Wednesday 6 March 2013

በታክሲ ውስጥ በተፈጠረ የ1.35 ብር አለመግባባት ረዳቱ በጥይት ተመታ

ከትናንት በስቲያ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ በአንድ የታክሲ ተሳፋሪና ረዳት መካከል በተፈጠረ የ1.35 ብር አለመግባባት ምክንያት ረዳቱ በጥይት ተመታ፡፡
ድርጊቱ የተፈጸመው ቦሌ መድኃኔዓለም ከሚገኘው ካልዲስ ካፌ ፊት ለፊት ሲሆን፣ ተጠርጣሪው አቶ ኪዱ ገብረ ሥላሴ ወዲያው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ ነጋ ንጉሡ የተባለው የታክሲ ረዳት ሃያት ሆስፒታል ለሕክምና ተወስዷል፡፡

የታክሲው አሽከርካሪ አቶ ጌትዬ ቆንጥር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተሳፋሪው ሽጉጡን ሊተኩስ የቻለው የአገልግሎት ማብቂያ ቦታቸው ላይ ሲደርሱ ውረድ አልወርድም በሚል ክርክር ነው፡፡ “ታክሲያችን አገልግሎት የሚሰጠው ከመርካቶ እስከ ቴሌ መድኃኔዓለም ድረስ ነው፡፡ በዚያ ቀንም ተሳፋሪዎችን ከካዛንቺስ ጭነን ወደ ቴሌ መድኃኔዓለም ለማድረስ እየተጓዝን ነበር፡፡ በስተመጨረሻም ቴሌ መድኃኔዓለም ስንደርስ ለሁሉም ተሳፋሪዎች እንዲወርዱ ስንናገር፣ ሁለቱ ግን ለመውረድ ፈቃደኛ አልሆኑም፤” ብለዋል፡፡

ከካዛንቺስ ቴሌ መድኃኔዓለም ድረስና ከካዛንቺስ ቦሌ ድልድይ ድረስ ታክሲዎች የሚያስከፍሉት ታሪፍ በተመሳሳይ 2.70 ብር ነው፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪው አቶ ኪዱ መሄድ የምፈልገው ቦሌ ድልድይ ነው በማለት ከሾፌሩና ከረዳቱ ጋር አምባጓሮ ቢፈጥርም፣ ሾፌሩም ሆኑ ረዳቱ ከዚህ በላይ መሄድ እንደማይችሉና ቢሄዱም በሕግ እንደሚጠየቁ ለተጠርጣሪው ይናገራሉ፡፡ በሁለቱም ንግግር የተበሳጨው ተጠርጣሪ ግን ምላሹ ከታክሲ መውረድ ሳይሆን በጎኑ የሰደረውን ሽጉጥ በማውጣት በሾፌሩ ላይ ማነጣጠር ነበር፡፡

ይህን የተመለከተው ረዳትም ሽጉጡን ከተጠርጣሪው ለማስጣል ትግል ይገጥማል፡፡ በዚህም መካከል ተቀባብሎ ከነበረው ሽጉጥ የተተኮሰች ጥይት የረዳቱ የግራ ጎን ውስጥ ተቀርቅራለች፡፡ ረዳቱም ከተጠርጣሪው አቶ ኪዱ ሽጉጡን ታግሎ በመቀበል በቦታው ለነበረው የካልዲስ ጥበቃ እንደሰጠው ጉዳዩን የሚመረምሩት ኮንስታብል አዱኛ ባኔ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከዚያም ፖሊስ ወዲያው በአካባቢው ደርሶ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር አውሎታል፡፡ ተጠርጣሪው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ የቀን ሠራተኛ ሲሆን፣ በነፍስ ማጥፋት ሙከራ ክስ እንደተመሠረተበትም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ተጠርጣሪውም የያዘው መሣሪያም ፈቃድ ያለው መሆኑን ፖሊስ ለሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

የታክሲ ረዳቱ ነጋ በሃያት ሆስፒታል ሕክምናውን እየተከታተለ ሲሆን፣ በሰውነቱ ውስጥ ያለውን ጥይት ለማውጣት ኦፕራሲዮን ሊሆን እንደሚችል ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment