Sunday 10 March 2013

ሲገርሙ አውስትራልያዎች …. ከግራጫ ፀጉር ጋር – ውድድር?

ከዬት እንደምጀመር ሳልወስን ጀመርኩት ብቻ ይሁን ….
የዛሬ ውጤት ለነገም መሰረት ነው። …. የትናንት ፍሬም ለዛሬ ዘር ነው።
ከሥርጉተ ሥላሴ 
ሲገርሙ አውስትራልያዎች …. ከግራጫ ፀጉር ጋር – ውድድር?
Artist and activist Tamagne Beyene in Norway, Oslo
መጀመሪያ ከቋጠሮ አስተያዬት ብነሳ ደስ ይለኛል። ወይ ለራስ ሲቆርሱ ….  እንዴት ነው ነገሩ …. ለመሆኑ እናንተ የት ነው የነበራችሁ? አትገርሙም?! ወያኔ ስልጣን ከያዘ እኮ ስንት ዓመት ሆነው? በዚህ ዓመት ሁሉ አውሮፓ ወያኔን እንቅልፍ መንሳት የጀመረው እኮ ምን አልባት እናንተ …. እእ …. እርግጥ ነው በድህረ ገፆች ታግላችሁ ሊሆን ይችላል። 
 
እንደገናም በዘመነ ቅንጅት በራዲዮ ትንሳኤ … በተረፈ ውድ የቋጠሮ ዝግጅት ክፍል ቀድሞ የጠላትን ሁለገብ ሴራ ሲመነጥር ከነበረው አውሮፓ ጋር መብለጥ ቀርቶ መወዳደር እንደማትችሉ ደራጃችሁም፤ ዕድሜያችሁም እንደማይፈቅድ ላስገነዝባችሁ እፈልጋለሁ። እሺ!

እንደ ታዳጊ ወጣትነታችሁ ግን ከአቀባበሉ ጀምሮ ያሳያችሁት ትጋትና በርታት፤ ያስገኛችሁትም ውጤት በቅጡ የተደራጀ ስለነበር ያኮራል። ለእኔ አውስትራልያ ያሉት ጓደኞቼ እንደገለጹልኝ ከሆነ ያልታዩ ግን ተግባራዊ ያደረጋችኋቸው እናት ሆድ ተግባራት እንደነበራችሁም ተረድቻለሁ። እግዚአብሄር ይስጣችሁ። ቅዱስ ቅናትም አሳደራችሁብኝ። በተጨማሪም ምንም ዓይነት የቅድመ መሰናዶ ችግርም እንዳልታዬባችሁም ተገንዝቤያለሁ። ማለት ዘመኑና ሀገሩ ከፈቀደው ሥልጣኔ ጋር አብራችሁ መጓዝ መቻላችሁ ለእኔ ሌላ አርት ነውና … ልምድም ተመክሮም ቤታችሁ ስለመሆኑ ሰንቄበታለሁና። ሌላው ግን መጨረሻ፤ ማጠቃለያ ላይ የተነሱት የቀጣይ የትግል መስመሮችን በሚመለከት አውስትራልያም ያሉት ወገኖች በተናጠል በስፋት ያነሱት ነጥብ ስለሆነ … ከአውስትራልያ የኢሰአት ዝግጅት አስተባባሪ ኮሚቴም ተከታታይ ቀጥ ያሉ የተግባር ዳገቶች ይጠብቀዋልና የሰበሰበውን ኃይል በተደሞና በአርምሞ፤ በፍቅርና በትህትና፤ በአክብሮትም ጭምር  ለቀጣይ ትግል ማሰማራት ይጠበቅበታል ብዬም አስባለሁ።
ሌላው ደቡብ አፍሪካ ላይም ቢሆን የታዬው የተጋድሎ እንቅስቃሴ ልዩ ክንድ ነበር። ደቡብ አፍሪካ ላይ የነበረው ታዳሚ ፍቅርን መሪው አድርጎ መቀበሉ፤ የቀራኒዮ፤ የጎለጎታ ውቅርን እንደ ታቦት መከብከቡ በራሱ ሌላ የፍቅር ዩንቨርስቲ ነበር፤ ትውልዱ የጀመረው አዲስ ድንግልና ቀና መንገድ ነበር። አብሶ በደህንነት ተግባር ገና ከአውሮፕላን ማረፊያው ጀምሮ የነበረው ጥንቃቄ እንኳንም ደማችን፤ እንኳንም የእኛ ሆናችሁ ያሰኛል። ደቡብ አፍሪካዎች ይህ የበቃ ተግባር ለህዝብ ክብር የሰጡት ቦታ ማሰታወሻነቱ ለዝንትዓለም ነው። አንዲት ክፈትት ምን ያህል ጥቃት እንደሚያስከትል፤ ምን ያህልም እንደሚያከስር፤ ምን ያህልም ቅስም ሊሰብር እንደሚችል ቀድመው በማወቅ ያደረጉት ሥልጡን ተግባር አንቱ ሊያሰኛቸው ይገባል። ሌላ የነበረውን ጠቅላል ዝግጅት በሚመለከት በቦታው የተገኘ አንድ ወንድም ሲነግረኝ  „የዓድዋ ድል ዕለት“ ይመስል ነበር ነው ያለኝ። በተጨማሪም እኔም በተመስጦ እንደተከታተልኩት ደቡብ አፍሪካ ላይ የተሰባሰቡት ወጣቶች ያሳዩት የጋለ ተጨባጭ ብሄራዊ ፍቅር የወያኔን ምስጣዊ ሴራ ያረገፈ፤ የገረፈና የቀጣም ነበር ማለት እችላለሁ።

አሁን ወደ ተነሳሁበት አነ ቋጠሮን ትንሽ ኮርኮም ማደረግ በእጅጉ ዛሬ አሰኝቶኛል። ተነካነ ብላችሁ ግብግብ ከብዕሬ ጋር መግጠም ካሰኛችሁም ያው „ የበላ ልበልኃን“ የፍቅር ሸንጎ እንሰይምና እንዳኛለን። እንደ አባት አደሩ … ኦን ላይን ምንትስ ቅብጥርስ የምትሉት የዘመኑ ልጆች ፈሊጥ ለእኔ አይመችም …. እንደ ለመድነው ዋርካ ሥር ….
አንጋፈው፤ ዕድሜ ጠገቡ የአውሮፓ የጸረ ወያኔ የእንቅስቃሴ ማዕበል ወያኔን እረፍት ነስቶ መቆሚያ መቀመጫ የነሳው ገና ከጥዋቱ ነበር። ዘመኑ የፈቀደላቸው የትግል ስልቶች ሁሉ የተግባር ቤተ ሙከራ አውሮፓ ነበር። የአውሮፓ እንቅስቃሴ አኃታዊነትም ነበረው። በዬትኛውም ዘመን የሚነሳው የአውሮፓ ጸረ ወያኔ እንቅስቃሴ አውሮፓ ዓቀፍ ሆኖ ነው አህዱ የሚለው።  በዚህም ምክንያት ትግሎቹ ተናጠላዊ አልነበሩም። ይልቁንም የተሰባሰቡና በሚገባ የተደራጁ፤ በሥርዓት የተመሩ ወላዊ ውል ነበሩ። ለዚህም ነው ተቃዋሚ ኃይሎችን የማሰባሰብ ምልክቶች የሚያሳዩባቸው ቅድመ መሰናዶዎች ይሁኑ ክንውኖች አውሮፓ ላይ ጥንስሳቸው የሚፈጠረው።

ከዛም በኋላም ቢሆን በታቀዱ ሁኔታዎች ተከታታይ የሎቢ ተግባራት በስፋት ሲከውንባቸው የኖሩት። በሁሉም የትግል ዘርፎች ሆነ ውጥኖችን ለማልማት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አውሮፓ እናትም አናትም ነበር። ይህን በጣም  በእርግጠኝነት መናገር የምፈለግው ጉዳይ ነው። አይደለም አውስትራልያ ስሜን አሜሪካ እንኳን እንደ ስፋቱ፤ እንደ አለው የስደተኛ የነፃነት መጠን ከአውሮፓ በልጦ የትግል እንቅስቃሴ ነበረው ለማለት ይቸግራል። አሁን ሲዊዚርላንድ በጠቅላላው ያሉ የከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ኢትዮጵውያን ቁጥር ቢበዛ አምስት ናቸው። ቺካጎ ግን ኢትዮጵያ ካሉትም የሚበልጥ ቁጥር እንደአለው ነው የሚነገረው። በዚህ ስሌት ሲኬድ … ሚዛኑን … ለውዶቼ ብያለሁ … ለነገሩ ይህን ሳስብ አንድ ነገር ትዝ አለኝ … ሕዝበ – ክርስትያኑን የሚመራው አካል የሌለው የመዳህኒተ – ዓለም አገልጋይ ቃለ ወንጌል ላይ ታላላቅ የሚባሉ ሀገሮች የሉበትም። ኢትዮጵያ ግን ስንት ቦታ ላይ እልፍኝ አስከልካይ ብቻ ሳይሆን በህገ አምላክ አንደበት ተገለጸች? ቢባል በላቤት ናት ብንል ሁላችንም የሚያስማማን ይመስለኛል።
ምን ለማለት ነው። ስደት ሽርሽር አይደለም። አማራጭ ሲታጣ ብቻ የሚወሰድ እርምጃ ነው። ስደት ያል-ልክ የተሰፋ ጥብቆ ወይንም ሽብሽቦ ነው። ለእኔ እርኃብን የሚሸሸውም ሆነ በፖለቲካ ሰውነቱ ያለውን ረገጣ በቃኝ ብሎ የሚወጣው ሁለቱም እኩል ናቸው። ሁለቱም ሽሽታቸው ወልጋዳውና ሸፋፋው የወያኔ አስተዳደር የፈጣራቸው መጠራቅቆች ናቸውና።

የአውሮፓ ስደት ደግሞ ውኃ ያዘለ ተራራ … ነው። ከቶ ቃሉ ገለጸልኝ ይሆን … ?! እእ! አፍ ያለው መቃብር ነው። ይህ ይሻል ይመስለኛል። ስደተኛው ሥሙን፤ የትምህርት ደረጃውን፤ የቤተሰቡን የኑሮ አቋም ሁሉ እዬለዋወጠ ከአንዱ ወደ አንዱ ክልትምትም ሲል፤ ከእሱም ሆነ ከዘመኑም የተጠጋ ዕድሜ፤ ሙያና ዕጣ ፈንታም አብሮ ሲነሳ ሲወድቅ ጀንበር ታዘቀዝቃለች። ላም ጣም የሌለው ኑሮ ሳይኖር፤ የነበረውን ብቃት ለአቶ ስደት ገብሮ፤ ወይ ከጸጋዎቹ ጋር ተላልፍ፤ ወይ ለአቶ ስደት ገብሮ፤ ወይ መክሊቱ ተሸብሽቦ፤ ፊቱም በውስጥ ነዲድ እሳት ተዥጎርጎሮ ኑሮ ከተባላ ተጋድሞ ከተሳካለት አገር፤ በአንዱ  እንደ ነገሩ ኑሮውን ይጀምራል። … በዚህ ለዛዛ በሉት፤ ቀዝቃዛ በሉት፤ የበረደው በሉት፤ ቀለሙ የነጠበ በሉት፤ ዳመናማ በሉት፤ ካፊያማ በሉት፤ ወጀባማ በሉት፤ ኩረትማ በሉት ህይወት ውስጥ ሆኖ ነው ከሀገሩ ፍቅር ጋር ጣትና ቀለበት ሆኖ የኖረው አውሮፓ ላይ ያለው ወገናችሁ።
ዛሬ ካለትናንት መነሻ የለሽ መደረሻ ቢስ ዕሳቤ ነው የሚሆነው። ዕሴቱም እንዲሁ። ትናት ካለዛሬ ደግሞ እርሾ የለሽ የእንጀራ ሊጥ ደንባሳ ነው የሚሆነው። አዎን! ትናንት የአውሮፓ ልጆች በሚያምኑበት የትግል መስመር ተሰልፈው ታግለው፤ ተግባር ቋጥረው ዛሬን አብርተዋል። የዛሬ ኢሰአት የትናት ውጤት፤ ተመክሮ፤ ፍሬ ቀል ነው። ስለሆነም ትናንት – የተሰዉ፤ ትናንት – የደከሙ፤ ትናንት – የባተሉ፤ ትናንት – ህይወታቸውን አበልዘው ደፋ ቀና ያሉትን ወገኖች ማሰባበሰብ ከፍቅር አክቲቢስቶች፤ ከፍቅር አንባሳደሮች የሚጠበቅ ለነገም የማይቀጠር ተግባር ነው። ቀነ ቀጠሮ ፈጽሞ አያስፈልገውም። ድንበር አልባ በሆነ ሁኔታ፤ ካለፕሮቶኮል ወይንም ካለእልፍኝ አስከልካይ ነፃነትን ለመወለድ ዛሬ በእኛ ወስጥ ነፃነት በመሆን ማለፍ አለበት። ስለምን ነው የምንታገለው? ለነፃነት አይደል? ታዲያ ከኛ ላይ ሲደርስ ለምን ፍላጎታችነን ጠቀራ እናለብሰዋለን? ለምንስ ነፃነትን ለመስጠት ጨካኞች እንሆናለን? ካባ እንደርብለት፤ ጃኖ እናልብሰው እንስራለት – ጥበብ። በስተቀር ይህ የታመቀ ፍላጎት ነገም ለራዕያችን መንጣሪ – መንጦላይት – ጦሮ ነው የሚሆነው።

የማከብራችሁ የቋጠሮ አዘጋጆች፤ ያው አውስትራልያ አኽጉርም ሀገርም ነውና ከአውስትራልያ የተለያዩ ከተሞች ስብሰባ በኋላም፤ ከኒዊዘላንድ ስብሰባም ስለ ትናንት ሆነ ስለ ነገ የተደመጠው ይህ ቁምነገር ነበር። የተከበሩ ጄኒራል ኃይሌ መለስ ባደረጉት ንግግግር „ከዚህ በፊት ተብሎ እንደሆን አላውቅም። እኔ ግን ኢሰአትን እሳት ብዬዋለሁ“ ሲሉ የተደመጡት ኢሰአት ለጠላት እሳት ለወገን እናት እንዲሆን ነው የብዙኃኑ ፍላጎት። ከኢትዮጵያ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች የእምነት የነፃነት እንቅስቃሴ የምንማረው ታላቁ ቁም ነገር፤ ለወቅቱ የሚስማማ የትግል ስልት ቀያሽነቱ – የታዳሚውን መጠን ከዕለት ወደ ዕለት አስፍቶለታል፤ ስንፍናንና ስልቹነትንና ተስፋ ቆራጭነትን ገድሎለታል። በሌላ በኩል ደግሞ ንቅናቄው በቀደምቱ ድክመቶች ላይ ፈጽሞ አልተመለሰባቸውም። ድንቅ ፍጹም ድንቅ ነው። እውነቱን ለመናገር የመሪነት ተከታታይነት ሥነ -ጥብብም ታይቶበታል።

እግዚአብሄር ይመስገን በዬቦታው የምቀርባቸው ወንድምና እህቶቼ የኢሰአት ታዳሚ ስለነበሩ የአነሱት መሰራታዊ ነጥብም በስስት፤ በቁጭት የገለጹልኝ ፍሬ ነገርም ይኽውን ነው። … እናንት እንደ መቋጫ ያነሳችሁትን ጠቋሚ፤ ገንቢ፤ መሪ አስተያዬት ነው የውስጥ ስሜታችን፤ ፍላጎታችን በሥርዓት ተክሊል የሚያጋባው። በሉ አውስትራሊያዎች በነካ አፋችሁ እስተያዬቱን ገፋ ማደረግ ሳይሆን እናንተም ለወቅቱ የትግል መስመር ባለቤት ስለሆናችሁ ጀምሩት። መቆስቆሻ አትፈልጉ። እናንተ ተቆስቆሱና የተበተነውና ኃይል፤  ኑልን ብላችሁ በእቅፍ – በፍቅር ለመቀበል …. እሸት ቅመሱ በሉና! … ሌላ ለአደባባይ የማይውል የታማችሁበት ነገርም ነበር። በግል በኢሜሌ ከመጣችሁ ሹክ እላችኋለሁ። ይህቺን ነጥብ አንድ ጊዜ ሞገደኛው ተክሌ የዛሬ ሁለትና ሶስት ዓመት ኢትዮ ዛሬ ላይ አስነብቦን ነበር። እኔም ነጥቡ መንፈሴን የገዛ ስለነበር ቀጥታ ለባለቤቱ አድርሻለሁ። ስለሆነም እኔም ወዳጆቼ ያነሷትን ነጥብ ስለማትመችኝ ከሆነ ብታስተካክሉት መልካም ስለሚሆን ኢሜሌ ቤት ለእንግዳ ይላችኋል … ይነገራችኋል – የታማችሁበትን – ከች በሉ። ቡናው ተፍልቶ ፍንጃሉ ተዘርግቶ ይጠብቃችኋል። ማን ሞኝ አለ በሉኛ!

አሁን ወደ ጊዜያዊ በአቴ ልመለስ፤ …  ከአውሮፓ ስበሰባዎችም ህዝባዊ ድምጽ ሙሉ ተሳትፎ የነበረበት ግልጽ ስብሰባ … የኖርዎዩን ለናሙና ባነሳ ደስ ይለኛል። አቶ የሱፍ ያሲን በትግል ዓለም፤ በጹሑፍ ዓለም፤ በፖለቲካ ሰውነትም ካላቸው ልምድ ተነሰተው „ለኢሰአት አሸክመን እንልከዋለን“ ያሉት ቁምነገርም ይኽው ነው።  በሶሊዳሪቲ ትግል ከሚታወቀው ሲዊዲኒም ይህ መሰረታዊና ወቅታዊም፤ መርኃዊ ጉዳይ መነሳቱ አይቀሬ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። መቼም የሲዊዲኑ ራዲዮ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ አህመድ የሚዲያን ሚና ማብራራሪያ ሲሰጥ ይህን ይዘለዋል ብዬ ፈጽሞ አላስብም።
ሌላ ያልጠበቁት ግን ሰፊ በሆነ አትኩሮት የተከታተልኩት የብራስልስ የቤልጄሙ ስብሰባ ነበር። እኛ ከሀገራችን ሁነት ጋር ምን ያህል እንደተራራቅነም እራሴን ወቅሼበታለሁ። በአፋር ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው የቤት ውስጥ ገደላ፤ መፈናቃል፤ መገፋት መንፈሴን አርመጥምጦታል። በመላ ሀገሬ የኼው እንደሚፈጸም አውቃለሁ። ግን ነገር ግን የአፋሩ የቆጠቆጠኝ ለዝርዝር መረጃው ባይተዋር መሆናችን ነው። ስለምን? ግንኙነታችን ውስን ስለሆነ ነው። ወያኔ አንድ ነገር ከሆነ ቦታ ላይ ይለኩሳል። በቃ ከዛ በኋላ በዛ ዙሪያ፤ ያለ የሌለ መንፈሳዊ ንብረታችንና ሃብታችን በዚያ ላይ ያሰማራና እሱ የአፓርታይድ ተልዕኮውን በጓዳ ስለሚከውን፤ ቀልባችን እዬበተነ ሁለገብ ቅኝታችን ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ ነው ያቃጠለኝ፤ ያንገበገበኝም። ለማንኛውም የብራስልስ ልጆችን የሞቀ፤ የጋለ፤ ጠላትን የሚያንደፈድፍ፤ ለወገን ብርታትና ጥንካሬ የሚለግሰውን ስበስባ በሚመለከት በአንድ ዕንቁ የ21ኛው ምዕተ ዓመት ታላቅ ንግግር ልቋጨው …  „ተዋርጄ ሱፉ ከምልበስ ሽርጤ ተመልሶልኝ በሀገሬ ተከብሬ ብኖር“ ይህ የዘመኑ የኛ ማርቲን ሉተር ራዕይ ነው ለእኔ ….

በአጠቃላይ ባልታፈኑ ግልጽና ሰፊ ውይይት በተካሄደባቸው ስበሰባዎች ቅብ ሳይሆኑ ነገን በጽኑ መንፈስ በድል ሊሞሸሩ የሚችሉ እጅግ ጠቃሚ ህዝበ ጠቀም፤ ዕንባ ጠቀም፤ ወገናዊነትን በብርቱ ክንድና በጠንካራ መንፈስ ሊያዋቅሩ የሚችሉ ገንቢ ሃሳቦች፤ አስተያዬቶች፤ ትንተናዎች፤ ማብራሪያዎች፤ ትምህርቶች፤ ቃለ ምልልሶች ተገኝተውባቸዋል። ይህ ሲታሰብ የቻሉትን ያህል ደፋ ቀና ያሉ ወገኖች ሁሉ ኃይላቸውን አሰባስበው፤ ሳይታክቱ ከቀጠሉ ትግሉ ራሱን እዬመራ፤ ቅን መሪዎቹን በአጋርነት አስልፎ ለድል ይበቃል የሚል ተሰፋ ይቋጥራል …. እነ ቋጠሮ በዚህች ነጥብ መንፈሴ ከመንፈሳችሁ ጋር ይጋባል ብዬ አስባለሁ። አሁን ወደ ፍራንከፈርት ልመለስ።
የፍራንክፈርቱ አማይን ህዝበ ጠቀም ስብሰባ እንደጠበቁትም ነው። እንዳልጠበቀኩትም ነው።
ክብሮቼ ትእግስታችሁን እሻለሁና ተከታተሉኝ።
እንደ ጠበቅኩት የሆነው። የጠበቅኩት ፍራንክፈርቶች የበሰለ፤ ያፈራ ተመክሮ ስላላቸው በቅድመ መሰናዶ ጊዜ እጥረትም ሆነ በባላቤትነት ቀደምትነት ስሜት ሳይጎዱ የታሰበውን ከግብ ያደርሳሉ የሚል ሙሉ ግምትና ዕምነት ስለነበረኝ አድርገውታል። ደማቅ ነበር። ውጤታማ ነበር። ከሁሉ ያሰደሰተኝ በመላ የአውሮፓ ስብሰባ የፍራንክፈርቱ የሴቶች ተሳትፎ ሙሉዑ ነበር። በታዳሚነት ሳይሆን በመሪነትም። ብቃቱም ሲመረመር ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ ሆኖ አላዬሁትም። ነገ አርብ ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀን ማርች ስምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ  ይከበራል። እርገቱ ለእኔ ፍራንክፍርት ላይ ተፈጽሟል ብዬ አስባለሁ።

እንዳልጠበቀኩት የሆነው። ዓይኔን እስኪደክመኝ ደረስ አስተውዬ አዬሁት። ቀደምቶች እንደ ገመትኩት ላገኝ አልቻልኩም። እንግዲህ ከቀደምቶች አቶ ጌታቸው ጋረደውን አይቻለሁ። ለዛውም መደረክ ላይ። ገርሞኛልም። እሳቸው እንዲህ መንፈሳቸውን የገዛ ገጠመኝ ኖሯቸው የድጋፍ ድምጽ መስጠት መቻላቸው – ድንቅ ፍጽምና ነው። ምንአልባትም ኢሰአት ከሙያቸው ህይወት ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ሊሆን ይችላል። ይህ ያጽናናል። በተረፈ ግን ገና ብዙ ይቀራል። ፍራንክፈረት በዓለም ዓቀፍ መደረክም የደራ የመረጃ ገብያ ነው። ዓለምዓቀፍ የመጸሐፍት ትርዒት፤ መቀመጫው ስፔን የሆነው /ቢዝነስ ኢኒሼቲብ ዳይረኬሽን – በእንግሊዘኛው እንዳለ ማቀረቡን መረጥኩት/ ዓለም ዓቀፍ የመኪና ትርዒት፤ ዓለም ዓቀፍ የሚደያ የሽልማት ዝግጅት፤ በእኛም ቢሆን በልዑል አስፋው ወሰን አሰራተ ካሳ የሚመራው እነ ድንቁ ፓንከራተስ፤ እንዲሁም የዓለም ዕውቅ የታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሐፊዎች  ይገኙበት የነበረው „ውረስ ኢትዮጵያ“ ሰፊ የሆኑ የታሪክ ማህደሮች የሚፈተሽበት ዓመታዊ ጉባኤ፤ ዓለም ዓቀፍ የስእል ኤግዚቪሽን፤ እንዲያውም በአንድ ወቅት ከዓለም ኢትዮጵያ ብቻዋን ተምርጣበትም የነበረው … ። ብቻ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ዓለምዓቀፍ ተጓዳኝ ተግባራት የሚከውኑበት ምስሶ ከተማ ስለሆነ ፍራንክፈርት አማይን ላይ ይታደማል፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪም ሁነቱ ያግዛል። ስለሆነም ኃይልን እንደ ገና፤ አዎን እንደ ገና የማሰባሰቡ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ይመስለኛል።
ሴት በተፈጥሮዋ ብዙ ጸጋ ስላላት እስኪ አህዱ ተብሏል … ክለቱ፤ ስለስቱ እያለ ፍራንክፈረት አማይን ላይ ዕድሜ ጠገብ ተመክሮዎችን፤ ልምዶችን ወደ ጸረ ወያኔ ትግል በአክብሮት፤ በልዩ መስህባዊ ሥርዓት የማሰባሰቡን ሂደት ተከታታይ መድረግ ቢቻል መልካም ነው። ከዚህ ጋር አምሰተርዳምም ቢሆን የከበሩ፤ ተቆርቋሪ ሙሁራን ወገኖቻችንን የማሰባሰቡ ድርጊት በግንባር ቀደምትነት ተግባር ሊውል ይገባልም እላለሁ። የኢሰአት ስትዲዮ እዛው ስላለ ፍሬ ጠገብ ውጤት ይጠበቅበታል። ስብሰባው እራሱ ከጠበቅኩት በላይ ነበር። በአጠቃላይ በዬአካባቢው የትናንት የእውነት አርበኞችና የተግባር ጀግኖችን የማሰባሰቡ ሂደት ያው ኃላፊነቱ ያለው ከፍቅር ላይ ስለሆነ፤ አቶ ፍቅር ተገቢውን አትኩሮት እራሱ ለሃብቱ ችሮ ሰብሉን ቢሰበሰብ መልካም ነው እልላሁ።

