Friday, 14 June 2013

በወገኖቻችን ስደት ላይ ስለሚሰማው የሰሞኑ ፌዝና ቧልት ጥቂት ስለማለት

June 13, 2013

ዶ/ር ዘላለም ተክሉ
በሰሞኑ ከዓባይ ተፋሰስ ፖለቲካ ቀጥሎ ታላቁ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ  ከሃገራችን በመቶ ሺዎች ተሰደው ስለሚወጡ ወገኖቻችን መሆኑ ይገነዘቧል:: ከ”መለስ ራዕይ” አስፈጻሚው “ጠ/ ሚንስትር” በተዋረድ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ እንደ ገደል ማሚቶ  በሚስተጋባው ዘገባ፣ ወገኖቻችን ከአረብ ሃገራት እስከ ደቡብ አፍሪካ፣አውሮጳና አሜሪካ ድረስ ህጋዊና ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች ተሰደው የሚኮበልሉት “ባደገችው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ያሉትን የስራና የንግድ ዕድሎች አሟጠው ሳይገነዘቡና ሳይሞክሩ” እንደሆነ እየተነገረ መሆኑ ሁላችንን እያስስገረመን እያስደመመን ይገኛል::
 
መቼስ እደዚህ ዓይነት ሽምጥጥ ያለ ሽወዳ ለህወሐት መንግስት አዲስ አይደለም:: የዚህን የተቀናጀ ፕሮፖጋንዳ ስመለከትና ሳነብ በ 2011 መጨረሻና 2012 መጀመሪያ አካባቢ በዚሁ ጉዳይ ያደረኩት አነስተኛ የዳሰሳ ጥናት ትዝ አለኝ:: በዚህ ጥናት ላይ ያገኘሁት መረጃ አሁን እየተለፈፈ ካለው አሰልቺ ድራማ ጋር አልጣጣም ስላለኝ ለናንተ ላካፍላችሁ ወደድኩኝ::

ጥናቱ የተካሄደው ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከጥቅምት እስከ ታህሳስ 2011 ቀጥታ በተሰበሰበ መረጃ (Primary data) ነበር:: የናሙና መረጃው ከአዲስ አበባ ብቻ የተሰባሰበበት ምክንያት ሁሉንም የአገሪቱ ክልሎች የሚወክሉ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሀብታምና ደሃዎች፣ ነጋዴውዎችና የመንግስት ሰራተኞች፣ ሥራአጥና ጎዳና ተዳዳዎች ሁሉ የሚኖሩበት ከተማ በመሆኑ ነው::  ከዚህ በተጨማሪም መረጃውን ለማሰብሰብ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ተቋማት ከሌሎቹ አካባቢዎች በተሻለ መልኩ መገኘት በመቻሉ ነው:: መረጃውም የተሰበሰበው ለ 200 ግለሰቦች የስልክ ቃለመጠይቅ ግብዣ ተደርጎላቸው ፍቃደኛነታቸውን ከገለጹ 151 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከተገኘ ምላሽ ነበር:: የናሙና መረጃው የተሰበሰበው Stratified Random Sampling በሚባል የስታቲስቲክስ ዘዴ ነበር:: 

በዚሁ ዘዴ ምላሻቸውን ከሰጡት ሰዎች ውስጥ በጾታ 64 በመቶውቹ ወንዶችና 36 በመቶዎቹ ደግሞ ሴቶች ነበሩ:: በዕድሜ አንጻር 41 በመቶዎቹ ከ 21-45 ዓመት፣ 35 በመቶዎቹ ከ 46-60 ዓመት፣ እንዲሁም 23 በመቶ የሚሆኑት ከ21 ዓመት በታችና ከ60 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው ነበሩ:: በትምህርት ደረጃም ሲደለደል ከናሙናው ውስጥ 49 በመቶዎቹ የ12ኛ ክፍልን ያላጠናቀቁ፣ 29 በመቶዎቹ የ12ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ፣ 19 በመቶዎቹ ሰርተፊኬት/ ዲፕሎማ ያገኙ፣ 3 በመቶዎቹ በጀመሪያ ዲግሪና 1 በመቶዎቹ በከፍተኛ ዲግሪ የተመረቁ ነዋሪዎች ነበሩ::

