Thursday, 6 June 2013

አገዛዙ ለሰላማዊ ሰልፉ ዕውቅና የሰጠው ፈጽሞ አማራጭ ስላልነበረው ነው – በእኔ አመለካከት!

ECADF Statment regarding Addis Ababa's demonstration

ክብሩ ደመቀ
ሕወሓት/ኢህአዴግ በሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጅነት የተካሄደውን ሰላማዊ ዕውቅና የሰጠው ወድዶና ፈቅዶ ወይም ሕገ-መንግሥቱ አጣብቂኝ ውስጥ ከትቶት አልነበረም። ይልቅስ አጣብቂኝ ውስጥ የከተቱት ሁለት ነገሮች ናቸው ፡-
1ኛ – ወቅታዊነት! በወቅቱ የሚካሄደውን ርዕሰ-ሃገራትና ከፍተኛ የዓለም ባለሥልጣናት (እንደ ጆን ኬሪ እና ባንኪ ሙን) በተገኙበት እንዲሁም በዓለም መገናኛ ብዙሃን እየተዘገበ በሚካሄደው የአፍሪካ ሕብረት 50ኛ ዓመት ጉባዔ ላይ ሰማያዊ ፓርቲ ለሚያካሂደው ሰላማዊ ሰልፍ ዕውቅና መጠየቁ፣
 
2ኛ – መደራጀት፣ ብስለት እና ቁርጠኝነት!!! የሰማያዊ ፓርቲና አመራሩ መደራጀት፣ ብስለት እና ቁርጠኝነት፤ ሕወሓት/ኢህአዴግ ከለመዳቸው የከሸፉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መግደርደሮች (ከይቅርታ ጋር በርካታ የከሸፉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና አመራሮች እንዳሉም ጭምር እምነት አለኝ) የተለየ መሆኑን መገንዘቡና ፓርቲውም የተጠየቀውን ዋጋ ከፍሎ ሕገ-መንግሥቱ የሚፈቅድለት መብቱን ከደጋፊዎቹ ጋር ከማራመድ ወደኋላ እንደማይል (that those guys were not bluffing) እየመረረው መረዳቱ።

“መንግሥት” አማራጭ እንዳልነበረው ሌላው ተጨባጭ ማስረጃ ደግሞ በሚያስደንቅ ቅንጅት፣ ኅብር፣ ምጥነት፣ ጨዋነት እና ሰላም የተካሄደውን ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ በተመለከተ የመንግሥት ግንኙነት ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚ/ር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል እና የሕወሓት/ኢህአዴግ ቃል አቀባይ አቶ ሬድዋን ሁሴን የሰጡት ከድንጋጤ የመነጨ የተፋለሰ መግለጫ ነው። በነገራችን ላይ እንደተለመደው “የኢትዮጵያ” ቴሌቪዥን አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባል ወይንም የሰልፉ ተሳታፊ ዜጋ አላነጋገረም፣ ወይንም አላቀረበም – በወፍ-በረር ቅኝት በመበተን ላይ ያለና ዘርዘር ያለ የሕዝብ ስብስብ ጠብቆ በካሜራው ከመቅረፅና ማቅረብ በስተቀር።

የ”መንግሥት” ወገኖችን አተያይ ስንቃኝ፤
በመጀመሪያ ከ”ኢትዮጵያ” ቴሌቪዥን ብንጀምር ከክስ አዘል ዘገባዎቹ መካከል፡- “የሰልፈኞቹ ጥያቄ በፍርድ ቤት በተያዘው የሙስሊሙ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች የሸባሪነት ክስ ላያ አተኩሯል፣ በኢቲቪ እና በመንግሥት ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልፀዋል፣ አትነሳም ወይ ይሄ ባንዲራ ያንተ አይደለም ወይ ሲሉ ነበር፣ በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ዕውቅና የተሰጠው የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ እንዳይታይ ሲከለክሉም ተስተውለዋል፣ በተቃውሞ ሰልፉ ማጠናቀቂያ የእስልምና ተከታዮች የስግደት ሥነ-ስርዓት ፈጽመዋል።”