ሌላ ምን ቀረኝ? አዎን ፍራንክፈርት አማይን ላይ በዕድሚያዋ ከሁሉ ያነሰች፤ በሥነ – ምግባሯ ግን ፍጹም የላቀች ምቀኝነትን የገደለች። አንዲት ትንሽዬ የኢሰአት ወጣትን አዬሁ። „የምን አለሽ መቲ“ አዘጋጅ። ጋዜጠኛ መተሰቢያ ቀጸላ። እንደምወዳት ጓደኞቼ ሁሉ ያውቃሉ። ውስጧን ስላዬሁት መወደድ ብቻ ሳይሆን እሳሳላታለሁም። ከዕድሜዋ በላይ፤ እንደ ሰው ፍጡር ከመሆኗም በላይ ለቅንነቷ ፍጹም የሆነ ድርብርብ አክብሮት አለኝ። በጣም ብዙ ሰው ያጣው፤ የነጠፈበት፤ ድርቅ የመታው፤ ግን ንጥር፤ ቅዱስ፤ ንዑድ ሥነ ምግባርን ቅንነትን ሰንደቅዓላማዋ ስላደረገች፤ የእሷ ፍላጎት ሁሉም ያለውን ይዞ ኢትዮጵያን ከጥፋት እንዲታደጋት ነው። ቃለ ምልሎሶቿ ሁሉ ይህን … ያስነብባሉ፤ ይተረጉማሉ፤ ያመሳጥራሉ። እና በርቀት ሳይሆን ውድ መታሰቢያ አክብሮቴና ፍቅሬ ካለሽበት በቅርብሽ ይደረስሽ ብያለሁ። አንቺ ለዘመኑ ወድ ናሙና ነሽ። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል። ይህን መክሊት እንደ አግባቡ ተግባር ላይ እንዲውል ከሚጠሩት ወጣት የቅንነት አርበኞች ወስጥ አንቺ ቀንዲል ነሽ። በርቺ! እንደ አንቺ ሁሉም ሰው አንዲሆንም በቅኗ፤ በንጹኋ ልቦናሽም አምላክሽን ጠይቂው። አንቺ ቅን ስለሆንሽ ከእኛ አንቺን መዳህኒታችን ይሰማሳልና …. ውስጣችን እንዲያጥብ፤ ጉድፉንና ግድፈቱን እንዲያጸዳ – በርትተሽ ንገሪው። ሱባኤ መጥቷል በዚህው ይሁን …. አደግድገሽ የቅንነት አምላክን ጠይቂው። ሁሉ አለን። ያለን እንዲሆነን ንገሪው ለአባታችን።

በተረፈ ታማኝ ወንድሜ አንጠልጥዬ ስጠራህ እጅግ ይመቸኛል። ሳልቸገር፤ ሳልጨነቅ፤ ዝክንትል በመልበሴ፤ ዲሪቶ በመታጠቄ ሳላፍርበት ከፊትህ ብቆም ከአንተ ጋር ብቀመጥም አልሰቀቅም። ተልዕኮህ ለወደፊት መንትያ ቢሆን ምርጫዬ ነው። መንትያው ተመሳሳይ ሦስት ልጆችን እንድትወልድ ነው እኔ የምፈልገው። ለነገሩ አንተም በሥጋ የወለድካቸው ሦስት ናቸውና። መልካቸውም በጣም ተመሳሳይ ነው። ቁምነገር … ወደ ልበል …
-       የፋይናንስ አቅምን መገንባት ተልዕኮህ ነበር … አፍርተኽበታል።
-       ኃይል ማሰባሰብ በቅንነት፤ ፍቅር ጠገብ አድርገህ … በሚመለከት ግን እንጃ እንደ እኔ አንተን የሚጠብቅ ተንበርክኮ ያልጀመርከው ይመስለኛል። በጉዞህ  ያላዬኃቸው፤ ያላገኘኃቸው፤ ከብዙ ጸጋቸው ጋር ፈርኃ እግዚአብሄር ያደረባቸው እኛን የሚበልጡም ተቆርቋሪ ወገኖች አሉና …. ገፋ አድርገህ በውስጣቸው ሂድባቸው። በሰማይ ቤት ታላቅ እልልታ የሚኖረው በጠፋው በግ ግኝት ስለሆነ። እርግጥ ነው  …. አልጠፉም አሉ። ግን ቀንና ቀን ሳይገጣጠሙ እዬቀሩ ልባቸውን እዬከፋቸው ረመጡን ታቀፈው ቤታቸው ቁጭ ያሉት፤ ከተገኙት በብዛት ቢበልጡ እንጂ አያንሱም። ሃብትን መሰብሰብ ዲታ ያደርጋል …. እሺ ወንድምዓለም! ሚሊዮነርነት በፍቅር መታደል ….

