Monday, 3 June 2013

ምከረው ምከረው እምቢ ካለ ሞክረው…አቤ ቶክቻው!!

እኔ እኮ ሁልጊዜ ግራ የሚገባኝ አቶ ሽመልስ ከማልን በእንዲህ ያለው ጉዳ ላይ ለምን እንደሚያጋፍጧቸው ነው፡፡ እርሳቸውስ ቢሆኑ አሁንስ አበዛችሁት ራሳችሁ ተናገሩ አይሉም እንዴ…!
ውይ የኔ ነገር ቆይማ ነገርን ከስሩ እንዲሉ ለወጋችን ትንሽ መሰረት ብጤ እንጣልላት፡፡

 ትላንት ሰማያዊ ፓርቲ ወንድ ሴት እስላም ክርስቲያን ሳትል በደለኛ ሁላ ና አደባባይ ውጣ እና መንግስትን አብረን እንቆጣው ብሎ ጠርቶ አልነበር… ታድያኮ ባማረ እና በደመቀ መልኩ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ ተጠናቋል፡፡ በእውነቱ ይህ ህዝብ ከመሪዎቹ የሚበልጥ አይደለምን…!
ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የማታ ማታ አስቦ አስቦ ሰልፉን የተመለከተ ዘገባ አቅርቧል፡፡ በዘገባው ላይ የሚመለከታቸው አካል ተብለው ማብራሪያ ሊሰጡ የተጋበዙት አቶ ሽመልስ ከማል ናቸው፡፡

መጀመሪያ ላይ አቶ ሽመልስ ሰልፉን አስመልክቶ የሚነግሩን አለ ሲባል የሰልፉ አስተባባሪ እርሳቸው ነበሩ እንዴ… ብዬ ተደንቄ ነበር፡፡ ኢቲቪ ግን ምንም አይደብረውም… የሰልፉን አስተባባሪዎች እና ተሳታፊዎች አንድ ጥያቄ እንኳ ሳጠይቅ ቀጥታ ከመንግስት ወገን ምላሽ እና ማብራሪያ እንዲሰጡ አቶ አቶ ሽሜን የሚጠራቸው…

የሆነ ሆኖ አቶው መጡና “በሰልፉ ላይ ሲንፀባረቁ የነበሩ መልዕክቶች ከህገመንግስቱ ጋር የሚጣረሱ ናቸው” ብለውን እርፍ አሉት፡፡ አቶ ሽመልስ ይሄንን ያሉት ሃይማኖት እና ፖለቲካ መነጣጠል አለባቸው ከሚል መነሻ እንደሆነ ሊያስረዱን ሞክረዋል፡፡ አባባላቸውን ከኢህአዴግኛ ወደ አማርኛ ስንቀይረው፤ የሀይማኖት ሰዎች የፈለገ በደል ቢደርስባቸው ዝም ብለው ዱዓ ያደርጋሉ እንጂ ለመንግስት አቤት አይሉም የሚል ይመስላል፡፡
እኔ የምለዎ አቶ ሽመልስ… ሃይማኖታቸወን ስላራመዱ ሰዎች መታሰር የለባቸውም… ብሎ መጠየቅ ህገ መንግስቱን እንደመናድ ከተቆጠረ፤ እርስዎን በቴሌቪዥን ማቅረብስ ህገመንግስቱን የመደርመስ ያህል ቢቆጠር ምን ይመስልዎታል…!

አሁንስ ይሄ ህገመንግስት አሳዘነኝ ምንድነው ይሄን ያህል በካርቶን ነው እንዴ የተገነባው በሆነው ባልሆነው የሚፈርሰው!
እዝችው ላይ አቶ ሽመልስ፣ ኢቲቪ እና አንዳንድ ስማቸውን ብንጠቅስም ባንጠቅስም ዋጋ የሌላቸው ሰዎች ሰልፉ ላይ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ይበዛል አይበዛም እያሉ ጉንጭ አልፋ እና ፌስ  ቡክ አልፋ ንግግር  ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ ተነቧልም፡፡ የሚያስቀው እነዚሁ ግለሰቦች ከሰልፉ ቀደም ብለው በሰልፉ ላይ ሙስሊሙ ህብረተሰብ አይሳተፍም እያሉ ሲቀሰቅሱ የነበሩ ናቸው፡፡

በሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ ላይ ሙስሊሙ ህብረተሰብ አዎ በብዛት ተሳትፏል፡፡ እንደኔ እምነት እንደውም ሰልፉ በሰላም ለመጠናቀቁ አንዱን አስተዋፅኦ ያደረገው ሙስሊሙ ህብረተሰብ በብዛት በመሳተፉ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከአመት ላለፈ ጊዜ ሰላማዊ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ስለነበረ ያንን ልምድ ለሰማያዊ ሰልፈኞች አጋርተዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
እና ሙስሊሙ ህብረተሰብ በብዛት መሳተፉ ጉዳቱ ምንድነው… ሙስሊሙ በደል ስለደረሰበት ስለሀገሩ ግድ ስለሚለው ተሰለፈ፡፡ ሴቷ በደል ስለ ሀገሯ ግድ ስለሚላት ተሰለፈች፡፡ ወጣቱ በደል ስለደረሰበት እና ስለ ሀገሩ ግድ ስለሚለው  ተሰለፈ፡፡ ጋሽ ታዲዮስ ታንቱም በደል ስለደረሰባቸው እና ስለሀገራቸው ግድ ስለሚላቸው ተሰለፉ፡፡ ታድያ ይሄ ምን ይገርማል…

አቶ ሽመልስ ሌላው ያሉን ነገር “ከቤኒሻንጉል የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ መንግስት ቀድሞ መልስ ሰጥቶታል” ብለዋል… አይ ጋሽ ሽሜ… እኔ እኮ ሁልጊዜ ርስዎን ለምን እንዲህ እንደሚጋፍጡዎት ነው የሚገርመኝ፡፡ አቶ በረከት ግን አይወዱዎት የምሬን ነው የምልዎ… እንዲህ ሲናገሩ የሰማዎ ሰው ሁሉ እኮ እንደኮሜዲያን እንጂ እንደባለስልጣን አይመለከትዎትም፡፡ አቶ ሽሜ ለማንኛውም ጥያቄው አፋናቃዮቹ ለፍርድ ይቅረቡ ነው፡፡ ይልቅ ከአፈናቃዮቹ ውስጥ ዝርዝርዎ እንዳይኖር ይስጉ…
የጋዜጠኞችን እስር ጉዳይ፣ የፕሬስ አፈናውን እና የኑሮ ውድነቱን አስመልክቶ የተነሱትን ጥያቄዎች፤ ኢቲቪም አቶ ሽሜም ሆን ብለው የረሱት ወይም በአጠቃቀስኩ ያለፉት ይመስለኛል፡፡ ግን እንዲህ በማደባበስ የትም አይደረስም፡፡

ኢህአዴግዬ ብልጥ ከሆነች የተጠየቀችውን በሙሉ ተግባራዊ አድርጋ ተቃዋሚዎቿን አፍ ማዘጋት ነው ያለባት፡፡
ምከረው ምከረው እምቢ ካለ ሞክረው… ነው እንግዲህ፡፡

No comments:

Post a Comment