ ተማፀነ፡፡

ሃላፊዎቹም ወደ ሰራተኛው ሄደው "ዛሬ የአንድ ወር ደሞዛችንን ባንለቅ ነገ ሁሉንም ደሞዛችንን ስራችንንም ጭምር እንደምንለቅ" አስረዱን እኛም ነገሩ ሲገባን ቃል ገባን፤ "ከነገሩ ጦም ይደሩ" ነውና፤ "ከጠቀመው ይውሰደው" ብለን የአንድ የአንድ ወር ደሞዛችንን እነሆ በረከት አልን፡፡ አቶ በረከትመን አቶ መለስም ፈገግ አሉልን፤ ያኔም መንግስት በመስሪያ ቤታችን ላይ ያሰበውን የጥራት ቁጥጥር ተወልን "እንዳሻሽ ሁኚ" የሚለውን ሙዚቃም ጋበዘን እኛም በደስታ ደነስን….! ጥራት ምናባቱ ጥሪት ነው ዋናው! ለአባይ በሰጠነው ጥሪት የጥራት ቁጥጥሩ ቀረልን እስይ እልልል…. አለልን!

የአባይ መዋጮ ነገር በሁሉም መስሪያ ቤቶች በተለይም በግል ቤቶች እንዲሁ ነበር፡፡ መስሪያ ቤቶች ከመንግስት ጋር አጓጉል ከመሳፈጥ ብለው፤ ለስራ ሃላፊዎች መመሪያ ያስተላልፋሉ፤ የስራ ሃላፊዎች ደግሞ በአለቆቻቸው ዘንድ ሞገስ ለማግኘት ብለው፤ ሰራተኞቻቸውን እጅህ ከምን ይላሉ፤ ሰራተኞችም ጠቅላላ ደሞዝ ከማጣ የአንድ ወር ደሞዜን ባጣ ይቀለኛል እና ይሁን ብለው ይለግሳሉ፡፡

ይህ በእንዲህ አንዳለ፤

ይቺ አባይ ትልቅ መሸቀያ ሆናለች፡፡ ደግሞ እኮ ሽቀላዋ ይሉኝታ አልባ መሆኗ ነው የሚገርመው፡፡ አንድ ወዳጄ አሁን ላለንበት "ግሎባል ዋርሚንግ" ስጋት ጭስ አልባ መሆን እንጂ ይሉኝታ አልባ መሆን ጠቀሜታ የለውም ብሎኛል፡፡ የኢህአዴግ ባለስልጣናቱ ግን በይሉኝታ አልባ ገንዘብ ስብሰባ ከሀገር ይወጡ እና አጓጉል የሆነ የቅስም ስብራት ሲደርስባቸው በንዴት የሚያወጡት ጭስ "ለግሎባል ዋርሚንጉ" ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ልብ አላሉትም… ስለዚህ እኛ ልብ እናስብላለን