በመቀጠል አቶ ሽመልስ ከማል ከሰነዘሩዋቸው ውስጥ ደግሞ፡- “….መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አለመግባት የሚለውን ሕገ-መንግሥት አጥብቆ ያከብረዋል……..በተደረገው ሰልፍ በፖለቲካና በሃይማኖት መካከል ሕገ-መንግሥቱ ያሰመረው መስመር ሲደረመስ የሚታይበት ሁኔታ አለ፣ በሃይማኖት ሽፋን ሽብርተኝነት ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያለውን ግለሰቦች የተከሳሾቹ ጠበቃዎች ከፍርድ ቤት ውጪ በሆነ ሂደት የፍርድ ሂደቱን ለማጨናገፍ መሞከር ሕግ አይፈቅድላቸውም፣ ከቤኒንሻንጉል ገምዝ የተፈናቀሉትን ሰዎች አስመልክቶ የዛሬዎቹ ሰዎች ኡኡታ ከማሰማታቸው አስቀድሞ መንግሥት ሁኔታውን አይቶ ፈጣን እርምጃና እርምት የወሰደበት ጉዳይ ነው ፣ ከዚህ ባለፈ እንዲህ ዓይነቶቹን ጉዳዮች….exceptions ወይም እንደ በስተቀር የሚወሰደውን ነገር (እጅግ በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰት ነገር ማለታቸው ነው) ዋና መደበኛ አሠራር አስመስሎ ያንን አጉልቶ ከዚያ ፖለቲካዊ ትርፍ አስልቶ ለማግኘት የሚኬድ ነገር ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል መታወቅ ይኖርበታል።”

በሌላ ወሬ የሕወሓት/ኢህአዴግ ቃል አቀባይ አቶ ሬድዋን ሁሴን “ሰማያዊ ፓርቲ ከአሸባሪዎች ጋር ፖለቲካዊ ጋብቻ መፈፀሙን እሁድ ለት በጠራው ሰልፍ በግልፅ አሳይቷል…” ብለዋል፡፡
ይህ ምን ይነግረናል? ምስክር በሦስት ይፀናል እንዲሉ አበው፤ ሦስት የመንግሥት ከፍተኛ አካላት (ኢቲቪ፣ አቶ ሽመልስ እና አቶ ሬድዋን) ከላይ የተጠቀሱትን መሠረተ-ቢስ ውንጀላዎች አካሂደዋል። በእነሱ ስሌት የበለጠ ጉዳትን ለማስቀረት በአጣብቂኝ ዕውቅና የሰጡት ሰላማዊ ሰልፍ ስኬታማነት ያስደነገጣቸውና ያበሳጫቸው የአገዛዙ ባለሥልጣናት የሰጡት  ይፋዊ መግለጫ የሚያሳየው፤ ቀድሞውኑ አማራጭ አጥተው የተስማሙበት ጉዳይ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊትም ተመሳሳይ ጥያቄ ላለማስተናገድ ሰማያዊ ፓርቲን፣ አመራሩንና፣ ተቃዋሚ ሕዝቡን እንደተለመደው “በሽብርና ሕገ-መንግሥት ለመናድ መሞከር” በመወንጀል (framing the opposition forces by criminalizing peaceful dissent) የመፃዒ የቤት ሥራቸውን መሠረት ጥለዋል።

ስለዚህ ቀድሞውኑም “መንግሥት” የምርጫ ‘97 ዓይነቱን የፖለቲካ ክፍተት ፈቀደ፣ ዲሞክራሲያዊ ብልጭታ አሳየ ወዘተርፈ በማለት ለሺህኛ ጊዜ በየዋህነት ለተታለሉ የዋህ ዜጎች እላለሁ – በእኔ አመለካከት ሕወሓት/ኢህአዴግ መፈናፈኛ አጥቶ ነው ይህቺ የፖለቲካ ክፍተት የተፈጠረችበት እንጂ ሃገሪቱን ወደየት እየመራት እንደሆነ ለማንኛውም የሚያመዛዝን አዕምሮ ግልጽ ነው።
“መንግሥት” አሁን በያዘው አካሄድ አገዛዙ እንዲህ ያለ የፖለቲካ አዎንታዊነት መፍጠር ማለት ወደ ጠፈር በመተኮስ ላይ ያለን ሮኬት ጠምዝዞ ወደምድር የመመለስ ያህል ይመስለኛል። በዚህም ምክንያት እላለሁ – ትግሉ መራራ ነው። የተኛ መንቃት፣ የተናጠለ መደራጀት፣ የበቃው ቁርጠኝነት ይሻዋል።

No comments:

Post a Comment