Sunday, 9 June 2013

ግብፅ በቅድመ ሁኔታ የታጠረ የድርድር ጥያቄ አቀረበች -ኢትዮጵያ ቅድመ ሁኔታውን አልተቀበለችም


ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለመጀመር የዓባይን ወንዝ የፍሰት አቅጣጫ በጊዜያዊነት ከቀየረች በኋላ፣ ግብፅ የፈጠረችው ፖለቲካዊ ውጥረት ባለፈው ሳምንት የተለየ መልክ ይዟል፡፡
ሱዳን በግድቡ ላይ ተቃውሞ እንደሌላት በመግለጽ ግብፅን ብቸኛዋ ተቃዋሚ አገር እንድትሆን አድርጋታለች፡፡ በሌላ በኩል ግብፅ በጉዳዩ ላይ የተለሳለሰ የሚመስል አቋም በማሳየት በቅድመ ሁኔታ የታጠረ የድርድር ጥያቄ ለኢትዮጵያ አቅርባለች፡፡
 
 መንግሥት በበኩሉ የግብፅ ጥያቄ በሳይንስ ላይ ያልተመረኮዘና ግልጽነት የሚጎድለው ነው ብሏል፡፡ የግድቡ ግንባታ እንዲቋረጥ የቀረበው ሐሳብም ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ሲል ቁርጥ ያለ አቋሙን ገልጾ፣ በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥም ድርድር እንደማይኖር አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓባይን የፍሰት አቅጣጫ ከቀየረች በኋላ የግብፅ መንግሥት ከፍተኛ ተቃውሞውን እያሰማ ሰንብቷል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በጋራ ያቋቋሙት የባለሙያዎች ቡድን በግድቡ ተፅዕኖ ላይ ያቀረበውንም ሪፖርት እንደማትቀበል ግብፅ አሳውቃለች፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመረችው የኃይል ማመንጫ ግድብ ግብፅና ሱዳን በቅኝ ግዛት ዘመን ውል መሠረት የሚያገኙትን የውኃ ኮታ የሚቀንስ በመሆኑ፣ የግብፅን ህልውና አደጋ ላይ ይጥላል የሚለው የግብፅ ዋነኛ መከራከሪያ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ ከአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት ማድረጋቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ከተወያዮቹ ዕውቅና ውጭ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት በተላለፈው በዚህ ውይይት ላይ፣ አክራሪ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ ጥቃት መክፈት እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱን ሲመክሩ ታይተዋል፡፡ በዚሁ ውይይት ላይ የተሳተፉትና የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎችን በመደገፍ አገሪቱን ማተራመስ ወይም በግብፅ የደኅንነት ኃይል ግድቡ እንዲወድም መደረግ አለበት የሚል ምክራቸውን ሲሰጡ የነበሩት አይማን ኑር የተባሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር፣ በሱዳን ላይም ትችታቸውን ሰንዝረው ነበር፡፡

በዓባይ ውኃ ፖለቲካ ዙሪያ ከግብፅ በተለየ ሁኔታ ዝምታን እየመረጠች ያለችው የሱዳን አቋም የሚያበሳጭ ነው ነበር ያሉት አይማን ኑር፡፡
የግለሰቡ ንግግር ያበሳጫት ሱዳን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የመንግሥት ቃል አቀባይ በሆኑት ሚስተር አህመድ ቢላል ኦስማን በኩል ምላሽ ሰጥታለች፡፡ በሱዳን ቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ ያደረጉት ሚኒስትሩ የግብፅ ባለሥልጣናት ሱዳንን ከመዝለፍ እንዲቆጠቡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ‹‹በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ሱዳን የያዘችው አቋም ግብፅን የሚያስደስት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የግብፅ ፖለቲከኞች በሱዳን ላይ የሰነዘሩት ዘለፋ ለግብፅ ፖለቲካዊ ፍላጐት ጥቅም የለውም ሲሉ አክለዋል፡፡
በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ወቅት ኢትዮጵያ እየገነባች ባለችው ግድብ ላይ የመንግሥታቸው አቋም ኢትዮጵያን የሚደግፍ መሆኑን፣ ምክንያቱ ደግሞ ሱዳንም በውጤቱ ተጠቃሚ ስለምትሆን ነው ብለዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት የዓባይን የውኃ ፍሰት የሚያሻሽል በመሆኑ ሱዳን በዝናብ ላይ ብቻ የነበራትን ጥገኝነት የሚቀንስ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በዓባይ ፖለቲካ ተወጥረው የሰነበቱት የግብፅ ባለሥልጣናት፣ በሳምንቱ መጨረሻ ላይም አለ የሚሉትን ችግር ከኢትዮጵያ ጋር ውይይት በማድረግ ለመፍታት የመምረጥ ፍላጐት አሳይተዋል፡፡
የግብፅን የውኃ ፍላጐት ለማስከበር የተሻለ ነው ባሉት ፖለቲካዊ ውይይት መሠረት ለኢትዮጵያ መንግሥት የውይይት ጥያቄ ያቀረቡ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ በማቆም ውይይቱ መጀመር እንዳለባት ጠይቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ የድርድር ጥያቄ ተስማምታ በጉዳዩ ላይ እልባት ካልተገኘ ግን፣ ግብፅ ማንኛውንም አማራጭ በመጠቀም ብሔራዊ ደኅንነቷን ለማስከበር እንደምትገደድ፣ የፕሬዚዳንት ሙርሲ የፖለቲካ አማካሪ የሆኑት አይማን አሊ መናገራቸውን የግብፅ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል፡፡

‹‹ግብፅ የራሷን ፍላጐት የማስከበር ፍላጐት እንዳላት ሁሉ የሌላው አገር መንግሥትና ሕዝብ የራሳቸውን ፍላጐት መከተል ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ በግብፅ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትል ልታረጋግጥ ይገባል፡፡ በተጨባጭ ዋስትና መስጠት ይኖርባታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ግብፅ ያሏትን አማራጮች በሙሉ ተጠቅማ ጥቅሟ እንዲከበር ታደርጋለች፤›› ሲሉ በማስጠንቀቂያ የታጀበ ዛቻ ሰንዝረዋል፡፡
ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ የተፈጠረውን የፖለቲካ ውጥረት በማርገብ ረገድ እየሄደችበት ያለው መንገድ የተደበላለቀ የሚመስል ሲሆን፣ በውይይት ለመፍታት ያሳየችው ፍላጐት በቅድመ ሁኔታ ታጥሯል፡፡ በሌላ በኩል ወታደራዊ ጉልበት የመጠቀም ፍላጐት እንዳላትም ለማሳየት እየሞከረች ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ላይ በቀጥታ ሥርጭት የተላለፈው የባለሥልጣናቱ ውይይት ሆን ተብሎ የተደረገ ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት የግብፅ የደኅንነት ኃላፊ በሆኑት መሐመድ ራፋት ሸሃታ የተመራ ልዑካን ቡድን ሱዳንን መጐብኘቱን የግብፅ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ነገር ግን የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዘገባውን አስተባብለዋል፡፡
ግብፅ ወታደራዊ ጥቃት የመጠቀም አማራጭ እንዳላትና ልትጠቀም እንደምትችልም በተደጋጋሚ መዘገቡን አስመልክቶ ምላሽ እንዲሰጡ የተጠየቁት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የግብፅን ወታደራዊ አማራጭ ‹‹የቀን ቅዠት ነው›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡ አቶ ጌታቸው ግድቡን ለማውደም ወይም ኢትዮጵያን ለማተራመስ በግብፅ ፖለቲከኞች ስለተሰነዘረው አስተያየት በሰጡት ምላሽ፣ ኢትዮጵያን ደካማ በነበረችበት ጊዜ እንኳ ለማተራመስ የተደረገው ሙከራ አለመሥራቱን፣ አሁን ደግሞ እጅግ በጣም በተሻለ ደረጃ ላይ ስለምትገኝ ከግብፅም ሆነ ከሌላ አገር የሚቃጣን ጥቃት ታከሽፋለች ብለዋል፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንት ምክንያታዊ ሆነው ወደ ግጭት የማይገባበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ በሆስኒ ሙባረክ ዘመን ኢትዮጵያን በአማፂያን አማካይነት ለማተራመስ የተደረገው ሙከራ መክሸፉንም አስረድተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው፣ የግብፅ የውይይት ጥያቄ ተቀባይነት ያለው መሆኑን፣ ነገር ግን የግድቡ ግንባታ መቆም አለበት በማለት ግብፅ ያስቀመጠችውን ቅድመ ሁኔታ ‹‹የማይታሰብ›› ሲሉ በትዊተር ድረ ገጽ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ከግብፅ ጋር ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስታውቆ፣ አንዳንድ የግብፅ ፖለቲከኞችና ባለሥልጣናት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን የሚጎዳ ፕሮፓጋንዳ መንዛታቸው እንዳሳዘነው ገልጿል፡፡ በትዕግስት አንዳንድ ጉዳዮችን ለማለፍ ቢፈልግም ገንቢ ያልሆኑ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች በመነዛታቸው፣ በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደርን በመጥራት የመንግሥታቸውን አቋም ጠይቀው ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቁንና ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን አስታውቋል፡፡ የግብፅ መንግሥት እስካሁን ለተጠየቀው ማብራሪያም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም፡፡

No comments:

Post a Comment