ሰሞኑን የአባይ ወሬ በከፍተኛ ደረጃ እየተርገበገበ ይገኛል፡፡ በተለይ ኢህአዴግን ወክለው ፌስ ቡኩን የተቀላቀሉ ተበካዮች… (ይቅርታ የፊደል ግድፈት አለ እናርማለን…) በፌስ ቡክ የኢህአዴግ ተወካዮች… ነጋ ጠባ አባይ አባይ እያሉ በጎርፍ ሊያስወስዱን ምንም አልቀራቸው፡፡ እኔ የምለው አንዳንድ ከእኛ የበለጡ የኢህአዴግ ካድሬዎችን ግን ልብ ብላችሁልኝ ከሆነ አባይ ራሱ በአንድ ለ አምስት አደረጃጀት ውስጥ የገባ የኢህአዴግ አባል አድርገው እኮ ነው የሚያዩት፡፡ እውነቱ ግን የታወቀ ነው፤ እንኳንስ ወንዙ እና ሰዉ እራሱ የኢህአዴግ አባል የሚሆነው ለአበሉ ብሎ ነው፡፡ (የዘንድሮ ኑሮ እንደሆነ በአበልም አልተቻለም!) እናም ያለ አበል የኢህአዴግ አባል የሚሆን ከተገኘ አስይዛለሁ… (በቅንፍም የማስይዘው ለፖሊስ ነው ብዬ ማብራሪያ እሰጣለሁ!) የምር ግን አንድ እኔ ነኝ ከአገር ተባርሬ እንኳ ኢህአዴግዬ እያልኩ የማቆላምጣት… እና አንድ እርሳቸው ነበሩ… እንጂ ሌሎቹ በሙሉ ለአበላቸው ሲሉ ነው…! ይቺ አስተያየት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝን እንኳ ሳይቀር ትመለከታለች፡፡ ድሮ የዘመናት ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሰራዊት… ይባል አንደነበረው የአሁኑን የኢህአዴግ ሰራዊት ግን የሚወልደው የኑሮ ውድነቱ ነው፡፡ አባል ካልሆኑ መብል የለማ!

ታድያ አባይ ለየትኛው አበሉ ብሎ ነው በአንድ ለአምስት አደረጃጀት ውስጥ የሚገባው…! የትኛው የኑሮ ውድነት አላስቆም አላስቀምጥ ብሎት "ከመሞት መሰንበት" ብሎ በአባልነት ይጠመቃል፡፡ በእውኑ ራሱ ጠማቂ ሆኖ ሳለ ይጠመቅ ዘንድስ እንዴት ይሆንለታል…!
ለማንኛውም አባይ ኢህአዴግ አይደለም፡፡ አባይ አንድነትም አይደለም፡፡ አባይ ኦነግም አይደለም አባይ ግንቦት ሰባትም አይደለም፡፡ አባይ ኢትዮጵያ ነው፡፡ አባይ ወንዝ ብቻም ሳይሆን ሀገር ነው፡፡ አባይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት እና ጸጋ ነው፡፡

በቅርቡ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከአውሮፓ ሀገራት ዩሮ ከምድረ አሜሪካ ደግሞ ዶላራቸውን ከአረብ ሀገራትም ድርሃማቸውን አፈስፈስ! አድርገው ለመውሰድ ትልልቅ ቦርሳ ይዘው ሄደውም አልነበር…? ሲመለሱ ግን ትልቁ ቦርሳቸው ብቻ ሳይሆን አነርሱም ሽምቅቅ ብለው ተጣጥፈው እና አንሰው ነበር፡፡ "እኔን ያሳንሰኝ" አይባልም መቼም ከዚህ በላይ የት ልነስ…!
ለዚህ ዋነኛ ሰበቡ ውጪ ሀገር በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያጋጠማቸው ተቃውሞ ነው፡፡

ባለስልጣናቱ ኢትዮጵያ እንደተለመደው፤ "ታመጫለሽ አምጪ አለበለዛ ቤቱን ለቀሽ ውጪ" ማለት የሚሳካ መስሏቸው ቢሄዱም ኢትዮጵይውኑ "አንሰማችሁም" አሏቸው! እውነትም አላቸው፤ እነርሱ ስንት ጊዜ "ድምፃችን ይሰማ" ቢሉ እሺ ብሎ አንድም ቀን ያልሰማቸው መንግስት ገንዘብ አምጡ ሲላቸው እንዴት ሊሰሙት ይችላሉ…!