-       የኢሰአትን ቤተሰብ በቋሚነትና በዘላቂነት መገንባት። የበላይም የበታችም መዋቅራዊ ሰንሰለት የሌለው፤ ሴሪሞኒያዊ ያልሆነ፤ አለቃው የኢሳት የባንክ ቁጥር ብቻ የሆነ። ነባሩን ከአዲሱ ጋር በማገናኘት የልምድ ተመክሮ መስመር መዘርጋት፤ ሥርዓት መፍጠር …. መንገድ ጠራጊ አይደለህ?! ይህንንም ባሊህ በለዋ! ዳታ ሳታበዛ … ከአጋሮችህ ጋር ….
በተረፈ በብዙ የኢትዮጵውያን ሀገር ጠቀም ስብሰባዎች ተሳትፊያለሁ። ይህን ያህል ገንዘብ ሲሰበሰብ ስሰማም ሳይም ግን የመጀመሪያዬ ነው። አሁን ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ብሏል ቋጠሮ ….  የእኔ ግን — አቶ ቋጠሮ —-  የእውነት ነው …. ሲዊዘርላንድ ውስጥ የተሰበሰበው ገንዘብ በሲዊዝ ገንዘብ ስለሆነ በዶላራ ሲተምን ብዙ ነው። የመጣው ሰው ደግሞ ያዬነው ነው። ስለዚህ ሙኒክ ከመጣው፤ ፍራንከፈርት ከተገኘው፤ ኖርዎይ ከተመመው ወገን ጋር ሲነጻጻር ሬሼው ቢወጣ የሲዊዝ ከሁሉም የላቀ ነው። ጥቂቶች የከወኑት ተግባር ለእኔ የጥቁር አንበሳ የድል ገድል ነው። የኪሳቸውን ጨርሰው፤ እዛው እዬተበደሩ፤ ወደ ግድግዳ ባንክ እዬሄዱ – ጥሪታቸውን እዬፈተሹ፤ ለማግስት ለነዳጅ እንኳን ያጡ ወገኖችን በዓይኔ አይቻለሁ። 7 ወይንም ስምንት ሆነው አንድ ትልቅ ጨረታ መወዳደር፤ መፎካከር እጹብ ድንቅ ነው። ምንም ያላልኩለት አለ? ስለ ለንደን። ለንደኖች ቅንነታችሁ ቢቀና አዲስ ትውልድ ይገናባል። ይህ ይበቃችኋል አይደል።
እንደ መቋጫ

በነፃነት ሀገር … ስለምን? አሁን እኔ በማናቸውም ሁኔታ ለምጽፈው መጣጥፍ አላፍርበትም። አንገቴም ቀና ያለ ነው። ተጎንብሼ አልሄድም። ወያኔን ወንበዴ ብል አላፍርም፤ የሽፍታ ስበስብ ብልም አልደነግጥም። በዬትኛው አቅጣጫ ጥያቄ ቢቀርብም አልርበተበትም። እርግጥ ወንበዴ ስል የማይመቻቸው ወገኖች ገጥመውኛል። ማለት መራዛማ መሰሪነቱን ከመሰረቱ ፈልፍለው ያልተገነዘቡ ስለሆነ ልቦናቸውን አምላኬ ይክፍትላቸው እላለሁ። እኔ ግን አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ። በቃ ያመንኩበትና በተጨባጭ የሆነውን ነገር ላይ ስለምነሳ። የኢትዮጵውያን ስብሰባ የሚያዘጋጅ ማንኛውም አካልም፤ የህዝብን የመተፈንሻ ቧንቧ ላይ ፈጽሞ ማዕቀብ ሊጥል አይገባም። ትናንት ከአማካሪ ጋር ነበርኩ። እጅግ የማከብረው አለቃዬ የነበረ ሌላ ክ/ሀገር ሊቀይር ማታ ከስንብቱ ላይ እንደምገኝ፤ ስለማዘኔም አጫወኳት። አንድ ጥያቄ ጠዬቀችኝ …  „አዲሱን ኢሜል ሰጥቶሻልን?“ ስትል አዎን ሙሉ አድራሻውን፤ የእሱንም የባለቤቱንም ስላት። „ታዲያ መገናኘት ትችላላችሁ።“ አለችኝ። አዬ ይበዛበታል ሥራ ስላት …. ምን እንዳለችኝ ታውቃላችሁ „ወይ ጉድ! ይህማ ምግብ አዘጋጅቶ መብላትን እንደ መከልክል ነው። ሰጥቶሻል ግንኙነቱን ቀጥይ“ አለችኝ።