ይህ ጥናት ያተኮረው አጠቃላይ የሃገሪቱን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና ድህነት ቅነሳ ሁኔታን ለመዳሰስ ነበር::  ስደትን ብቻ በተመለከተ በተናጠል ለጥናቱ ተካፋዮች የቀረቡላቸው ጥያቄዎች ( 1) እድሉን ብታገኝ/ኚ ከሃገርህ/ሽ ተሰደህ/ሽ መውጣት ትፈልጋለህ/ሽ አትፈልግም/ጊም? (2) ለመሰደድ የምትፈልገው/ጊው በምን ምክንያት ነው? የሚሉ ነበሩ:: ለእነዚህን ሁለት ጥያቄዎች የተሰጠው ምላሽ ሲተነተን የተገኘው ውጤት በጣም አስደንጋጭ ሆኖ ነበር ያገኘሁት:: የተሰበሰበው መረጃ ተተንትኖ ከዚህ በታች በቀረበው ቻርት መሰረት ሦስት አራተኛው ወገኖቻችን  (3/4ኛው) አገራቸውን ጥለው ለመሰደድ ምንም እንደማያመነቱ ያመለከቱ ሲሆን የመሰደዳቸው ዋነኛው ምክንያትም 66 በመቶ በኢኮኖሚ ችግር እንዲሁም 14 በመቶ ደግሞ በሀገራቸው ያለው ዕድልና ተስፋ መሟጠጥ እንደሆነ ታውቋል:: ተምሮ ወይም ጥሪት አካብቶ ለመመለስ የሚመኘውም  ከአምስቱ ዜጋ አንዱ ብቻ እንደሆነም ታውቋል::

Ethiopian immigrants flow
ትንሽም ቢሆን ካገኘነው ሳይንሳዊ መረጃ እንደተረዳሁት ህዝባችን የሚሰደደው “ስላደገችው ኢትዮጵያ” ግንዛቤ በማጣቱ ሆኖ አላገኘሁትም::   ኢኮኖሚው በእርግጥ ቢያድግ ኖሮ አብዛኛው ህዝብ በሀገር ውስጥ ሰርቶ የማግኘት፣የመሻሻልና በደስታ የመኖር ዕድልና ተስፋው ባደገ ነበር:: በእርግጥ ህዝቡ በሃገሩ ቢተማመን ኖሮማ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በህገ ወጥ መንገድ ወደ የመን፣ ሊቢያ፣  ሊባኖስ፣ ሳውዲ አረቢያና ሌሎች አረብ ሃገራት ተሰደደው በየእስር ቤቶችና በየበረሃው ባልተንገላቱ፣ ባልተደበደቡና ባለተደፈሩ፣የፈላ ውኃ በአናታቸው ባልተደፋ፣ በእምነታቸው ሰበብ እስር ቤት ባለተወረወሩ ነበር::

 የተወራለት የኑሮ መሻሻልና ሰርቶ የማደግ ተስፋ እውነት በሃገሪቱ ቢኖርማ ኖሮ እህታችን ዓለም ደቻሳ ወደ ሃገሯ አልመለስም እያለች አስፋልት ዳር እንደ እንስሳ ስትጎተት የዓለም ህዝብ በቪዲዮ ባላያትና በመጨረሻም ህይወቷን ማጣቷ ባልተሰማ ነበር::  ተስፋውና ዕድገቱ እንደተፎከረበት ቢሆንማ ከኖርዌይ በግዳጅ ወደሃገራቸው ሊባረሩ የተዘጋጁ ብዙ ወገኖቻችን ላለመመለስ ባለመኑና ባልተማጸኑ ነበር::
ለኔ ከህዝባችን ውስጥ ሦስት አራተኛው “በሃገሩ ያለውን አበረታች ዕድል ባለማወቅ ነው የሚሰደደው” የሚለው መከራከሪያ ፌዝና ቡዋልት እንጂ ውሃ የሚቋጥር እውነታ ሆኖ አላገኘሁትም::
እናንተስ?

No comments:

Post a Comment