Friday, 21 June 2013

ግብፅ የህዳሴውን ግድብ በአየር ማጥቃት የሚያስችል አቅም የላትም ስትራትፎር


ግብፅ የኢትዮጵያን ሕዳሴ ግድብ በአየር ለማጥቃት ከኢትዮጵያ ያላት የአየር ርቀት ይገድባታል ሲል ስትራትፎር የተባለው መሠረቱን በአሜሪካ አገር ያደረገ ጂኦፖለቲካ እና ሴኩሪቲ ምርምርና ጥናት የሚያደርግ ተቋም በድረ ገጽ አስነብቧል።

ተቋሙ ባሰራጨው ትንታኔ ላይ እንዳሰፈረው፤ “በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው የአየር ርቀት ለግብፅ ጦር ሰራዊት ሁኔታዎችን አስቸጋሪ ያደርገዋል” ብሏል። ተቋሙ አያይዞም፤ “ግብፅ አየር በአየር ነዳጅ የሚቀባበሉ ተዋጊ የጦር ጀቶች ባለቤት ለመሆን ያደረገችው የአቅም ግንባታ የለም። 

አሁን በግብፅ አየር ኃይል እጅ የሚገኙ የጦር ጀቶች ከግብፅ አየር ሃይል በመነሳት በተወሰነ የአየር ክልል ውስጥ የማጥቃት አቅም ያላቸው እንጂ በጣም ብዙ ርቀት በመጓዝ ማጥቃት የሚችሉ አይደሉም” ሲል የግብፅን የአየር ጥቃት አቅምን አጋልጧል።

“ግብጾች ትንሽ ያላቸው መፅናኛ የሕዳሴው ግድብ ለሱዳን ድንበር የቀረበ መሆኑ ነው። የሱዳን የአየር ሃይል ቤዝ መጠቀም ከቻሉ አንዳንድ የግብፅ የጦር ጀቶች ማጥቃት በሚችሉበት ራዲየስ ውስጥ የህዳሴው ግድብ ሊወድቅ ይችላል። ሆኖም ግን ከሱዳን ግዛት ውስጥ በመነሳት የሚደረግ የአየር ጥቃት ውስብስብ የፖለቲካ አደጋዎች ያስከትላል። በዓለም ዓቀፍ መድረክም ሱዳንና ግብፅ ውጤቱን ተከትሎ የሚከፍሉት ዋጋ ይኖራል። ሱዳን ለኢትዮጵያ የድንበር ተጋሪ ከመሆኗ አንፃር ከኢትዮጵያ መንግስትም በሚሰነዘር ቀጥተኛ ወታደራዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆኗ አይቀርም” ሲል ተቋሙ በትንታኔው አስነብቧል።

ሌላው የግብጾች አማራጭ ልዩ የጦር ሰራዊት ኮማንዶ ማሰማራት ነው ያለው ተቋሙ፤ ይህም ቢሆን የራሱ የሆነ ችግሮች አሉት። ግድብ ወሳኝ መሰረተ ልማት ከመሆኑ አንፃር የማያቋርጥ ጥበቃ የሚደረግለት ነው። በአብዛኛው ቋሚ የጦር ሰራዊት ጥበቃ ይደረግለታል። ኢትዮጵያም የተለየች አይደለችም፤ ይህንኑ ጥበቃ ታደርጋለች። ስለዚህም ግድቡ ላይ አደጋ ለማድረስ የግብፅ ልዩ ኮማንዶ ኃይል እድል እና ክህሎት ሊኖረው ይገባል። ሆኖም ይላል፣ ትንሽ ቁጥር ያለው የኮማንዶ ሃይል ምንም ያህል ክህሎት ቢኖረውም መሰረታዊ አደጋ የማድረስ አቅሙ ዝቅተኛ ነው ሲል ስልቱን ያጣጥለዋል።
የሱዳን መንግስት በበኩሉ በመንግስት ቃል አቀባዩና በማስታወቂያ ሚኒስትር በኩል ለሕዳሴው ግድብ ያለውን ድጋፍ በይፋ ከማረጋገጡም በላይ ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ተጠቃሚ ትሆናለች ሲል ማስታወቁም ይታወሳል።
ስትራትፎር የሚባለው ተቋም ከአሜሪካ መንግሥት የስለላ ድርጅቶች እና የባሕር ኃይል ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ይታወቃል።
በፋኑኤል ክንፉ የሰንደቅ ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment