Tuesday 11 June 2013

ዓባይን በራሳችን መገደብ አንችልም፤ እስካሁን የተሰበሰበው ገንዘብ ገና 6 በመቶ ያህሉ ነው አምባሳደር ሃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ!!


   ኢሳት ዜና -ህዳሴውን ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያ ሕዝብ መዋጮ ብቻ መሸፈን ወይም ዳር ማድረስ እንደማይቻል አምባሳደር ኃይሉ፡- ወልደጊዮርጊስ ገለጹ።

በሥራ ዓለም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት በተለያዩ ኃላፊነቶች የሠሩት፣ የፈረንሳይ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉትና በአሁኑ ጊዜ በዐባይ ዙሪያ መንግስትን እያማከሩ ያሉት አምባሳደር ሀይሉ ወልደጊዮርጊስ ይህን የገለጹት፤ እሁድ ለህትመት ከበቃው ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር በዓባይ ግድብ ዙሪያ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው።

“ የዓባይ ውሀ በህግ ላይ የሚያቀርበው ፈተና” በሚል ርዕስ በፈረንሳይኛ መጽሐፍ ያሳተሙት አምባሳደር ሀይሉ ለህዳሴው ግድብ እስካሁን ከህዝብ የተሰበሰበው ገንዘብ ገና ከ 5 ቢሊዮን ብር እንዳላለፈ አመልክተዋል።

የግድቡ ግንባታ የሚተይቀው ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ነው ያሉት አምባሳደር ሀይሉ፤ይህን ያህል ገንዘብ በራሳችን ለማዋጣት ያዳግተናል ብለዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የ ዓባይን ግድብ ያለምንም የውጪ እርዳታ በራሳችን እንሠራዋለን በማለት በተደጋጋሚ መናገራቸው ይታወሳል።
 ግብፅ የኤክስፐርቶች ቡድን ያቀረበውን ሪፖርት ተቀብያለሁ ብላ ካረጋገጠች፣ ወዲያውኑ ኢትዮጵያ የውጭ ዕርዳታ ታገኛለች የሚል አመለካከትና እምነት ስላላት ነው ጉዳዩን ለማደናቀፍ ደፋ ቀና የምትለውም-ብለዋል አምባሳደሩ።

አምባሳደሩ አክለውም፦<<ግድቡ ተጠናቅቆ ሥራ ላይ ቢውል ግን ተጠቃሚዋ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ግብፅና ሱዳንም የጥቅሙ ተጋሪ ይሆናሉ ።እነሱ ግን ይህ በጎ ጐኑ አይታያቸውም፡፡ የግብፆች ትልቁ ጥርጣሬያቸው ኢትዮጵያ በሕዝቡ መዋጮ ብቻ የግድቡን ግንባታ የማጠናቀቅ ወይም ዳር የማድረስ አቅም ስለሌላት ይህንን ክፍተት ለመሸፈን ከሌሎች አገሮች በስውር ዕርዳታና ብድር ልታገኝ ትችላለች የሚል ነው>>ብለዋል-።
ስለሆነም ይህንን ለማጨናገፍ ሲሉ የማስፈራራት ዘመቻ እያካሄዱ እንደሆነ እና ለዚህም ተግባራዊነት መልዕክተኞቻቸውን ወደተለያዩ አገሮች በመላክ የማግባባት ሥራ እያካሄዱ ስለመሆናቸው የገለጹት አምባሳደር ሀይሌ፤<< ደቡብ ሱዳን እንኳን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን እንዳትቀበል ወይም እንዳትፈርም ብዙ ተፅዕኖ አድርገውባት ነበር፡፡ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጐንም እንዲሁ አግባብተዋል፡፡ >>
ከ አምባሳደሩ ገለፃ ለመረዳት እንደተቻለው ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል ለሚባለው ለግድቡ ሥራ እስካሁን የተዋጣው ገና 6 በመቶ ያህሉ ነው። ይህ ማለት ከተጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ግድብ ገና 94 በመቶ የሚሆነው ወጭ ይጠብቀዋል።
እስካሁን የኢትዮጵያ ህዝብ በፈቃድም፣ያለፈቃድም እንዲያዋጣና ቦንድ እንዲገዛ ተደርጎ የተሰበሰው 6 በመቶ ነው። ሀቁ ይህ ከሆነ አምባሳደሩ እንዳሉት ግድቡን ያለውጪ ዕርዳታ ካለበት ቦታ ብዙም ማንቀሳቀስ አይቻልም።
ከዚህ አኳያ የግድቡ ሥራ መቀጠልና አለመቀጠል የሚወሰነው፤ ኢትዮጵያ እርዳታን ለማግኘት፤ግብጽ ደግሞ እርዳታን ለማስከልከል እያደረጉ ባሉት ትግል- እንደሆነ የዘርፉ ሙያተኞች ይናገራሉ።
የዓባይ ግድብ ተጀምሯል ከተባለ ጊዜ አንስቶ በርካታ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ኢትዮጵያ ግድቡን በራሷ አቅም ልትሠራው እንደማትችል ሲናገሩ መቆየታቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment