Tuesday 19 March 2013

አንድ የዲግሪ ምሩቅ የመንግስት ሰራተኛ ረሃብተኛ እየሆነ ነው!! ነቆራና ሌሎችም ወጎች ከህይወት እምሻው


ረጅም ጉዞ ለማድርግ ሚኒ ባስ ላይ ተሳፍሬያለሁ፡፡
ከአጠገቤ አሁንም አሁንም ሰአቷን የምታይ ወጣት ሴት ተቀምጣለች፡፡
ሁኔታዋን ሳየው ጨነቀኝ፡፡
“ሰላም ነው?” አልኩኝ
“ረፈደብኝ፡፡ ዛሬ ከረፈደብኝ ጉዴ ነው!”
ድምፅዋ ደግሞ ከተጎሳቆለ ፊቷ የባሰ ያሳዝናል፡፡

ትንሽ ካወራኋት በኃላ አንድ መንግስት መስሪያቤት በኤክስፐርትነት እንደምትሰራና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዳላት ተረዳሁ፡፡

ከተግባባን በኃላ የሆድ የሆዷን ታዋየኝ ጀመር፡፡

“እጄ ላይ የሚገባው ደሞዝ 865 ብር ነው፡፡ ፡፡ የቤት ኪራዬ 300፡፡ ለዛውም ከከተማ የትናየት፡፡ አስፋልት ለመድረስ 30 ደቂቃ በእግሬ ኳትኜ፡፡ ክፍለ ሃገር ላሉት እናትና አባቴ ካለዚያ መኖር ስለማይችሉበወር 150 ብር እልካለሁ፡፡ የሚተርፈኝ 400 ምናምን ብር፡፡ እህ! አስቢው! መብላት አለብኝ፡፡መልበስ አለብኝ፡፡ትራንስፖርቱ እንደምታይው ነው፡፡ በታክሲ መሄድ ከተውኩማ ቆይቼ ነበር…ሰሞኑን ግን ብዙ ግዜ ስላረፈድኩ አውቶብስ ለመጠበቅ ፈራሁ፡፡ ከሁለት አመት ወዲህ ምግብ እንኳን በስርአቱ መብላት አልችልም፡፡ አይገርምሽም…?ምግብ መብላት አልችልም!”

የምላት ስላጣሁ ራሴ ወሬ ጀምሬ ራሴ ዝም አልኩ፡፡

“ከዩኒቨርስቲ በዲግሪ ተመርቄ ሌላው ቢቀር መራብ አለብኝ?!” ስትለኝ ድንገተኛ ራስ ምታት ያዘኝ፡፡

ጉዳዩ ለኔም ለናንተም አዲስ አይደለም፡፡ ኑሯችን ነው፡፡ የቀን ቀን ውሏችን ነው፡፡
እንደሷ አይነት ብዙ ሰዎች አውቃለሁ፡፡

ነገሩን ግን እንዲህ አድርጎ ያስቀመጠልኝ ሰው አላውቅም፡፡

እውነት አንድ ሰው መጀመሪያ 10 እና 12 አመት ሲማር ከርሞ፣ ዩኒቨርስቲ በትምህርት 4 አመት አጥፍቶ፣ ከፍተኛ ሙያ የሚጠይቅ ስራ ላይ ባለሙያ ተብሎ ተቀጥሮ ፤

ሌላው ቢቀር (ይሰመርበት!) ሌላው ቢቀር ወር አጋማሽ ላይ ከምሳ እና ከእራት መምረጥ፣ ወሩ መገባደጃ ላይ ደግሞ መራብ አለበት?

አለበት ወይ?

No comments:

Post a Comment