እና ….  በነፃነት ሀገር ለነፃነት በሚያታገል የሚዲያ ስብሰባ ላይ በግልጽ መወያዬት፤ መነጋጋር፤ ሃሜትም ካለ እስኪ ንገሩን … መባል አለበት። ህዝባዊ ስብሰባዎች የተኮረኮሙ መሆን የለባቸውም። አሰራራቸውም ወጥ መሆን አለባቸው። አንድ ሰው እኮ ብዙ ነው ለእኔ … የሚያወጣውም ወጪም ቀላል አይደለም። እንኳንስ ብዙኃኑ … ይህንን በከተሙ ስብሰባዎች የተገኙ ተመክሮዎች ለኢሰአት ሆነ ትግሉን ለሚመሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ትንፋሽ ናቸው። በር ተዘግቶ ስብሰባ አይሆንም። እኔ ከኢሰአት ፕሮግራሞች እጅግ የምወደው የአድማጮችን አስተያዬትን ነው።  የለንደኑ የሰብአዊ መብት ረገጣ በኢትዮጵያ ዝግጅትንም፤ ስለምን? የዕንባን ጠረን ቢመረኝም እንኳን ስለማጣጥምበት፤ የሀገሬን የወዝ በት የማወራርድበት፤ የወገኔን ለዛና ናፍቆቱን የምመገበት ስለሆነ። …. ስለዚህ ህዝባዊ ስበሰባዎች ክፍት መሆን አላባቸው። አድማጭነት ብቻ እእ! ከተናቀው፤ ካልታሰበውና ከተዋረደው የሚፈጥር ወይንም የሚወለድ የነጠረ ሃሳብ፤ ምንአልባትም የሚቀድስ፤ ፈር ቀያሽ አብነትም ሊሆን ይችላል። …. እንደ አጋጣሚም ከበሰለ እስተያዬትና ጥቆማ የተሰወረብን ቁልፍ ሊገኝ ይችላል። ለዚህ እኮ ነው … ሁሉ እያለን ያ … የጫካ 22 ዓመት ….

መቼም እኔ እንደሚገባኝ የፓለቲካ ድርጅቶች ይሁኑ ንቅናቄዎች እና ሚዲያዎች የራሳቸው ድርሻ አላቸው። ድርሻን ለመወጣት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አንዱ ለሌላኛው ምርኩዝ፤ አንዱ ለሌላኛው ማገር ናቸውና የትኛውም ብሄራዊ ስብሰባ ላይ ፍሬ ነገሩ፤ የህዝብ ውስጣዊ ስሜት፤ የሚጠቁሙ መንፈሶችን ማግኘቱ ላይ ሊሆን ይገባል።  እርግጥ ነው …. በሀገራችን ዓለምዓቀፍ ወጥ ሚዲያዊ ስብሰባ ሲደረግ ይህ የመጀመሪያው ነው። አጋጣሚውም አግዞ ብዙ የጥበብ ታዳሚ ጠሪው ፍቅር ነበር። እንዳዬሁት ስብሰባ ለሚለው ቃል ባዕድ የነበሩ እህትና ወንድሞቼ ታደምውበት አይቻለሁ። ጠይቄያቸውም ስለነበር መደሰታቸውን ገልጸውልኛል። ስለሆነም ይህን ኃይል በቋሚነት የዕንባ አጋር የማደረግ ተግባር  … ወሳኙ መርኽ ሊሆን ይገባል።
ሌላው ግን የት ቦታ እንደሆነ አላስታውስም። በትልቁ ፊት ለፊት ታዳሚዎችን „እንኳን ደህና መጣችሁ“ የሚል የፍቅር መስተንግዶ ከአንደኛው የአውሮፓ ሀገር ስብሰባ መድረክ ላይ አንብቢያለሁ። ማለፊያ ነው። ይህን የጻፋችሁና ያስቀደማችሁ የኢሰአት አስተባባሪ ኮሚቴዎችን እጅግ ከልብ አመሰግናችኋለሁ። እንዲህ ነው እንጂ „ከፍትፍቱ ፊቱ“ እንዲሉ ስለሆነም ትልቅ የልዩነት ግርዶሽ በመስበር ትምህርት ቤት ስለሆናችሁ አድንቄያችኋለሁ። ለእናቴ ትውፊትም ዘብ ጠባቂም ስለሆናችሁ – ኮርቸባችኋለሁ። ፍቅርም ማለት፤ – የነፃነት ወታደር መሆን ማለትም ይሄው ነውና! እኔ በስብሰባ ቦታ ስገኝ ሆነ መጣጥፍ ሳነብም፤ ወይንም ቪዲዮ ሳይም፤ ወይንም ራዲዮ ሳዳምጥም የሁሉንም ነገር ሆድ ዕቃ ነው የምፈትሽው። ቸርን እንሰንብት።
ነፃ ሚዲያ አራሱን ይፈጥራል። እራሱንም ይሰራል፤ እራሱንም ያነጥራል!
ነፃ ሚዲያ የህዝብ የውስጥ ስሜት ጽኑ ዋቢ ነው። አደራ አውጪም!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
ሥርጉተ ሥላሴ

No comments:

Post a Comment