Wednesday 2 January 2013

የጋዜጠኛ እና መመህርት ርዮት አለሙ ይግባኝ ለታህሳስ 26 ተቀጠረ አቤ ቶክቻው

እንደምን ዋላችሁ አንድ ዜና አስነብባለሁ...

የጋዜጠኛ እና መመህርት ርዮት አለሙ ይግባኝ ለታህሳስ 26 ተቀጠረ

ይህ ቀጠሮ ለመጨረሻ ጊዜ የተባለ ነበረ። ጋዜጠኛይቱ ከዚህ በፊት በዋለው ይግባኝ ሰሚ ችሎት የአስራ አራት አመቱ ፍርድ ወደ አምስት አመት ዝቅ ቢደረግላትም እርሷ እና ጠበቆቿ ግን ምንም ማስረጃ ባለቀረበብን ክስ 5 አመት ምን በወጣት ብለው ጉዳያቸውን ወደ ሰበር ሰሚችሎት ይዘው መሄዳቸው ይታወሳል።

ሰበር ሰሚውም፤ መጀመሪያ ለጥቅምት 20 ቀጠራት፤ ከዛም ጥቅምት 20 ሲደርስ ደግሞ ለታህሳስ 24 ቀጠራት፤ አሁንም ታህሳስ 24 ደረሰ።

ፍርድ ቤት በርካቶች በጊዜ ነበር የደረሱት። የዌብሳይት አዘጋጆች፤ የጋዜጣ ዘጋቢዎች፤ ነገሩን ለመታዘብ የመጡ ፈረንጃ ፈረንጆች የጋዜጠኛይቱ ቤተሰቦች እና እግዜሩም ጭምር ዳኞቹ የሚሉትን ሊሰሙ በግዜ ታድመዋል።

ቀጠሮው ሰባት ሰዓት ተኩል ነበር። ነገር እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ ቀብራሮቹ ዳኞች አልመጡም። ከአንድ ሰዓት መዘግየት በኋላ ዳኞቹ በፍርድ ቤቱ መንበር ተሰየሙ። ከዚህ በፊት ከነበሩት ዳኞች ውስጥ አንደኛው በጉዳት ወይም በአቅም አልያም ለጨዋታው ስልት ሲባል ተቀይረዋል።

ፍርድ ቤቱ ከተለያዩ ክፍለ ሀገሮች የመጡ ሰበር መዝገቦች የሚታዩበት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነው። የዕለቱ ዳኞች፤ ከጋሞጎፋ ጀምረው ከኦሮሚያ እና ሌሎችም አካባቢዎች የመጡትን ሰበር ሰሚ አቤት ባዮች መዝገብ ተመለከቱ። የአብዛኛዎቹንም ሰበር አይገባውም እያሉ መዝገባቸውን ዘጉት። ሰበር አቤት ባዮቹም ቅስማቸው እንደተሰበረ እሺ ብለው ከመውጣት ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም።

የጋዜጠኛይቱን ጉዳይ ሊከታተሉ የመጡ ብዙሃን፤ የርዮት አለሙ ይግባኝ ምን ይባል ይሆን ብለው በጉጉት እየተጠባበቁ ነው። ግን ምንም አልተባለም ጉዳዩን በቅጡ አልመረመርንም ተብሎ ለታህሳስ 26 ዳግም ተቀጠረ።

“ምናልባትም አንደኛው ዳኛ አዲስ ስለሆኑ ገና ነገሩን እስኪረዱት ሊሆን ይችላል” ብለው የገመቱ አሉ። “ማን ያውቃል ከነገ ወዲያ መልካም እንሰማ ይሆናል” ብለው ተስፋ ያደረጉም አሉ። “ከቀጠሮው ብዛት ይግባኙ አግባኝ አስመሰሉትኮ” ብለው ያሽሟጠጡም አሉ። "በቀጠሮ ብዛት አምስት አመቱ ሊሞላ ነውኮ..." ብለው የሰጉም አሉ።

ዜናው በዚህ አበቃ!

No comments:

Post a Comment