በውጪ ሀገር ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለይም ሀገር ቤት ከመንግስት መሬት ወስደው ቤት መስራት ያልጀመሩቱ… ከአባይ በፊት በርካታ መገደብ ያለባቸው ነገሮች አንዳሉ ጮክ ብለው እየተናገሩ ነው፡፡ ያ ማለት ግን አባይን መቃወም ማለት አይደለም፡፡ አባይ ይገደብ የሰብአዊ መብጥ ጥሰትም ይገደብ፡፡ አባይ ይገደብ እስርም ይገደብ፡፡ አባይ ይገደብ ስልጣንም ይገደብ፡፡ አባይ ይገደብ የእምነት ጣልቃ ገብነትም ይገደብ፡፡ አባይ የግደብ የፕሬስ አፈናውም ይገደብ፡፡ ያኔ የምናመነጨው ሃይል ለጎረቤት ሀገር ብቻ ሳይሆን ለመላው አለም ይበቃል… ስለዚህ ስሙን… ነው የሚሉት፡፡

ይህንን በቅጡ ያልሰሙ የኢህአዴግ የስጋ ዘመዶች ግን በአባይ ላይ ትንፍሽ የሚለውን ሁሉ የኢትዮጵያ ጠላት ማድረጋቸው ሳያንስ ራሱ አባይን በአንድ ለአምስት አደረጃጀት የታቀፈ የኢህአዴግ አባል አድርገውት ቁጭ አሉ! ይሄንን አባይ ቢሰማ ከአጠገቡ የበቀለች ዛፍ ላይ ይሰቀል ነበር፡፡

ከዚች ጋ የምትመሳሰል አንዲት ጨዋታ እነሆ እንደማሳረጊያ ትሁን!

ሰውዬው ሀገር ያስቸገረ ዘራፊ ነበር፡፡ ታድያ የሆነ ጊዜ በቁጥጥር ስር ይውል እና ስቅላት ሊከናወንበት ህዝብ የተሰበሰበበት አደባባይ በአንገቱ ሸምቀቆ ገብቶ ሳለ፤ ንጉሱ አንድ ዕድል ሰጡት "እስቲ እዚህ ከተሰበሰባችሁት ውስጥ እኔ ይሄንን ሰው ባል አድርጌ መክሬ ገስጬ እመልሰዋለሁ፤ የምትል ሴት ካለች ትምጣ" አሉ፡፡ ይሄን ጊዜ አንዲት በሀገሩ የታወቀች እና በዘርፈ ብዙ ችግቿ የምትተች ቢመክሯትም አልሰማ ያለች (ስናጠጋጋም እንደ ኢህአዴግ ያለች ሴትዮ እንበላት) በጥቅሉ በክፉ አመሏ የተነሳ ባል አጥታ ቁማ የቀረች ሴት፤ "እኔ አድነዋለሁ… እኔ መክረዋለሁ…" ብላ ወደ ንጉሱ ዘንድ ቀረበች፡፡ ወንጀለኛውም ወደ ሴትዮዋ ዘወር ብሎ ቢያይ ያውቃታል… አትሆነውም፡፡ አንገቱ ከገመድ ውስጥ ነው… በልቡም የእርሷ ባል ከመባልስ… አለና በአንደበቱ ደግሞ "አጥብቀው…!" አለ!
እና ወዳጄ ኢህአዴግዬ ያለውን ይበለኝ እንጂ ይህን ግን እነግርዎታለሁ፤
አባይ የማንም ባል የማንም አባልም አይደለም፡፡ እርሱ የኢትዮጵያ አብራክ ክፋይ ነው! የማይሆን ጋብቻ ከሚፈፅም…. "አጥብቀው" ብሎ ጥልጥል ቢል ይመርጣል፡፡ አባይ የኢትዮጵያ ነው፡፡ የኢትዮጵያውንን ድምፅ የማሰማ አባይን ሊደፍርም፣ ሊወሽምም፣ ሊያገባም፣ ሊያግባባም ይከብደዋል፡፡

ስናበቃም እንላለን…

ከባዱን ነገር እንደማመጥ እና እናቅልለው!

ወዳጄ ይበሉ ይቺን ታኸል ካወጋን የጤና ያድርግልን፤ ይበሉ ያሰናብቱኝ!
አማን ያሰንበተን!

No comments:

Post a Comment