Tuesday 29 January 2013

ዛሬ ማክሰኞ ነው። አቤ ቶክቻው

የዛሬው ማክሰኞ እንዳለፈው ሳምንት አይነት ማክሰኞ አይደለም። ምክንያቱም ብሄራዊ ቡድናችንን ከአለም ጋር ሆነን የምናይበት ቀን ስለሆነ ነው።

ከሰላሳ አንድ አመታት በኋላ ፆማችንን ፈተን በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ እድሉን ማግኘታችን ትልቅ ድል፤ ትልቅ እድልም ነው። ብሄራዊ ቡድናችን የኢትዮጵያ ልጆች ለኳስ ባዳ እንዳልሆኑ ይልቁንም ትንሽ እሳት ቀረው እንጂ መጠነኛ ብስለት ቢታከልበት ኖሮ “አጃኢብ” የሚያሰኝ ቡድን ሊወጣው እንደሚችል ብዙዎች ሲስማሙ ሰምቻለሁ። እሳት ተብሎ የተገለፀው ልምድ ነው ለአንድ ቡድን ልምምድ ብቻ ሳይሆን ልምድም ጭምር በጣም ወሳኝ እንደሆነ ኤርሚያስ አማረም ፍስሀ ተገኝም ሲናገሩ ሰምቻለሁ። 
 
(በነገራችን ላይ ኤርሚ እኮ ደቡብ አፍሪካ የሄድክ መስሎኝ ነበር። በእውነቱ አሁን ባለህበት ርቀት ሆነህ ያንን ሁሉ ቅርብ እና ጥልቅ መረጃ ማቅረብ ተአምር ነው። አንተ ታምረኛ ጋዜጠኛ ዘገባህ ይብዛልን!)

በነገራችን ላይ የደቡብ አፍሪካው ጨዋታችን ስፖርት ብቻ አልነበረም። እንደውም ከስፖርቱ ይልቅ ሌላው ነገር ይጎላል።
የኢትዮጵያ ጨዋታዎች የሚካሄዱበት ስታድየም ውስጥ ያለው የፖለቲካ ስብጥር በኢትዮጵያ ፓርላማ ውስጥ ቢኖር ጥሩ ነበር። ግን የለም። የኢትዮጵያ ፓርላማ በጥሩ አትክልተኛ እንደተከረከመ ፅድ ነው። እንደውም በክፉ እንዳይተረጎምብኝ ብዬ እንጂ በሰለጠኑ የኮብል ባለሞያዎች እንደተጠረበ ድንጋይ ነው። ሁሉም ተመሳሳይ ቅርፅ እና መልክ አላቸው። ብል የተሻለ ነው።

የሆነው ሆኖ በደቡብ አፍሪካው ጨዋታ፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሀገር ፍቅር ሲጨፍሩ ሲያለቅሱም አይተናል። ከዛም አልፎ ጨርቅ ጥለው ሲያብዱም ተመልክተናል። ይሄ ሁሉ ሆኖ የሀገር ፍቅር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ላልገባቸው ደግሞ በቡርኪናፋሶ ስንሸነፍ ራሱን ያጠፋ ኢትዮጵያዊ መኖሩንም እንጠቁማለን!

አዎ የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ለኛ ኳስ ጨዋታ ብቻ አይደለም። ብዙ ነገር ነው እንጂ…

የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ጥያቄ በስታድየሙ ሲስተጋባ አይተናል። አለምም አብሮን አይቷል። መንግስት ኢትዮጵያን ያሸብራል ብሎ የፈረጀው ኦነግ አርማውን አንግቦ “ጀባዱ መሌ” እያለ ብሄራዊ ቡድኑን ሲያበረታታም ተመልክተናል።

ይሄ ጨዋታ ለመንግስታችንም ጨዋታ ብቻ አልነበረም። ገና ተጫዋቾቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲያቀኑ ከተሸለሙት ብር ላይ ቦጨቅ አድርጎ ቦንድ አስገዝቷቸው፤ እዛም ስትሄዱ ህዝቡ ቦንድ እንዲገዛ አድርጉ ብሎ መክሮ ነው የሸኛቸው። ሌላም ሌላም…

እናም ይሄ ብዙ ነገር የነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏችን ዛሬ ወይ ይጠናቀቃል ወይ ደግሞ ማን ያውቃል… ይቀጥል የሆናል።
ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ባለ መቶ ሰባ ሚሊየን ህዝብ ባለቤቷ ናይጄሪያ እና የዘጠና አንድ ሚሊየን ህዝብ ባለቤቷ ኢትዮጵያ ጨዋታ ይደረጋል። ናይጄሪያዎች በህዝብ ብዛት እና በልምድ ብዛት ቢበልጡንም በደጋፊ ብዛት እና በብሄራዊ መዝሙር ርዝመት እንበልጣቸዋለን። የናይጄሪያዎች ብሄራዊ መዝሙር አርባ ስምንት ሰከንድ ሲረዝም የእኛ ደግሞ አንድ ደቂቃ ከሃያ ሰከንድ ርዝማኔ አለው።

በመጨረሻም

በአንዱ የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ከእኛ ብሄራዊ ቡድን በላይ የረዘመ ብሄራዊ መዝሙር የሰማ አንድ ወዳጃችን “ከኛ የበለጠ ችግር ያለበት ሀገር አለ ማለት ነው… ችግር ሲበዛ እኮ ነው ብሄራዊ መዝሙር የሚረዝመው” ብሎናል። ይሄንን ነገር ላረጋገጠልን ውለታ ከፋይ ነን!
ለማንኛውም ድል ለዛች “እማማ” ለምንላት ሀገር ኢትዮጵያ!

No comments:

Post a Comment